"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday, 2 August 2012

ትንሽ ወሬ፤ “መለስን ጥራ ሲሉት በረከት መጣ!



በመጀመሪያ ርዕሱን ቁልብጭ ለማድረግ ብዬ የተከበሩትን ሰዎች አንተ በማለቴ ይቅርታ ጠይቃለሁ። (በቅንፋችንም ካለፉት ጊዜያት ልምድ በመነሳት ባለስልጣኖቻችንን እኔ የተከበሩ ብዬ ስጠራ አንዳንድ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች የተቀበሩ ብለው እንደሚያነቡ ተደርሶበታል። ነገር ግን ይህ አግባብ አለመሆኑን ለማሳሰብ እወዳለሁ። ምክንያቱም ቀብር ገና ነውና…! የተቀበሩ አይባልም እላለሁ!)
ትለንት ቀን ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዜና እወጃ “የአቶ መለስ ጤና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ” የሚል ዜና ሰምተን፤ አለቅጥ ተደስተን፣ ልባቸን በሀሴት ሰክራ ዋለች። አንዳንዶችም “አላዛርን ከሞት ያስነሳ ታምሩ የማያልቅ ጌታ እንደምን ያለ ፅድቅ ቢሰሩ እንዲህ አስነሳቸው…!”  እያሉ ለአምላካቸው ምስጋና አቀረቡ! ዝርዝር ዜናውን ለመስማት ጋዜጠኛይቱ “ምሽት ላይ እንገናኝ” ብላ ቀጠረችን።
ምሽት ለካስ እንዲህ ቀርፋፋ ነው…!? ምሽቱን መጠበቅ የአለም ፍፃሜን ከመጠበቅ እኩል ረዘመብን።
በሀሳባችን መለስ እንደወትሮው ከዙፋናቸው ጉብ ብለው “ስለ ተጨነቃችሁልኝ አመሰግናለሁ… ትንሽ ጉንፋን ብጤ ይዞኝ ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያን ሰላም ማየት ያማይሹ የውጪ ሃይሎች የሻቢያ ተላላኪዎች እና የሀገር ውስጥ ነጭ ለባሾች ብዙ ነገር ሲያስወሩ እንደነበር ሰምቻለሁ እኔ ግን ይኸው አለሁ።” ሲሉን እየታየን ፈነደቅን።
እንዳይመሽ የለ መሸ። በዜናው እወጃ ላይ ግንባር ቀደሙ ወሬ ቀን ቀጠሮ የያዝንለት የአቶ መለስ ጤና ተሻሻለ የሚለው ሆነ። ለወትሮው እርሳቸው ተይዘው የአርሶ አደሩ ምርት ተሻሻለ የሚል ዜና መስማት የታከን ሰዎች ርዕሱ ብቻ አጠገበን!
ቀጥሎ በአይናችን እስክናያቸው ወይም በስልክ ድምፃቸውን እስክንሰማ እየጠበቅን ከቀናት በፊት “ሞታቸውን አረጋገጥኩ” ያለውን ኢሳት ቴሌቪዥንን እያብጠለጠልን ዝርዝሩን መጠባበቅ ጀመርን።
ዝርዝሩ መጣ
የመጡት ግን አቶ መለስ ሳይሆኑ አቶ በረከት ስምዖን ናቸው። “የትራንስፎርሜሽን እቅዱ እየተሳካ ነው…” ሲሉ ጀመሩ። ምን ለማለት ፈልገው ነው? “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህመም የትራንስፎርሜሽን እቅዱ አካል ነው!” ሊሉን ነው እንዴ…!? ብለን መነጫነጭ ጀመርን። ጆሯችን የአቶ መለስን ድምፅ አይናችንም ምስላቸውን የናፈቅን ግለሰቦች አቶ በረከትን ጠላናቸው…! እርሳቸው ግን የእኛ ጭንቀትም የጠቅላያችን ህመምም ግድ የሰጣቸው አይመስሉም እግራቸውን አነባብረው። ስለ ግድቡ ግንባታ ስለ ስኳር ልማት ጅማሮ ማውራታቸውን ቀጠሉ… ኦ… ኦ… “ኧረ ወደ ገደለው ይግቡልን” አረ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ያምጡልን!
አቶ በረከት እንደ ድሮ “ኤንትሬ” መኪና ዞረው ዋናውን መንገድ ለመያዝ ብዙ ከተቸገሩ በኋላ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህና ናቸው! በአሁኑ ሰዓት እረፍት ላይ ይገኛሉ” ብለውን መግለጫቸውን ጨረሱ።
እንዴ አቶ በረከት ይህንንማ ነግረውናል… ኧረ የተወራውን የሚያከሽፍ ማስረጃ ያምጡልን… ኧረ ሞቱ የተባሉት እርስዎ አይደሉም እርስዎን ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን አሳዩን! ኧረ የህግ ያለህ፣ ኧረ የመረጃ ያለህ፣ ኧረ የማስረጃ ያለ…! ብለን ብንጮህም ሰሚ የለም። ይሄን ጊዜ የመጣው ይምጣ ብለን ተረትን “መለስን ጥራ ቢሉት በረከት መጣ!”
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዜናው ቀጥሎ የቀረበው የህትመት ዳሰሳ ፕሮግራም ዛሬም ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ እንጃ ማህበራዊ ድረ ገፆችን ክፉኛ አጣጥሏል። ጎረምሶቹ ጋዜጠኞች ራሳቸውም ፌስ ቡክ እና ትዊተር ገፅ እንዳላቸው ገልፀው ያለ ምንም ተቆጣጣሪ የፈለጋቸውን እንደሚፅፉ እና ያ ግን መታመን እንደሌለበት ሲናገሩ ሰማኋቸው። በእውነት አሳዘኑኝ። ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ክፉኛ ቁጥጥር ስላስለመዳቸው ቁጥጥር አልባ ነፃ መረጃ ሁሉ ውሸት ይመስላቸዋል። አላዩ የፌስ ቡክ ወዳጆቻችን እንዴት ያለ የህሊና ቁጥጥር እንዳለባቸው…! አላዩ የፌስ ቡክ ወዳጆቻችን መረጃ አልባ ወሬን እንዴት እንደሚፀየፉ…!
ለማንኛውም ግን “ይቺ ጠጋ ጠጋ እቃ ለማንሳት ነው” እንዲሉ የአራዳ ልጆች በተደጋጋሚ ማኅበራዊ ድረ ገፆችን ኢቲቪ እያጣጣለ ነውና ሊዘጉብን ይሆን ብለው እየሰጉ ያሉ ብዙ ናቸው።

No comments:

Post a Comment