(ናትናኤል ፈለቀ)
ኅዳር 12 ቀን 2005 ዓ.ም በሥራ ጉዳይ ወደ ጋሞ ጎፋ ዞን ዋና ከተማ አርባ ምንጭ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ለሁለት ቀን ተኩል የሚበቃኝን ሸክፌ ከመሥሪያ ቤቴ በተመደበልኝ መኪና ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ለሚነሳው በረራ ለመድረስ ወደቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ በቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን በኩል ወደ ቦሌ የሚወስደውን መንገድ ይዘን ስንጓዝ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ ላይ የተደረደሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት አቀባበል ወይንም ሽኝት የሚደረግለት ባለሥልጣን/እንግዳ እንዳለ ስለጠቆመኝ መንገዱ ሳይዘጋ ቦሌ ለመድረስ ጥረት እንዲያደርግ ለሹፌሩ ጠቆምኩት፡፡ ብዙም ሳንጓዝ አትላስ ሆቴል የትራፊክ መብራት ላይ ስንደርስ በስፍራው የነበሩት የትራፊክ ፖሊሶች ወደ ቺቺንያ ወይንም ወደ ቦሌ ሩዋንዳ የሚወስደውን መንገድ እንድንጠቀም አስገደዱን፡፡ ወዲያውኑ ሰዓቴን ተመለከትኩ፤ ለሰባት ሰዓት ሩብ ጉዳይ ይላል፤ ብዙም አልተረበሽኩም፡፡ በስተቀኝ በኩል ታጥፈን በውስጥ ለውስጥ አቋራጭ መንገድ ጥቂት ከሄድን በኋላ መልሶ ዋናውን መንገድ ስላገናኘን መኪናውን አቁመን እንግዳውን እስኪያልፍ መጠባበቅ ጀመርን፡፡
በዚያው ሰሞን ወደ ሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ሄዶ የነበረ አንድ የሥራ ባልደረባችን በአምስት ቀን ቆይታው ሁለት ጊዜ በመንገድ ያለፋቸው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በከተማው መንገድ ላይ ሲጓዙ እሳቸው ከሚጓዙበት አቅጣጫ በተቃራኒው የሚወስደው የመንገዱ ጎን ክፍት እንደሚሆን የነገረኝን ለሹፌሩ እያጫወትኩት ሳይረን እያሰማ የሚከንፈውን ሞተረኛ ተከትለው ካልተሳሳትኩ አምስት መኪኖች በፍጥነት ወደ ቦሌ የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሲያልፉ አየን፡፡ ካለፉት መኪናዎች ሦስቱ ባለግርማ ሞገሶቹ ጥቋቁር ሼቭሮሌቶች ነበሩ፡፡ ያለፉት ባለሥልጣን ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መሆን አለባቸው (በእርግጥም ነበሩ፤ ለሥራ ጉብኝት ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ እያቀኑ)፡፡ እንደ ሥራ ባልደረባችን ከሆነ ፕሬዝዳንት ካጋሜን የሚያጅቡት አንድ ሞተረኛ ፖሊስ ከፊት እና አንድ መኪና ከኋላ ሆነው ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ይህን ሁሉ ጥበቃ የሚደረግላቸው ከፕሬዝዳንት ካጋሜ ይልቅ ለደኅንነታቸው የሚሰጉ መሪ ስለሆኑ ነው? ወይስ ኢትዮጵያዊያን ከሩዋንዳዊያን ይልቅ አስፈሪ ሕዝብ ስለሆንን? ይህንን እቆቅልሽ እያሰላሰልኩ መንገዱ ተከፍቶ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የአገር ውስጥ በረራ የሚደረግበት ጣቢያ ቁጥር 1 ደረስኩኝ፡፡