"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday 8 August 2012

“እስላም ክርስቲያኑ ባንድ ሆነ ፆማቸው… ከአምላክ ለመድረስ ቀጠሮ እንዳላቸው” ማን ያውቃል




የአሁኑ አመጣጤ ክርስቲያን ወዳጆቼን አንኳን ለፆመ ፍልሰታ አደረሳችሁ ለማለት እና ሙስሊም ወዳጆቼን ደግሞ የተጀመረው “ዱዓ” ይቀጥልልን ብሎ ለማበከር ቢሆንም “በልጅ አመካኝቶ ይበላል እንኩቶ” እንዲል እንኮቶ ያማረው አባት… እግረ መንገዴን  ከመጣሁ አይቀር ኮስተር ብዬ የማነሳው አንድ ጉዳይ አለኝ።

ትላንት አንድ መረጃ ለጥፌ ነበር። መረጃው “በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በህቡዕ የሚንቀሳቀስ” አንድ ንቅናቄ ያወጣው መግለጫ ነበር። ይህ መግለጫ “የሰራዊቱ አባላት ከዚህ በኋላ ህዝብ ላይ አንተኩስም እስከ መቼ ለአምባገነን መሪዎች አግዘን፤ እኛ መሳሪያ ታጥቀን ቀበቶ እና መቀነት ብቻ የታጠቀውን ህዝብ እንደበድባለን!? ይሄ ነገር ነውር መሆኑን አየን ከዚህ በኋላ እንዲህ አይነት ነገር ላለመፈፀም ዝግጅታችንን አጠናቀናል”  የሚል ነበር።

ታድያ በዚህ ወሬ የተነሳ በርካታ አስተያየቶችን ተቀብያለሁ። “እሰይ የኔ ወሬ አቀባይ በርታልኝ” ብለው ያበረታቱኝ እንዳሉ ሆነው አንዳንድ ወዳጆች ደግሞ “አንተ ከሀገር ወጥተህ እኛን ልታስጨርስ ነው!” የሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል። ይህ ወቀሳ ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች ፉርሽ መሆኑን እንደሚከተለው አስረዳለሁ!

ሀ    የንቅናቄው መግለጫ የሚለው የመንግስት ግልበጣ ላድርግ አይደለም፣ ጫካ ገብቼ ጦርነት ልክፈትም አላለም። ከዚህ በኋላ መንግስት ተኩስ ባለኝ ቁጥር ግን ህዝቤ ላይ አልተኩስም ነው ያለው።  በኛ የጨዋታ ስልት ሲቀርብ ደግሞ “ክላሽ እኮ ካውያ አይደለም… ሰውን ያበላሻል እንጂ ልብስን አያሳምርም!”  ስለዚህ ከእንግዲህ ፖሊስም ሆነ ሌላው የጦር ሃይል ከህዝቡ ወገን ነው እንጂ የህዝቡ ወጊ አይደለም ነው ያለው። ታድያ ይሄ እንዴት ሆኖ ነው ህዝብ ማስጨረስ የሚሆነው??? (ጥያቄ ምልክት ጨምሩልኝ!)



ለ    ንቅናቄው ይቺን ብሎግ እንደሚዲያ አክብሮ መግለጫውን ላከልኝ እኔም ጉዳዩ የህዝብ ነውና ለአንባቢያኖቼ አካፈልኩ እንጂ መግለጫውን ያወጣሁት እኮ እኔ አይደለሁም። እኔ ከሀገር ብወጣም ባልወጣም ይህ ንቅናቄ መፈጠሩ አይቀርም ነበር። እንጂ እኔ ኮሎኔር አይደለሁ ጄነራል አይደለሁ… (አማረኝ እናንተ ሃሃ…!) “እዛ ሆነህ ልታስጨርሰን” የምባለው በምን የተነሳ እንደሆነ አልገባኝም።

በጥቅሉ ከዚህ በፊትም አንዳንድ ወዳጆች ከመሬት ተነስተው፤ “እዛ ሆናችሁ እኛን ልታስጨርሱ” እያሉ በውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ ላይ ወቀሳ መሰንዘር አመል ሆኖባቸዋል። አንዳንዴማ አሜሪካ እና አውሮፓ ለሚደረግ ተቃውሞ ሰልፍ ሁሉ “እዛ ሆናችሁ አታስጨርሱን!” የሚሉ ወቀሳዎች ይመጣሉ። የሚገርመው ብዙ ግዜ እንደዚህ የሚሉት ከእኛ በላይ “ለመንግስት አሳቢ ላሳር” የሚሉ የመንግስታችን ደጋፊ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ናቸው። እውነቱን ለመናገር እነዚህ ወዳጆቻችን የሚደግፉት “ይጨርሰናል” የሚሉትን መንግስት ከሆነ፤ በጨራሽነታቸው ወደር የሌላቸውን እንደ “አተት” የመሳሰሉ በሽታዎችን እንደደገፉ አውቀው ዛሬ ነገ ሳይሉ ንስሃ ሊገቡ ይገባል።

እኔ በበኩሌ መንግስቴ “ጨራሽ” ነው ብዬ አላምንም… (አሁንማ እራሱ አልቋል…! ብለው አያሽሟጡ… እኔ ስለ እርሳቸው አላወራሁም!) ነገር ግን ከእኔ የበለጡ የመንግስቴ ደጋፊዎች እንደሚሉት “ጨራሽ” እንኳ ቢሆን፤ “አንተ ውጪ ሆነህ እኛን ልታስጨርስ” የሚለው ንግግር አግባ አይደለም። ለመሆኑ እኔ ወጥቻለሁ እንዴ!? እኔም ሆንኩ ሌላው በውጪ ሀገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ከተሰደደው እሱ ይልቅ ሀገር ውስጥ ያለው እሱ አይበልጥምን!? እውነት እውነት እላችኋለሁ ውጪ ካለሁት እኔ ይልቅ ሀገር ውስጥ የቀረሁት እኔ የእጥፍ እጥፍ እበልጣለሁ።  እናም የማስጨርሰው ሌላ አካል የለም። የሰማሁትን ወሬ ማቀበል ማንንም የማስጨረስ አላማ የለውም። ሰዎቻችን አይምሯቸው ተነክቶ ሊጨርሱን ከተነሱ ደግሞ የማልቀው እኔው ራሴ ነኝ!  “የገደልንም እኛ የሞትንም እኛ” ያሉት ማን ነበሩ…!?

ለማንኛውም ክርስቲያን ወዳጆች እንኳን ለፆመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ። እንግዲህ አሁን እስላም ክርስቲያኑ ፆሙ ገጥሟል።  ሁለቱም ወገኖች በየ ቤተ አምልኳቸው ከሚያደርጉት ፀሎት በተጨማሪ በየ እስር ቤቱ መከራቸውን የሚያዩ ዋና ዋና ወኪሎች አሏቸው። ለክርስቲያኑ የዋልድባ መነኮሳት ለሙስሊሙም የአንዋር ኡስታዞች በር ተቆልፎባቸው ወደ አምላክ እየጮሁ ነው።

ከዚህ ስንንነሳ ዘንድሮ ፆማችን ብቻ ሳይሆን መከራችንም ገጥሟል ማለት ይቻላል። ይህም ወዳጅነታችንን ያጠነክረዋል። አንዳችን ለአንዳችን  ድምፃችንን ከፍ አድርገን ከፀለይን ደግሞ ከፈጣሪ ዘንድ ተሰሚነታችን ይጨምራል። እናም እንበርታ…!

ወደ በኋላ በሌላ ጨዋታ እስክንገናኝ… ሰላም ይቆዩኝ ወዳጄ!

No comments:

Post a Comment