"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday, 20 October 2012

“የጥቁርም የነጭም ደም ቀይ ነው” የመለስ ድራማ!! ኢህአዴግ ለመክሰስ ሲፈልግ ፊልም እንደሚደርስ ተረጋገጠ


swidish journalists in addis
የኦጋዴን ጉዳይ ሲነሳ ኢህአዴግ ይደነግጣል። ስለ ኦጋዴን አንዳችም ጉዳይ እንዲነሳበት አይፈልግም። የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ በኦጋዴን ተፈጽሟል ያለውን ይፋ ሲያደርግ ኢህአዴግ በተለዩት መሪው፣ በህዝብ ግንኙነቱና እንግሊዝ አገር ባሉት አምባሳደሩ በኩል የማስተባበያ ዘመቻ ከፍቶ ነበር። በኬንያ ስደት ጣቢያ የሚገኙትን የክልሉ ነዋሪዎችን ያነጋገረው የቢቢሲው መርማሪ ጋዜጠኛ ሪፖርት ብቻ ሳይሆን ሂውማን ራይትስ ዎችም የከረረ መግለጫ አውጥቶ ነበር። ከአገር በቀል የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች መካከል የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄም በተመሳሳይ የኦጋዴንን አጀንዳ በማንሳት ጥሪ በማስተላለፍ ቅድሚያ እንደነበረው መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢህአዴግ በሃሰት ላይ የተመረኮዘ መረጃ በማዘጋጀት የሚመራውን ህዝብና የዓለም ህብረተሰብን እንደሚያወናብድ የሚያጋልጡ መረጃዎች በየጊዜው ይፋ ይሆናሉ። “ታላቅ ስህተት ሰርተናል፣ስህተቱ ህይወታችንን ሊያሳጣ ይችል ነበር …” በማለት አዲስ አበባ ከርቸሌ ውስጥ ሆነው ይቅርታ የጠየቁት ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች፣ ሰሞኑን ይፋ ያደረጉት ነገር ቢኖር ይህንኑ ኢህአዴግ ሊከድነው የሚደክምበትን ሃቅ ነው።
የተቀነባበረ ድራማ  “እንደ ሆሊ ውድ” ፊልም ማዘጋጀት የዓለምን ህብረተሰብና የሚመራውን ህዝብ ያጭበረበረው ኢህአዴግ በሞት በተለዩት መሪው አማካይነት ሲምልና ሲገዘትበት የነበረውን ማጭበርበር ማርቲን ሺብዬና ዩሃን ፐርሸን አጋልጠዋል። አቶ መለስ “የጥቁርም የነጭም ደም ቀይ ነው” በማለት ለፈጠሩት ፓርላማ ሲፈላሰፉና በህግ የበላይነት እንደሚያምኑ እያስጨበጨቡ ሲናገሩ የነበሩትን ሁሉ እርቃኑን በማስቀረት ሁለቱ ጋዜጠኞች ህያው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።በኢትዮጵያ በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ደጋፊዎች፣ በጋዜጠኞችና ስርዓቱን በሚቃወሙ ዜጎች ላይ የሚለጠፈው “የአሸባሪነት” ወንጀል የተቀነባበረ የፈጠራ ፊልም መሆኑን አረጋግጠዋል።
ቀደም ሲል መለስ፣ አሁን ደግሞ ሃይለማርያም እየማሉበት ያለው የህግ የበላይነት ቁማር መሆኑን፣ ፍርድ ቤቶቻቸው የቁማር መጫወቻ፣ ዳኞቻቸው ታላቁን ሙያ ያረከሱና ሙሉ በሙሉ በተቀናበረ ድራማ የሚፈርዱ መሆናቸውን ሁለቱ ጋዜጠኞች ላገራቸው ሚዲያዎች፣ ለቢቢሲ አፍሪካና ለአሜሪካ ሬዲዮ አስታውቀዋል። በዚህም ተግባራቸው ቀደም ሲል የበደኖና የወተር፣ በቀርቡ ደግሞ “አኬልዳማ” የተሰኘው የመወንጀያ ዶክመንተሪ ኢህአዴግ ቆርጦ እየቀጠለ፣ እያስፈራራና በቅድመ ሁኔታ እየተደራደረ የሚያመርተው የግፍ አገዛዙ ማስቀጠያ የማታለያ ሸቀጡ ስለመሆኑ አመላክተዋል።
በተለይም የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍለ ጊዜ በዝርዝር ያቀረበው የሁለቱ ጋዜጠኞች ቃለ ምልልስ አገር ቤት የተለያዩ ጉዳዮችን አስነስቷል። “በደኖ ኢንቁፍቱ /የማይጠግበው ዋሻ/፣ አርባ ጉጉ፣ ደደር፣ ወተር፣ ቆቦ … አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል። የጎሳ ፖለቲካ ጣጣ ሰለባ ያደረጋቸው የኢትዮጵያ ልጆች ከነ ህይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ ተጥለዋል። በጅምላ እንደ ባዳ ተጨፍጭፈዋል።ኢህአዴግ ህዝቡን ከመጠበቅ ይልቅ ለተራ የፖለቲካ ትርፍ በተቀነባበረው ወንጀል ስር ፊልም ያቀናብራል። የፖለቲካ ቁማር ይቆምራል። ራሱ ገደል ከቶ በሃዘን ሙዚቃ ታጅቦ ራሱ ከገደል ሲያወጣ የሚያሳይ ዘግናኝ ፊልም ለህዝብ እያሳየ እንባ ያራጫል። በሃሰት ፊልም እያመረተ ያጭበረብራል። የሁለቱ ስዊድን ጋዜጠኞች ሰሞኑን ያረጋገጡት ነገር ቢኖር ይህንኑ ነው” የሚል አስተያየት ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ተልኳል።
መለስ ቀይ መስቀልን ጨምሮ በኦጋዴን የሚገኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ሲያስወጡ ምን አስበው ነበር? ለሚለው የብዙዎች ጥያቄ ምላሽ የተገኘ ይመስላል። “መለስም አረፉ፣ እኛም አረፍን የምንለው መቼ ነው” በማለት የሚጠይቀው ቀን 2004 ዓ ም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ነጥቦችን በመዘርዘር ስለ ኦጋዴን ችግር ያወጣው መግለጫ:-

“… ለወራት ያህል በመለስ ታማኞች ትዕዛዝ ሰጪነት የተከበቡት ኦጋዴኖች በረሃብ ተጠበሱ። ችግሩ ሲጠናባቸው ሽማግሌ በመላክ “በረሃብ ማለቃችን ነው። እኛ ንፁሃን ዜጎች ነን። ህፃናት እየተጎዱ፣ ከብቶቻችን እያለቁ ነው’’ በማለት ከከበባው ለመውጣት  ጥያቄ ቢያቀርቡም ትእዛዝ ከተላለፈላቸው የጦር አዛዦች ያገኙት መልስ ጥይት ነበር። በተፈጥሯቸው አንድ ቀበሌ መኖር የማይችሉ ዘላኖች (አርብቶ አደሮች) ከቦታ ቦታ መዘዋወር ተከልክለው ለአራትና አምስት ዓመታት እንዴት ኖሩ? ምን ያህልስ ሰብዓዊ ቀውስ ደረሰ? ከአመታት የስቃይ ኑሮ በኋላ የመጨረሻው የፍርድ ቀን ደርሶ በኦጋዴን የጅምላ ጭፍጨፋ ተካሄደ። ንፁሃን ጉድጓድ ተምሶ በጅምላ እንዲቀበሩ ተደረገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መለስ ስለ ኦጋዴን ሲነሳ ያማቸው ጀመር። ከዋናው የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ጋር የሰላም ስምምነት አድርጌያለሁ ቢሉም አካባቢውን ገለልተኛ ወገኖች ገብተው እንዲመለከቱት ፈቅደው አያውቁም። ሰሞኑን  የስዊድን ጋዜጠኞች  ላይ የተወሰደው ርምጃም የዚሁ ‹ምስጢር ይወጣብኛል› ፍርሃቻ አካል ስለመሆኑ ጥርጥር የለንም … ”
“… ኦጋዴን በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ተድበስብሶ ቢከርምም ዛሬ በሶማሊያ የተከሰተውን አስፈሪ ርሃብ ተከትሎ ይፋ መሆን ጀምሯል። ድርጅታችን በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ ክልል፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተፈፀሙትን ጭፍጨፋዎች በመቃወም እንዳደረገው ሁሉ በኦጋዴን የተፈፀመው ጭፍጨፋ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ነው። የኦጋዴን ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ በመሆኑ ይህ መግለጫ የሚደርሳችሁ አካላት በሙሉ ድርጊቱን በመቃወም አግባብ ያለው ተፅዕኖ በማድረግ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መድረክ ትግላችሁን እንድትቀጥሉ አጥብቀን እናሳስባለን” ሲል ጥሪውን አስተላልፎ ነበር። (የመግለጫው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል)
ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች ኦጋዴን ዘልቀው የተደበቀ ምስጢር ለማውጣት የተከለከለውን መስመር በማለፍ የወሰዱት ርምጃ አስደናቂ የሚደርገው በርካታ ምክንቶች አሉት። አሜሪካ ድምጽ አማርኛ ክፍለ ጊዜ በስፋት የተረከው ጉዳይ በዘርፉ ለተሰማራነው ሁሉ ትምህርት የሚሰጥ፣ ሙያው ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን የሚያስገነዘብ፣ በበረሃ መንከራተትን የሚጠይቅ፣ የተደበቀ እውነትን በማጋለጥ መረጃን መስጠት ምን ያህል ክቡር እንደሆነ የሚያመላክት ነው። (አሜሪካ ድምጽ ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል)

No comments:

Post a Comment