"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday, 15 August 2012

እስከመቼ ከባለድል አትሌቶች ጀርባ ተደብቀው ያጭበረብራሉ?


August 14, 2012


አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ሀላፊዎችና የፕሬስ አታሼ ከባለድል አትሌቶች ጀርባ ተደብቀው እስከመቼ ያጭበረብራሉ?
“ፊሽ – የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ፕሬስ አታሼን አነጋግርና አትሌቶችን ለቃለ መጠይቅ የምናገኝበትን መንገድ እስቲ አመቻች” የሚለው ጥያቄ የመጣው የ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታዎች የኦሎምፒክ ዜና አገልግሎት (Olympic News Service) ውስጥ በምሰራበት ወቅት የአትሌቲክስ ቡድን ስፖርት ባለሞያ ከሆነው ባልደረባዬ ነበር። የዜና አገልግሎቱ ስራውን ሲጀምር ወደለንደን የሚመጡት የኦሎምፒክ ቡድኖች ህዝብ ግንኙነት ወይም ፕሬስ አታሼ ሀላፊዎች የብሪታኒያ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ቁጥር መረጃ ከሀላፊዎቹ ስም አጠገብ የሰፈረበት የመገናኛ ብዙሀን መመሪያ አነስተኛ መጽሀፍ ተሰጥቶን ነበር። ታዲያ ባልደረቦቼ የእኔን የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪነት እና ቀድሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረኝ የሬድዮ ጋዜጠኝነት ሞያን ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድንን በተመለከተ መረጃዎችን የማሰባሰብ ሀላፊነቱን ለእኔ ሰጡኝ። ባልደረቦቼ ያላወቁት ነገር ቢኖር ከኢትዮጵያ የመንግስት ድርጅቶች መረጃ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ነዳጅ ማውጣት የሚቀል መሆኑን ነው።
የመጀመሪያው ስራዬ የነበረው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ፕሬስ አታሼ ማን እንደሆነ መፈለግ ነበር። ከጥቂት አሰሳዎች በኋላ ገበያው ታከለ የሚል ስም የተሰጠን የመገናኛ ብዙሀን የግንኙነት መረጃ መመሪያ ላይ ተጽፎ አየሁ። ገበያው ታከለ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የገንዘብ ያዥ እንደነበሩ ስለማውቅ ‘እውነት ከሰውዬው ጋር ትክክለኛ የሚዲያ ስራ መስራት ይቻላለን?’ የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አስገደደኝ። ሌላኛው የአእምሮዬ ክፍል ደግሞ ‘ምንአልባት ነገሮች ተለውጠውና ተሻሽለው ይሆናል’ የሚል ሀሳብ አነሳና በሁለት ሀሳብ ተወጥሬ ለማንኛውም ሰውዬውን ላግኛቸውና የግንኙነት መስመራችንን ላመቻች በሚል ስልክ ለመደወል ስዘጋጅ ከገበያው ታከለ ስም አጠገብ የስልክ ቁጥር እንደሌለ ተገነዘብኩ። ቀጣዩ አማራጭ የነበረው ከሀገርቤት የሚመጡ ጋዜጠኞችን በመገናኘት የአቶ ገበያው ታከለን አድራሻ ለማግኘት መሞከር ቢሆንም የቀድሞ ባልደረቦቼም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው ለማወቅ ሰከንዶች አልወሰደበኝም። በሮች ሁሉ ዝግ የነበሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከኦሎምፒክ ስታዲዬሙ አጠገብ የሚገኘው የአትሌቶች መለማመጃ ቦታ ላይ ያገኘሁት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ቡድን አባል ስለቡድኑ አንዳንድ ዝግጅቶች እንዲነግረኝ ስጠይቀው “ለቃለምልልስ ከላይ ትእዛዝ ማግኘት አለብኝ” የሚል መልስ ከመስጠቱ በተጨማሪ “የፕሬስ አታሼውን ስልክ ቁጥር ነገ አመጣልሀለሁ” ብሎኝ ከተለያየን በኋላ እንደተደበቀኝ የለንደን ኦሎምፒክ ተጠናቀቀ።
በኦሎምፒኩ የፕሬስ አታሼው ቀዳሚ ስራ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ግንኙነቶችን በመፍጥር ለሚመለከተው አንባቢ፣ ተመልካችና አድማጭ ስለሚፈልጋቸው ሰዎች መረጃዎችን እንዲያገኝ ማስቻል ቢሆንም ገበያው ታከለ ግን አይደለም የኢትዮጵያ አትሌቶችን ሊያገናኝ እራሱም ሳይገናኝ ቀርቷል።

የለንደን ኦሎምፒክ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ወደከተማዋ የመጡት የተለያዩ ሀገሮች ኦሎምፒክ ቡድኖች ፕሬስ አታሼዎች የሚሰሩትን ውጤታማ እንቅስቃሴ አንባቢዎቼ ብታዩ ኖሮ በኢትዮጵያ ቡድን ሀላፊዎች እጅግ በጣም ነበር የምታፍሩት። የአሜሪካ ቡድን ፕሬስ አታሼ “በዚህ ቀን ሎሎ ጆንስ፣ ሳኒያ ሪቻርድስ፣ አሊሰን ፊሊክስ፣ አሽተን ኢተን እና ትሬይ ሀርዲ ጋዜጣዊ መግለጫ ይኖራቸዋል” የሚል መልእክት ለመገናኛ ብዙሀን ሲበትኑ፤ የቦትስዋናው ወኪል ደግሞ አማንትሌ ሞንሾ መቼ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚኖራት የሚያሳይ መረጃ ይልክልናል። ጀርመናዊኑ አትሌቶች መቼ ለጋዜጠኞች ክፍት የሆነ የልምምድ ጊዜ እንደሚኖራቸው ፕሬስ አታሼው ሲነግራችሁ፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬስ አታሼ ደግሞ “ኦስካር ፒስቶሪዬስ በዚህ ቀን እና በዚህ ቦታ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል” ይላችኋል። የጣሊያን ፕሬስ አታሼ ከሀገሩ አትሌቶች ጋር የተገናኙ መረጃዎችን በተለያዩ መንገዶች ሲልክላችሁ፣ የኬኒያው ደግሞ ዴቪድ ሩዲሻ፣ ቪቪዬን ቼሪዮት እና ሳሊ ኪፕዬጎ ከጋዜጠኞች ጋር ውስን ደቂቃዎች ያሉት የቃለመጠይቅ ፕሮግራም እንደሚያደርጉ አስቀድሞ ይነግራችኋል። ገበያው ታከለ እና ባልደረቦቹ ታዲያ ይሄንን ከማድረግ ይልቅ በየሀበሻ ሬስቶራንቱ እየዙሩ ክትፏቸውን መብላት፣ ቸኮሌት መሰብሰብ፣ ፌስታል ሞልቶ ወደአረፉበት ቦታ አምሽቶ መግባት እና ወደሀገራቸው ሲመለሱ አትሌቶቹ ለፍተው ባገኙት ውጤት ምክንያት የሚሸለማቸውን ነገር ምን እንደሆነ ማሰላሰል ነበር ስራቸው።
አትሌቶች ከተወዳደሩ በኋላ ወደመልበሻ ቤታቸው ከመመለሳቸው በፊታ የሚያልፉት የመገናኛ ብዙሀን በቆሙበት “ሚክስድ ዞን” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሲሆን ይህ ቦታ ጋዜጠኞች አትሌቶቹን ስለውድድሩና ስለብቃታቸው የሚጠይቁበት ቦታ ነው። እዚህ ቦታ ላይ አትሌቶቹ ለጥያቄ መልስ ያለምስጠት መብት ቢኖራቸውም አብዛኞቹ ለማውራት ፈቃደኞች ናቸው፤ በተለይ ለየሀገሮቻቸው መገናኛ ብዙሀን። ሚክስድ ዞኑ መግቢያ ላይ ውድድር ያላቸው አትሌቶች ሀገሮች ፕሬስ አታሼዎችን ማየት የተለመደ ነው። የእነሱ ቀዳሚ ስራ አትሌቶቻቸው ልክ ውድድራቸውን እንደጨረሱ ወደሚክስድ ዙኑ ሲመጡ አትሌቶቹን ይዘው የሀገሮቻቸው መገናኛ ብዙሀን ጋዜጠኞች ወደቆሙበት ቦታ መውሰድ እና ለሌላ ቋንቋ ተናጋሪ መገናኛ ብዙሀን የአትሌቱ አስተርጓሚ ሆኖ ማገልገል ሲሆን፣ እኔም ሆንኩ የሌላ ሀገር ጋዜጠኛ አትሌቶቹን ለማናገር ከፈለገ ሊያቆሙለትም ዝግጁ ናቸው። ታዲያ እዛ ሚክስድ ዞን ያልነበረና በጭራሽም ያልታየ የፕሬስ አታሼ ቢኖር የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ተወካዩ ገበያው ታከለ ብቻ ነበር ብል እያጋነንኩ አይደለም።
ለነገሩ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች በአስተሳሰባቸው ከአብዛኞቹ የቡድኑ ሀላፊዎች ፍጹም በተሻለ መልኩ የሰለጥኑ እና ቅኖች በመሆናቸው ወደ ሚክስድ ዞኑ ሲመጡ ለጥያቂ ሳስቆማቸው ሁሉም ለመቆም ፈቃደኞች እና ደስተኞች ነበሩ። ነገር ግን እንግሊዘኛ ቋንቋን አቀላጥፈው መናገር የሚችሉት እጅግ በጣም ጥቂቶች በመሆናቸው ፕሬስ አታሼያቸው አጠገባቸው አለመኖሩ በአስተርጓሚነት እንኳን እንዳይረዱ አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያዊያኖቹ ታላላቅ አትሌቶች ለእኔ ሲቆሙ ያዩ የኦሎምፒክ ዜና አገልግሎት ባልደረቦቼ እጅግ በጣም ከመገረማቸው በተጨማሪ የሌሎች አገሮች ጋዜጠኞች ልክ አትሌቶቹን ከጠየኩ በኋላ ቶሎ ወደቢሮ ገብቼ የተናገሩትን የመረጃ መሰብሰቢያው ውስጥ ከማስገባቴ በፊት እንድተረጉምላቸው ይጠይቁኝ እና መረጃዎቹን በዚህ መልኩ ያገኙ ነበር። በተለይ ከሴቶች 5 ሺህ ሜትር ማጣሪያ በኋላ በመጀመሪያው የማጣሪያ ቡድን ውስጥ የነበሩት ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር አብረው ወደ ሚክስድ ዞኑ ሲመጡ “መቼም የደከማቸው ሯጮችን በተራ ለመጠየቅ በሚል ብዙ አላቆማቸውም” ብዬ እያሰብኩ እንዳለ ሁለቱም ፈቃደኛ መሆናቸውን ከተለመደው በእጅ የመጨባበጥ ሰላምታችን በኋል ገልጸውልኝ ፊት ለፊቴ የነበረችው መሰረትን እየጠየኩ ጥሩነሽ ቆማ ስትጠብቀኝ “ምን አለ የቡድኑ ሀላፊዎችም እንደእንዚህ አትሌቶች ቅኖች በሆኑ” የሚለው ሀሳብ ውስጤ ይመላለስ ነበር። አጠገቤ የነበሩት የሮይተርስ፣ ኤ.ኤፍ.ፒ እና ኤ.ፒ ጋዜጠኞች የፎቶ ካሜራቸውን አውጥተው ሁለቱን ድንቅ አትሌቶች ያነሱ ነበር። ልክ ሁለቱንም ቃለምልልስ አድርጌ እንደጨረስኩ የጋዜጠኞቹ የመጀመሪያ አስተያየት “እንዴት ትእግስተኞች ናቸው” የሚል ነበር። ታዲያ ቃለምልልሱን በፍጥነት እየተረጎምኩላቸው እያለ አንደኛው ጋዜጠኛ “ፕሬስ አታሼያቸው የታለ?” የሚል ጥያቄ አነሳ። ‘እዚህ ድርሽ ብሎ አያውቅም’ የሚል መልስ ሥሰጥ፤ እነሱም ሊያገኙት ሞክረው እንዳልተሳካላቸውና ቢያንስ ሚክስድ ዞን እንኳን ሲመጣ እናገኘዋለን ብለው ጠብቀው እንደነበር ነገሩኝ።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ፕሬስ አታሼ ሚክስድ ዞን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአንዱም ኢትዮጵያዊያን የሜዳሊያ ባለቤቶች በተገኙባቸው የፕሬስ/ሚዲያ ኮንፍረንሶች ላይ አልተገኙም። ኢትዮጵያዊያን የሜዳሊያ ባለቤቶች ያደረጓቸውን ፕሬስ ኮንፍረንሶች ላይ በሙሉ ስገኝ የመጀመሪያው ስራዬ ገበያው ታከለን መፈለግ ነበርና ሰውዬው የትም ሊታዩ አልቻሉም። “የት ናቸው?” ምን አልባት ከኦሎምፒክ ስታዲዬሙ ይልቅ በርካታ የሀበሻ ምግቤቶች በሚገኙባቸው የለንደን ጎዳናዎች ካሊዶኒያን ሮድ፣ ፊንስበሪ ፓርክ እና ሸፐርድስቡሽ አካባቢ እያውደለደሉ ይሆናል የሚል ነበር ለራሴ የምሰጠው መልስ።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ሀላፊዎች እና የሀገሪቷ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በድንቆቹ አትሌቶች ብርታትና ጥንካሬ በሚገኙ ውጤቶች ጀርባ ተደብቀው እያጭበረበሩ ሲኖሩ ቆይተዋል። አትሌቶች ላይ ጫናን እና ጭንቀትን ከመፍጠር እና የህዝብን ገንዘብ ከማጭበርበር ውጪ ሌላ ስራ የላቸውም። የኦሎምፒክ ስታዲዬሞች የሚያስገባቸው አጋጣሚው ተመቻችቶላቸው እያለ የሀገራቸው አትሌቶች ያደረጓቸውን ውድድሮች በሙሉ ቁጭ ብለው የተመለከቱ የኢትዮጵያ ቡድን ሀላፊዎች እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ልክ የፍጻሜ ውድድሮች ሲኖሩ ብቻ ስታዲዬም በመገኘት የፉገራ አርበኝነታቸውን ባንዲራ በማውለብለብ ለማሳየት ከመሞከር ውጪ አትሌቶቻቸው ድጋፍ ሲጠይቋቸው “አለሁ” ብለው አይገኙም ነበር።
ወደሀገራቸው ሲመለሱ ከባለድሎቹ አትሌቶች ቀድመው ከአውሮፕላኑ ደረታቸውን በመንፋት የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያን መሬትን የሚረግጡት እነዚህ ስራ-ፈት የቡድን ሀላፊዎችና ከህዝብ በተዋጣ ገንዘብ የተገዙ የለንደን እቃዎች የወጠሯቸው ሻንጣዎቻቸው ናቸው። ከዛ በኋላ ያለምንም እፍረት “የገንዘቡና የተለያዩ ሽልማቶች ተካፋይ ካልሆንን” ይላሉ። እነዚህ የማያፍሩ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ሀላፊዎች እና አባላት ከጋዜጠኞች “ለምንድነው የተጠበቀውን ያህል ሜዳሊያዎች ያላገኘነው?” የሚል ጥያቄ ከቀረበላቸው ያለምንም እፍረት ወጣቶቹን እና አቅማቸው በሚችለው መጠን የለፉ አትሌቶችን ከመተቸት ወደኋላ እንደማይሉ አልጠራጠርም፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት አድርገውታልና።

No comments:

Post a Comment