"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Monday 13 August 2012

የግፍና የሰቆቃ እስር በኢትዮጵያ ወህኒ ቤቶች ቀጥሏል


e
የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ መሆን ኦነግ መሆን አይደለም። ወያኔ ግን ንጹሐንን ኦነግና አሸባሪ በማለት ያስራል። ከላይ የምታዩአዋቸው በ እስር ቤት ከሚገኙ የኦሮሚያ ተወላጆች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ኢህአዴግ እስር ቤቶቹን “ማረሚያ ቤቶች” እያለ ቢጠራቸውም፣ መጠሪያው እውነተኛውን የእስር ቤቱን ገጽታ ስለማይገልፀው እንደ ቀድሞ ስሙ “ወህኒ ቤት” ተብሎ ቢጠራ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ወህኒ ቤቶች ከዚህ በፊት ከነበሩት የከፉ ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የግፍና የሰቆቃ እስሩ እጅግ ሰብአዊነት በጐደለው ሁኔታ በፖለቲካ አስተሳሰብና በዘር ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ነው፡፡ ቃሊቲ ወህኒ ቤት እስር ቤት ብቻ ሳይሆን የመረጃ ማዕከልም ነው፡፡ የመላው አገሪቱ የዕለት ተዕለት መረጃ በትኩሱ በቅብብል ይደርሳል፡፡ በመላው የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ያለው ሁኔታም በየዕለቱ ይሰማል፡፡
ባለፈው ጽሁፌ ራሴን ለማስተዋወቅ እንደሞከርኩት በዚህ የዘረኞች ወህኒ ቤት 19 ዓመት ከ8 ወር ቆይቼአለሁ፡፡ እኔ ከዚህ ሳልወጣ አራትና አምስት ጊዜ ተመላልሶ የታሰረ እስረኛ አጋጥሞኛል፡፡ የሸዋሮቢት፣ የዝዋይና በቅርቡ ሥራውን የጀመረው የቂሊንጦ ከፍተኛ ወህኒ ቤት በመረጃ ደረጃ የሁለት የጐረቤታሞች ያህል መረጃ እንለዋወጣለን፡፡ በዚሁ መሠረት ዛሬ ህዝብ ስለማያውቃቸው ድብቅ እስር ቤቶችና በየድብቅ እስር ቤቶቹ ስለሚፈፀሙ ግፈኛ ድርጊቶች ላውጋችሁ፡፡ ወያኔ/ኢህአዴግ “በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካና የህሊና እስረኛ የለም” ይለናል፡፡ ምንም እንኳን መኖሪያ ቤታችን ቃሊቲ ቢሆንም የመንግስትን መረጃ በተሟላ ሁኔታ እንከታተላለን፡፡ ሬዲዮ ከተከለከልን ሦስት ዓመት ቢልፈንም፣ በቃሊቲ ኢቴቪ 24 ሰዓት ይሰራል፡፡ የውጭ ሚዲያዎች የሚያወሩትን ውጭ ካለው በበለጠ እንሰማለን፡፡ በተጨማሪም ጠያቂዎቻችን ሁሉንም ነገር ይነግሩናል፡፡

የሀገራችን ግዙፍ እስር ቤቶች ሰነድ እንደሚያመለክተን 90% የሚከተሉት ድርጅቶች እስረኞች ናቸው፡፡ ኦጋዴን ነፃ አውጭ ግምባር፣ የቤንሻንጉል ህዝብ ንቅናቄ ነፃነት፣ ትንሳኤ ኢትዮጵያ አርበኞች ግምባር፣ ኦነግ፣ የሲዳማ ነፃነት፣ ደሚት (የትግራዩ)፣ የአፋር ነፃነት ግምባር፣ የጋምቤላ ህዝብ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የደቡብ የፍትህና እኩልነት ግምባር፣ አርበኞች ግምባር፣ ግንቦት 7 ናቸው፡፡ ታሳሪዎቹ የድርጅቶቹ ተከታዮች አሊያም ተዋጊ አባሎቻቸው ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ የድርጅቶቹን ስም እንኳን የሰሙት ከታሰሩ በኋላ ነበር፡፡ የየአካባቢያቸው ደህንነቶችና ካድሬዎች ከፖሊስና ከዐቃቤ ህግ ጋር እየተቀናጁ በፈጠሩት ክስ የተሰጣቸው ስም ነው-አሸባሪነት፡፡
በሀገራችን በሚገኙ እስር ቤቶች ማለትም ድሬደዋ፣ ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ሸዋሮቢት፣ ዝዋይ የፌደራል እስር ቤቶች ተብለው ሲጠቀሱ ከነዚህ ውጪ የክልል እስር ቤቶችና በበርካታ የክልል ከተሞች፣ በመሀል አዲስ አበባ በሚገኙ ቪላዎች፣ በደህንነት ተቋሞችና ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ጭምር ስውር እስር ቤቶች ተወቋቁመዋል፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት የተመሰረቱ በርካታ የሸቀጣሸቀጥና የእህል ማከማቻ መጋዘኖችን ኢህአዴግ ወደ ስውር እስር ቤትነት ቀይሯቸዋል፡፡

የራሱን ችግር ሳይፈታ ሰላም አስከባሪ ነኝ፤ የሚለው ወያኔ/ኢህአዴግ ገበናው ሲፈተሸ ራሱ ፀረ ሠላም ነው፡፡ ወጣቱን ኃይል ማሰር ተቀዳሚ የስርዓቱ አምባገነናዊነት ማሳያ ቢሆንም ይበልጥ የስርአቱን አስከፊነትና አደገኝነት የሚያረጋግጠው አባትና ልጆችን እንዲሁም ወንድማማቾችን፣ ባልና ሚስትን፣ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ፣ በዘር ምክንያት አድኖ በጭካኔ የሚያስርና ለዕድሜ ልክ እስር የሚወረውር አምባገነን ስርዓት ነው፡፡ የሚፈፅማቸውን ድርጊቶች ለተመለከተ ይህ ስርዓት የዘር ማጥፋት ድርጊት እየፈፀመ መሆኑም ግልጽ ይሆንለታል፡፡ ለዚህ እኩይ ተግባሩ ቀድሞ ፈርዶ ለይምሰል የሚያቀርባቸው የክስ መዝገቦች የሚዘረዘሩት ክሶች፡-
- የሀገርን ግዛትና አንድነትን መንካት
- ሽብርተኛ
- ኦነግ፣ ግንቦት 7 በሚል ነው፡፡
ይህን በአሁኑ ጊዜ “ሀገራችን ሠላም ነው፤ ዕድገት እያስመዝገብን ነው፡፡ ኢህአዴግ በምስራቅ አፍሪካ ተደማጭ ነው” እያለ ከሚነግረን የተለየነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ 21 ዓመታት ሙሉ ታፍኖ እየተገዛ ነው፡፡ መብቴን ሲል ተለጣፊ ስም እየተሰጠው ወደ እስር ቤት የሚወረወረው ወጣት ቁጥሩ እጅግ ብዙ ነው፡፡ አገር ጥሎ የሚሰደደውም የትየለሌ ነው፡፡ ኢህአዲግ “ለሱማሌ ሠላም ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡ ዲሞክራሲያችን ለአፍሪካ ምሳሌ ሆነ፤ እከሌ የሚባል ፈረንጅ ምስክርነቱን ሰጠ ወዘተ” በማለት የራሱን ጉድ ደብቆ ባዶ የፕሮፓጋንዳ ጩህቱን ይጮሀል፡፡ ይህን ባዶ ፕሮፓጋንዳ ማየት የፈለገ ሌላ ማስረጃ ሳያስፈልገው ሀገራችን ሠላምነች ወይ? የተረጋጋ ፖለቲካ አለ ወይ? ብሎ ቢጠይቅ መልሱ ከኢቴቪ፣ ወይም ከአቶ ሽመልስ ከማል፣ (በረከት) ሳይሆን የገሀዱ ሀቅ ሀገሪቷ ወዴት እየሄደች እንደሆነ ለማየት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን እስር ቤቶችን መፈተሸ በቂ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ድብቅ እስር ቤቶች ከሕዝብ ለምን ተደበቁ? ምንስ እየተሠራባቸው ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ዜጎች ከመላው ሀገሪቷ ተለቃቅመው የታጐሩበትን ሚስጢራዊ እስር ቤቶች ምስጢር ለማወቅ ይረዳችሁ ዘንድ የማውቀውን ላስረዳችሁ፡፡ ለምሳሌ የ90 ዓመቱ አዛውንት ከነልጆቻቸው የታሰሩበትን ቀልቤሳ ጢሎና ልጃቸው አብረሃም ቀልቤሳ፣ ከጉምዝ ብሔር የ85 ዓመቱ መንግስቱ ቦንድ፣ ከነልጁ የታሰረው ኢንጅነር ጁማ ሩፋኤል፣ ኦባንግ ኦሎቾ የጋምቤላ ጦር አዛዥ ወርቁ በለጠ የአርበኞች ግምባር (ም/ሊ)፣ የግንቦት 7ቱ ኮረኔል አበረ፣ ሻለቃ መኮንን፣ የሲዳማው ንቅናቄ አባላት፣ የሱማሌው ከሊፋ አሊ፣ የኦነግ መቶ አለቃ አብደላ አፋ ወዘተ . . . እውነት ለብሔራቸው ሥጋት፣ ለአገራቸው ሽብርተኛና ወንጀለኛ ሆነው ነው የታሰሩት? ወይስ ለብሔራቸው መብትና ጥቅም ለራሳቸው ነፃነት ሲታገሉ? ሀቁ ለኢህአዴግ ዘረኛና አምባገነናዊ አገዛዝ ሥርዓት ሥጋት ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ በእኔ እምነት የፖለቲካ እስረኞች ናቸው፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ለዕድገቷም ሆነ ለውድቀቷ እነዚህ ህዝቦቿ ናቸው፡፡ ስለዚ ለምን ይህ ሁሉ የፖለቲካ እስረኛ ዜናው ለህዝብ እንዳይሰማ ተደረገ? በአብዛኛው የተያዙት በጦርነት ቆስለው ሱዳን ውስጥ በመታከም ላይ እያሉ ነው፡፡ የታሪክ ጠላታችን የሆነችው ሱዳን እያነቀች እየሰጠች ነው፡፡ ቢሆንም ትግሉ ተቀጣጥሎአል ብሎ መመስከር ይቻላል፡፡ ይህ ለህዝብ አንዳይሰማ ወያኔ/ኢህአዴግ የህዝብን ስሜት ለማስቀየር ሲምፖዚየም፣ ዐውደ ጥናት፣ የልማት ስብሰባ፣ ወጣት ሊግ፣ ሴት ሊግ እያለ ህዝብን ያደናግራል፡፡ መሠረታዊ ፍላጐት እንኳ ሟሟላት አቅቶታል፡፡ በሰፊው በገበያ ላይ ይገኙ የነበሩት ዘይትና ስኳር እንኳን ኮንትሮባንድ ሆነው ነጋዴዎችን በአፈና እያሳሰሩ ናቸው፡፡ ኢህአዴግ ብዥታ ለመፍጠር ፕሮፓጋንዳ ሊነዛ ይችላል፡፡ ግን ሀቁን እስር ቤቶች አፍ አውጥተው ይናገራሉ፡፡ የወያኔ መንግስት ወንድም የሆነው የሊቢያ መሪ ጋዳፊ ከዚህ የበለጠ ምን ግፍ ሠራ? ሌሎች አፍሪካ ሀገሮች ከአፍሪካ ቀንድ የተሻለ ዴሞክራሲ ስርዓት ዘርግተው ህዝባቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ አፍሪቃ ቀንድ ግን ሰብአዊና ዲሞክራሲ ስርዓት በፍፁም ያልዘረጉ ጨፍጫፊዎች የነገሱባት ናት፡፡ ቀጠናው ለረዥም ዓመታት በመንግስትነት የተቀመጡ አምባገነን መሪዎች ያሉበት ነው፡፡ ስለዚህ ከጋዳፊ ምንም የሚለያቸው ነገር የለም፡፡ ይገላሉ፣ አካለ ጐደሎ ያደርጋሉ፣ ያስራሉ፣ በባዶ ፕሮፓጋንዳ ህዝባቸውን ይዋሻሉ፡፡
ሌላው ድብቁ የስቃይ ቦታ ጦር ኃይሎች ጀርባ የደርግ ደህንነት የነበረው ግቢ ነው፡፡ ይህ ግቢ በከተማችን እንደወጡ የሚጠፉ ዜጐች አፋልጉኝ ፎቶ የሚወጣባቸው ዜጐቻችን የሚታጐሩበት ዘግናኝ ቦታ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ሲገቡ ወደየት ቦታ እንደ ተወሰዱ እንዳያውቁ አይንዎትን እተያዙበት መኪና ውስጥ ይታሰራሉ፡፡ እዛ ግቢ ውስጥ ለረዥም ዓመታትም ሊታሰሩ ይችላሉ፡፡ የሰው ልጅ ስጋው ተበጣጥሶ የሚወድቅበት፣ በጋለ ብረት የሚቃጠልበት፣ ወንድ ልጅ እንደ እንስሳ የሚኮላሽበት፣ ጥፍሩ የሚነቀልበት፣ እንደ እንስሳ እንዲመገብ የሚገደድበት፣ የስቃይ ቦታ ነው፡፡ እዚህ እስር ቤት እስከ ሁለት ዓመት ታስረው ከቆዩ በኋላ ቅብብሎሹ ይቀጥላል፡፡ ወዴት? ካሉ ወደ ማዕከላዊ ይላኩና እንደ አዲስ ምርመራው ማዕከላዊ ይቀጥላል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ለዚህ አይነቱ የግፍ ሰለባዎች ለመጥቀስ ያህል ዶ/ር ፈንታሁንንና መቶ አለቃ አብደላ ከሊፋን መጠይቅ ይቻላል፡፡ በዚህ የማሰቃያ ስፍራ የወንድ ብልት የዘር ፍሬ በስቴፕለር ይጣበቃል፡፡ ውሃ ኮዳ ይታሰርበታል፡፡ ሌሎች ተዘርዝረው የማያልቁ እጅግ ዘግናኝ የግፍ ድርጊቶችማ ይፈፀማሉ፡፡
የስዊዲን ጋዜጠኞችና የእነ ከሊፋ አሊ እስርና ዶክመንተሪ ፊልም ቅንብር ጊዜውን ጠብቆ ይፋ ስለሚሆን ለዛሬው ልለፈው፡፡ ከዚህ ቀደም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቲርና የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጅት ፊት ለፊት ስለተቃጠለችውም ታክሲም ጉዳይ ለጊዜው ላቆየው፡፡ በአጠቃላይ ግን በፈጠራ ዶክመንተሪ ፊልም ባዶ ፕሮፓጋንዳ መለፈፍ ከደርግ ውድቀት የአለመማር ውጤት ነው፡፡ “ምንም የፖለቲካ እስረኛ የለንም፡፡ ሀገሪቷ ሠላም ነች፡፡ የተረጋጋ ፖለቲካ አለ” እየተባልን እስከመቼ እንታለላለን? አሁን ዜጐች በየወህኒ ቤቱ ታጉረው ያሉትን የክስ መአት እያወቁ ህዝብን መዋሸት እስከመቼ?
ይህ ፁሁፍ እስከሚፃፍበትም ደቂቃ ኢህአዴግ በሁሉም የሀገሪቷ እስር ቤቶች አዳዲስ እስረኛ እያስገባ ይገኛል፡፡ ይህንን መካድ አይቻልም፡፡ እስር ቤቶች አፍ አውጥተዋል፤ ይህ እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ ሲሆን በሰፊው የውሸት ድራማውን በማጋለጥ ወደ ፊት እናቀርባለን፡፡ ቸር እንሰንብት። in

No comments:

Post a Comment