የጠቅላይ ሚኒስትሩን መሞት ቀድመው የተረዱት የግብፅ ባለስልጣናት “ከቀጣዩ መንግስት ጋር በአባይ ጉዳይ ላይ መግባባት ይኖረናል ብለን እናስባለን!” ሲሉ በደስታ መናገራቸውን ሰምተናል።
አሁን በቅርቡ ደግሞ አልሸባብ ሆዬ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት መደሰቱን ገልፆ ከዚህ በኋላ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ትበታተናለች ሲል “ቅዠቱን” ጮቤ እየረገጠ ሲነግረን፤ መቼም ጆሮ አልሰማ አይልምና አድምጠናል።
ይሄ ስለ ኢትዮጵያውያን ማንነት ጠንቅቆ ካለመረዳት የመጣ የግንዛቤ ችግር የፈጠረው ፈንጠዝያ ነው።
እርግጥ ነው ባለፉት ግዜያት በተለይም አንዳንድ የኢህአዴግ ዋና ካድሬዎች የአቶ መለስን ስዕል ከኢትዮጵያችንም በላይ አጉልተው ለማሳየት መከራቸውን ሲያዩ እኛም “ተዉ ይሄ ነገር ጥሩ አይደለም” እያልን በመምከር አበሳችንን ስናይ ከርመናል።
በተለይ ከሆነ ጊዜ በኋላ የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶግራፍ በየአደባባዩ እና በየቢሮው እየተሰቀለ ሀገሪቷ የእርሳቸው ሳሎን ቤት እስክትመስል ድረስ እጅግ የተጋነነ ስዕል ሲሰጣቸው ቆይተዋል። ከዛም በላይ “አባይን የደፈረ ጀግና!” በሚል ውዳሴ ግድቡ የእርሳቸው እና የኢህአዴግ ብቻ በማድረግ ታሪካዊ የሚባል ስህተት ሲሰራ ቆይቷል። ይህም በብዙዎች ዘንድ እርሳቸው ከሌሉ አባይም ሆነ ሌላው ልማት የሌለ መስሎ እንዲሰማቸው አድርጓል።
እንደ ምሳሌ ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አቶ መለስ ስልጣን ቢለቁስ? የሚል ጥያቄ በተጠየቁ ግዜ የመለሱትን መልስ ማንሳት በቂ ነው። ዶክተሩ መለስ ስልጣን ቢለቁ “ተተኪዎች ሀገር ያስተዳድራሉ የተጀመሩትን ይጨርሳሉ የተበላሹትን ያስተካክላሉ” ብለው አይደለም የመለሱት፤ ይልቁንም “ግድቡን ለማን ትተው…? የጀመሩትን ልማት ሳይጨርሱ ምን ሲደረግ ስልጣን ይለቃሉ…? ይሄማ አይሆንም!” ነበር ያሉት።
ይህ ግለሰብን ከሀገር በላይ አግዝፎ የማየት እና የማሳየት ችግር ትልቅ ጥፋት እንደሆነ የሚታወቀው እንዲህ ያለው ቁርጥ ቀን ሲመጣ ነው።
ይህ የተጋነነ ስዕል ነው ዛሬ አልሸባብም ሆነ የግብፅ ባለስልጣናት መለስ ከሌሉ ኢትዮጵያ የማትኖር አይነት የልብ ልብ እንዲሰማቸው ያደረገው።
አባይ የአቶ መለስ አይደለም። አባይ እንኳንስ ሌላው ቀርቶ የኢህአዴግም አይደለም። አባይ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።
በነገራችን ላይ አባይ የተደፈረው ዛሬ በኢህአዴግ ዘመን አይደለም። ንጉስ ኃይለ ስላሴም ሆኑ ደርግ በአባይ ላይ የሰሯቸው ጥልቅ ጥናቶች ዛሬ ለተጀመረው ግንባታ መሰረት ናቸው። እንደውም በአባይ ጉዳይ ላይ ኢህአዴግ ከሚወቀስባቸው ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው የራሱን የሆነ ወቅታዊ እና የተጠናከረ ጥናት ሳያደርግ በነዚህ የቆዩ ጥናቶች ላይ ተንተርሶ በመቻኮል ወደ ግንባታ መግባቱ ነው።
በአባይ ጉዳይ ላይ የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም ቅሉ ግብፆች እንደሚያስቡት ግን ግንባታው መለስ ሲኖር የሚቀጥል መለስ ሲሞት ቀጥ የሚል አይደለም።
ባለፈው ግዜ አቦይ ስብሀት እንዳሉት፤ ከእርሳቸው በፊት ደግሞ እኛ እንዳልነው አባይን መለስ አልደፈሩትም። ኢህአዴግም አልደፈረውም። የደፈረው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። እናም “የኢትዮጵያ ህዝብ” የሚባለው በህይወት እስካለ ድረስ በዓባይ ላይ የተለየ ድርድር እና የተለየ አቋም ይኖራል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።
እርግጥ ነው አባይ የግብፅ ፍቅረኛ እንደሆነ እናውቃለን። እዚህ ላይ ተቃውሞ ያለው ያለመኖሩን ያኸል ኢትዮጵያ ደግሞ የሰማኒያ ሚስቱ እንደሆነች የሚጠራጠር ኢትዮጵያዊ አይኖርም። ኖሮም አያውቅም።
አቶ አልሸባብም “በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ትበታተናለች” በሚል የሰጠው አስተያየት ለአቶ መለስ ስንሰጠው ከነበረ የተጋነነ ስዕል ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። በአልሸባብ ቤት ከአቶ መለስ በኋላ የኢትዮጵያ ጥንካሬ የለም። ይሄ ትልቅ ዜሮ የሚያሰጥ ግድንግድ ኤክስ ነው።
ኢትዮጵያ ድሮም ነበረች አሁንም ትኖራለች። መለስ ሲኖሩ የሚጠብቅ መለስ ሲሞቱ የሚረግብ ጥንካሬ የለንም።
ውድ የኢህአዴግ መንግስት ተቃዋሚዎች ሆይ በየስትራቴጂ መግለጫዎቻችሁ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት መመስከር ያለባችሁ ግዜ ላይ እንዳላችሁ አመላክቶኛል።
ውድ የኢህአዴግ ደጋፊዎች በየ ሀዘን መግለጫዎቻችሁ ላይ የሞተው መለስ እንጂ ኢትዮጵያ እንዳልሆነች መመስከር ያለባችሁ ግዜ ላይ እንዳለባችሁ አመላክቶኛል።
“ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም!”
No comments:
Post a Comment