"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Monday, 15 October 2012

የረጅም ጊዜ እግርኳሳዊ ስቃይ በጥልቅ ደስታ ተተካ


  ·
October 15, 2012
By Fisseha Tegegn

ኢትዮጵያን ወደአፍሪካ ዋንጫ ከረጅም ጊዜ በኋላ የመለሷትን ሁለት ጎሎች ያስቆጠሩት አዳነ ግርማ እና ሳልሀዲን ሰኢድ እንዲሁም ደጋፊዎች ደስታቸውን በተለያየ መልኩ ሲገልጹ

ስቃይ መጨረሻው እንዲህ ሊያምር ከሆነ እንኳንስ ተሰቃየሁ የሚል አስተያየት ላይ ለመድረስ የተቃረብኩበት ቀን ቢኖር የኢትዮጵያ እና ሱዳን ጨዋታን የመሩት ሴኔጋላዊው ዳኛ የጨዋታው ማብቂያን እና ኢትዮጵያ ከ31 አመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ያረጋገጠው ፊሽካቸውን ድምጽ ሲያሰሙ ነበር። አዎ፤ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን መስራች አባል የሆነችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ለመጨረሻ ጊዜ ከተሳተፈች 31 አመታት አልፈዋል።

በረጅም ጊዜ እግርኳሳዊ የስቃይ ስሜት የተወጠረው አእምሮዬ ታዲያ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ያስብ የነበረው ልክ ሌሎች ጨዋታዎችን ሲያይ እንደሚያስበው “ምን አይነት አሰላለፍ ይዘው ይገባሉ? እንዴት ክፍት ቦታዎችን ይጠቀሙባቸዋል? ምን አይነት ታክቲክ ይጠቃማሉ?” የሚሉ ጥያቄዎችን ሳይሆን፤ “ታሪክ ‘ኑ እና ውሰዱኝ’ ብሎ እጁን ከዘረጋ በኋላ ይነሳን ይሆን” የሚለውን በፍራቻ የታጀበ ስሜትን ነበር።

አትፍረዱብኝ ከ31 አመታቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ስቃይ ውስጥ ቢያንስ ከ15 አመታ በላይ የሚሆነውን አብሬው ተሰቃይቻለሁ። እጅግ በጣም በማከብራቸውና በማደንቃቸው የእግርኳስ ተጨዋቾች በተለያየ ጊዜ የተገነቡት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኖች ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ሳይችሉ ሲቀሩ ያየ ልብ እና አእምሮ እንዴት አሁን አይጨነቅ?


የኢትዮጵያ እግርኳስን በንቃት መከታተል ከጀመረኩበት ግዜ አንስቶ ሀገሪቷ እንደካሳዬ አራጌ፣ አንዋር ያሲን፣ አንዋር ሲራጅ፣ ኬኔዲ ደምሴ፣ ቴዎድሮስ በቀለ፣ አሰግድ ተስፋዬ፣ አሸናፊ ግርማ እና ሙላለም ረጋሳን የመሳሰሉ በጣም የማደንቃቸው ተጨዋቾችን ብታፈራም እነዚህን የመሰሉ ተጨዋቾች ያካተተው ብሄራዊ ቡድኗ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሊሳተፍ አልቻለም።

ታዲያ የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያን ከቤኒን ጋር አዲስ አበባ ላይ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ያለምንም ግብ ሲያጠናቅቅ “ሌላ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሊሆን ነው” ያልኩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሱዳንን አዲስ አበባ ላይ በአዳነ ግርማ እና ሳልሀዲን ሰኢድ ጎሎች 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከሜዳ ውጪ የተሻለ ውጤት ያስመዘገበ በሚለው ደንብ ወደአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ የመረጥኩት አደሳሰት በመዝለል እና በመቦረቅ ሳይሆን “እያየሁ ያለሁት እውነት ነው?” የሚል ጥያቄን ባዘለ ጸጥታ የሰፈነበት ስሜት ነበር። በጨዋታው ላይ ከመቀመጫዬ ተነስቼ የጨፈርኩት የመጀመሪያዋን ጎል አዳነ ሲያስቆጥር ብቻ ነበር። ምክንያቱም ያቺ ጎል እኔን ብቻ ሳይሆን የተመልካቹን እና እራሳቸው የተጨዋቾቹንም ስሜት ፍጹም የቀየረች ነበረች እና። ሁለተኛዋን ጎል ብዙም ሳይቆይ ሳልሀዲን ሲያስቆጥር ደንዝዤ ቀረሁ። ከሰከንዶች በኋላ ስባንን ጨዋታውን በትኩረት እና በንቃት ከማየት ይልቅ “ይሄ ሰአት ደግሞ አይሮጥም እንዴ?” የሚል ብቻ ሆነ አእምሮዬ ውስጥ የሚመላለሰው።

የኢትዮጵያን እግርኳስ በንቃት የምንከታተል እና ስንከታተል የነበርን ሰዎች ሲሳለቁብን የነበረውን ጠንቅቀን እናውቀዋለን። “አይ እናንተ ደግሞ፤ ምንድነው ለዚህ ለሞተ እግርኳስ እንዲህ መንጫጫት” ስንባል ከርመናል። አሁንም በአንድ ውጤት የኢትዮጵያ እግርኳስ ጣራ ነካ እያልኩ አይደለም። ግን ያ መሳለቂያ የሆንበት የኢትዮጵያ እግርኳስ ሲያፌዙብን የነበሩትንም ላይ እና ታች ሲያዘልል ማዬቴ አስደስቶኝ ነው እንጂ።

ቅዳሜ እና እሁድ በጠራራ ጸሀይ በየስታዲዬሞቹ በመገኘት የክለብ እግርኳሶችን ስንከታተል የነበርነው፣ መኪና እያጠቡ እና የተለያዩ ትናንሽ ስራዎችንም እየሰሩ የስታዲዬም መግቢያ ትኬት መግዣ የምትሆናቸው ገንዘብ በማጠራቀም እረጅም ሰአት ተሰልፈው ትኬት የሚገዙት፣ ደህና ምግብ መብያ የሚሆናቸው ገንዛብን ትኬት መግዣ በማድረጋቸው ጾማቸውን እንዳያድሩ ከጨዋታ ማብቂያ በኋላ ከስታዲዬም ወጥተው ዳቦ መሀል ሙዝ ከተው በመብላት አዳራቸውን ያሳለፉት፣ አጋጣሚዎችን በመጠቀም የትኬት ዋጋ ድንገት ሲጨመርባቸው ያላቸውን አብቃቅተው እና “እስቲ ይሁን” ብለው ሁሉን በውስጣቸው በመቻል ትኬቱን ገዝተው ስታዲዬም የሚገቡት፣ ትኬት መግዛት ባለመቻላቸው ኳስ ስለሚወዱ ብቻ ስታዲዬም በሮች ላይ ቆመው በመጠበቅ ልክ ጨዋታው ሊያበቃ አስር እና 15 ደቂቃዎች ያህል ብቻ ሲቀሩት በነጻ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው እና ያቺ እድል እንኳን ስለተሰጠቻቸው በሩ ላይ የቆሙ ፖሊሶችን አመስግነው በደስታ የቀረችዋን ደቂቃ ስላዩ የሚቦርቁት እና የሚደሰቱት ህጻናት እና ወጣቶች ናቸው በዚህ ድል ከማንም በላይ መደሰት የሚገባቸው።

ለዚህም ነበር ይሄንን የኢትዮጵያ እና ሱዳን ጨዋታ ሳይ ከጭፍን ስሜታዊነት በስተቀር ሌላ ምንም የማይበት መንገድ ያልነበረኝ። ምን አልባት ከተረጋጋሁ በኋላ ቁጭ ብዬ ጨዋታውን እንደገና ሳየው ስህተቶች እና ግሩም እንቅስቃሴዎችን ነጥዬ ላወጣ እና ሰፋ አድርጌ ልወያይባቸው እችላለሁ። አሁን ግን ስሜቴን ብቻ ለማስተናገድ ነው ሰውነቴ አቅም ያለው።

የመጀመሪያው ግማሽ የጨዋታ ክፍለ-ጊዜ ያለምንም ግብ ሲጠናቀቅ የጨዋታውን ግማሽ እንደሌላው ጊዜ ልተነትነው አልቻልኩም። ታዲያ “እኔ እንዲህ የሆንኩ እነዚህ የዚህ ሁሉ ህዝብ ሃላፊነት የተጣለባቸው ወጣቶች እንዴት ይሄን ሁሉ ጫና መቋቋም ይችላሉ?” ብዬ ጠየኩና አንደኛው የአእምሮዬ ክፍል በጣም አዘነላቸው። ሌላኛው የአእምሮዬ ክፍል ደግሞ እንደለመደው ብዙ እንዲጫኑና የተቻላቸውን አድርገው ውጤቱን እንዲያመጡት ይፈልጋል፣ ተጨማሪ ይጠይቃል።

በመጀመሪያው ግማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጥቂት የማግባት እድሎችን ቢያገኝም እድሉን ያገኙት ተጨዋቾች ወደጎል ያልቀየሩበት ምክንያት ባለመቻላቸው ሳይሆን ሁኔታዎች በፈጠሩት ጫና ምክንያት ነው ብዬ እራሴን አሳመንኩ እና “ምናለ አንድ ጎል አግብተው ከዚህ ሁሉ ጭንቀት በገላገላቸው” አልኩ።

የደጋፊዎች ጫና በእግርኳስ ተጨዋቾች ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ እጅግ ግዙፍ መሆኑን ማወቅ የፈለገ የቀድሞው የጋና ብሄራዊ ቡድን አምበል ስቴፈን አፒያን ይጠይቅ። አፒያ ራሱን ከጋና ብሄራዊ ቡድን ተጨዋችነት በቅርቡ ካሰናበተ በኋላ የውሳኔው ምክንያት ምን እንደሆነ ሲጠየቅ “ጋናውያን ደጋፊዎች የሚፈጥሩብን ጫናን መቋቋም አልቻልኩም። ለምን አፍሪካ ውስጥ የራስህ ደጋፊዎች ከመጠን ያለፈ ጫና በመፍጠር ስራህን እንድትጠላ እንደሚያስገድዱ አይገባኝም። በቃኝ።!” በማለት ነበር የመለሰው።

ደጋፊዎች አውቀው ነው አላስፈላጊ ጫናን ተጨዋቾቻቸው ላይ የሚፈጥሩት ብሎ መናገር ያስቸግራል። የሚያበረታቱ መስሏቸው ሳያውቁት ጫናን የሚፈጥሩ ደጋፊዎች እንዳሉ ግን በጭራሽ አይካድም። በአበረታች እና ጫና በሚፈጥሩ ደጋፊዎች መካከል ያለው ልዩነት ሁኔታዎችን የሚያዩባቸው መንገዶች ናቸው።

አበረታች ደጋፊዎች የቡድናቸው ወይም የወከላቸውን ስፖርተኛ አቅም እና ችሎታ፣ እንዲሁም ለማግኘት እየታገለበት ያለውን ተግባር አስቸጋሪነት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ሜዳ ላይ ለሚፈጸሙት ትንሽም ሆኑ ግዙፍ አዎንታዊ ተግባሮች በተለያየ መልኩ ድጋፋቸውን ይሰጣሉ።

ጫናን የሚፈጥሩ ደጋፊዎች ግን ቀድሞ የሚታያቸው የሚሰሩ ስህተቶች ናቸው። መወያያቸውና የእድሜያቸው ማራዘሚያዎች ስህተቶች ሲሆኑ ሁኔታዎች እንደጠበቋቸው መሄድ ካልጀመሩ የራሳቸውን ስፖርተኞችና ቡድኖች ለመተቸትና ለመሳደብ ጊዜ አይወስድባቸውም።

የእድል ነገር ሆኖ በአዲስ አበባ ስታዲዬም የኢትዮጵያ እና ሱዳን ጨዋታን ሊከታተል የተገኘው አብዛኛው ተመልካች አበረታች ደጋፊ ነበር። ግን ተፈትኗል። ሱዳን ፈትኖታል። ጨዋታውን ሲከታተል የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢፊ ኦኑራ ለቢቢሲ አለፍ አለፍ እያለ በየጨዋታው መሀል ከሰጣቸው አስተያየቶች መካከል አንዱ “ይህ ጨዋታ ያለጎል መጓዙን ከቀጠለ የባለሜዳው ቡድን [የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን] ደጋፊዎች ተስፋ እየቆረጡና ዝም እያሉ ነው የሚሄዱት” የሚለው ነበር። የሱዳን ብሄራዊ ቡድን አላማም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ጎል ከማግባት በተለያየ መልኩ በመከልከል ደጋፊውን ማበሳጨት ነበር።

ግን ምስጋና ለአዳነ ግርማ እና ሳልሀዲን ሰኢድ ጎሎች ይግባና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን፣ ያ ለ31 አመታት ያህል ስንበሳጭበት የቆየነውን የብሄራዊ ቡድን እግርኳስ ሙሉ በሙሉ እረስተን በተለያየ መልኩ የደስታ ስሜታችንን እንድንገልጽ አስቻለን።

ምናልባት “ማለፍ አይገባችሁም” በማለት የሚተቹን ደፋሮች ይኖሩ ይሆናል። “እዛ ሄዳችሁ ምንም አታመጡም” የሚሉንም አይጠፉም። ያለው ብቸኛው አማራጭ እነዚህ ተጠራጣሪዎቻችንን እረስተን መደሰት ብቻ ነው። የእናንተን አላውቅም፤ እኔ ግን ይሄንን ደስታዬን ማንም እንዲነጥቀኝ አልፈልግም፣ አይነጥቀኝምም።

የእኔ ትውልድ የምላቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ገና በዚህ እድሜዬ አየዋለሁ ብዬ ያልገመትኩትን እንዳይ ስላስቻሉኝ ከልብ ነው የኮራሁት። ኢትዮጵያ ከሶስት አስርት አመታት በኋላ ወደአፍሪካ ዋንጫ ተመለሰች።

እንኳን ደህና መጣሽ!


No comments:

Post a Comment