"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Friday 31 August 2012

ከኢቲቪ ምስሎች በስተጀርባ – የሚዲያ ትንተና – በያሬድ ጥበቡ


ዳያሰፖራ ውስጥ በምንኖረው ኢትዮጵያውያን መሃል የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕይወትና ሞት እንዳከራከረን ኖሮአል ። ሰሞኑን ደግሞ የሽኝት ስርአታቸው ሌላው ድራማ ነው ። ዛሬ 10ኛ ቀኑን የያዝው ይህ ድራማ ራሱን ለፖለቲካ ትንታኔ በሚያውስ መልኩ እየተተወነ ይገኛል ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ቦሌ አየር ማርፊያ ሲደርስ፣ የኢቲቪ ካሜራ ትኩረት አቶ በረከት ላይ ስለነበረ፣ “የመለስ መንግስት ወራሸ ሰለሆኑ መሆን አለበት” የሚል ትርጉም ነበር የሰጠኝ ።
የወያኔ አመራር አባላትን ለማየት ብሞክር ከስዩም መስፍን በቀር አንዳቸውም አይታዩም ። “እየዶለቱ ቢሆን ነው ቦሌ ያልተገኙት” ብዬ ከራሴ ጋር ተሟገትኩ ። የሃዘኑ ትርኢት ቀጠለ፣ ሆኖም የነዚህ የወያኔ ቱባ ባለስልጣኖች ክስመት እተጋነነ ሄደ ። ወዴት ገብተው ይሆን ብለን ስንጨነቅ፣ ዕድሜ ለአውራምባ ታይምስ፣ የመለስ ወንድም ቤት ሐዘን መቀመጣቸውንና፣ አቦይ ስብሃት “መለሰ ብቻውን አይደለም የሞተው፣ ወያኔን ቀብሮ እንጂ ነው!” እያሉ ማንባታቸውንና በጠባብ ብሄርተኝነትና በሙስና እየተከሰሱ ከድርጅቱ የተባረሩትንና የተሰናበቱትን ሁሉ ማሰባሰብ መጀመራቸውን ሰማን ። ከዚህ ዜና ብስረት በሁዋላ ደግሞ የሚከተሉተን የሚዲያ ትዝብቶች ለማድረግ ቻልን ።
በሚቀርቡት የመለስ ገድሎች ሁሉ፣ ተሓህት፣ ህወሓት፣ ወያኔ የሚባሉ ድርጅቶች ውስጥ የታገሉና የመሩ መሆናቸውን በሚያስረሳ መልኩ፣ መለስ ከኢህአዴግና ኢትዮጵያ ጋር ብቻ ተዳብለው እንዲታዩ ተደረገ ። ከጎንደርና ወሎ ገበሬዎች ጋር ሲወያዩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ይበልጥ አመዘኑ ። ስለ ስውዬው ማንነትም ሰብዕናቸውን የሚመሰክሩት እነ ስብሃትና አባይ መሆናቸው ቀርቶ እነ ሬድዋንና ኩማ ሆኑ ። የወያኔ መሪዎች ወይ አኩርፈው አንተባበርም ብለዋል፣ ወይም ኢቲቪ መንደር ድርሽ እንዳይሉ ታግደዋል ። መለስ የብሄረሰቦችን እስር ዘለው ለኢትዮጵያ ሴቶችና ወጣቶች ህይወታቸውን የሰጡ ታጋይ ሆነው ቀረቡ ። በዚህ ሁሉ መሃል የወያኔ አንጋፋዎች ምስል ተዳፍኗል ።
እሮብ በማለዳ በ12 ሰአት ዜና ላይ ቀዳሚዎቹ ሶስት ዜናዎች፣ በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ቢሾፍቱ በሚገኙ የአየር ሐይል አባላት፣ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ሰራተኞች ለጠቅላይ ሚኒሰትሩ ራዕይ ቀጣይነትና ለህገ መንግስቱ ያላቸውን ታማኝነት መግለጻቸውን የሚያበሰር ነበር ። ጥያቄው ለምን ይህ አስፈለገ የሚል ነው ። ለህገመንግስቱ ያላቸውን ታማኝነት ይዞ ምን ለማድረግ? አሰላለፉ ግልፅ ይመስላል ። የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ራዕይ እናስፈጽማለን ብለው በአቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ዙሪያ በበረከት አስተባባሪነት ሚዲያውን ይዘው በቆሙትና፣ ኒቆዲሞስ መኖሪያ ቤት ዙሪያ በተኮለኮሉት የወያኔ ጎምቱዎች ። ይህንኑ ጥርጣሬ የሚያጠናክሩ ትርኢቶችም በዛሬው ዕለትም ቀጥለዋል ።
ሐሙስ ምሽት የአዲስ አበባ ሴቶች የጧፍ ማብራት ትዕይንት በመስቀል አደባባይ ነበር ። መድረኩ ላይ ግዙፍ ከሆነው የመለስ ፎቶግራፍ ስር፣ በህይወታችው ሳሉ ያልተደመጡትና ስንናፍቀው የኖርነው “በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ…” የሚል ጥቅስ ይታያል ። ሴቶች ሲያነቡ፣ ሲገጥሙ ከቆዩ በሗላ ምክትል ከንቲባው አቶ አባተ ስጦታው ብቅ ብለው፣ የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ራዕይ ከመተግበረና አንድነታቸንን ከመጠበቅ የሚቀናቀኑንን እናወግዛለን ይሁን እናወድማለን የሚል አንድምታ ያለው ንግግር አደረጉ ። ለመንግስት የውጪ ተቃዋሚዎች ያልተሰነዘረ መሆኑን በሚያሳበቅ መልኩ ነው ያን ያሉት ። ለምን? በመስቀል አደባባዩ ሰልፍ ማሳረጊያ ላይ አስተባባሪው “የፌዴራል ፖሊስ የሙዚቃ ባንድ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙርን ማርሸ አሰምቶ ሰልፉ ይጠናቀቃል” ቢሉም፣ አስቀድሞና መዝሙሩን ተከትሎ የቀረበው ግን ኢህዴን ውስጥ ሳለን ህላዌ ዮሴፍ ያቀነባበረው፡
ስንቶች ተኮላሽተው ከአረንቛ ዘቀጡ
ሰንቶች ተደናብረው ከጎዳና ወጡ፤
ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው
ነግ እልፍ እንሆናለን ታሪክ ምስክር ነው
የሚለው መዝሙር ነበር። ለምን?
የመዝሙር ነገር ካነሳን አይቀር፣ ህወሓት ስለ መስዋእትነት ብዙ የዘመረ ድርጅት መሆኑን እናውቃለን ። እኔ ራሴ እንኳ የምዘምረው “ጀጋኑ ብጾት” አንዱ ነው ። ሆኖም በትግራይ ቲቪ ፕሮግራሞች እንኳ እነዚያ መዝሙሮች አይደመጡም ። የአማርኛ ዋሸንትም በእኩል ደምቆ ይቀርባል ።
ምናልባት ይህ ሁሉ በወያኔ መሪዎች ትብብር፣ የመለስን የመጨረሻ ስንብት እድሜ ልኩን ሲዋጋ የኖረውን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ተቀበሎ እንዲሄድ የሚደረግ፣ ይዞት ከቆየው ስልጣን ጋር የሚመጣጠን የፖለቲካ ሽግግር ሊሆን ይችላል ። ይህ ቢሆን እሰዬው ነው ። ትልቅነት ነው ። ምናልባትም የህወሓት አመራር አባል የሆኑት አቶ አባይ ፀሃዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ በኢቲቪ መታየታቸው ተፋጠው የቆዩት ቡደኖች መሃል ዕርቀ ሰላም መውረዱን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል ። ወይም ቀድሞ ወያኔ ውስጥ በነበረው ክፍፍል እንዳደረጉት ሁሉ፣ ተሸናፊውን ወገን የማሽተት ክህሎት ያላቸው ሰው ሰልፍ ማስተካከላቸውም ሊሆን ይችላል ። ሆኖም ከኒቆዲሞስ ግቢ ድንኳን የሚሰማው ልቅሶ ግን ያንን አይጠቁመንም ። እንዲያውም ፍርሃትህ ምንድን ነው ብትሉኝ፣ እነ በረከት “ሁሉን ነገር በቁጥጥር ስር አድርገናል ሽግግሩ ከቀብር በሗላ ቀስ ብሎ ይደርሳል” ብለው በፈጠሩት የሚዲያ የበላይነት ሲዝናኑ፣ “ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረስናቸው” የሚል አምባገነን እንዳይቀድማቸው ነው ።
 

No comments:

Post a Comment