"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday 3 July 2012

ዕሁድን በቃሊቲ – ከርዕዮት ኣለሙ ጋር“የሞትንም እኛ ያለንም እኛ”


Posted by admin on July 3, 20120 Comment

በጋዜጠኛ ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን (አዲስ አበባ)
ዕለተ ሠንበት ነው ፡- ዕሁድ፡፡ ሰኔ 17 ቀን 2004 ዓ.ም፡፡ ረፋዱ ላይ ከጥቂት የቀድሞው ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ጓደኞቼ ጋር የሆድ የሆዳችንን ለማውጋት ተቀጣጥረናል፡፡
ስድሰት ኪሎ፡- ከአንበሳ ግቢ ትይዩ አምስት ያህል ካፌዎች አሉ፡፡ ሁሉም ካፌዎች ከቤታቸው ውጪ በረንዳቸው ላይ፣ ከበረንዳቸው አልፈው እስከ አስፋልቱ ጠርዝ ድረስ ባለዣንጥላ ጠረጴዛ ዘርግተው አገልግሎት ይሠጣሉ፡፡ በርካታ ተገልጋዮች አሏቸው፡፡
አብዛኞቹ ተስተናጋጅ ካፌው ውስጥ ዘልቀው ከመስተናገድ ይልቅ ውጪ መቀመጥን ይመርጣሉ፡፡ እኛም እንዲሁ ለአስፋልቱ ቀረብ ብሎ የተዘረጋውን ጠረጴዛ ከብበን ተቀምጠኛል፡፡ ቡናችንን አዝዘን ወግ እየጠረቅን ሳለ አንድ ጋዜጣ አዟሪ በክንዱ ከያዛቸው ጋዜጦችና መፅሔቶች አንድ አንድ መርጦ አቀበለን፡፡
Reeyot Alemu
እዚያ ቦታ አብዛኛው ተስተናጋጅ ከሻይ ቡና ባሻገር ከመፅሔትና ከጋዜጣ መረጃ ለመቃረም የሚመጣ መሆኑ ያስታውቃል፡፡ በየጠረጴዛው ጋዜጣ ወይም መፅሔት የማያነብ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ካፌዎቹ የላይብረሪ አገልግሎት ጭምር የሚሰጡ ናቸው ቢባል ግነት አይሆንም፡፡

እኛም ፊታችን ከተኮለኮሉት ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደየምርጫችን እያነሳን ማንበብ ጀመርን፡፡ “ሪፖርተር”፣ “አዲስ አድማስ” ፣ “አዲስ ጉዳይ” መፅሔትን እየተቀባበልን ገረፍ ገረፍ ማድረጉን ተያይዘነዋል፡፡ “ሪፖርተር” ጋዜጣ በውስጥ ገፁ የያዘው ዜና ነው የእኔን ትኩረት የሳበው፡፡ በእስር ላይ ስለምትገኘው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ይግባኝ ጉዳይ ያወራል፡፡ዜናው ከሳሽ አቃቤ ህግ ርዕዮት ዓለሙ ባቀረበችው ይግባኝ አቤቱታ ላይ የሰጠውን ምላሽ ወይም ያቀረበውን ክርክር ያትታል፡፡
ዜናውን እያነበብኩ ርዕዮት ዓለሙን በዓይነ ህሊናዬ ላያት ሞከርኩ፡፡ እናም! ድንገት በዓይነ ሥጋ ለምን አላያትም ብዬ ራሴን ጠየቅኩ፡፡ ጊዜ አላጠፋሁም፡፡ ወሰንኩ፡፡ ምክንያቱም ቀኑ ሠንበት ነው፡፡ እሁድ እስረኛ መጠየቅ ይቻላል፡፡
ሞባይሌን አወጣሁና ደወልኩ ፡፡ወደ ስለሺ ሐጎስ፡፡ ሰለሺ ሐጎስ ከርዕዮት ዓለሙ ጋር ተጠርጥሮ ማዕከላዊ ለምርመራ ገብቶ ነበር፡፡ ከወራት በኋላ ግን ተለቀቀ፡፡ ስለሺ እስረኝነትን አይቷል፡፡ ስለዚህ ስለ እስረኛ የመጠየቂያ ሠዓት (በተለይም ስለርዕዮት) ከእኔ የተሻለ መረጃ አለው፡፡
“… ርዕዮትን መጠየቅ የሚቻለው ከ6 ሠዓት እስከ 6፡30 ነው፡፡ አኔም እሷን ጥየቃ ልሄድ ከቤት እየወጣሁ ነው” አለኝ፡፡
የሞባይሌን ሰዓት አየሁ፡፡ ከቀኔ 5 ሠዓት ይላል፡፡ ከስለሺ ጋር አብረን ወደቃሊቲ ለመሄድ 4 ኪሎ ተቀጣጥረን፡፡
ከ 4 ኪሎ ስቴዲየም፣ ከስቴዲየም በቀጥታ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መረሸን፡፡ 45 ደቂቃ ፈጀብን፡፡ የማረሚ ቤቱ በር ላይ ስንደርስ ለ6 ሰዓት 5 ደቂቃ ቀርቷል፡፤
የሌሎች እስረኞች የጥየቃ ሠዓት ተጠናቋል፡፡ ጠያቂዎች በፍጥነት ግቢውን ለቀው እየወጡ ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ልጆቻቸውን፣ ጓደኞቻቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን በተወሰነው ሠዓት ደርሰው መጎብኘት ያልቻሉ 30 ያህል ሰዎች በረኞቹን (ፖሊሶችን) ይለምናሉ፡፡ “ዓይናቸውን ብቻ አይተን እንመለስ፤ የያዝነውን ቀለብ ብቻ እንስጣቸው፤ እባካችሁ ተባበሩን” እያሉ ይማፀናሉ፡፡
ፖሊሶቹ የጥየቃ ሠዓት ማብቃቱን ለማስረዳት እየሞከሩ ተማፅኖውን መቀበል እንደማይችሉ ረጋም ቆጣም ብለው ይናገራሉ፡፡
በዚህ መሀል ስለሺ ሐጎስ “እኛ ልዩ ጠያቂዎች ነን” አለ፡- ለአንዱ ፖሊስ አሻግሮ ራሱንና እኔን በጣቱ እየጠቆመ፡፡
“ልዩ ጠያቂ” የሚለው አገላለፅ የረፈደባቸውን ጠያቂዎች ጥርጣሬ ውስጥ ሊከት ይችላል፡፡ የአድልዎና የመገለል ስሜት ይፈጥርባቸው ይሆናል፡፡ ለእኔ ግን ባዕድ አይደለም፡፡
ምክንያቱም በአንድ ወቅት “ልዩ ተጠያቂ” ነበርኩ፡፡ ከመላው እስረኛ የቤተሰብ ግንኙነት ሠዓት ውጪ ውሱን እስረኞች ተለይተው የሚጠየቁበት የማረሚያ ቤቱ የጊዜ ሠሌዳ ነው፡፡ ይህንን እያሰብኩ የኪስ ቦርሣዬን ለጥበቃው አስረክቤ ወደ ማረሚያ ቤት ውስጥ ዘለቅሁ፡፡
“ከቅንጅት መሪዎች ጋር በታሠርኩ ጊዜ እዚህ ጋ ነበር ከቤተሰብ ጋር የምገናኘው፤… እዚህ ጋ ይህን ያህል ወራት፣ እዚያ ጋ ደግሞ ….” እያልኩ ትውስታዬን አብሮኝ ላለው ስለሺ ሀጎስ እየነገርኩ ዓይኖቼን በርቀት ወረወርኳቸው፡፡
በግምት በ300 ርቀት ጥቂት ጠያቂዎች ታዩኝ፡፡ ከ 10 አይበልጡም፡፡ “የሴቶች ክልል ያ ነው” አለኝ ስለሺ፡፡ ርዕዮትን በዓይነ ስጋ ለማየት ጥቂት እርምጃዎች ቀርተውኛል፡፡
ርዕዮት ዓለሙ ከመታሰሯ በፊት በመንፈስ እንጂ በአካል አላውቃትም፡፡ በእርግጥ በፅሁፎቿ አውቃታለሁ፡፡ በጋዜጣ ላይ ፎቶዋንም አይቼዋለሁ፡፡ ጠይም ወጣት ትመስለኝ ነበር፡፡
14 ዓመት እስራት ከተፈረደባት በኋላ ያቀረበችወ የይግባኝ ማመልከቻ ተቀባይነት አግኝቶ የቃል ክርክር በሚሠማበት ዕለት ነው በአካል ያየኋት፡፡ ይግባኝ ተሠምቶ ከችሎት በፖሊስ ታጅባ ስትወጣ ፊት ለፊት አግኝቼአት በድፍረት እጄን ዘረጋሁላት፡፡ እናም ስሜን ነገርኳት፡፡ እየጨበጠችኝ ስሜን ከነአባቴ ጠርታ በደንብ እንደምታውቀኝ ነገረችኝ፡፡ በቃ በዚያች ቅፅበት ለጥቂት ሰኮንዶች ነው በአካል የተያየነው፡፡
እነሆ አሁን ለሁለተኛ ጊዜ በአካል ላያት እስር ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ተገኝቻለሁ፡፡ በመጠየቂያው ስፍራ ከርዕዮት ፊት ለፊት አራት ወጣቶች ቆመዋል፡፡ ሁለቱ ሴቶች ናቸው፡፤ ሁለቱ ወንዶች፡፡ ከሁለቱ ወጣቶች አንዱ የፍትህ ቋሚ አምደኛ ኃይለገብርኤል ነው፡፡
መጠየቂያው አጥር አጠገብ ለመድረስ አምስት እርምጃ ያህል ሲቀረኝ የርዕዮት ፊት የፈገግታ ፀዳ ሲያንፀባርቅ ታየኝ፡፡ አንድ እስረኛ ከምንም በላይ የሚያስደስተው ጠያቂዎችን ማየት መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ሰው የተራበ ሰው፣ ሰው ሲያገኝ መከፋቱን ሁሉ ይረሳል፡፡ እናም ይሰቃል፤ ይኼው ርዕዮትም እየሳቀች እተፍለቀለቀች ወደ እኛ ፊት መጣች፡፡
በዚያች ቅፅበት ግን አንዳች የድንጋጤና የግርታ ስሜት ተሰማኝ፡፡ በእኔና በእሷ መሀል በአንድ ሜትር ስፋት ያህል ከተገጠገጠው አጥር መሀል ለመሀል ከቁመት በላይ የሆነ ረዥም የሽቦ አጥር ተጋርጧል፡፡ እንዴት ብዬ ሠላምታ እንደማቀርብለት ሳስብ በሽቦው አጥር መሀል እጇን ሰደደችልኝ፡፡ ሶስት ጣቶቿ ብቻ ናቸው የሽቦውን አጥር ለማለፍ እድል ያገኙት፡፡ እኔም እንደሷ እጄን ወደ እሷ ላክሁት፡፡ ሶስት ጣቶቼ ብቻ ናቸው የሽቦውን አጥር የተሻገሩት፡፡ ርዕዮት ከተረከዟ ብድግ ብላ እና ተንጠራርታ ጣቶቼን ሳመቻቸው፡፡ እኔም አፀፌታውን መለስኩ፡፡ ጣቶቿን ሳምኳቸው፡፡ ጣቶቿን ስስማቸው ከንፈሮቼ ሲርበተበቱና ሲንቀጠቀጡ ተሠማኝ፡፡ የሀዘን ስሜት ወረረኝ፡፡ አልቅስ አልቅስ አለኝ፡፡ ግን አላለቀስኩም፡፡
“እንባ እንባ ይለኛል
እንባ ከየት አባቱ
ደርቋል ከረጢቱ…” እንዲል በዓሉ፡፡
ቢሆንም ልቤ እያለቀሰ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ እናም የእሷንና የእኔን የእስር ሁኔታ እያነፃፀርኩ ለአፍታ በትዝታ የኃሊት ነጎድኩ፡፡
እኛ እስር ቤት በነበርን ጊዜ በእኛና በጠያቂዎቻችን መሀል የተዘረጋ ባለፍርግርግ የሽቦ አጥር አልነበረም፡፡ በነፃነት ሙሉ መዳፋችንን ሰድደን ከወዳጆቻችን ጋር መጨባበጥ እንችል ነበር፡፡ በደንብ ከተንጠራራን ደግሞ በእግሮቻችን ጣቶች ቆመን ከጠያቂዎቻችን ጋር ጉንጭ ለጉንጭ እንሣሳም ነበር፡፡
ርዕዮት ግን በሙሉ መዳፉ ወዳጆቿን የምትጨብጥበት ሁኔታ የለም፡፡ ጣቶቿን ብቻ ነው የምታወሳቸው፡፡ የእጅ መዳፍ ታግቶ፣ ጣት ነፃነት የማግኘቱ ነገር ራሱን የቻለ ምፀት መሠለኝ፡፡ አመመኝ ፡፡
ግን ደግሞ ተፅናናሁ፡፡ ርዕዮት ፍፁም በሆነ የራስ መተማመን ስሜት መሆኗን አስተዋልኩበት፡፡ ክብ ቅርፅ ያለው የቀይ ዳማ መልኳ ፀዳና ጥርት ብሏል፡፡ የፈገግታ ፀዳል ፈሶባታል፡፡ ቁመቷ መሀከለኛ ነው፡፡ ሸንቃጣ ናት፡፡ ልብ ብዬ እያየኋት ዕድሜዋን ገመትኩ፡፡ ምናልባት 25 ዓመት፣ ቢበዛ ለ30 ሁለት ፈሪ ቢሆናት ነው፡፡ በዚህ የወጣትነትና የብርታት ዕድሜዋ የእሰር ቤት መራር ህይወት ለመጋት መገደዷ አሳዘነኝ፡፡ ሴት መሆኗ ደግሞ፣ ደግሞ ደጋግሞ ታሰበኝ፡፡ ከፊቷ ያለው ያላጣጣመችው ህይወትና ዕድሜ በከንቱ እየባከነ መሆኑ አንገበገበኝ፡፡
እሷ ግን የሆነውን ሁሉ በፅናት እየተቀበለች ነው፡፡ መንፈሷ ጠንካራ ነው፡፡ መራሩን የእስር ቤት ሕይወት እያወዛችና የቀልድ ወለላ እየቀባባች አወራችኝ፡፡ የፍርድ ቤት ይግባኟን የክርክሯን ደርዝ፣ የወደፊቷን ተስፋዋን እጥር ምጥን አድርጋ አጫወተችኝ፡፡ ስለዚህ ተፅናናሁ፡፡ በተስፋዋ ውስጥ ተስፋ እደረኩኝ፡፡ ቸር ተመኝቼላት ተሠናበትኳት፡፡
ርዕዮትን የኋሊት ትቼ ቃሊቲ ማረሚያ ቤትን ለቅቄ ስወጣ የአቤቶ ኃይለ መለኮት አባባል ታወሠኝ፡፡ “የሞትንም እኛ የለንም እኛ” ሲሉ የተናገሩት፡፡ አቶ ብርሃኑ ድንቄ በ 1951 ዓ.ም “የኢትዮጵያ አጭር ታሪክ” በሚል ርዕሥ ለህትመት ካበቋት ከሲታ መፅሐፍ ውስጥ ነው የአቤቶ ኃይለ መለኮትን ምጥን ታሪክ ያነበብኩት፡፡
አቤቶ ኃይለ መለኮት “የሸዋ ትውልደ መንግሥት” የዘር ሀገር መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ ድንቄ ይነግሩናል፡፡ አባታቸው ንጉሥ ሣሕለ ሥላሴ የሸዋ ንጉስ ሆነው 34 ኣመት ከገዙ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ በአንኮበር ሚካኤል የአባታቸውን ቀበር ካስፈፀሙ በኋላ እንዲህ የሚል አዋጅ አስነገሩ፡- “የሞትንም እኛ ያለንም እኛ ባለህበት እርጋ”
እናም በአባታቸው ዙፋን ተቀመጡ (ገፅ 53) ሲሉ ይተርካሉ አቶ ብርሃኑ ድንቄ፡፡
“ከአቤቶ ኃይለ መለኮት አጭር ታሪክ የበለጠ የመሰጠኝና የማረከኝ ቀጥሎ ያለው ነው፡፡ ቃል በቃል ልጥቀሰው፡- “አፄ ኃይለ መለኮት በሚገዙበት ጊዜ ባለሟሎቻቸው ‘ወንድሞችዎ አቤቶ ሰይፉና አቤቶ ዳርጌ ስለማያስገዙዎት ቢያስሯቸው ይሻላል’ ብለው ምክር ቢሰጡዋቸው፣ እኔ በምገዛበትና በምደሰትበት ጊዜ ከማን ጋር ደስ ሊለኝ ነው ብለው አሳፈሯቸው” (ገፅ 53/ሰረዝ የኔ)
ከዚያስ ምን ሆነ?
“በዚህ አኳኋን ቅንነታቸውን ርህራሄያቸውን የተመለከቱ ወንድሞቻቸው እስከፍፃሜው ድረስ የወንድም አሽከር ሆነው ከማገልገላቸው በቀር አንዳች ሁከት አላነሱባቸውም” (ዝኒ ከማሁ) ይህችን የአቤቶ ኃይለ መለኮት ምጥን ታሪክ ምነው ዛሬ በተደገመ የሚል ስሜት አነሆለለኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የአቤቶ ኃይለመለኮትን ታሪክ ቢደግሙት ምን አለ አሰኘኝ፡፡
አቤቶ ኃይለመለኮት እኔ በምገዛበትና በምደሰትበት ጊዜ ወንድሞቼን አስሬ ምን ደስ ሊለኝ ነው እንዳሉ ሁሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስም ልጄን አስሬ ደስታዬ ምንድነው ቢሉ የክብር ካባ ይደርባሉ እንጂ አያፍሩም፡፡ ምክንያቱም ርዕዮት ዓለሙን ባይወልዷትም ልጃቸው ማለት ናት፡፡ ከልጃቸው ሰምኃል ከፍ የምትለው 4 እና 5 ዓመት ቢሆን ነው፡፡ ይህቺን የልጃቸውን እኩያ ወጣት ማሠር ትውልድን ማሰር ነው፡፤ ጥፋት ብታጠፋ እንኳ በቁጣ ብቻ የምትመለስ ወጣት ናት፡፡
Wosenseged Gebrekidan (Photo- Awramba Times)
እርግጥ ነው ጠ/ሚ/ር መለስ ርዕዮት ዓለሙ በመታሠሯ የሚደሰቱ አይመስለኝም፡፤ አንድ ሰው ሌላ ሠው በማሰር ደስታ የሚያገኝ ወይም ደስታ የሚሠማው አይመስለኝም፡፡ይህንን ሥል አቶ መለስ “ርዕዮት የታሠረቸው ህግና ሥርዓት ለማስከበር፣ የህግን የበላይት ለማረጋገጥ ነው” ሊሉ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ እንደዚያም ከሆነ ርዕዮት ዓለሙ የህግ የበላይነትን ተማምና ለጠ/ፍ/ቤት የይግባኝ አቤቱታ ማቅረቧ ብቻው ንፅህናዋን ያሣያል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሌላ ምንም ማሣመኛ፤ ሌላ ምንም ምክንያት መደርደር ሳያስፈልግ እስመጨረሻው በህግ ፊት ለመቆም መወሰኗ ብቻ ርዕዮት ትፈታ ዘንድ በቂ ነው ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህም ይፍቷት!!
ክቡር ጠ/ሚ/ር መለሥ ግዴለዎትም ይፍቷት፡፡ “የሞትን እኛ ያለንም እኛ” ብለው ይፍቷት፡፡ ግዴለዎትም እንዲህ ብለው ይፍቷት፡፡ የአፄ ኃይለመለኮትን ታሪክ ይድገሙት፡፡ ይድገሙትና ቅንነትዎን ያሣዩን፡፡ ይድገሙትና በክብር ላይ የክብር ካባ ይደርቡ፡፡ ይድገሙትና የአዲሱን ትውልድ መፈታት ያብስሩ፡፡
ይህ የእኔ የግል አቤቱታ ነው፡፡ በግል የቀረበ የቅንነት ተማፅኖ ነው ፡፡ ደግሞም አቤቱታዬን እንደሚሰሙ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በርዕዮት ዓለሙ መታሰር እርስዎ ደስታ እንደማይሠማዎ አውቃለሁ፡፡ እናም ሐምሌ 10 ቀን 2004ን (ጠ/ፍ/ቤት ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ የያዘበት ቀን ነው) በተስፋ እጠብቃለሁ፡፡ ርዕዮት የወጣትነት ህይወቷን በእስር ቤት ማባከን የለበትምና፡፡
አበቃሁ!!
/ጋዜጠኛ ወሰነሰገድ ገብረኪዳን፣ በቅርቡ ለንባብ የበቃው ‹‹የቃሊቲ ምስጢሮች›› ጸሐፊ ነው/

No comments:

Post a Comment