"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Monday 15 October 2012

የአርቲስት ዳምጠው አየለ ጥሪ !!






“ሰው ናፈቀኝ፣ ልጆቼና አገሬ ታወሱኝ፣ ባህሌና ልማዴ የት ገባ….?” የሚሉት የአንድ ስደተኛ ጥያቄዎች ለመቶ አለቃ ዳምጠው አየለ ተረት ሆነውበታል። አርቲስት ዳምጠው አየለ ከሁርሶ የመኮንኖች ማሰልጠና ማዕከል የመኮንንነት ትምህርት ተከታትሏል። ለሰላሳ ሁለት ዓመታት በምድር ጦር የሙዚቀኛ ሻለቃ አገልግሏል። በተለይም በባህላዊና አገር በሚያሞካሹ ዜማዎቹ የሚወደደው ዳምጠው አገሩን፣ ሁለት ልጆቹንና ባለቤቱን ጥሎ በስደት ኖርዌይ ከገባ ሰባት ዓመታት አሳልፏል። የስልሳ ሶስት ዓመቱ ዳምጠው ያጋጠመውን ጊዚያዊ ችግር አስመልክቶ ከጎልጉል የአውሮፓ ዘጋቢ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። ዳምጠው ችግር እንዳጋጠመው ሲሰማ አስቸኳይ ድጋፍ ላደረጉ ወገኖች፣ ድርጅቶች፣ ማህበሮች፣ ላደረጋችሁት በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር የዝግጅት ክፍላችን በዚህ አጋጣሚ ለማመስገን ይወዳል።

“… አዎ፤ እኔም ራሴን እጠይቀዋለሁ። ጀግና ሲወድቅ አይቻለሁ። የጦር ሜዳ መከራና እሳት አይቻለሁ። ባልዋጋም በኦጋዴንና በሳህል ግንባር ኤርትራ ተገኝቼ የመከራን ወጋገን ተመልክቻለሁ። ጀግና ወድቆ ሲነሳ ማየቴ ትዝ ይለኛል። ምንም እንኳን በርካታ የክፉ ቀን መቋቋሚያ ልምድ ቢኖረኘም ካቅሜ በላይ ሆነብኝ። ችግር እንዳይፈታኝ አጥብቆ የያዘኝ የኑሮ ልምዴና ወታደርነቴ እያደር ላላ። እድሜዬ እየገፋ ሲሄድ ነው መሰል ባባሁ። በጀርባዬ ተኝቼ ኮርኒስ እያየሁ ልጆቼንና ባለቤቴን በማሰላሰል ደከመኝ። አስባለሁ፣ አወጣለሁ፣ አወርዳለሁ ለውጥ የለም። አናቴ ጋለ። ደም ግፊት ያዘኝ። ሌላውም ተከተለኝ። ታመምኩ። እኔ ተቆንጥጬ ያደኩ፣ ለባህሌና ላገሬ ልዩ ክብር ያለኝ ሰው ነኝ። የአገሬ ሽታ ይመጣብኛል። ከብቶች ሽታቸው ይናፍቀኛል… ታዲያ ይህንን ሁሉ አጥቼ እንዴት የምታውቀኝ የድሮው ዳምጠው ልሆን እችላለሁ?”

ጎልጉል፦ ስሜት የሚነካ ዜና ሰማን፤
ዳምጠው፦ በርግጥ ተገደድሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ፈጣሪ ደግ ነው። በኖርዌይ ወገኖቼ ኮርቻለሁ። ደረሱልኝ። ደገፉኝ። አበረታቱኝ። በህይወት ዘመኔ አልረሳውም።

ጎልጉል፦ ምን ገጠመህ?
ዳምጠው፦ ስደት ጠባሳው ቀላል አይደለም። የውስጥ ስሜቴን አጣሁት። ታመምኩ። ልጆቼና ባለቤቴ ራቡኝ። ሰባት ዓመት ናፍቆት ለበለበኝ። ባዶ ቤት ታቅፌ ገፋሁት። ዓመታት በተቆጠሩ ቁጥር ቤተሰቦቼን የማይበት ተስፋዬ አለቀ። ቀደም ሲል ኦስሎ እያለሁ ወንድምና እህት የሆኑኝን የኦስሎ ወገኖች እየተቀላቀልኩ ብቸኛነትን መቋቋም ችዬ ነበር። ከሶስት ዓመት በፊት የመኖሪያ አድራሻዬን ቀየርኩ።

ጎልጉል፦ ለምን?
ዳምጠው፦ ኦስሎ እያለሁ እርዳታ በማገኝበት ስርዓት ውስጥ አልነበርኩም። በዛ መልኩ መቀጠል ስላልነበረብኝ እየተደገፍኩ ለመኖር ባቀረብኩት ጥያቄ መሰረት ወደ ዮቪክ ተዛወርኩ። ላለፉት ሶስት ዓመታት ብቻን ትልቅ ቤት ታቅፌ ገፋሁት። የሚያናግረኝ አልነበረም። ከትምህርት ቤት ስመለስ ብቻዬን ቤት ውስጥ ስቀመጥ ከቀን ወደ ቀን ብቸኛነቱ ጎዳኝ። በሽተኛ ሆንኩ። ሁኔታው እየከፋ ሲሄድ ሃኪሜ የአገሩ ሰዎች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ መኖር አለበት በማለት ወደ ኦስሎ ተዛወርኩ።


ጎልጉል፦ መልካም አጋጣሚ ሆነልህ ማለት ነዋ?
ዳምጠው፦ ነበር። ምን ያደርጋል መካከል ላይ ያላሰብኩት ነገር ተፈጠረ። ደነገጥኩ። ለማስተካከል ብሞክርም አልሆነም…

ጎልጉል፦ ምን ገጠመህ?
ዳምጠው፦ አዲስ የገባሁበት ኮሙና (የመኖሪያ ቦታ) ድጋፍ የሚያደርግልኝ ከሶስት ወር በኋላ መሆኑንን አረዳኝ። በየወሩ ሲደረግልኝ የነበረው ድጋፍ እንደማይቀጥል አስታወቁኝ። ስራ የለኝም። ገቢ የለኝም። አገኝ ከነበረው ገቢ ልጆቼንና ቤተሰቦቼን ስለምረዳ ተቀማጭ የለኝም። ስለዚህ ውሳኔው አስደነገጠኝ። ራሴን ከፎቅ ላይ በመወርወር ለማጥፋት ወስኜ ነበር። /ንግግሩን ገታ፤ ሲቃ ያዘው/ በመካከሉ የዘወትር የክፉ ቀን ደራሽ ሆኑት ዶ/ር ሙሉ ዓለም ደረሱ… መናገር አልችልም…

ጎልጉል፦ ዶ/ር ሙሉ ዓለም ማን ናቸው?
ዳምጠው፦ በኖርዌይ የሚኖሩ ወገን ናቸው። በድንገት ህይወቴን ታደጉ። የወር ቤት ኪራይ ከኪሳቸው ከፈሉ። እስከመጨረሻው እንደሚረዱኝ አረጋገጡልኝ። ተረጋግቼ እርዳታ እስከማገኝ እንድኖር መከሩኝ። ኖርዌይ ወንድምና እህቶች እንደማይተውኝ፣ እንደማይጥሉኝ በተደጋጋሚ አስረዱኝ። ዶ/ር ሙሉ አለም ለስደተኞች ቀድሞ በመድረስ የሚታወቁ ውድ የወገን ፍቅር ያላቸው ሰው ናቸው። እድሜ ይሰጣቸው ዘንድ ከመመኘት ውጪ የምለው የለኝም። እርሳቸውን ለአብነት ጠቀስኩ እንጂ ኖርዌይ ያሉ ወገኖች ችግር ላይ መሆኔን ከሰሙበት ጊዜ ጀምሮ አልተለዩኝም።

ጎልጉል፦ ወታደር ነህ? ብዙ የህይወት ተሞክሮ አለህ። እንዴት በቀላሉ እጅህን ሰጠህ?
ዳምጠው፦ ውትድርና መከራን መሸከም የሚያስችል ልምድና ተሞክሮ የሚያጎናጽፍ ሙያ ነው። ሰላሳ ሁለት ዓመት በውትድርና ጦር ሰራዊት ቤት ኖሬያለሁ። እንዳልከው ለችግር እጄን መስጠት አልነበረብኝም። የኔ ግን ተደራረበ። በሰው ተከቦ መኖር የለመድኩ ሰው ነበርኩ። አርቲስት እንደመሆኔ ከሰው ተገልዬ አላውቅም። ኖርዌይ ከመጣሁ ሰባት ዓመት ሞላኝ። በተለይ ያለፉት ሶስት ዓመታት ሰው ራበኝ። ተጨዋች ነኝ። ሰው አጣሁ። ከማን ጋር ላውራ? ከማን ጋር ናፍቆቴን ልጋራ? ቤተሰቦቼ ጋር በደወልኩ ቁጥር ስልክ ዘግቼ አለቅሳለሁ። እንባዬ ይወርዳል። ከቤት እንዳልወጣ በረዶ ነው። ወጥቼስ የት እሄዳለሁ? አድሜዬ ገፋ። አሁን ስድሳ ሶስት ዓመት ሞላኝ። በሽተኛ ሆንኩ። ቤተሰቦቼን ሳላይ ባዶ ቤት ህይወቴ ቢያልፍስ? እላለሁ።

ጎልጉል፦ ቤተሰቦችህን ለማስመጣት ሞክረሃል?
ዳምጠው፦ ስልክ ስደውል ባለቤቴና ልጆቼ የሚጠይቁኝ ይህንኑ ነው። ሌሎች ቤተሰቦቻቸውን ይወስዳሉ። አንተ ምን ሆነክ ነው ይሉኛል። ሁሌ የምሰጣቸው መልስ መልሶ ያሳምመኛል። የተሰጠኝ የጥገኝነት ፈቃድ ቤተሰቦቼን ማስመጣት ያስችለኛል።

ጎልጉል፦ ከተፈቀደ ችግሩ ምንድን ነው?
ዳምጠው፦ ስራ የለህም ነው የሚሉት። በርግጥ ስራ የለኝም። አሁን ኦስሎ ወንድሞችና እህቶች ስራ እንዳገኝ እየተሯሯጡ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለኖርዌይ ኢትዮጵያዊያን ህብረትና መደጋገፍ ያለኝን አክብሮት ለመግለጽ እፈልጋለሁ።

ጎልጉል፦ በኖርዌይ ያለው መቀራረብና መተጋገዝ በመልካም ጎኑ የሚያነሱት በርካቶች ናቸው። መልካም ፈቃዳቸው ከሆነ ዶ/ር ሙሉ ዓለምን ወይም የሚመለከታቸውን እንጋብዛለን። አንተ ግን ቤተሰቦችህን ለማስመጣት ከተከለከልክ ለምን በህግ አትጠይቅም?
ዳምጠው፦ ገንዘብ ያስፈልጋል። በዚህ አጋጣሚ በህግ አግባብ ሊረዱኝ የሚፈልጉ ካሉ ደስተኛ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ።

ጎልጉል፦ ባለሙያ ነህ። ለምን በሙያህ እየሰራህ ጠቅመህ ለመጠቀም አልሞከርክም?
ዳምጠው፦ አንዱ በሽታዬ እሱ ነው። በሃዘን፣ በናፍቆት፣ በብቸኝነት፣ በወገን ርሃብ፣ በአገር ፍቅር፣ በሚስት ርሃብ፣ በልጆች ፍቅር ችጋር፣ በብሶት፣ ራሱ ስለስደት፣ ስለ ባህል ረሃብ፣ ስለ አየር ንብረት ወዘተ ስሜቶቼ በተፈራረቁ ቁጥር በእውነተኛ ስሜት ውስጥ ሆኜ ያዘጋጀኋቸው ስራዎች አሉኝ። በርካታ ስራዎች አሉኝ። ብቻዬን ኦና ቤት ውስጥ ሆኜ ያዜምኳቸው እውነተኛ ስሜቶቼ አሉ። ግን ከማን ጋር ልስራቸው? ኖርዌይ የተሟላ ሁኔታ የለም። ስለዚህ ልምዴንና ስራዎቼን ለወገኖቼ ሳላካፍል ማለፌን ሳስበው እታመማለሁ። ህመሜ ከቀን ወደቀን እየጨመረ በሽተኛ አደረገኝ። ከቤተሰብ ረሃብ ጋር ተዳምሮ ውስጤን አሳሳው። እናም መልስ የሌለው ጥያቄ ነው። በአሁኑ ደረጃ እኔ ሰባራ ነኝ።

ጎልጉል፦ ከዚህ ቀደም በሙያህ እንድትሰራ የሚረዱህ ማግኘትህን ተናግረህ ነበር …
ዳምጠው፦ ተናግሬ ነበር። በተደጋጋሚ ቃል የገቡልኝ ነበሩ። አሜሪካና ካናዳ ሄጄ መሰራት እንድችል ስፖንሰር እናደርግሃለን ያሉ ወገኖች ነበሩ። እስካሁን በተግባር የሆነ ነገር የለም። አይመችም ጊዜው አስቸጋሪ ነው። ወደፊት የምናየው ይሆናል። እድሜ ካለ ማለቴ ነው። ሞት ቀጠሮ የለውም። (ሳቀ… ) በሙያዬ እንድሰራ ለሚረዱኝ ሁሉ አድራሻዬን አንተ ዘንድም እንደሚገኝ እገልጻለሁ። የረሱኝም ካስታወሱኝ አለሁ።

ጎልጉል፦ ፈሪ ሆነሃል?
ዳምጠው፦ ያልተነካ ግልግል ያውቃል እንደሚባለው ወግ ሆነብኝ። አስበው ማታ ማታ ኦና ቤት ተቀምጬ የልጆቼ ድምጽ ይሰማኝል። ባለቤቴ የምትጠራኝ ይመስለኛል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሰባት ዓመት ቀላል አይደለም። በተለይ ያለፉትን ሶስት ዓመታት ያሳለፍኩት እንደ መንፈስ ብቻዬን እያወራሁ ነው። መኝታ ቤት አላውቅም። አልጋ አላውቅም።

ጎልጉል፦ የት ትተኛለህ?
ዳምጠው፦ መኝታ ቤት ተኝቼ አላውቅም። ቲቪ እያየሁ ሲደክመኝ እዛው አርፋለሁ። ምን አለኝና መኝታ ቤት አርፋለሁ? መኝታ ቤት የምገባው ልብስ ለመቀየር ነው።

ጎልጉል፦ በሙያህ አሁን ብቁ ነኝ ትላለህ?
ዳምጠው፦ እንግዲህ በቅርቡ ስዊድንና ጣሊያን በተካሄደ የኢሳት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ የናፈቀኝን መድረክ አግኝቻለሁ። የተዋጣለት ስራ መስራቴን መስክረውልኛል። እኔ በመሳሪያ በተሞረደ ድምጽ አልሰራም። ድምጼም ሙያዬም የተፈጥሮ ነው። በየትኛውም ወቅት ስራ ከተባልኩ ዝግጁ ነኝ።

ጎልጉል፦ በዛው ለምን አልቀጠልክም?
ዳምጠው፦ ዝግጅት ሲኖራቸው ይጠሩኛል። እኔም አገራዊ ሃላፊነቴን እወጣለሁ። ስለ አገርና ባህል ሳንጎራጉር ደስ ይለኛል። ለኔ ስለ አገር ከመዝፈን በላይ የሚያስደስተኝ ነገር የለም። አገሬን ተነጥቄያለሁ። እያንጎራጎርኩ ተራራውን፣ አየሩን ፣ ባህሉን፣ ወጉን፣ ሠንደቅ ዓላማውን፣ ህዝቡን ሳናግር እኮራለሁ። ከገንዘብ በላይ አርቲስት ሃብቱ ህዝብ ነው። ራሳችንን ካላረከስን ህዝብ አይጥለንም። ኖርዌይ ያገኘሁት ይህንኑ ክብር ነው።

ጎልጉል፦ የሙያ ባልደረቦችህን ታገኛለህ?
ዳምጠው፦ አረጋኸኝ ወራሽ ይደውልልኛል። ሻምበልም ደውሎልኝ ያውቃል። በተረፈ አገር ቤት ካሉት ጋር ተገናኝተን አናውቅም።

ጎልጉል፦ አብሮ ስለመስራት አልተነጋገራችሁም?
ዳምጠው፦ ላይመቻቸው ይችላል። ታማኝ በየነን ላገኘው ሞክሬ አልቻልኩም። በርካታ የአገር ጉዳዮችን ስለሚያንቀሳቅስ አይመቸውም። ወደፊት ላገኘው እሞክራለሁ።

ጎልጉል፦ የሰርግ ዘፈን ትችላለህ?
ዳምጠው፦ ልታገባ ነው? ወይስ ስራ አገኘህልኝ? በሚገባ እሰራለሁ።

ጎልጉል፦ ቢያንስ በባህላዊ መሳሪያ ባለህበት አገር ሰርግ ለምን አትሰራም?
ዳምጠው፦ እኔ መሳሪያ መጫወት አልችልም። የሚያመቻች ከተገኘ እኔ በድምጼ ድፍን ስካንዲቪያንን እያካለልን መስራት እንችላለን። ለሰርግ ዘፈንና ለስክስታውማ ባለቤቱ ነበርኩ፡፡

ጎልጉል፦ ጥሬ ስጋ ካልበላህ አትጫወትም ይባላል?
ዳምጠው፦ ስጋ ትወዳለህ ለማለት ፈልገህ ከሆነ አዎ ጥሬ ስጋ እወዳለሁ። የስጋ ዘርፉንም ጠንቅቄ አውቃለሁ። ብልቷን ባይነት ባይነት አጥርቼ አውቃለሁ። የዛሬን አያድርገውና ጾም ካልሆነ ያለ ስጋ አልበላም ነበር። ስጋ መቆረጥ ስለማውቅ ትልልቅ ሰዎች ስጋ አብሬያቸው እንድበላ ይጎትቱኝ ነበር። የምን ስጋ አነሳህብኝ?

ጎልጉል፦ ለትዝታ ነው? ከቤተሰብህ ባንተ የወጣ አለ?
ዳምጠው፦ ልጄ እንደኔ ነው አሉ። አስራ ሁለት ዓመት ሲሆነው ጥዬው ወጣሁ አሁን አስራ ዘጠኝ ዓመቱ ነው።

ጎልጉል፦ ስታገኘው ምን ትለዋለህ?
ዳምጠው፦ ምክሬ አንድ ነው። እኔ ባለመማሬ ተጎድቻለሁ። ቋንቋ ይቸግራል። አስተርጓሚ ሰው እያስቸገርኩ ነው። ተማር አለበለዚያ ዋጋ የለህም እለዋለሁ። በደወልኩ ቁጥር ስለ ድንቁርና ሳልነግረው አላልፍም። ገፍቼ አለመማሬ ያንገበግበኛል። ፈጣሪ የልቤን ተረድቶ በልጆቼ ሊክሰኝ ያሰበ ይመስለኛል። ጥሩ ደረጃ ላይ ነው። የደረጃ ተማሪ ነው።

ጎልጉል፦ የማውቅህ ዳምጠው አልመሰልከኘም?
ዳምጠው፦ አዎ፤ እኔም ራሴን እጠይቀዋለሁ። ጀግና ሲወድቅ አይቻለሁ። የጦር ሜዳ መከራና እሳት አይቻለሁ። ባልዋጋም በኦጋዴንና በሳህል ግንባር ኤርትራ ተገኝቼ የመከራን ወጋገን ተመልክቻለሁ። ጀግና ወድቆ ሲነሳ ማየቴ ትዝ ይለኛል። ምንም እንኳን በርካታ የክፉ ቀን መቋቋሚያ ልምድ ቢኖረኘም ካቅሜ በላይ ሆነብኝ። ችግር እንዳይፈታኝ አጥብቆ የያዘኝ የኑሮ ልምዴና ወታደርነቴ እያደር ላላ። እድሜዬ እየገፋ ሲሄድ ነው መሰል ባባሁ። በጀርባዬ ተኝቼ ኮርኒስ እያየሁ ልጆቼንና ባለቤቶቼን በማሰላሰል ደከመኝ። አስባለሁ፣ አወጣለሁ፣ አወርዳለሁ ለውጥ የለም። አናቴ ጋለ። ደም ግፊት ያዘኝ። ሌላውም ተከተለኝ። ታመምኩ። እኔ ተቆንጥጬ ያደኩ፣ ለባህሌና ላገሬ ልዩ ክብር ያለኝ ሰው ነኝ። የአገሬ ሽታ ይመጣብኛል። ከብቶች ሽታቸው ይናፍቀኛል… ታዲያ ይህንን ሁሉ አጥቼ እንዴት የምታውቀኝ የድሮው ዳምጠው ልሆን እችላለሁ?

ጎልጉል፦ ምግብ መስራት ትችላለህ?
ዳምጠው፦ (ሳቅ) ልታሰለጥነኝ ነው? ወይስ …

ጎልጉል፦ በተደጋጋሚ “የጋን ውስጥ መብራት ሆኛለሁ” ስትል ትደመጣለህ፤
ዳምጠው፦ የገለጽኩት መሰለኝ። አንድ የኪነት ባለሙያ ለሁሉም ነገር ስሜቱ ቅርብ ነው። በተፈራረቁብኝ ስሜቶች ውስጥ ሆኜ ያዘጋጀኋቸው በርካታ ስራዎች አሉ። ስለ አገር፣ ስለ ስደት፣ ስለ ሰው ርሃብ፣ ስለ ልጆች ናፍቆት፣ ስለ ትዳር ጓደኛ ፍቅር ርሃብ፣ ስለ ብቸኛነት፣ ስለ ቅዠት፣ ስለ ሃሳብ ጎርፍ በራሴ ስሜት ውስጥ ያለፉ እውነታዎችን ሰብሳቤያለሁ። በሙያዬም ቢሆን በቂ ምስክር ያለኝ ነኝ። ይህንን ሁሉ ነገር ይዤ ማለፍ አልፈልግም። ለሌሎች ማስተላለፍ አለብኝ። በተለይ ለአገሬና ለመጪው ትውልድ የሚሆን ስራ መስራት እፈልጋለሁ። ለዚህ ነው የጋን ውስጥ መብራት ሆኛለሁ የምለው። የተሸከምኩትን ስለማውቅ ነው። ውለታቸውን ዘርዝሬ በማልጨርሰው በኖርዌይ ወገኖቼ ስም አንድ ነገር ባደርግ ደስ ይለኛል።

ጎልጉል፦ የቀድሞ ሰራዊት ሲባል ትቆጣለህ። ለምን?
ዳምጠው፦ እኔ እስከማውቀው የኢትዮጵያ አለኝታ ነበር፣ ግዳጁን በአግባቡ ሲወጣ የነበረ። ወደፊት ታሪክና ጊዜ ይፋ የሚያወጣው ግፍ የተፈጸመበት ታማኝ ሰራዊት ነበር። ጨዋና በሙያው የተከበረ ሰራዊት ነበር። ብቃቱንና አገር ወዳድነቱን በግፍ እንዲበተን ከተደረገ በኋላም አሳይቷል። ይህ ሰራዊት ምንጊዜም የሚረሳ አይደለም። የቀድሞ፣ የደርግ ወዘተ ብለው ሲጠሩት ደስ አይለኝም። አግባብም አይደለም። በዚህ ብናበቃስ?

ጎልጉል፦ አሁን ስላለህበት ሁኔታ ንገረኝና እንሰነባበት?
ዳምጠው፦ አሜሪካና ካናዳ፣ በተለይም አሜሪካ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ቁጥራቸውና ከፍተኛ ስለሆነ፣ ይህንኑ በመረዳት ቃል የገቡልኝ ችግሬን ተመልክተው ስሞት ከሚያለቅሱ ከወዲሁ የሚችሉትን ቢያደርጉልኝ፣ ስፖንሰር አፈላልገው ቢወስዱኝ ስል እማጸናለሁ። አሁን ያለሁት በኖርዌይ ወንድሞችና እህቶች እጅ ነው። ስደተኞቹ ወገኖቼ እየረዱኝ ነው። ስራ ፍለጋ እደከሙልኝ ነው። ሙሉ በሙሉ ህይወቴን እየመሩልኝ ነው። ለሶስትና አራት ወር ሌላ አማራጭ የለም። በዚህ አጋጣሚ በኖርዌይ ያሉትን ወገኖች ዘርዝሬ አልችልም ምስጋናዬ ይድረሳችሁ። ልዑል እግዚአብሄር ውለታችሁን ይክፈለው። ክፉ ምኞት በተመኘሁበት ሰዓት የደረስክልኝ ዶ/ር ሙሉ አለም ከልቤ ላመሰግንህ እወዳለሁ። ያንተን ልዩ የሚያደርገው ምናልባትም ይህንን ምስጋና የማቅረብ እድል ሳላገኝ ከክፉ ምኞቴ ጋር ቀርቼ ቢሆንስ በሚል በየዋህነት ሳስበው መኖሬ ስለሚደንቀኝ ነው። ቀና አሳቢነት ለራስ ቢሆንም ሳላመሰግን ማለፍ ባለመቻሌ ስምህን ጠቅሻለሁ። ለኖርዌይ ወገኖች ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ። አሳልፋችሁናልና ምስጋናዬ ታላቅ ነው።

(ለንባብ ያመች ዘንድ ከአርቲስት ዳምጠው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደ አስፈላጊነቱ ቅደም ተከተሉን ማቀያየራችንን እንገልጻለን። አርቲስት ዳምጠው አየለ ቃለ ምልልስ ለማድረግ ስላደረገልን ትብብር ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ምስጋናችንን እናቀርባለን።)

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልና

No comments:

Post a Comment