"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday 5 September 2012

የኢህአዴግ ስብሰባ ሊቀ መንበሩን ሳይመርጥ ተበተነ


   (ኢ.ኤም.ኤፍ ልዩ ዘገ) የመለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ የተጠራው የኢህ አዴግ ስራ አስፈጻሚ አካላት ስብሰባ በዋና ዋና የስልጣን ሽግሽግ ጉዳይ ሳይስማማ መበተኑን በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ የደረሰው ዝርዝር ዘገባ ያስረዳል። በዘገባው መሰረት በኢህ አዴግ የጉባዔ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ስብሰባው ለመለስ ዜናዊ  የህሊና ጸሎት በማድረግ ነበር የተጀመረው። ከዚያም የአዲስ አበባ ህዝብ እና የሌላ አገር መሪዎች ያደረጉት የሃዘን መግለጫ ጉዳይ የመጀመሪያው መነጋገሪያ አጀንዳ ነበር።
ይህ የህዝቡ ሃዘንም ህዝቡ ምን ያህል ኢህአዴግን እንደሚወደው አመላክች ጉዳይ መሆኑን፤ እራስን በማሞገስና በኩራት በመጀቦን ነበር ስብሰባው የቀጠለው። በስብሰባው ላይ ከጠቅላላው 36 ተሰብሳቢዎች መካከል ሲከራከሩና ብዙ ሲናገሩ የነበሩት የሚከተሉት የድርጅት አባላት ነበሩ። ከህወሃት በኩል አባይ ወልዱ፣ ድ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ጸሃየ በርኼ፣ በየነ ምትኩ፣ አዜብ መስፍን፣ ቴዎድሮስ ሃጎስ፣ አባዲ ዘሙ እና ደብረጽዮን ገ/መስቀል ሲሆኑ፤ በኢህዴን / ብአዴን በኩል ደግሞ ደመቀ መኮንን፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አዲሱ ለገሰ፣ አያሌው ጎበዜ፣ ብርሃን ኃይሉ፣ በረከት ስምኦን እና ተፈራ ደርበው ተገኝተው በህወሃት ሰዎች ላይ ጫና የሚያሳድር ንግግር ሲያደርጉ ነበር የቆዩት። የኦህዴድ እና የደቡብ ህዝብ ተወካዮች በትግራይ እና በአማራ ድርጅቶች መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት ሲያደርጉ ነበር የተስተዋለው። ኦህዴድ በአቶ አለማየሁ አቶምሳ እየተመራ እነ ግርማ ብሩ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ አባዱላ ገመዳ፣ ሙክታር ከድር እና 4 ሌሎችንም ይዞ ሲቀርብ፤ የደቡብ ህዝቦች ደግሞ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መሪነት እነ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ሬድዋን ሁሴን፣ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያምና 5 ሌሎችን በስብሰባው ላይ አሳትፏል። እስከ ምሽት ድረስ በዘለቀው በዚህ ስብሰባ ላይ በተለይ በአቶ በረከት ስም ኦን በኩል የሚቀርቡ ሃሳቦች ሆን ተብለው በህወሃት ሰዎች ውድቅ ሲሆኑ ነበር የተስተዋለው። በተለይም የኢህ አዴግን መሪ ወይም ሊቀ መንበር ማስመረጥን አስመልክቶ የተነሳው ሃሳብ በወ/ሮ አዜብ መስፍን እና በሌሎች የህወሃት አባላት የመረረ ተቃውሞ ቀርቦበታል። በተለይም ህወሃት አንድ አባሉ (መለስ ዜናዊ) በመሞቱ ምክንያት የሰው እጥረት እንዳለበት ገልጿል። በዚህም መሰረት ህወሃት በሚቀጥሉት 15 ቀናት የራሱን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መቐለ ላይ እንዲጠራ፤ ከዚያም በመለስ ዜናዊም ሆነ አሁን ብቃት የላቸውም በሚላቸው አመራር አባላት ምትክ ሰው እንዲያሟላ ተብሏል።

 ከዚያ በተረፈ ግን የርስ በርስ ውዝግቡን ካበረዱት ሌሎች አጀንዳዎች መካከል፤ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበረበት ወቅት የነደፈውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አሁን ያለውን የህዝብ ተነሳሽነት በመጠቀም እንዴት አድርገን እናሳካዋለን የሚለው አጀንዳ ነበር። በዚህም መሰረት በተለይ አሁን ያለውን የህዝብ ተነሳሽነት ይዞ ለመቀጠል “5 ለ 1” (ለ5 ሰው አንድ ሰው የሚመደብበት የአፈና መዋቅር ነው) የሚለውን የኢህአዴግ አደረጃጀት አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። በተለይ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ተጨማሪና የተሻለ የህዝብ አደረጃጀት አስፈላጊነቱ ታምኖበት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባላት የተስማሙት። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በተለይ የከተማውን ወጣት ለመያዝ  የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ማህበራት ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለዚህም የአዲስ አበባ ከንቲባ ኦቦ ኩማ ደመቅሳ ብዙ ስራ እንደሚጠብቀው ተገልጿል።

ከዚያ ውጪ በተለይ የአማራ ክልል ፕሬዘንዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ደጋግመው እንደገለጹት በገጠር የተፋሰስ ልማት፣ የመስኖና የተለያዩ የውሃ አሰባሰብ ዘዴዎች እንዲሁም በዘመናዊየግብአት አቅርቦትና የሙሉ ፓኬጅ አጠቃቀም በተመለከተ ገበሬውን ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የባቡር እና የህዳሴው ግድብ ጉዳይ በተያያዥነት ተነስቶ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ውይይት ተደርጓል።
36 አባላት የሚገኙበት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አካል ተነጋ ግሮ መፍትሄ ሊሰጥባቸው የሚገቡ የሰብአዊ አያያዝ ጉዳዮች፣ በ እስር ቤት የሚገኙ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ፤ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ የተነሱ ጥያቄዎች፣ አወዛጋቢውን የዋልድባ ገዳም፣ በትምህርት እና በጤና ፖሊሲ ጉዳይ የኢህአዴግ አውውም ምን መሆን እንዳለበት በውይይቱ ላይ ሳይነሳ ቀርቷል። ሌላው ቀርቶ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ጉዳይ ርዕስ ተሰጥቶት ውይይት አልተደረገበትም።
በአጠቃላይ ህወሃት የጎደሉ አባላቱን አሟልቶ ለሚቀጥለው ስብሰባ እንዲገኝ ነው ውሳኔ የተላለፈው። የሚቀጥለውም ስብሰባ ከአዲሱ አመት በኋላ በሳምንቱ ይደረጋል ተብሏል፤ ትክክለኛው ቀን አልተወሰነም። በሚቀጥለው የኢህአዴግ ስብሰባ ላይ ዋና አጀምዳ የሚሆነው የድርጅቱን ሊቀ መንበር እና ምክትል ሊቀመንበር መምረጥ ይሆናል። እስከዚያው ግን ለህወሃት የቤት ስራ ተሰጥቶታል። መቀሌ (መቐለ) ላይ 45 አባላት ያሉበት ማዕከላዊ ኮሚቴው ይሰበሰባል። ከማዕከላዊ ኮሚቴው መካከል ደግሞ ከዚህ በፊት ራሳቸውን ከህወሃት አመራር ያገለሉት፤ አሁን ግን በፌዴራል የመንግስት መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት እነስዩም መስፍን፣ አባይ ጸሃዬ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ፤ እንዲሁም በመለስ ዜናዊ እና በአዜብ መስፍን ምክንያት አኩርፈው ራሳቸውን ከአመራር ያገለሉት፤ በፌዴራል መንግስት ውስጥ ብዙም ሚና የሌላቸው ነገር ግን በህወሃት ውስጥ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉት አርኸበ እቑባይ እና ስብሃት ነጋ በመጪው የህወሃት ስብሰባ ላይ ተፅ እኖ ማምጣት ብቻ ሳይሆን፤ እንደገና ተመርጠው የስራ አስፈጻሚ አባል ከሆኑ በኋላ፤ በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በሚደረገው ስብሰባ ላይ በመለስ ዜናዊ ምትክ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ለመሆን ይወዳደራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመሆኑም በአሁን እና በቀጣዩ ስብሰባ መካከል ሁለት ነገር ይጠበቃል። አንደኛው በህወሃት ውስጥ የሚኖር የውስጥ ሽኩቻ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የህወሃትን ሽኩቻ አሸንፈው ወደ ለኢህአዴግ ስብሰባ በአዲስ መንፈስ አዲስ አበባ የሚመጡት የህወሃት ሰዎች ምን እንደሚፈጥሩ በጉጉት ይጠበቃል። ሆኖም ህወሃት እንደመለስ ዜናዊ አይነት መሪ ስለማያገኝ፤ “በሌሎች ድርጅቶች ይዋጣል” ተብሎ ይጠበቃል። እስከዚያም ድረስ በረከት ስምኦን ሌሎች ድርጅቶች በጎንዮሽ የሚያደርጉት ምክክር ሊኖር ይቻላል፤ ይህም ምክክር ዳግም የህወሃት የበላይነት በድርጅቱ ውስጥ ተመልሶ እንዳይመጣ ማድረግ እንደሚሆን በድርጅቱ ዙሪያ የሚሰነዘሩት አስተያየቶች እያመዘኑ ነው። ሌሎች ድርጅቶች የህወሃትን የበላይነት ላለመቀበል የሚያደርጉት አዝማሚያ እንደመልካም ጅምር የሚታይ ቢሆንም፤ ይህ በራሱ ግን ከሌላ አስፈሪ ኃይል ጋር ያጋጫቸዋል። ይህም ሃይል የፖሊስ፣ የመከላከያና የደህንነት ክፍሉ ይሆናል። የነዚህ መሳሪያ ታጣቂ ኃይሎች የበላይ ሃላፊዎች በሙሉ የህወሃት አባላት ናቸው። እናም ሌሎች ድርጅቶች የህወሃትን የበላይነት ላለመቀበል የሚያደርጉት ትግል፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ከህወሃት ወታደራዊ ኃይል ጋር ሊያጋጫቸው ይችላል። ለሁሉም ግን መጪዎቹ የህወሃት እና የኢህአዴግ ስብሰባዎች ወሳኝነት ስላላቸው ሁሉንም አብረን እንከታተል።

No comments:

Post a Comment