"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday 24 October 2012

የማለዳ ወግ . . . ዘልቆ ሊያመን የሚገባው በኮንትራት ሰራተኞች ላይ የሚደርሰው ግፍ ! ለዚህስ ማን ነው ተጠያቂው ?



    ይህ የምትመለከቱትን ፎት ያነሳሁት በጅዳው አለም አቀፍ
አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በሚገኝ የጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች
አንድ ጽህፈት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ይህች የምታይዋት እህትም
ምን እዚያ አመጣት እንዳትሉ ! ከአንድ ወር ከሳምንት በፊት
በኮንትራት ስራ ከሀገር ቤት የመጣች መሆኗን ሳውዲው
የእድሜ ባለጸጋ አሰሪዋ ተነገረውኛል፡፡ እኔም ሆንኩ ይህንን
ጉድ አብረውኝ የሚመከቱ እህቶቸ ሁላችንም ወደ ሃገር ቤት
የሚሸኙ ዘመዶቻችንና ወዳጆቻችን አጅበን ነና የመጣነው
የዚህች እህት ወደ አየር መንገዱ ለምን እንዳመጣች መጠየቅ
አላስፈለገኝም ፡፡ በሰውነቷ ላይ ባረፈውን እስራትና ድብደባ
ከመገለ እጇና ገላዋ ላይ ሰንበር የመሰለ የጉዳት ምልክት ይታያል፡፡ እኒህ የተረገሙ አሰሪዎችዋ ይህች የኮንትራት ስራተኛ እህት ይህንን በደል ተሸክማ ወደ ሃገር ቤት ለመሰደድ እንድትችል ሲሸፋፍኑ ፈጠሪ አጋለጣቸው፡፡ ይህን የታዘቡት ኢዮጵያውያን ነብሮቹ እህቶች ነበሩ፡፡ይህችን እህት ቀርበው ጠየቋት፡፡ የደረሰባትን በደል እያነባችና እጆችዋን እያሳየች ገለጸችላቸው ፡፡ በአየር መንገዱ ወደ ሃገር ቤት ሰውለመሸኘት የመጡት እኒህ እህቶች ብዙም ሳይቆዩ አሰሪዎቿን አፋጠው ወደ ፖሊስ ወሰዱት . . . እኔም ጉዳዩን ሰምቸ ወደ ተባለው ቦታ;በፍጥነት አመራሁ፡፡ ግርግሩን ታዘብኩና የሆነውን የሰማሁት ሰብዕናቸው አስገድዷቸው የተበዳይ ተከላካይ ሆነው የቆሙትን እህቶቸንና የበዳይ ሙግት ያዳመጥኩት ወደ ፖሊስ ቀርበው ሳለ ነበር ፡፡  የፖሊስ ሃላፊውና ተራ ወታደሮች በዚህች ኮንትራት ሰራተኛ ላይ የሆነው አሳዝኗቸው አሰሪዋን በጥያቄ ሲያጣድፉት ደረስኩ፡፡ እኔም ጥቁር አባያ ለብሳ ነጭ የራስ ላይ ጥምጣም ያድረገቸውን እህት ተመለከትኳት፡፡ ታሰራ እንደነበር የቆሰለ ምልክት በእጇ ይታያል፡፡ ጉዳቷን እያዟዟርኩ ለመረጃ ፎቶ ከመሰብሰቤ አስቀድሞ ወደ አንድ የጂዳ ቆንስል አንድ ምክትል ሃላፊ ወደ ሆኑት ወደ ቆንስል ሸሪፍ ኬሪ ኦስማንን ስልክ ደውየ ያየሁትንና መረጃውን አቀበልኳቸው ! ቆንስል ሸሪፍ "የጉዳይ ፈጻሚዎችን ስልክ ውሰድና ደውል!"  ሲሉ ቢመክሩኝም ወደ ጉዳይ ፈጻሚዎች ደውየ ምላሽ በማጣቴ ወደ እርሳቸው እንደ ደዎልኩ ገለጸኩላቸው ፡፡ በማስከተልም ስለሁኔታው ይረዱ ዘንድም በቦታው የነበሩትን የፖሊስ ሃላፊ እንዲያነጋግሩ አደረግኩ፡፡ ይህ ሲሆን ጉዳይ ፈጻሚዎችን በእርሳቸው በኩል ጉዳይ    አነጋግረው አስፈላጊውን እርዳታ ለዚህች እህት እንዲያደርጉ ተማጽኛቸው በመግባባት ስልኩን ዘጋን፡፡ ሰአቴ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር 1፡58 (እንደኛ ሰአት አቆጣጠር ከሌሊቱ 7፡58) ይላል ግማሽ ሌሊት ይላል ፡፡  ጉዳዩ ወደ ፖሊስ ያደረሱት እህቶቸ ከእድሜ ባለጸጋው አሰሪ አልፎ ከጎማሳው ልጃቸው ጋር ፍጥጫ ይዘዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ከፖሊስ ሃላፊው ቢሮ
ውስጥ ነው . . . የኮንትራት ሰራተኛዋን ሰውነት መጎሳቆል የተመለከቱ ተራ ፖሊሶች ሳይቀር አሰሪውንና
ልጃቸው የሰሩት ስራ ተገቢ እንዳልሆነ አጥብቀው በማስረዳት ፍጥጫውን ለማብረድ በመሞከር ላይ
ናቸው ፡፡ . . .ነገሮች አላምርህ ሲሉኝና አሰሪው አረብና ልጅ በጥድፊያ በደል የደረሰባትን እህት
ለማሳፈር ሲጣደፉ ደግሜ ወደ ቆንስል ሸሪፍ ደወልኩ፡፡ ስልካቸው በተደጋጋሚ ተይዟል ምልክት
ሰጠኝ፡፡ ከግማሽ ሰአት በኋላ ግን ያደረግኩት ሙከራ ተሳክቶ በእጀ ላይ በሚገኝ በአንድ የኮንትራት
ውል ላይ ፊርማቸው ያስቀምጡት ቆንስል ሸሪፍን አገኘኋቸው፡፡ . . .  ከቆንስል ሸሪፍ ጋ ባደረግነው
ረዘም ያለ የስልክ ውይይት በዚህ ሰአት ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ገለጹልኝ፡፡ መልሳቸው ግን
ለእኔም ሆነ ጉዳዩን ይዘው ሲሞግቱ ለነበሩትን እህቶቸን የተሰማን ወሽመጣችንቆረጠው !  ድጋፍ
ማግኘት ካለብን የራሳችን ጠባቂዎች ድጋፍ የማግኘት ተስፋችን ገፈፈው !  ፊቴ ሲለዋወጥና ስበሳጭ ያየችኝ ከጸጉር እስከ ጥፍሯ ሙሉ በሙሉ በአባያ የተሸፈነች ትንታግ እህት ከአደረገቸው "ሪቃብ" ፊቷን ወደ እኔ አዙራ "ወንድም ! " አለችኝ ከተሸፋፈነችበት ጥቁር አባያ"ሪቃብ" ውስጥ በሚዎጣ ጉልበት ባለው ድምጽ፡ ". . . ተዋቸው ! በቃ ቢመጡስ ምን ያደርጋሉ ! ወስደው አይከራከሩ አይደግፏቸው ! ወደ ሃገሯ ትሂድ . . .ተዋት ትሂድ ቢመጡስ ወስደው ከግቢው አይደል የሚጥሏት ትሂድ
በሃገሯ ምድር ከቤተሰቦቿ ጋር በአፈሯ ትሙት !  እናንተ ግን ጀዛከላኩም ኽይር !(ፈጣሪ
ዋጋውን ይስጣችሁ ! " . . . ስትል ብስጭት ብላ ተናገረች ! . . . ወደ አሰሪዎቹ ዞራም ንጹኅ
በሆነው አረብኛ ቅላጼዋ በኮንትራት ሰራተኛ እህታችን አሰሪዎች ፊቷን አዙራ እጇን ወደ ሰማይ
እያጣቀሰች " ጥሩም ከስረራችሁ ጥሩ መጥፎም ከሰራችሁ ዋጋችሁን አላህ ይስጣችሁ ! ከሰው
ፍርድ አይጘኝም ! ፍርድ የአላህ ነው ! " ስትል በሃይለ ቃል ተናግራቸው ጥላን ወጣች ! ሄደች .
. .  ተግተን መብቷን ለማስከበርና ፖሊሶችን ማሳመን የቻልነው ሳይቀር ተስፋ ቆረጥን . . .
ሙግቱን አቁመን ሁኔታውን ለማረጋጋት ከፖሊሶች ክፍል ወጠን ከቅርብ ርቀት ከለው
የመንገደኞች መጠባበቂያ ወንበር ተቀምጠን መነጋገር ጀመርን . . .
     እዚህ ግባ የማይባል ያደፈ ነጭ የማይባል ባህላዊውን የአረቦች ልብስ ቶብ ያጠለቁት አሰሪው ሳውዲና አብሯቸው ይህችን እህት ይዞ የመጣውን ወንድ ልጃቸውን "ለምን ደብደባችኋት?" ስል ሁኔታውን እያረጋጋሁ ጠየቅኳቸው ፡፡ የሰጡን ምላሽ ግን "እብድ ናት!" የሚል ነበር ፡፡ እብድ ከሆነች ለምን ወደ ሃገሯ እንድትመለስ አደረጉም ?  አልኳቸው መለሱልኝ እንዲህ ሲሊ " ልጀ ካመጣኋት ወር ከአስራ አምስት ቀን አልሆናትም ፡፡ቋንቋ አታውቅም ፡፡ አትግባባም ፡፡ ንጹሕ አይደለችም፡፡ ስራ አትችልም፡፡ ጤነኛ አይደለችም፡፡ይህን ሰራተኛ ላቀረበልኝ ኤጀንሲ ባነጋግራቸው አንቀበልህም ከፈለግክ ወደ ሃገሯ መልሳት ፤ አሳፍራት አሉኝ ምን ላድርግ ?" ሲሉ ለማግባበት በመሞከር መለሱልኝ ፡፡ ከሀገር ቤት ስትመጣ አብዳ አለመሆኑን ከራሳቸው አስረግጨ በእጇ ላይ የሚታየው የበለዘና ገላና በሺቦ ማሳይ ገመድ በጭካኔ መታሰሯንና በአግባቡ አለመያዟና እንደሚያሳይ በመጠቆም ቢያማት እንኳ ወደ ተገቢው ሃኪም ቤት ለምን አልወሰዷትም? ስል ለጠየቅኳቸው አሰሪዋ ሲመልሱ አብዳ ልብሷን አውልቃ ስትሄድ በቤተሰብ አባላት ጉዳት እንዳታደርስ ለማድረግ በጨርቅ ሻሽ እንዳሰሯትና ያበደ ለማሳከም ሰራተኛ እንዳላስመጡ የገለጹልኝ  ሳያግባባን ቀረ፡፡ መልሳቸው ፍጹም የማይዋጥ ቢሆንም ሙግት ሳልከፍት ወደ ሌላው ጥያቄየ አመራሁ ፡፡ ይህ ሲሆን የተወሰኑ ተሳፋሪና ዘመድ አዝማድን ለመሸኘት መጥተው ጉዳዩን የሚከታተሉ የኔ ቢጤ እህቶች ከአጠገቤ አራቁም፡፡ እርስ በርስ ተነጋገርንና ደመወዝ የመቀበል
ያለመቀበሏን ጥያቄያችን አሰሪዋን ጠየቅናቸው ፡፡ ደመወዝዋ አምስት መቶ ሪያል መሆኑን አባትና ልጅ ክችም በማለት ሲገልጹልን ይህው የአንድ ደመወዝዋንም ከሸጎጡላት ከፖርሳዋ እንዳስቀመጡላት አፋጠን ስንይዛቸው ፖርሳውን ለፍተው አሳዩን፡፡ "ደግሞ አምስት መቶ ደሞዝ ብሎ ነገር አለ እንዴ ?" ስንል ብንጠይቃቸውም በዚህ ደመወዝ በኮንትራት እንዳስመጧ ገለጹልን !
ተስፋ ቢሶች ሆንን ! በግምት እድሜዋ ከ17 የማትበልጠውን የዚህች እህት በቤተሰብ አባላት የአስገድዶ መድፈር እንዳልተደረገባት ነገር ግን ተደጋጋሚ ሙከራዎች በአሰሪውና በልጆች እንደተደረገባት የተረበሸችውን ልጅ አረጋግተው ሲጠይቋት እንደነገረቻቸው አንዷ እህት አጫወተችን፡፡ እንግልት ጎድቷታልና ከኔ ፊት ደጋግማ የምትናገረው ነገር ቢኖር በደሏን አይደለም ! " ምንም አልሆንኩም ወደ ሃገሬ ስደዱኝ" ትላለች !  ያልደረቀ ቁስል የበለዘና የተንጎሳቆለ ገላ ይዛ "  ምንም አልሆንኩም !"  ማለቷ ጠልቆ ተሰማኝ፡፡ ከገባችበት መከራ ለመውጣት እንጅ በደል ስይደርስባት እንዳልቀረ ግልጽ ሆኖልኛል !  ግን ምንም ማድረግ አልችልም ! መርዳት ያልቻልነውና የምንጨብጠው ያጣነው የግፉእ እህታችን በደል " እህ !" ብለን ለማየትና ለመስማት የታደልነው የነገ ምስክሮች በቁጭት ደበንን ! እኔ የማደርገው ግራ ገብቶኝ በቁጭት ስዋልል ህመሟ ያመማቸው የሚያነቡ እህቶች እንባቸውን ጠርገው ጉስኩሏ እህት ውሃና ጭማቂ ገዝተው ሰጧት ፡፡ በጥድፊያ ከእጃቸው ተቀብላ እየተጣደፈች ጠጣችው . . . ! ብዙም ሳትቆይ አሰሪዋ ወደ ፓስፖርት ጽህፈት ቤቱ ይዟት ገባ . . . እኛ ወደዚያ መግባት አይፈቀድልንም ! በአይናችን ተከተልናት . . . በስስት ዞራ አንዳፍታ ሰርቃ አየችንና አሰሪዋን ተከትላ ገባች. . . ! ለሁለት ሰአታት ቁስሏን እያሳየን በዳይዋን ስንሞግት ያመሸነው እኔም ሆንኩ የቀሩት  እህቶች ከጎናችን የሚከላከል የለምና ከዚህ በላይ መሄድ አይቻለንም . . . ለእኛስ ቢሆን ማን አለን ? እናም ቀጣዩ የዚህች እህት መጨረሻ የት እንደሚሆን አናውቅም . . . አሰሪዋ ወደ ሃገሯ ይላካት አይልካት የምናውቀው ነገር የለም !  ብቻ የምንፈልገውን የማሳካት አቅሙ ባይኖረንም የምንችለውን አድርገናል፡፡ አስከትሎ የወሰዳትን አሰሪዋን በስራው ረግመን ፤ እህታችን በአይናችን ሸኝተን እርስ በርሳችን ተመሰጋገነን ተለያየን ! አዎ ! በመቶ ሺዎችን ወደ አረብ ሃገር በህጋዊ ኮንትራት ሰም ይመጣሉ፡፡ በአንጻሩ ሁሌም  ተጨባጭ መረጃን ይዥ እንደምንለው ለመብታችን መከበር ተግተው መስራት ያለባቸው
በአካባቢው የሉም ! ከሁሉም በላይ የኮንትራት ሰራተኞች ደሞዛቸውን ሲቀሙ ፤ ሲደፈሩ ሲታመሙና ሲያብዱ መብታቸውን የሚያስከብር ፤ ችግሩ ምንድነው ብሎ የሚጠይቅ የሚከላከልላቸው የለም ! አሁን አሁንማ አሰሪዎች በደል አድርሰው ሲታመሙ ሲያብዱባቸው ቲኬት እየቆረጡ በአየር መንገዱ ጥር ግቢ ጥለዋቸው የሚሄዱበት በገሃድ እየታየ ያለ እውነታ
አሳሳቢ የሆነና ጸሃይ የሞቀው እውነት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሃላፊዎች በኮንራት የሚመጡትን ያህል በደል ደረሰብን የሚሉ ያበዱና አካለ ስንኩል እየሆኑ ወደ ሃገር የሚመለሱ እህቶች ቁጥር እያሻቀበ መሄዱንና መቆጣጠር ከሚችሉት በላይ እየሆነ መሄዱን ተመልክቻለሁ፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሃላፊዎችንና ሰራትኞችን አነጋግሬያቸው የኮንትራት ሰራተኞች ጉዳይ አንስተው ሲያጫውቱኝ "  በገፍ እንቀበላለን ፤ አሰቃቂ በደል የደረሰባቸውን ደግሞ በተመሳሳይም ሁኔታ ባይሆን በአስደንጋጭ ሁኔታ እንሸኛለን !" ሲሉ አሳሳብነቱን በአጽንኦት ገልጸውልኛል ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን በአንጋፋው አየር መንገዳችን ሃላፊዎችና የመንግስታችን ሃላፊዎች በቅንጅት በመስራት ያልቻሉበት ለም እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ለመቆጣጠር
አቅሙ ያላቸው የመንግስታችን አካላት በቅንጅት በመስራት በኮንትራት ሰራትኞች ላይ የተሸፋፈውን በደል ፈጽመው ሲታመሙባቸውና ሲያብዱ ጥለዋቸው የሚሄዱትን አሰሪዎች እንኳ በህግ ፊት ለማቅረብ የሚሰሩት ስራ አለመኖሩ ያሳዝናል፡፡ ብቻ ሁሉም እንደ ቀረነው ተራ ዜጎች ከንፈራቸው ይመጣሉ ! በቃ ይህው ነው !
  የመጣሁበትን ሽኝት ፈጻጽሜ ከመሄደ አስቀድሞ አብረውን ከነበሩት እህቶች መካከል አንዷ ምልክት ሰጠችኝና ነበርና ወደ እርሷው
ተጠጋሁ፡፡ "ጋዜጠኛማ ከሆንክ ይህም አለልህ !"  ስትል በጀመረቸው ንግግሯን በመቀጠል አንዲት
የኮንትራት ሰራትኛ የዓዕምሮ ህመም ተለክፋ በአሰሪዎቿ እየተሸኘች እንዳለች ጠቆመችኝ ፡፡ ወደ
ተጠቆምኩት እህት ተጠጋሁ ፡፡ ለግላጋ ወጣት ናት . . . ይህችኛዋ እህት በአገሩ ባህል ግዴታ የሆነውን
ጥቁር አባያ እንኳ አላደረገችም ! ግራ እየገባኝ በአግራሞት እያየሁ ተጠጋኋት ! ፓስፖርትና ቲኬትዋን
የያዘውን ወጣት ለማነጋገር ሞከርኩ፡፡ ይህ ወጣት የአሰሪዋ ልጅ እንደሆነና የዓእምሮ ህመም እንዳለባት
ገልጸልኝ ፡፡ ይህ የሆነው መቸ ነው ? የሚለውና ተከታታዩ ጥያቄየ አላማረውም መሰል መልስ ሳይሰጠኝ
ወዲያውኑ ምስኪኗን እህት አስከትሎ ከአጠገቤ ሸሸ ፡፡ . . .ከቅርብ ርቀት ናቸውና እንደመጠጋት እያልኩ
በአይኔ ተከተልኳት ፡፡ የደስ ደስ ያላት ጉብል ክብ ፊቷን ከወዲያ ወዲህ እያማተረች በማየት ለራሷ ፈገግ
ትላለች፡፡ በእርግጠኝነት በዓዕምሮ ህመም መነደፏን ነሁለል የሚለው አይኗና አስተያየቷት ያሳብቃል ፡፡
ይህችኛዋ የመጣችው መቸ ይሆን ? ማንስ አመጣት ? ምንስ ገጠማት ? ችግሯና የተደበቀው ታሪኳስ
ምን ይሆን ? በጤና ለስራ ተግታ መጥታ ምንስ ሆና አዕምሮዋ ተዛባ ? ለምን ወደ ሃገር ቤት ደባብቀው ይመልሷታል ? ስል መልስ
የማላገኝለት ጥያቄ በውስጤ ተመላለሰ ! ይህችኛዋ እህት ወደ አውሮፕላኑ መግቢያ ቲኬት Boarding pass ተሰጥቷት በፊት ለፊቴ አልፋ ሄደች ! በጤና መጥታ ዓዕምሮዋን ተሰርቃና ነሁልላና የምትመለሰው እህት ሰውነቷ የደከመ ቢሆንም ቀጥ ብላ በመራመድ ከወዲያ ወዲህ እየተቁለጨለጨች የአሰሪዋን ልጅ ተከትላ ሄደች ! . . . ከጥቂት ሰአት በኋላም አይሆኑ ሁና ሀገር ቤት ትገባና ለአገሯ መሬት ትበቃለች ! ይህን አውቃለሁ ! ይህ ሁሉ ሲሆን የት እሷ የት እንደምትሄድ ፤ ሄዳስ የት እንደምታርፍና ሌላ ሌላውን ስለማወቋ የማውቀው የለም ! ፈጣሪ ይርዳት እንጅ ምን ይባላል ! ?    
  የቆንስልና ኢንባሲ ሃላፊዎቻችን የኮንትራት ሰራተኛ ቅጥር ህግና ደንብ አለ ብለው ሰራተኛና አሰሪን ኮንትራት ያፈራርማሉ፡፡ ከወረቀቱ ላይ ፊርማችውን ሲያስቀምጡ ከሚሰበስቡት ገንዘብ ውጭ ግን ዜጎች የት እንዳሉ፤ ምን እንደሚሰሩ ፤ ምን በደል እየደረሰባቸው እንደሆነ የሚያውቁት ነገር የለም !  በደል እንዳይደርስ መከላከልና በደል ሲደርስ ማጣራት ቀርቶ በደል ደርሶ ድረሱልን ሲባሉ እንዲህ እንዳሁኑ አይደርሱልንም ! . . . ግን እስከ መቸ ? በህጋዊ ኮንትራት ሰራተኞች ላይ የሚደርሰው ግፍ ማን ያቁመው? ስል አሁንም መልስ በማላገኝለት ጥያቄ ራሴን ለመበጥበጥ ተገደድኩ ! .  . .ከአየር መንገዱ ይህን መሰል ጉድ አይቸ እንደምጣሁ ይህችን ማስታወሻ ስሞነጫጭርወደ ጅዳ የሚመጡ የኮንትራት ስራተኞች የሰራተኛ ውል መመልከቱን ያዝኩ !
ኢትዮጵያን የኮንትራት ሰራተኞችን ወደ ሳውዲ አረቢያ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ መንግስትና የዜጎች ብቸኛ የሆኑ የኢንባሲና የቆንስል መስሪያ ቤቶች ይህንን በእጀ የሚገኘውን የስርተኛ ውል አውጥተው እያፈራረሙ እንደሚገኙአውቃለሁ ፡፡ የዜጎችን መብት ለማስከበር የወጣው የስራ ውል ህግ የዜጎችን መብት የማስከበር ጥንካሬ መላላት ይታይበታል በሚል አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች የኛን ኮንትራት ከፊሊፒንና ከኢንዶኖዥያ የሰራትኛ ውል ጋር ያመሳስሉታል፡፡ እኔ ደግሞ አባቶች ሲተርቱ   " ጽድቁ ቀርቶ . . .በቅጡ በኮነነኝ !"  እንደሚሉት የስልጡኖቹና የተሻሻለው ህግ ቀርቶ ያለውን አንድ ገጽ የስራ ውል የሚያከብርልን የመንግስታችን ተወካዮች እጦት ሁሌም የማልቀበልው ህመም ሆኖኛል !  ከዚህ ጋር አያይዥ የምታዩት የስራ ውል "ሀ "  እና  " ለ " ጨምሮ ከ 1 እስከ 26 ተራ ቁጥር ውስጥ የስራው አይነት ፤ ደመወዝ    ፤ ህክምና ፤ እረፍት እና ሌላ ሌላም ተዘርዝሯል፡፡
መዘርዘሩ ባይከፋም ከስራ ውሉ ከተዘረዘሩት ውስጥ አብዛኛው ከወረቀት ላይ የቀረ የማይተገበር ስለመሆኑ ግን ከበቂ በላይ እማኞችን
ማቅረብ ይቻላል ! እማኞች ደግሞ የሚመጡት ከሩቅ አይደለም በጅዳ ቆንስል መጠለያወች ሞልተው ተርፈዋል ፡፡ በጅዳ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከአርባ ያላነሱ በመጠለያው እንደነበሩና ቦታው በመሙላቱ በቆንስሉ ታዛ "የመጠጊያ ያለህ!" እያሉ ሲለምኑ ተመልክቻለሁ መረጃም አለኝ ፡፡  በሪያድ ኢንባሲም በተመሳሳይ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ከጅዳው በባሰ ደረጃ ዜጎቻችን አብደውና በውስጠ ደቄ ተቀስፈው ተጥለው ለመገኘታቸው ከበቂ በላይ መረጃ አለ ፡፡ ይህ በገሃድ የሚታይ መደበቅ የማይቻለን እውነታ ነው !
  ታዲያ እውነቱና ሃቁ ይህ ከሆነ ለዚህ መሰሉ የትውልድ ጥፋት መፍትሄው ምንድን ነው ? እየደረሰ ላለው ግፍ ማን ነው ተጠያቂው
ግፉ ቀጥሏል ! እኔ ያየሁትን እነግራችኋለሁ ፤ የሰማሁትን አሳያችኋለሁ ! ዘልቆ ሊያመን የሚገባው በኮንትራት ሰራተኞች ላይ የሚደርሰው ግፍ መቋጫው ቢጠፋ ማስታገሻ ልንፈልግለት ይገባል ! ነግ በኔ ነው ! ያማል  ! ያማል !  ያማል ! ጀሮ ያለው ይስማ !
ቸር ያሰማን . . .
ነቢዩ ሲራክ

No comments:

Post a Comment