"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday, 26 May 2012

የቤተመንግስት ሹክሹክታ


የቤተመንግስት ሹክሹክታ

SHARE THIS
TAGS
Share in top social networks!
lencho leta
 በዚህ ወቅት የመለስ አስተዳደር የሚያሳስበው ዋና አጀንዳ ምን እንደሆነ ማወቅ በጣም ጠቃሚ ይመስለኛል። በአንጻሩ መለስ ዜናዊ የሚያሳስበውን አለማወቅም ተቃዋሚ ሃይላት ታክቲክና ስትራቴጂያቸውን በትክክል እንዳይነድፉ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። መረጃዎችን በመተንተን አሳባቸውን የሚያካፍሉንን ስናነብ ሰንብተናል። ብዙውን ጊዜ የሚፃፉት አሳቦች እንደየግለሰቦች የፖለቲካ አመለካከት የተቃኙ ናቸው።
“የመለስ ፍላጎት ይህችን ታሪካዊት እና የሃብታም ደሃ የሆነች ሃገር ካደጉት አገራት ተርታ ማሰለፍ ነው” እያለ የሚናገር ደፋርም ያጋጥማል። እንዲህ ያለውን ንግግር፣ “እግዜር ይስጥልኝ” ከሚል ፈገግታ ጋር መሸኘት ይገባል።
ብዙውን ጊዜ እውነታና የሚዲያ ዘገባዎች ጎን ለጎን እንደሚጓዙ መንታ መስመሮች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ በመስመሮቹ መካከል ምስጢር መፈለግ እንኳ ያስቸግራል። ዛሬ የሚነገረን ወሬ ከሁለት አመታት በሁዋላ ለሚፈፀም ነገር አስፈላጊ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ቀደም፣ “የመጨረሻ አንጓ” የሚል ቃል አንስቼ ነበር። ለአብነት እስክንድር ነጋ የታሰረው በፃፈው መጣጥፍ ምክንያት፣ ወይም የትጥቅ ትግል ከሚያካሂዱ ተቃዋሚዎች ጋር የስልክ ግንኙነት ስላደረገ  ነው ብሎ ማመን አይቻልም። ከእስክንድር ነፃ ብእር ይልቅ፣ እስክንድር በመታሰሩ የሚያስከትለው ጉዳት እንደሚበልጥ መለስ ዜናዊ ያውቃል። ወያኔ በባህሪው ሽቦ ወጣሪ ነው። ሽቦው ከርሮ ከመበጠሱ በፊት ግን መልሶ ያላላዋል።
የፖለቲካ ቁማር እንደ ሂሳብ ቀመር ነው። በመሆኑም የወያኔ መሪዎች የፖለቲካ ሂሳባቸውን እንዴት እንደሚያሰሉ ፎርሙላውን ማወቅ ጠቃሚ ነው። ቢቻል በሚዲያ ከሚናገሩት ይልቅ፣ አረቄ ላይ የሚጨዋወቱትን ለመስማት በመሞከር የተደበቀውን እውነት ለማግኘት መሞከር ተገቢ ይሆናል። የዚህን መጣጥፍ ርእስ፣ “የቤተመንግስት ሹክሹክታ” የሚል ርእስ የሰጠሁትም ከሚዲያ ውጭ የተነገሩ አንዳንድ አቅጣጫ ጠቋሚ ወጎችን ለማንሳት በመፈለጌ ነው።
ቀጣዩ ምርጫ “ከምርጫ 97” ባላነሰ ሁኔታ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የወያኔ ሰዎች የሚያወሩት ወይም የሚያስወሩት ለምን ይሆን? ወያኔ በ2002  ምርጫ 99.6 % ማሸነፉን በፈጣጣው ነግሮናል። ደጋግመው እንደሚሰብኩንም አገሪቱ በልማት እየመጠቀች ነው። የወያኔው አይዲዮሎግ በረከት ስምኦን በአዲሱ መፅሃፉ እንደተረከውም የኢትዮጵያ ገበሬ እንደ አምባሳደሮች ሙሉ ሱፍ መልበስ ጀምሮአል። ከዚያም ባሻገር ከጠላና ከአረቄ ተላቆ ቢራና ጉደር መጠጣት ጀምሮአል። ይሁን እንጂ በረከት ከባህርዳር ወደ አዲሳባ ሲመላለስ ለአንድ ቀን እንኳ በመኪና ተጉዞ፣ እግረ ቀጫጭኖቹን ባለቁምጣ የጎጃም ገበሬዎች ቢያይ ኖሮ እንዲህ ብሎ ባልፃፈ ነበር። ቴሌቪዥናቸውም ይህንኑ ሲሰብክ ይውላል። (በርግጥ ‘ሰው ለሰው’ የተባለው ተከታታይ ድራማ ባይኖር ኖሮ የኢቲቪ ቀብር ገና ድሮ በተፈፀመ ነበር የሚሉ አሉ።)
ወያኔ ስለ ቀጣዩ ምርጫ አስጊነት ከወዲሁ ለምን ያወጋል? እንደ ምርጫ 2002 በቀላሉ አምታቶ ማለፍ አይችልምን? መለስ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር ካለመፈለጉ ጋር የተያያዘ ምን አዲስና ልዩ ነገር ይኖራል? ወይስ በሰበካ ብቻ ሰማይ ጥግ የደረሱ የልማት እቅዶች ችግር ገጠማቸው? የአባይ ግድብ መጠናቀቅ አጠራጥሮ ይሆን? ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ይጠናቀቃል የተባለው  የ3000 ኪሎሜትር የባቡር ግንባታ ቃልኪዳንስ እምን ደረሰ? እንደ ጀርመኑ ባቡር (DB) እንደ ዘንዶ ይወነጨፋል፣ ከመቀሌ ወደ ጂንካ በአንድ አዳር ይገባል፣ ከጂንካ ተነስቶ ሌሊቱን ሲገሰግስ አድሮ፣ እንደ አጥቢያ ኮከብ ሊነጋጋ ሲል ሱልልታ ይታያል” እንደተባለው መፈፀም አልተቻለም ይሆን? መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ ወቅታዊ ጉዳይ የወያኔ ጭንቀት አይደለም።
ከ2015 ምርጫ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ብጫቂ ወጎች ከቤተመንግስት አምልጠው በመውጣት ላይ ናቸው። ትኩረቴን ለመሳብ የበቃውና ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ ነጥብ፣ ኦህዴድ የተባለው የኢህአዴግ አባል ድርጅት ሊሸጥ ስለመሆኑ መስማቴ ነው። ያለጨረታ ግዢውን የሚፈፅሙት ኦቦ ሌንጮ ለታ እና ዶክተር ዲማ ነገዎ ሲሆኑ፣ አሻሻጮቹ ደላሎች ደግሞ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅና የጅማው አባጂፋር የልጅ ልጅ አባቢያ አባጆቢር መሆናቸው ይሰማል። ሹክሹክታው እውነት ከሆነ መረጃው ልብ የሚሰቅል ብቻ ሳይሆን፣ ጉዞው ወዴት እንደሆነ ለመገመት የሚያስቸግር ነው። ምክንያቱም ኦነግን ከወገብ በላይ ቆርጦ፣ ከወገብ በታች ኢህአዴግ ከሆነ ድርጅት ጋር ሰፍቶ ኢትዮጵያን የምታክል ሃገር መምራት እንዴት እንደሚቻል መገመት ስለሚያዳጋት ነው። መለስ ምንም ማድረግ የማይሳነው ብልጣ ብልጥ ፖለቲከኛ መሆኑን ባውቅም፣ ኦነግና ኦህዴድን አዳቅሎ ከኦህዴድ የተሻለ ታማኝ ድርጅት መፍጠር ግን የሚሳካለት መስሎ አይታየኝም። የመረጃውን እውነትነት የሚያጠናክሩ  አንዳንድ ተጨባጭ እንቅስቃሴዎችም መታየት ጀምረዋል። በሁለት በኩል አደገኛ ስለት ያለውን ይህን መረጃ ለማመንም ሆነ ለመጠራጠር ኦህዴድ ያለበትን ሁኔታ መገምገም ጠቃሚ ሳይሆን አይቀርም።
ርግጥ ነው፣ መለስ ዜናዊ በኦህዴድ ጠቅላላ ሁኔታ ተስፋ የቆረጠው አሁን አይደለም። ከመነሻውም ኦህዴድ ራስምታት እንደሆነበት ዘልቆአል። መለስ ላለፉት ሃያ አመታት ሙሉ ኦህዴድን ከመውቀስና ከመዝለፍ የተቆጠበበት ጊዜ አልነበረም። በ1986 ኦህዴድ ሁሉም ነገር ተበለሻሽቶበት በነበረበት ወቅት፣ መለስ አመራሩን ሰብስቦ፣ “…ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፣ እምቢ ካልክ ድንጋይ ተብለህ ትወረወራለህ” ብሎ ከተረተባቸው በሁዋላ “…ቀጥ ብላችሁ የማትሰሩ ከሆነ ተደራድሬ ኦነግን አምጥቼ አስቀምጣለሁ” ብሎ እንዳስፈራራቸው እኔ ህያው ምስክር ነኝ። በርግጥ በዚህ አባባሉ በህወሃት አመራር ውስጥ የደረሰበት የፖለቲካ ኪሳራ ቀላል አልነበረም። የኦህዴድ አመራር አባላት እንደ በረከት እና አዲሱ ለህወሃት ታማኝ ሊሆኑ አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን፣ በአቅም እጥረት ምክንያት ተጋልጠው እያጋለጡት ሲቸገር ኖሮአል። ይህ ብቻም ሳይሆን፣ የሃገሪቱን ሃብት መዝረፍ የስርአቱ ጠቅላላ ባህርይ ቢሆንም፣ የኦህዴዶቹ አዘራረፍ ጥበብ የለሽ በመሆኑ መለስን ሁልጊዜ አፈሰባራ የሚያደርጉት መሆኑ ሌላው ቁስሉ ነበር። በርግጥ እንደ ግርማ ብሩ አይነት ያነበቡ የኦህዴድ አባላት የአቅም ችግር ባይኖርባቸውም ከኢህአፓነት ማላቀቅ ለመለስ ቀላል አልነበረም። በዚህም ምክንያት ከመለስ ጋር ተማምነው ሰርተው አያውቁም። ለዚህም ይመስላል መለስ፣ በአንድ ወቅት ስለ ግርማ ብሩ ሲናገር፣ “…በቀጭን ክር ላይ መራመድ የሚችል ሰው” ብሎ የገለፀው። አባዱላ ገመዳ የፓርላማውን መዶሻ ከመረከቡ ከ18 ወራት በፊት ጀምሮ  ማግለል ተጀምሮ ነበር። ጁነዲን ከኢህአዴግ ጋር በቀጭን ገመድ ተንጠልጥሎ ቢገኝም፣ አንድም ጊዜ እምነት ተጥሎበት አያውቅም። አለማየሁ አቶምሳ ከመነሻውም በኦነግነት ይጠረጠራል። በኦነግነት የማይታማ የኦህዴድ ነባር አመራር አባል ቢኖር ጄኔራል ባጫ ደበሌ ብቻ ነበር። ባጫ ባለ ሰባት ፎቅ ባለቤትና የጦር መሳሪያ ንግድ ደላላ እንደመሆኑ ጊዜ አጊኝቶ ፖለቲካ ውስጥ ሊገባ አልቻለም። ኩማ ኦነግም፣ ኦሮሞም ሆኖ አያውቅም። ከዚህ ባሻገር ያለው ካድሬና ተራ የኦህዴድ አባል ሙሉ በሙሉ ፀረ ህወሃት ነው ማለት ይቻላል። ለዚህም ነው በረከት በአንድ ወቅት፣ “…እያንዳንዱ የኦህዴድ አባል ቢፋቅ ኦነግነቱ ፈጥጦ ይወጣል” ያለው። በርግጥ ኦነግ ላይ ቅሬታ ያላቸው በርካታ የኦህዴድ አባላት አሉ። ቅሬታቸው ግን “ኦነግ ደክሞ አዳከመን፣ አጋልጦ ለህወሃት አሳልፎ ሰጠን” በሚል ብቻ ነው። መለስ ይህን ሁሉ ጠንቅቆ ያውቃል። የመለስ ስልጣን በተንሸራተተችባት በማንኛዋም ደቂቃ ኦህዴድ ቀዳሚው የህወሃት አጥፊ እንደሚሆን መለስ አሳምሮ ያውቃል። በመሆኑም ከወዲሁ ለኦህዴድ ጉዳይ መላ ለመፈለግ መታሰቡ በእውነቱ የህወሃትን ደደብ አለመሆን የሚያመለክት ነው። ስለዚህ መለስ ዜናዊ የኦህዴድን መጪ አደገኛነት ለመቀነስ ኦህዴድን ለመሸጥ ቢያስብ ምክንያቱ አሳማኝ ሊሆን ይችላል። እዚህ ላይ ኦህዴድን የመሸጥ አስፈላጊነቱ ይሄ ብቻ ላይሆን ይችላል። የህወሃትም ሆነ የመለስ ስጋት ኦሮሞ ብቻ አይደለም። ከኦሮሞ ባላነሰ አማራንም ይፈራል። ከኦሮሞና ከአማራም ባልተናነሰ የትግራይንም ህዝብ ይፈራዋል። የሚፈራውን ህዝብ የሚመራ ሰው በየጊዜው የደከመበትንም ሆነ የጠነከረበትን ባልደረባ እየሸጠ መሄድ ቀላል የማይባል የፓለቲካ ብልሃት ነው። በመሰረቱ መለስ የማኪያቬሊ አንባቢና አድናቂ መሆኑን ልብ ይሏል። እራሱ የፈጠራቸውን ድርጅቶች ሲሸጥ መለስ የመጀመሪያው አይደለም። በአመራር ዘመኑ ውስጥ ህወሃትን ራሱን ብዙ ጊዜ እያፈረሰ ሲገነባ እዚህ ደርሷል። የኢህአፓ ግንጣይ የሆነውን ኢህዴንን በልኩ እየመተረ እየሰፋ እዚህ አድርሶታል። ኦህዴድም፣ ሲበተንና ሲሰበሰብ ከርሞ አሁን ለመጨረሻው ሽያጭ እየቀረበ ነው። መለስ ይህን ያደረገበት ምክንያት ኦህዴድ ባሁኑ ጊዜ አመራር አልባ ሆኖ ተስፋ በመቁረጡ ሊሆን ይችላል። የኦህዴድ የታችኛው መዋቅርም ከአሰራር ውጭ መሆኑ ይሰማል።
ሌንጮና ዲማ በበኩላቸው ኦህዴድን መግዛት በርግጥም ያዋጣቸዋል። ምክንያቱም ኦህዴድን ኦነግ ለማድረግ አንዳችም የቅስቀሳ ስራ መስራት አይጠበቅባቸውም። ጥቂት ወንጀለኛ አመራር አባላቱን በማሰናበት ብቻ ኦህዴድ በሰከንዶች ልዩነት ኦነግ ይሆናል። እዚህ ላይ ያልገቡኝና ያልተመለሱልኝ ጥያቄዎች ግን አሉ።
የመለስና የሌንጮ የመግባባትና የስምምነታቸው መሰረት ከቶ ምን ሊሆን ይችላል? የድርድራቸው ማእከልና ያግባባቸው የጋራ ፍላጎት ምንድነው? አልገባኝም። መረጃም የለኝም። ማለት የሚቻል ነገር ግን ይኖራል። ሌንጮና ዲማ የዋህ ፖለቲከኞች አይደሉም። የአበሻን ተንኮል አሳምረው የሚረዱ ናቸው። ያግባባቸው አንድ የጋራ የሆነ ማእከላዊ ነጥብ ግን የግድ ይኖራል። ከ2015 በሁዋላ መለስ (ስልጣኑን የሚለቅ ከሆነ?) በስልጣን ዘመኑ ለፈፀማቸው ጥፋቶች ተጠያቂ እንዳይሆን ማድረግ የድርድሩ ማእከል ሊሆን ይችል ይሆን? በርግጠኛነት ግን የድርድሩ ማእከላዊ ነጥብ ገንዘብና ሰልጣን ሊሆን አይችልም። ሌንጮ ለታ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትን፣ ዶክተር ዲማ ነገዎ ደግሞ የፊንፊኔ ከንቲባነት ቃል ተገብቶላቸው ሊሆን ይችላል። ይህም ቢሆን የስምምነታቸው ማእከላዊ ነጥብ ሊሆን አይችልም። ሌንጮና ዲማ በገንዘብና በስልጣን የመደራደር ሰብእና እንደሌላቸው በቅርብ የሚያውቃቸው ሁሉ ይመሰክርላቸዋል። ከመለስ ጋር የተደራደሩበትና ወደ ሰላማዊ ትግል ለመግባት የወሰኑበት ዋና ማእከላዊ ነጥብ የግል ጥቅም ሊሆን አይችልም። መርሃቸውን ለተራ ዝና ወይም ለቆሻሻ ገንዘብ ሊለውጡ አይችሉም። እንደኔ አስተያየት ሊያግባባቸው የሚችለው ዋና አጀንዳ ከወደፊቱ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ሌንጮ ለታ ደጋፊዎቹን ይዞ አዲሳባ በመግባት የቀጣዩ መንግስት ዋና ባልደረባ ከሆነ፣ የአካባቢያችን የፖለቲካ የሃይል አሰላለፍ ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ጥያቄ የለውም። “ለውጡ ማንን ይጠቅማል?” ለሚለው አንገብጋቢ ጥያቄ ግን ለጊዜው አስተያየት የለኝም። የማከብረው ኦቦ ሌንጮ ለታ ለሁለተኛ ጊዜ ታሪካዊ ስህተት እንደማይሰራ ግን ተስፋ አደርጋለሁ።

No comments:

Post a Comment