"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday 5 July 2012

በማር የተለወሰ መርዝ (በኢቲቪው ዶኩመንታሪ ላይ ያተኮረ ሒስ)





በነስሩዲን ዑስማን (ከአዲስ አበባ)

‹‹ምን ያቀርቡ ይሆን?›› በሚል በጉጉት የጠበቅሁትን ‹‹አንዲት ሐገር ብዙ ሃይማኖቶች›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የኢቲቪ ዶኩመንታሪ በጥሞና ተከታተልሁት፡፡ የፕሮግራሙ ዓላማ አክራሪነትን ማውገዝ፣ የሃይማኖት መቻቻልን ማጎልበት ይመስላል፡፡

የኢቲቪ ዶኩመንታሪ ብዙ ጊዜ በሾላ ድፍን ‹‹አክራሪ ቡድኖች›› እያለ ስለሚያወሳ በትክክል ማንን ማለቱ እንደሆነ ወይም ማንን ዒላማ እያደረገ እንደሆነ ለእኔ ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ ስለዚህም በዚህ ረገድ በአጠቃላይ የፕሮግራሙ ይዘት ላይ የማቀርበው ድፍን እና ጭፍን ተቃውሞ የለም፡፡ በፕሮግራሙ ላይ በቀረቡ ሰዎች የተሰጡ አስተያየቶችንም በፀጉር ስንጠቃ ደረጃ መተቸት አልፈልግም – ብዙ ሊተቹ የሚችሉ ሐሳቦች ቢኖሩም፡፡ ነገር ግን ላልፋቸው የማይገቡኝ የዝግጅቱ ግዙፍ ነውሮች እና ህፀፆችን በማያሻማ ቋንቋ ለመተቸት እፈልጋለሁ፡፡ ይህንን ለማድረግ የተገደድሁት እነዚህ ‹‹ግዙፍ ነውሮች›› እና ‹‹ሕፀፆች›› በማር የተለወሱ መርዞች ሆነው ስላገኘኋቸው ነው፡፡ ጽሑፌን በሦስት ርዕሶች ከፋፍዬ የማቀርብ ሲኾን እስከመጨረሻው ታነቡት ዘንድ እጋብዛለሁ፡፡ …


የ‹‹አክራሪነት›› ትርጉም

በፕሮግራሙ ላይ ለ‹‹አክራሪነት›› ትርጓሜ ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ ከተሰጡት ትርጓሜዎች ውስጥ የፌደራል ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣኗ እና ሌሎች ሁለት አስተያየት ሰጪዎች በተነጻጻሪ የሃይማኖት ጥናት ላይ ያተኮሩ የስነ መለኮታዊ ውይይት መጻሕፍትን እና ሲዲዎችን የ‹‹አክራሪነት›› መገለጫ አድርገው ማቅረባቸው እንደ ሙስሊም አሳዝኖኛል፡፡ አዘጋጁ ይህንን የሰዎቹን አስተያየት ያስደገፈበት ምስል ደግሞ ‹‹እውን ኢየሱስ አምላክ ነውን?›› የሚል ርዕስ ያለውን የሸኽ አህመድ ዲዳት መጽሐፍ ነበር፡፡ …

በተነጻጻሪ የሃይማኖት ጥናት (Comparative religion study) እና በስነ መለኮታዊ ክርክር (theological debate) ላይ ያተኮሩ መጻሕፍት በየትኛውም የዓለም ክፍል የ‹‹አክራሪነት መገለጫ›› ተደርገው ሲጠቀሱ ተሰምቶ አያውቅም፡፡ የስነ መለኮታዊ ክርክር ስነ ምግባርን ባልጠበቀና ቅዱሳን መጻሕፍቱን መሠረት ባላደረገ መልኩ ጥላቻን እና የግል ስሜትን መነሻ ያደረጉ ድንበር ዘለል ዘለፋዎችን አጥብቀው ከሚያወግዙት አንዱ ነኝ፡፡ በሃይማኖቶች ላይ ምሁራዊ ምርምር ማድረግ እና የምርምሩን ውጤት በመጽሐፍ መልክ ማውጣት እንደምን የ‹‹አክራሪነት መገለጫ›› ተደርጎ እንደተወሰደ ግን በፍፁም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ‹‹አዲስ ኪዳን›› የ‹‹ብሉይ ኪዳን›› መጻሕፍትን እንደሚያጣቅስ ሁሉ፣ ቅዱስ ቁርአንም ቀደምት ነቢያትንና በእነርሱ ላይ የወረዱ ቅዱሳን መጻሕፍትን እና አስተምህሮቶቻቸውን ይጠቅሳል፡፡ ለምሳሌ፣ በቅዱስ ቁርአን የሱረቱ አል ኢምራን የመጀመርያዎቹ 100 አያዎች (አንቀጾች) ‹‹አህለል ኪታቦችን›› (በተለይም ክርስቲያኖችን) በስፋት ያወሳሉ፡፡ ስለዚህም ሙስሊሙ ቁርአንን መሠረት አድርጎ ቀደምት መጻሕፍትንና አስተምህሮዎቻቸውን ሊመረምር ሃይማኖቱ ግድ ይለዋል ማለት ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ክርስቲያኑም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ ቁርአንን እና አስተምህሮቱን ሊመረምር፣ ብሎም ሁለቱም (ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑ) ከምርምራቸው ያገኙትን ዕውቀት በመጽሐፍ መልክ አትመው ገበያ ላይ ማውጣት መብታቸው ነው፡፡ ይህ በምንም መስፈርት የ‹‹አክራሪነት መገለጫ›› ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡

‹‹ለገበያ የሚሠሩ ሲዲዎች እና መጻሕፍት?››

በዚሁ ዶኩመንታሪ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት ትምህርት ሲዲዎች እና መጻሕፍት በብዛት ለሕዝቡ በሽያጭ መቅረባቸው ‹‹ገበያ ተኮር›› ተብሎ ተብጠልጥሏል፡፡ ይህ የግለሰቦች አስተያየት ሲሰጥም ኢቲቪ የዳዒ ያሲን ኑሩን የዳዕዋ ሲዲዎች ምስል አሳይቶናል፡፡ በቴሌቪዥን ሚዲያ ‹ትረካ› እና ‹ምስል› ተደጋግፈው ነው መልዕክት የሚያስተላልፉት፡፡ እናም የሃይማኖት መጻሕፍት እና ሲዲዎች በብዛት ገበያ ላይ የመቅረብ ሁኔታ በገደምዳሜ የ‹‹አክራሪነት መገለጫ›› ተደርጎ ሊጠቀስ የተፈለገ ይመስላል፡፡ ከሆነ ትልቅ፣ እጅግ ትልቅ ስህተት እየተሠራ መሆኑን በአጽንኦት መናገር እፈልጋለሁ፡፡

ገበያ ላይ ከሚገኙት መጻህፍት እና ሲዲዎች ውስጥ ጽንፈኝነትን የሚያበረታታ፣ ነውጠኝነትን የሚሰብክ ካለ እርሱን ነጥሎ ለሕግ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በተቀረ ስለ ይዘታቸው አንድ እንኳ ሳይናገሩ እንዲያው በድፍኑ የሃይማኖት መጻሕፍት መበራከትን እንደ አደጋ ማየት እና በገደምዳሜ የ‹‹አክራሪነት መገለጫ›› አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ግን በጣም አሳፋሪ እና አሳዛኝም ነው፡፡ እስከማውቀው ድረስ፣ በመስጂዶች ደጃፍ እና በመጻሕፍት መደብሮች ውስጥ ከሚገኙ ኢስላማዊ መጻሕፍትና ሲዲዎች ውስጥ ጽንፈኝነትን የሚኮንኑ፣ ከሌላ እምነት ተከታዮች ጋር ተሳስቦ እና ተከባብሮ የመኗኗርን አስፈላጊነት የሚሰብኩ፣ ልመናን በማንኳሰስ ሠርቶ የመኖርን ፀጋ የሚያወድሱ፣ በሐቅ የመነገድን ትሩፋት የሚያስተምሩ፤ የወላጆች፣ የልጆች፣ የጎረቤት ወዘተ. ሐቅን ስለመጠበቅ አስፈላጊነት የሚያስረዱ በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት እና ሲዲዎች ካላቸው ኅብረተሰብን በእውቀት የማነጽ ፋይዳ አኳያ ሊበረታቱ እና ሊመሰገኑ ሲገባ፣ ለአክራሪነት ስጋት ትረካ ደጋፊ ምስል ተደርገው ጥቅም ላይ መዋላቸው አንድም ከሙያዊ ድንቁርና፣ አልያም ለኢስላማዊ ዕውቀት መዳበር ካለ የግል የጥላቻ ስሜት የመነጨ ይመስላል፡፡

የዶክተሩ ትንቢት እና መፍትኄው

በዶኩመንታሪው ላይ ዶ/ር አብዱላህ አንትፕሴ የተሰኙ ምሁር በአፍሪካ አዳራሽ ካደረጉት ንግግር ተቀንጭቦ የቀረበ አንድ ሐሳብ አድምጠናል፡፡ ዶ/ር አብዱላህ ‹‹አገራችሁ ደሃ በሆነችበት በአሁኑ ሰአት ያላችሁ ሰላምና የመቻቻል ባህል፣ ወደፊት ሐብት ስታገኙ መልኩን ይቀይራል›› በማለት ለዚህ አባባላቸው ናይጄሪያን እና ሌላ አንድ አገርን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በእርግጥም ድንቁርና በነገሰበት አገር ሐብት ሲመጣ የግጭት መንስዔ ቢሆን አይገርምም፡፡ ኢቲቪ ከሰውየው ንግግር ውስጥ ለዚህ ችግር ያቀረቡትን መፍትኄ አላስደመጠንም፡፡ በእኔ እምነት ለዚህ መፍትኄው የኅብረተሰባችንን ሁለንተናዊ ዕውቀት በትምህርት ማነፅ እንጂ፣ የዕውቀት ምንጭ የሆኑ መጻሕፍት እና ሲዲዎች መብዛታቸውን በክፉ ዓይን ማየት አይደለም፡፡ ጥሩ የሃይማኖት ዕውቀት ያለው ማንኛውም ሙስሊም፣ መንስዔው ምንም ይሁን ምን፣ በአሰንዳቦ የተፈፀመውን የአብያተ ክርስቲያናት እና የፕሮቴስታንት አማኞች መኖሪያ ቤት መቃጠልን አጥብቆ ያወግዛል፡፡ የዚያኑ ያህል ጥሩ የሃይማኖቱ እውቀት ያለው ክርስቲያን በጉራጌ ዞን የተፈፀመውን የመስጆዶች መቃጠል አጥብቆ እንደሚያወግዝ አልጠራጠርም፡፡ በነገራችን ላይ እ.አ.አ በ1994 በሩዋንዳ በሦስት ወራት ውስጥ 800 ሺህ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎች በግፍ ሲጨፈጨፉ በርካታ የሁቱ ቀሳውስት ጭፍጨፋውን የመደገፍ እና የማበረታታት ሚና እንደተጫወቱ፣ በአንጻሩ ከሁቱ ሙስሊሞች 99 በመቶ የሚሆኑት በጭፍጨፋው ላይ እጃቸውን እንዳላስገቡ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ኢስላም የሰላም ሃይማኖት ለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ የሚሆነው ይህ ጥናት በመገናኛ ብዙኃን እምብዛም አልተራገበም፡፡ ተቃራኒው ቢኾን ኖሮ፣ በተለይ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ነገሩን እንደምን ሊያስተናግደው ይችል እንደነበር አስቡት እስቲ ….

የ‹‹PalTalk ጂሐዲስት›› እንደማስረጃ

አዘጋጁ በኢትዮጵያ የአክራሪነት አስተሳሰብ ስለመኖሩ በማስረጃ ሊያረጋግጥልን ወደ ኢንተርኔት ሄደና ጉግልን ከፈተ፡፡ ከዚያም ‹‹ፓልቶክ›› የተሰኘውን ከዓለም ዙርያ ማንነታቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ዙርያ የየግላቸውን ሐሳብ የሚያንፀባርቁበትን የውይይት ገጽ ከፍቶ የአንድ ማንነቱ ያልታወቀ እና ሊታወቅም የማይችል ግለሰብን ድምፅ አሰማን፡፡ ግለሰቡ ስለ ጂሐድ አስፈላጊነት፣ ምን ያህል ወታደርና ወታደራዊ መኮንኖች እንደሚበቁ ወዘተ. ሲቀበጣጥር ሰማን፡፡ ይሄ ማንነቱ የማይታወቅ ግለሰብ በአማርኛ ስለሚናገር ኢትዮጵያዊ፣ ስለ ጂሐድ ስለሚያወራ ሙስሊም፣ በድምሩ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሙስሊም›› ተደርጎ እንዲወሰድ እና ኢትዮጰያ ውስጥ ጂሐድ የማወጅ ሐሳብ ያላቸው ‹‹አክራሪ ሙስሊሞች›› አሉ የሚል ግንዛቤ እንዲፈጠር ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ በ‹ፓልቶክ› ድምፁ የተሰማው ይህ ግለሰብ መሐመድ ይሁን ገብረመድኅን ሊታወቅ እንደማይችል የዶክመንታሪው አዘጋጅም ሆነ አለቆቹ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን በፕሮግራሙ ላይ የተደመጠው የዚህ ግለሰብ ድምፅ ‹‹ፓልቶክ›› ከሚባል፣ ማንነቱ ያልታወቀ ማንኛውም ግለሰብ ያሻውን ከሚናገርበት የኢንተርኔት መድረክ ላይ የተቀዳ መሆኑን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደማያውቅ የሚያውቁት እነ አቶ በረከት ስምፆን ሕዝባቸው ይህንን የነስሬ ይሁን የገብሬ የማይታወቅ ንግግር እንዲሰማ አደረጉ፡፡ የዚህ ዓላማ በአገሪቱ ያሉ የሌላ እምነት ተከታዮችን ማሸበር ይመስለኛል፡፡ ከቶ ከዚህ ሌላ ትርጉም ሊኖረው ይችላልን?! መንግሥታችን በቁጥጥሩ ሥር ያለውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ሕዝቦቹን ለማሸበር፣ ብሎም ሙስሊሙ እና ክርስቲያኑ እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያይ ለማድረግ አልሞ እንዲህ ያለ ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ሲሠራ ማየት የሚያሳፍር እና የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የሚያስደነግጥም ጭምር ነው፡፡

እንዲህ ያለ ንግግር በግል ጋዜጣ ላይ ታትሞ ቢወጣ፣ ወይ በግል ራዲዮ ጣቢያዎች ቢደመጥ ኖሮ በአገራችን ሕግ መሠረት ምን እንደሚደረግ የታወቀ ነው፡፡ የጋዜጣው አሳታሚም ሆነ የጣቢያው ባለቤት እንዲሁም ድምፁን ለህዝብ እንዲሰራጭ የፈቀደው አዘጋጅ እና ጋዜጠኛ መቀመቅ እንደሚወርዱ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ግና እነሆ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይህንኑ በሕዝቦች መካከል አለመተማመን የመፍጠር ወንጀል አለከልካይ ሠራው! ሠርቶም ለሕዝብ አቀረበው፡፡ በዚህ የነስሬ ይሁን የገብሬ ባልታወቀ የአንድ ግለሰብ ድምጽ፣ የመንግሥት ሚዲያው ኢቲቪ ለክርስቲያን ወንድሞቻችን ብቻ ሳይሆን ለእኛ ለሙስሊሞችም ጭምር፣ ‹‹ሙስሊሞች ጂሐድ ሊያውጁ እየዶለቱ ነው›› የሚል መርዘኛ መልዕክት አስተላለፈ፡፡ … ፕሮግራሙ በአመዛኙ በሃይማኖት መቻቻል ዙርያ በርካታ መልካም መልካም ሐሳቦች የተደመጡበት ቢሆንም ቅሉ፣ ከዚህ በላይ የጠቃቀስኳቸውን ግድፈቶች እና መርዘኛ መልዕክቶችም አስተላልፏል፡፡… …. ‹‹በማር የተለወሰ መርዝ›› ይሏል ይሄ ነው፡፡ … ኧረ ተዉ! ኧረ ተዉ ኃላፊነት ይሰማችሁ! ኧረ ተዉ፣ ያሰባችሁልን መስላችሁ አገራችንን እና ሕዝቧን ወደ ጥፋት አትምሩ! ኧረ ተዉ ኃላፊነት ይሰማችሁ! ኧረ ተዉ ሚዲያ በሩዋንዳ የሰራውን ከባድ ወንጀል ለመሥራት አታኮብኩቡ! ኧረ ተዉ ይህ አካሄዳችሁ አያምርም! ….. ኧረ ኃላፊነት ይሰማችሁ! ኧረ ተዉ ኃላፊነት ይሰማችሁ! ………………

አላህ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይባርክ፡፡ አላህ ይድረስልን፡፡ አላህ ከክፋትና ከጥፋት ኃይሎች እኩይ ሤራ ይጠብቀን … አሚን፡፡

No comments:

Post a Comment