"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Monday 22 October 2012

‹‹‹‹‹‹ቃሊቲ››ን በጨረፍታታታታ በተመስገን ደሳለኝ





ከአውራምባ ታይምስ
‹‹ቃሊቲ››ን በጨረፍ ‹‹‹‹‹‹ቃሊቲ››ን በጨረፍታታታታ
በተመስገን ደሳለኝ
ክፍል-፪
የዛሬ አስራ አምስት ቀን የቃሊቲ ትርክቴን ያቆምኩት ምን ላይ ነበር? … ያን አስከፊ እስር ቤት አንስቼ ለመጣል ከአፋፍ ደርሼ ነበር መሰለኝ፡፡ ኧረ እንዲያውም በፍርድ ቤት ፖሊስና በቃሊቲ ፖሊስ መካከል ርክክቡ ሁሉ ተፈፅሟል፡፡ ያውም ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር በአንዲት ብጣቂ ደረሰኝ! (ልውውጡ እንዲህ ነው፡- የፍርድ ቤቱ ፖሊሶች እኔን ሰጡና በልዋጩ ከቃሊቲ ፖሊሶች አንዲት ካርኒ ተቀበሉ) መቼም የአገሬ መንግስት በሚጠቅመውም በማይጠቅመውም ንፉግ መሆን ስለሚወድ እንጂ ደረሰኙን ሁለት ቢያደርገው ምን ይጎዳ ነበር?
ጥራዝ ሙሉ ቢሆንስ? ለሰው ልጅ…? የሰው ልጅ መሆኔ ነው… ‹‹የሰው ልጅ መሆኔ ነው…››የሚል ዘፈንህ በሬዲዮን፣ አሊያም በሌላ መንገድ ሰምተኸው ይሆናል፤ ቃሊቲ ግን ይሄ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ወንጀለኛ›› ነህ፡፡ በወንጀለኛና በሰው ልጅ መካከል ደግሞ ትልቅ ልዩነት አለ-በቃሊቲ፡፡
…ዕድሜዋ በግምት ወደ 50 የሚጠጋ፣ በክንዷ ላይ የአስር አለቃ ማዕረግ የለጠፈች (ሳጅን) በጥያቄ ታጣድፈኝ ጀመር፤ ለነገሩ በጥፊ ከመጣደፍ በጥያቄ መጣደፍ በብዙ የተሻለ ነው ብዬ ስለገመትኩ ያለቅሬታ ነበር የጠየቀችኝን ሁሉ የመለስኩላት፡፡
‹‹ስምህ ማነው?›› የተረከብሽበት ወረቀት ላይ አለልሽ ልላት አሰብኩና ተውኩት፡፡ በምትኩ ሙሉ ስሜን ነገርኳት፡፡
‹‹ብሔርህ ምንድን ነው?››፣ ‹‹እግዜዬር ይይልህ ኢህአዴግ!›› በሆዴ ያልኩት ነው፡፡ በአፌ ግን እንደምንም ቀጣጥዬና ሰፋፍቼ ብሄሬን ተናገርኩ፡፡ መቼም በብሶት ተወልዶ፣ ለበርካታ ብሶቶች መወለድ መንስኤ የሆነው ኢህአዴግ በእግዜር ፊት ለፍርድ ቢቀርብ (በሰው ፊት እንኳ ይቀርባል ብሎ ማሰቡ አዳጋች ነው) ከሚከሰስባቸው ክሶች መሀከል ዋነኛው ሀገሬውን በአያት ቅድማያቱ (አያት ቅድማያቱን የማያውቀውን ደግሞ በሩቅ ዘመዱ)

በመከፋፈሉ ይመስለኛል፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ሐረሪ፣ አፋር… የሆነ ሆኖ የሳጅን ጥያቄ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን አስታወሰኝ፡፡ ‹‹ፕሮፍ›› ከሚጠሉት ጥያቄ ሁሉ
‹‹ብሔርዎት ምንድን ነው?›› የሚል እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ዛሬም ድረስ የሚጠቀሙበት የቀበሌ መታወቂያ ‹‹ብሔር›› የሚለው ቦታ ላይ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› የሚል ውድ ቃል ተፅፎበት ይገኛል፡፡ ይህ የሆነው ግን በቀበሌዎቹ በጎ ፍቃድ አይደለም፡፡ በፕሮፍ የማይታጠፍ ብርቱ ተቃውሞ እንጂ፡፡ እናም ከ80 ሚሊዮን ህዝብ የቀበሌ መታወቂያም ላይ ሆነ የምርጫ ካርድ ላይ ብሔሩን ሳያፅፍ የወሰደ ብቸኛ ሰው ቢኖር ፕሮፍ ይመስሉኛል፡፡
እንዲያውም እርሳቸው ይንገሩኝ፣ ከመጽሐፎቻቸው ወይም ከቃለ መጠይቆቻቸው ላይ በአንዱ ላንብበው ማስታወስ ተሳነኝ እንጂ እንዲህ ብለው ነበር፡- ‹‹የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ አንድ መምህር ነበሩ፡፡ ሁልጊዜም ክፍል ገብተው ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት ‹እናንተ ምንድር ናችሁ?› ሲሉ ይጠይቁናል፤ ‹የሰው ልጅ› ስንል እንመልስላቸዋለን፡፡ ይህ ሁኔታም ሶስት ጊዜ ከተደጋገመ በኋላ ነው ትምህርት የምንጀምረው፡፡›› እንግዲህ ፕሮፍ የሚሉን በአንድ ሀገር ውስጥ ተከልለው በአንድነት የሚኖሩ ህዝቦች ሊተሳሰሩበት የሚችሉት ‹‹ሰው›› በሚለው ክቡር ቃል ብቻ ነው፡፡
ኢህአዴግ ከዚህ አይነቱ አመለካከት ደም የተቃባ ነው፡፡ የሉሲ ዘሮች እንደሆንን ይደሰኩርልናል እንጂ አማራ የሚባል ዝንጀሮ፣ ኦሮሞ የሚባል ዝንጀሮ፣ ትግሬ የሚባል ዝንጀሮ… የት እንደሚገኝ አይነግረንም፡፡
ሰለዚህም የየብሄራችንን አባወራ ዝንጀሮ ካልነገረን በብሔር መከፋፈላችንንም አለመቀበል እንችላለን፡፡ ወይም ‹‹ሉሲ›› የተሰኘችው ምንጅላታችን የዝንጀሮ ዝርያ አይደለችም የሚል ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ሊሰጠን ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ራሱ ኢህአዴግ አቶ መለስ እንደሚሉት (ነፍሳቸውን ይማረውና) አጥር ላይ ተንጠልጥሏል፡፡
መቼም ሳጅን ብሔሬን የጠየቀችኝ ልትጎዳው ወይም ልትጠቅመው የምትፈልገው ብሔር ኖሮ አይመስለኝም፡፡ ትዕዛዝ ሆኖባት እንጂ፡፡ (በነገራችን ላይ ቃሊቲ ያለው አድሎና መድሎ በብሔር ላይ የተመሰረተ
ነው ብዬ አላስብም፡፡ ወይም ለአጭር ጊዜ ብቻ በመታሰሬ ሳላስተውል ቀርቼ ይሆናል፡፡ ሆኖም በጥቂት ቀናት ቆይታዬ እንዳየሁት ከሆነ በቃሊቲ ያለው ግልፅ አድሎ እና መድሎ ተከሳሹ በፈፀመው ወይም በተጠረጠረበት ወንጀል ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ለምሳሌ የሶስት ዓመት ህፃንን አስገድዶ የደፈረ ወይም የሰው ገንዘብ ለመዝረፍ ሲል ንፁሃንን የገደለ ከየትኛውም ብሔር ቢመጣ ከእስረኝነት መብቱ ላይ ጥቂት እንኳ አይሸረፍበትም፡፡ በግልባጩ የተከሳሹ ወንጀል ከኢህአዴግ ጋር የተያያዘ አሊያም መንግሥትን አስከፍቶ ከሆነ እውነት እውነት እልሀለሁ ለእርሱ ቃሊቲ የተረገመ ምድራዊ ሲኦል ነው፡፡ መብቱ ብቻ ሳይሆን ከራሱ ላይም አንዳች ነገር ሊጎድል ይችላልና፡፡
ለምሳሌ እስክንድር ነጋ ከቤተሰቡ ውጭ ሌላ ዘመድ ወዳጅ እንዳይጠይቀው ፅኑ ዕግድ ተጥሎበታል፡፡ አንዱአለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፣ ናትናኤል መኮንን እና ስማቸውን የማላስታውሰው ሌሎች ለውጥ ፈላጊዎች የዚህ ገፈት ቀማሽ ናቸው፡፡ ርዕዮት አለሙ ደግሞ ጠያቂ ባይቀነስባትም፣ የመጠየቂያ ሰዓት ተቀንሶበታል፡፡ ርዕዮት አብረዋት እንደታሰሩ ሴቶች ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ እንድትጠየቅ አልተፈቀደላትም፡፡ የርዕዮት መጠየቂያ ሰዓት ከስድስት ሰዓት እስከ ስድስት ተኩል (ለ30 ደቂቃ) ብቻ ነው፡፡ እናም በየመንደሩ ሳይቀር የሚሹለከለኩ የባቡር መስመሮች እዘረጋለሁ፣ አባይን እገድባለሁ የሚለው ኢህአዴግ እንዲህ ነው፡፡ ግለሰብን ሳይቀር ለማበሳጨት፣ ለማማረር የማያንቀላፋ መንግስት፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻ ደግሞ ታሳሪዎቹ ፀባቸው ከመንግስት ጋር ስለሆነ ብቻ እንደሆነ ደግሜ እነግርሃለሁ፡፡
‹‹የምትሰራው ምንድን ነው?››
‹‹ጋዜጠኛ ነኝ›› ካቀረቀረችበት ቀና ብላ አየችኝ፡፡ እንደገና አይኗን ወደ ክስ ቻርጁ መለሰች፡፡ ደግማ ከላይ
እስከታች ገረመመችኝ፡፡ አንዴ ወደ ክስ ቻርጁ፤ አንዴ ወደእኔ እያፈራረቀች ስትመለከት ነገረ ስራዋ ግራ አጋብቶኝ
‹‹ምነው! ችግር አለ?›› ስል ጠየኳት፡፡
‹‹ምንም ችግር የለም፡፡›› ጫን ባለ ድምፅ ቀጠለች ‹‹ምን አድርገህ ነው የታሰርከው?››
‹‹ክስ ቻርጁ ላይ አለልሽ››
‹‹ክስ ቻርጁ በደንብ አይገልፅም››
‹‹ደጋግመሽ እይው፤ እኔም ለራሴ አልገባኝም›› ከፊት ለፊቷ ተቀምጦ በተመሳሳይ መልኩ አንድ እስረኛን
እያናዘዘ ላለ ጎልማሳ ፖሊስ ክስ ቻርጁን አቀበለችው፡፡ እሱም ለደቂቃ ካተኮረበት በኋላ እንዳልገባው ገልፆ መልሶ
እኔኑ ጠየቀኝ፡፡
‹‹ለእኔም ግልፅ አይደለም›› ለእርሷ የነገርኳትን ደገምኩለት፡፡ ይህን ጊዜ ‹‹ዝም ብለሽ ቻርጁ ላይ ያለውን
ፃፊው›› አላት፡፡ ሳጅኗም በክስ ቻርጁ መሰረት ‹‹የሰውን ሃሳብ ማናወጥ እና ማሳመፅ›› በሚል መዘገበችው፡፡ የሰውን ሃሳብ በምን ይሆን ያናወፅኩት?
ከዚህ በኋላ አሻራ እንድነሳ ተደረገና ከሰባት እስረኞች ጋር ወደ ሌላ ክፍል ተወሰድኩ፡፡ በክፍሉ ውስጥ ያለው ፖሊስ ቁጡ ይመስላል፡፡ ገና ከመድረሳችን ‹‹ውጡ፣ ተሰለፉ….›› በሚሉ ትዕዛዛት በጩኸት አጣደፈን፡፡ ይኸው ፖሊስ በረድፍ አሰልፎን ሲያበቃ በየተራ እያስገባ ፎቶ እንድንነሳ አደረገና ግዴታውን ጨርሶ ወደ ሌላ ክፍል አስገባን፤ አሁን የተረከበን ፖሊስ ደግሞ ‹‹ፈታሽ›› ነው፡፡ የያዝናትን እያንዳንዷን እቃ ልምድ ባካበቱ እጆቹ በጥንቃቄ በርብሮ ሲያበቃ ኪሶቻችንን ፈተሸና ስራውን ጨረሰ፡፡ እነዚህ ሂደቶች የሚያጥሩት እንዲህ በአጭሩ ሲተረኩ እንጂ ሲተገበሩማ ከአንድ ሰአት ከግማሽ በላይ ይወስዳሉ፡፡
ከዚህ በኋላ የቀረው በቦታው ያለነውን እስረኞች ወደመታሰሪያ ቤት ማስገባት ነውና ሰባቱን እየነዱ ከወሰዱ በኋላ ለእኔ ‹‹አንተ እዚሁ ቆይ!›› የሚል ፖሊሳዊ ትዕዛዝ ሰጡኝ፡፡ ሁኔታው ግራ ቢያጋባኝም እንደታዘዝኩት ክፍሉ ውስጥ ባለ አግዳሚ ወንበር ላይ አረፍ ብዬ ከእስረኞች ለምን እንደተለየሁና ቀጥሎ ምን ሊከሰት እንደሚችል ማንሰላሰል ጀመርኩ፡፡ እንዲህ እያንሰላሰልኩ ለካስ እንቅልፍ ወስዶኝ ኖሯል፡፡ እናም በግምት ከአንድ ሰአት በኋላ ‹‹ተነስ!›› የሚል የፖሊስ ትዕዛዝ ከሸለብታዬ አናውጦ ቀሰቀሰኝ፡፡ ዕቃዬን ይዤ እንድወጣ ተነገረኝ፡፡ እኔም ወጣሁ፤ መጀመሪያ ከሳጅን ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ያገኘሁት ፖሊስ እየመራ እኔ እየተከተልኩ አንድ አነስተኛ ግቢ ጋ
ስንደርስ ‹‹እዚህ ጋ ቁጭ በል›› ብሎኝ እርሱ ወደ ግቢው ውስጥ ገባ፡፡ (በነገራችን ላይ ቃሊቲ እጅግ በጣም ሰፊ
ግቢ ቢሆንም ውስጡ በበርካታ ግቢዎች የተከፋፈለ ነው) ጥቂት ቆይቶ ተመልሶ መጣ፡፡ እኔን አልፎም ከግቢው በር ፈንጠር ብለው ወደቆሙ ሁለት ‹‹ኮማንደሮች›› አጠገብ ሄዶ ወደእኔ አቅጣጫ በጣቱ እየጠቆመ የሆነ ነገር ነገራቸው፡፡ ኮማንደሮቹም ለደቂቃ ያህል ከተመለከቱኝ በኋላ ፖሊሱ የሚነግራቸውን ማዳመጥ ጀመሩ፡፡ በእኔ ጉዳይ እየተነጋገሩ እንደሆነ ቢገባኝም ምን እያሉ እንደሆን ላውቅ አልቻልኩም፡፡ ከሁኔታቸው ግን አንድ ያልተግባቡበት ጉዳይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ከጥቂት መወዛገብ በኋላ ሰውነቱ ደንደን ያለው ኮማንደር በመገናኛ ራዲዮኑ ተነጋግሮ ሲያበቃ ወደእኔ ተጠግቶ ከፊት ለፊት ባለው የጥበቃ ማማ ላይ የተቀመጠውን ፖሊስ ጠርቶ በቁጣ ይፈትሸኝ ዘንድ አዘዘው፡፡ ይህ ኮማንደር ከፍርድ ቤት የተረከበውን እስረኛ ሳይሆን በከባድ ውጊያ ላይ የማረከውን ጠላቱን የሚያናግር እስኪመስል ድረስ ምንጭቅጭቅ አደረገኝ፡፡ በምን ተከስሼ እንደመጣሁና ማን እንደሆንኩ ይዞኝ የመጣው ፖሊስ ሳይነግረው አልቀረም፤ እንደ ክፉ ባላጋራው አየኝ፡፡ በድጋሚም ዕቃዬ
ተመነቃቅሮና ኪሴ ተበርብሮ ተፈተሸ፡፡ ኮማንደሩ ፍተሻውን በጥንቃቄ እየተከታተለ ነው፡፡ ፈታሹ ፖሊስ ከያዝኩት ፌስታል ውስጥ ቲሸርቶችን ማውጣት ሲጀምር ‹‹ቲ-ሸርቶቹ ፅሁፍ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው አረጋግጥ›› ሲል ኮማንደሩ ትዕዛዝ ሰጠ፤ መቼም ኮማንደር በያዝኩት ቲ-ሸርት ላይ ‹‹ስሜ ተጠቅሶ እረገማለሁ›› ወይም ‹‹እወገዛለሁ›› ብሎ እንደማያስብ ስለማውቅ ምን አይነት መልዕክት ያለው ፅሁፍ ከቲሸርቶቼ ላይ እየፈለገ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ፍተሻው እንዳለቀ ‹‹ዕቃህን ሰብስብና ተከተለኝ!›› አለ-ከመሬት ተነስቶ የጠላኝ ኮማንደር፡፡ ጓዜን እንደምንም ሸካክፌ ተከተልኩት፡፡ ከላይ የጥበቃ ማማ ያለበት ከሲሚንቶ የተሰራ ቤት ጋ ስንደርስ ቆመና ከኪሱ ቁልፍ አውጥቶ ከፈተው፡፡ ሶስት በሶስት የምትሆን ኦና ቤት፡፡ ‹‹ግባ!›› ከአስደንጋጭ ቁጣ ጋር ተያይዞ የመጣው የኮማንደር ትዕዛዝ፡፡
ባዶዋ ክፍል ከገባሁባት በኋላ በሯ ከውጭ ሲዘጋ ሙሉ በሙሉ አይንን በሚወጋ ጨለማ ተዋጠች፡፡ ከጨለማው በተጨማሪም ክፍሏ አንዳች ክፉ ሽታ አውዷታል፡፡ ‹‹ምንድር ነው የሚሸተው? እነዚህ ሰዎች እንደደርግ ዘመን ሰው እየገደሉ ይቀብራሉ እንዴ?›› በውስጤ አሰብኩ፡፡ በእርግጥ ደርግ የአፄ ሃይለሥላሴ ባለሥልጣናትን እና ‹‹ፀረ አብዮተኛ›› ያላቸውን ወጣቶች ከርቼሌ ግቢ ውስጥ ገሎ እንደቀበረና ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ አፅማቸው በቁፋሮ እንደወጣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሰማሁት ወሬ ድንገት ትዝ ብሎኛል፡፡ ሆኖም ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ ፍራሼን አንጥፌ ጋደም አልኩ፡፡ ከግማሽ ሰአት በኋላ ሽታውንም ጨለማውንም ለመድኩት፡፡ ከውጭ የዘቦቹ ኮቴ ይሰማል-የጥበቃ ማማው ላይ ሲወጡና ሲወርዱ፡፡ የመፅሀፍ ቅዱሱ ያዕቆብ በበረሃ ተኝቶ መልአክት ሲወጡና ሲወርዱ አየበት የተባለው መሰላል ትዝ አለኝ፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ በግምት ለሰአታት ከቆየሁ በኋላ ቀን ፍርድ ቤት ከአንበሳ ቤት የእስር ጓደኛዬ ጋር ተካፍዬ ከበላሁት በርገር ውጭ ምንም እንዳልበላሁ ትዝ ሲለኝ ረሃብ
ሞረሞረኝ፡፡ እናም በያዝኩት ፌስታል አንዳች የሚበላ ነገር እንዳለ ስለማውቅ ከተጋደምኩበት ተነስቼ ፈታተሽኩ፤ በርገር አገኘሁ፡፡ አወጣሁት፤ ሁለቴ እንደገመጥኩለት በጨለማ መብላቱ እንደአንዳች ነገር ስለቀፈፈኝ፣ የታሰርኩበትን ክፍል በር መደብድብ ጀመርኩ፡፡ ከውጭ ያለ ፖሊስ
‹‹ምን ፈለክ?›› አለ በአስገምጋሚ ድምፅ፤
‹‹በሩን ክፈትልኝ››
‹‹ለምን?››
‹‹በጨለማ ራት መብላት አልቻልኩም›› ‹‹ተወውና ተኛ! አይከፈትም››
ይህን ግዜ አእምሮዬ ወደህንድ ይዞኝ ነጎደ፡፡ መፃሀፉን ባላስታውሰውም አንድ ያነበብኩት ነገር ትዝ አለኝ፡፡
በሒንዱ ኃይማኖት ጀንበር ካዘቀዘቀች በኋላ ምግብ አይበላም፡፡ ይህ ከእምነቱ ትዕዛዛት አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በጨለማ ሲበላ ነፍስ ያለው ነገር ከምግቡ ጋር ተደባልቆ ነፍስ እንዳይጠፋ ለኃይማኖታዊ ጥንቃቄ ነው፡፡
እኔ ግን እንደው ምክንያቱን ሳላውቀው በጨለማ መብላቱን ጠላሁት፡፡ እናም ፖሊሱ እንዳለው ትቼው እንደራበኝ ተኛሁ፡፡ …የሚያነጋግሩት ሰው ሳይኖር፣ ያውም በጨለማ የተዋጠ ክፍል ውስጥ ለብቻ መሆን እንዴት ይጨንቃል?
መቼና እንዴት እንቅልፍ እንደወሰደኝ አላወኩም፡፡ ብቻ የጭለማ ቤቷ በር ተንጓጉቶ ተከፈተና ለሽንት እንድወጣ ተነገረኝ፤ በማረሚያ ቤቱ ደንብ የእስረኞች ክፍል የሚከፈተው ከጥዋቱ አስራ ሁለት ሰአት ሲሆን፣ የሚዘጋው ደግሞ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰአት ነው፡፡ የጨለማው ክፍል እስረኞች ግን ሌላው እስረኛ ከመውጣቱ አስቀድሞ ከሌሊቱ አስራአንድ ሰአት ለሽንት እንወጣለን፡፡ እኔ በዚህ ሰአት ለሽንት እንድወጣ የተፈለገው እስረኞች ከክፍላቸው ሳይወጡ ነው፤ ነገርየው ማንም እስረኛ እንዳያየኝ ለማድረግ ነው፤ ማታም ለሽንት የሚከፍቱልኝ እስረኞች በየክፍላቸው ከገቡና በር ከተዘጋ በኋላ ነው፡፡ እናም ለጥቂት ደቂቃ መፀዳጃ ቤት ተጠቅሜ፣ ፊቴንም እንደነገሩ ውሃ አስነክቼ ወደ ክፍሌ ተመለስኩ፤ በሩ ከውስጥ ወደ ውጭ ተስቦ ተዘጋ፤ ጭለማውም ተመልሶ በእኔ ላይ ነገሰ፡፡
የሆነ ሆኖ ብዙም ሳይቆይ በአንደኛው መስኮት በኩል በምስማር በተበሳች ቀጭን ቀዳዳ ብርሃን ሲገባ አየሁ፡፡ አይኔን ወደቀዳዳዋ አስጠግቼ ወደውጭ ለማየት ሞከርኩ፡፡ ብዙም አልተሳካልኝም፡፡ ተውኩትና ክፍል ውስጥ ‹‹ወክ›› ማድረግ ጀመርኩ፤ ጥቂት ከተንቀሳቀስኩ በኋላ ጨለማው አይኔን ስለወጋኝ ፍራሼ ላይ ተጋደምኩ፡፡
ጨለማ ቤት የመታሰር ቅጣቱ በጨለማ የመከበብ ዕዳ ብቻ አይደለም፡፡ ጨለማው ከመግዘፉ የተነሳ አይንህ መስራትና አለመስራቱን ማረጋገጥ ይሳንሀል፡፡ እንዲሁ ተዳፍኖ የሚቀር፣ ሲከፈትም የማታይ እስኪመስልህ ድረስ የአይንህን ብርሃናማነት ትጠራጠራለህ፡፡ ማረጋገጫህ ምንድን ነው? ምንም! አንዲትም የብርሃን ሰበዝ ተሰርቆ በማይገባበት ልስን ጨለማ ማረጋገጫህ ምንድን ነው? በተስፋ መቁረጥ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ፤ ምን ያህል ሰአት እንደተኛሁ ሳላውቅ በሩ ተከፈተና አንድ ፖሊስ ከቤተሰቦቼ የተላከ የምሳ ሳህን ሰጥቶኝ በሩን መልሶ ዘግቶ ሄደ፡፡
ጥቂት ቆይቼ በሩን ደበደብኩ
‹‹ምንድን ነው?››
‹‹ሰአት ስንት ነው?››
‹‹ሃያ ጉዳይ››
‹‹ለስንት?››
‹‹ለስድስት›› ሳሃኑን ፈትቼ ለመመገብ ሞከርኩ፤ ግን አሁንም አልቻልኩም፤ ከዚህ በፊት ተሞክሮው ስላልነበረኝ በጭለማ መመገብ እንደሚከብድ አላውቅም ነበር፡፡ ጥቂት ጉርሻዎችን በውሃ አምጌ ከጎረስኩ በኋላ የበረሮ ድምፅ ስለሰማሁ ተውኩትና እስከአሁን ምን ያህል በረሮ ከምግቡ ጋር ቀላቅዬ እንደጎረስኩ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ከአሳቤ ሳልላቀቀ እንቅልፍ አሸነፈኝ፡፡ ስነቃ በጣም ብዙ ሰአት እንደተኛሁ እርግጠኛ ስለሆንኩ አሁንም በሩን ከውስጥ ወደውጭ ደበደብኩ
‹‹ምን ፈለክ?›› አለኝ የቅድሙ ድምፅ፡፡
‹‹ሰአት ስንት ነው?››
‹‹ጤና የለህም! አሁን ጠይቀህኝ ነግሬ የለህ እንዴ?››
‹‹አሁን አይደለም የጠየኩህ፡፡ ለስድስት ሃያ ጉዳይ ላይ ነው››
‹‹ታዲያ አሁን ስድስት ተኩል እኮ ነው››
‹‹ይቅርታ እንቅልፍ ወስዶኝ ስለነበር ብዙ ሰአት የተኛሁ መስሎኝ ነው››
መልስ የለም፤ ለራሴ ፈገግ አልኩ፡፡ ለካስ ሀምሳ ደቂቃ ተኝቼ ነው እንዲህ ብዙ ጊዜ ያለፈ የመሰለኝ፡፡ …የሚነበብ ነገር አልያዝኩም፤ ብቸኝነቱ ደግሞ ሊውጠኝ ደርሷል፤ ክስ ቻርጄን አነሳሁና ሚስማር ወደበሳት ቀዳዳ አስጠግቼ አንድ አንድ ፊደል ላይ እያነጣጠርኩ ማንበብ ጀመርኩ፤ በዚህ አይነት መልኩ አንድ አራቴ ደጋግሜ ካነበብኩ በኋላ ግን ጨለማው ብዥ አለብኝና ምንም ነገር ማየት ተሳነኝ፡፡ በጣም ደነገጥኩ፤ እንደምንም በዳበሳ ፍራሼ ላይ ሄጄ ተኛሁ፡፡ ያ የአይኔ ብርሃን ጥርጣሬ መልሶ ተቆጣጠረኝ፡፡ ሥጋት! አይን ያለ ቅንጣት ብርሃን ተራ ብልቃጥ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ከተጋደምኩበት ተነሳሁ፡፡ መልሼ ተኛሁ፡፡ በዚህ አይነት ድግግሞሽ ቀኑ መሸና ለሽንት ተከፈተልኝ፡፡ ተመስገን! አይኔ ብርሃን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ህልው መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡ ከሽንት ቤት መልስ ደግሞ መልሶ ተዘጋብኝ፡፡ ሌሊቱም እንዲሁ ስቆም፣ ስተኛ አለፈ፡፡ እናም ወፍ ጭጭ ሳይል ለሽንት ተከፈተልኝ፡፡
ወጣሁ፤ ተመልሼ ገባሁ፡፡ይህን ጊዜ የዝነኛው አሽሙረኛ አቤ ቶኪቻው ‹‹ከምገባ ወጣሁ›› ፅሁፍ ውልብ አለብኝና ድንገት ደርሶ ፈገግ አሰኘኝ፡፡ የጨለማ ፈገግታ… ዛሬ እለቱ ቅዳሜ ነው፡፡ በተለምዶ እስረኞች በወዳጅ ዘመድ በብዛት የሚጠየቁበት ቀን፤ የእስረኞች ሳምንታዊ ‹‹አውደአመት››፤ በጉጉት የሚጠበቅ ዕለት፡፡ በግምት ወደ ሶስት ሰዓት ላይ የእስር ቤቱ የበር ቁልፍ ጥቂት ተንጓጉቶ
ወለል አለ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ ስንቅ የሚመጣበት ሰዓት አልደረሰም፡፡ ለምንድር ነው የተከፈተው? ስል አሰብኩ፡፡ አንድ የፖሊስ ኃላፊ በፍራሼ ላይ እንደተንጋለልኩ ጥቂት ካስተዋለኝ በኋላ ‹‹ዕቃህን ይዘህ ውጣ›› አለኝ፡፡ ‹‹ወዴት ነው የምወጣው?›› ስል ጠየኩት፡፡ ‹‹ዝም ብለህ ያዝና ተከተለኝ››… ዝም ብዬ ወዴት ነው የምከተለው? እነዚህ ሰዎች ምን ሊያደርጉኝ ነው? ቀይ ሽብር ሊያፋፍሙብኝ? ወይስ… የተለያዩ ሀሳቦች በውስጤ ተመላለሱ፡፡
ይቀጥላል፡፡





No comments:

Post a Comment