"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday, 3 July 2012

በላሽው አንጀቴን በላሽው ጭር ባለው ሜዳ ዲሲ ላይ ያለሽው

  – ከአቤ ቶኪቻው
ከትላንት ወዲያ ጁላይ 1 ቀን 2012 የተጀመረው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባህል ፌስቲባልን በያለንበት ሆነን በፎቶም በቪዲዮም አይተነው ነበር።
በነገራችን ላይ ይሄ በርካታ አመታትን ያስቆጠረው አንጋፋ የፌስቲቫል ዝግጅት ESFNA በሚል መጠሪያ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ባለፉት ሰሞናት ከፍተኛ የይገባኛል ውዝግብ እና ክርክር ሲደረግበት ቆይቶ፤ ዛሬ ዳላስ ላይ የከተሙት ዋናውን ስያሜ ሲይዙ፤ በሼክ መሃመድ አላሙዲን የሚመሩት “ሃብታሞቹ” ደግሞ የፈጀውን ይፍጅ ብለው ESFNA የሚለው ላይ ONE የሚል ጨምረውበት የራሳቸውን ቡድን በማዋቀር ዲሲ ላይ ከትመው ነበር። (አክትመው ብል ይሻላል መሰለኝ… እንዴት? ማለት የጨዋ ደንቡ ነውና እንዴት ብለውኝ ይምጡ በአዲስ መስመር…)
ፌስቲባሉ በዳላስ እና በዲሲ እኩል ነበር የተጀመረው። በመጀመሪያ በዲሲ የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ ፎቶግራፍ በፌስ ቡክ ላይ ተለጥፎ ተመለከትኩ። ስታድየሙ ባዶ ከመሆኑ የተነሳ የሚከራይ ቤት ነበር የሚመስለው። እውነቱን ለመናገር አንዱ ተንኮለኛ ዝግጅቱ ከመጀመሩ በፊት ሄዶ ባዶውን ስታድየም ፎቶ አንስቶ የለጠፈልን ነበር የመሰለኝ። ትንሽ እናጋነው ብንል፤ የዲሲ ስታድየም ራቁቷን የቆመች አዕምሮዋ የተናወጠ ሰው መስላ ነበር።

ነጋዴው ሼክ መሃመድ አላሙዲን ረብጣ ዶላራቸውን አፍስሰው ስፖንሰር ያደረጉት ዝግጅት፤ እርግጥ ነው ትልቅ ስታድየም፣ ትልቅ ስፒከር እና ጮክ ብሎ የሚናገር ሰውዬ መግዛት እንደቻለ በቪዲዮ ላይ ተመልክተናል። ነገር ግን ተመልካች መግዛት አልቻለም። (በነገራችን ላይ በቪዲዮው እንዳየሁት ከሆነ ስታድየሙ ሲያስተጋባ፤ “እንዴት ነው ነገሩ እዚህ ቦታ የክብር እንግዳዋ የገደል ማሚቶ ነች እንዴ…!?” ብዬ ጠይቄ መልስ አላገኘሁም!) አንዳንድ
ሽሟጣጮችም፤ “ወይ እንደ ግንቦት ሃያ ሰልፍ አበል ቢሰጡን ሰብሰብ ብለን አንሄድ ነበር። እነርሱ ግን ወይ አበል የላቸው ወይ አመል የላቸው ግራ የገባ ነገር ሆነብን” ሲሉ የማሽሟጠጥ ግዴታቸውን ተወጥተዋል። (በቅንፍም እንደው ለሽሙጥ እንዲመች ተብሎ እንጂ በዲሲው ድግስ ላይ “ዜር ፎር” በሚመስል መልኩ ተንጠባጥበው የተገኙት ተዳሚዎች አበላቸውን “ላፍ” ያደረጉ አባሎች መሆናቸው ጭምጭምታ አለ!)
በተቃራኒው ደግሞ ዳላስ ከተማ፤ ዋናው የሰሜን አሜሪካ ባህልና ስፖርት ፌስቲበል አዘጋጆች በምስኪን ድምፅ “አትመልከቺ ሱፍ አትዬ መኪና” ብለው ጠርተው እውነትም በርካታ ታዳሚ በስታድየሙ ተገኝቷል።
በተመለከትኩት ቪዲዮላይ የቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” ሙዚቃ ደምቆ ሲዘፈን ህዝቡ ባንዲራ ይዞ “ጀዲካ” እያለ ሲያስነካው ተመልክቻሁ። አሁንም ትንሽ ላጋን እና ስታድየሙድምቀት በአዲስ አበባ የ97ቱን ሰልፍ ይመስል ነበር።
እኔ የምለው ግን እነ ሼኩ ምን ነካቸው? ምንስ ሳውድ አረቢያ ቢኖሩ ስለ ኢትዮጵያውያኑ ባህል እና ወግ እንዴት አያውቁም? የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ ብዙ ጊዜ ከምስኪኖች ጋር ነው የሚቆመው ብዙ ጊዜ ከገንዘብ ይልቅ ፍቅር ነው የሚገዛው ከጉልበተኛው ይልቅም ልቡ ለምስኪን ታደላለች…! ይሄንን አለመረዳት ልቦና ማጣት ነው። አረ ይተዉ ሼኩ ወደ ልቦናዎ ይመለሱ… አቶ አብነት ቆይ እያጠራቀምኩልዎ ነው ሌላ ቀን እንነጋገራለን!
የሆነው ሆኖ ትላንት ዲሲ ጭር ብላ ውላለች ይህንን የሰማችው ዳላስ “እኔ ጭር ልበልልሽ” ብላ ተቆርቋሪነቷን ገልፃላታለች አሉ። በዳላስ የከተመው ህዝብም “ዶሮ በጋን” ለሆኑት የዲሲ አነስተኛና ጥቃቅን ታዳሚዎች እና አዘጋጆች አንድ የድሮ ዘፈን እየዘፈኑላቸው ነው አሉ፤
“በላሽው አንጀቴን በላሽው ጭር ባለው ሜዳ ዲሲ ላይ ያለሽው”
ወዳጄ፤ እስቲ ወዳጅነታችንን ያጠንክረው… እስቲ ሰላምና ፍቅሩን ያምጣልን… እስቲ ልዩነታችንን ያጥብብልን!
አሜን አሜን አሜን…!

No comments:

Post a Comment