"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday 20 October 2012

ቱጃሯ ሱራና ኦህዴድ ከጫት ንግድ በስተጀርባ ያለው ቁማር!!


khatlines and sura
በማናቸውም የአገሪቱ ባለስልጣናትና ተቋማት ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ይፋ የማያደርጉት የአገር ውስጥ የጫት ፍጆታና ገቢ በውስጡ ከፍተኛ ዝርፊያ ይከናወንበታል። ከዝርፊያው ጋር በተያያዘ አቶ መለስን ጨምሮ ከፍተኛ ሹማምንትና ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን በቅድሚያ ስማቸው ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው። የጎልጉል የኦህዴድ ምንጮች የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትርና የንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚኒስትሩ በጫት ንግድ ዙሪያ የሚጫወቱትን ሚና አጋልጠዋል። ያገኘነውን መረጃ ለንባብ ያመች ዘንድ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

የጫት ንግድ ዝምድና – ወ/ሮ ሱራ

በደርግ የአገዛዝ ዘመን ወደ ጅቡቲ ኤክስፖርት መደረግ የጀመረው ጫት ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የወያኔ አባላትን ቀልብ አልሳበም ነበር። ባለስልጣናቱና የቀድሞው ታጋዮች ጫት ተጠቃሚ ስላልነበሩ ስለ ጫት ንግድና ከፍተኛ ፍጆታ እንዳለው መረጃው የላቸውም። እንደውም ጫት “የሚበሉ” ሲመለከቱ ይገረሙ ነበር።
ወ/ሮ ሱራ ጅጅጋ ይኖሩ የነበሩ የሶማሌ ተወላጅ ናቸው። በቅርበት የሚያውቋቸው የሃርጌሳ ሶማሌ ጎሳ አባል የሆኑ ሙሉ የሶማሌ ዜግነት ያላቸው ሴት እንደሆኑ ይናገራሉ። ወይዘሮዋ የጫት ንግድ ስራ የጀመሩት ጅጅጋ ሲሆን ከቀን ወደ ቀን ገቢያቸውን በማሳደግ ወደ ሶማሌ ማጓጓዝ ጀመሩ።
የኦጋዴንን በረሃ በሌሊትና በቀን እያቆራረጡ ሶማሌ የሚገቡትን ላንድ ክሩዘር መኪኖች በመጠቀም ሶራ የጫት ንግዳቸውን አስፋፉ። ሲሉም ጅጅጋ የሚመጣላቸውን ጫት ከመረከብ ይልቅ ራሳቸው ከሐረር ዙሪያና ከአወዳይ አካባቢ በቀጥታ ከገበሬዎች በመግዛት ወደ ጅጅጋና ወደ ሶማሌ በበረሃ በማስረግ ሃብት ሰበሰቡ።
በኋላም ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው ወደ ሶማሊያ ሃርጌሳ ጫት ላኪ ሆኑ። ከድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያ ዘወትር ጫት በኢትዮጵያ አየር መንገድ በማመላለስ የተወለዱበትን አገር የጫት ኮታና ንግድ ለብቻቸው ተቆጣጠሩ። ሃብታቸው እየገዘፈ ሲመጣ የማጓጓዣ ወጪያቸውን ለመቀነስ የራሳቸውን አውሮፕላን ለመግዛት ፈቃድ ጠይቀው ተፈቀደላቸውና በራሳቸው አውሮፕላን ጫት ማጋዙን ተያያዙት። ሃብታቸው ገዘፈ። የጫት ማከፋፈያ መደብ ላይ ተቀምጠው አንድና ሁለት እስር ሲቸረችሩ የነበሩት ሱራ ከበሩ።

የጫት አቅርቦት ሞኖፖሊ

ሱራ የገንዘብ አቅማቸው ሲያድግ ወደ ምዕራብ ሐረርጌና ምስራቅ ሐረርጌ ክልላቸውን አሰፉ። አርሶ አደሩ ውስጥ በመግባት የጫት ማሳዎችን በኮንትራት በመግዛት በሞኖፖል ያዙት። የተሰበረ ጫት ከመግዛት ይልቅ ማሳውን በሞኖፖል በመያዝ በሚፈልጉት መጠን ማግበስበስ ያዙ። በየወረዳው ወኪሎቻቸውን አስቀምጠው ሥራውን ተቆጣጠሩት። የቀድሞውን የደርግ መንግስት የደህንነት ሰዎችና ኮማንዶዎች አደራጅተው የመንግስት ያህል ጡንቻቸውን አጎለበቱ። ሚዲያ እንኳን አጠገባቸው ሊደርስ ቀርቶ ፈራቸው። የሚታጀቡና ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉላቸው ባለሃብት ሆኑ። ጉልበታቸውን ተማምነው በሊዝ የያዙትን የጫት ማሳ ከገበሬ ማኅበራት አመራሮች ጋር በመሆን ወደፊት በሚከፈል እዳ ወደ ሶማሌና በቀን ሁለትና ከዛም በላይ በረራ በማድረግ ከበሩበት።  የኦህዴድ የንግድ ድርጅት የሆነውን ቢፍቱ የጫት ንግድን ሳይቀር ጉሮሮው ላይ ቆመው አንገዳገዱት። በኋላ ላይ እንዳይሆን አድርገው በብር አሽመደመዱትና ሶማሌ ውስጥ ከጀመረው የጫት ንግድ አባረሩት። ኦሮሚያና አስተዳደሮቹ የህዝባቸውን ብሎም የፓርቲያቸውን ጥቅም እንኳን ማስከበር ሳይችሉ ቀሩ። አሁን ድረስም እንደዛው ነው።
እልህ ውስጥ የገቡት የኦህዴድ ሰዎች የፖለቲካ ስልጣናቸውን በመጠቀም ሱራን እጃቸውን ለመጠምዘዝና የሶማሌን የጫት ኤክስፖርት ለመጠቅለል ዘመቻ ጀመሩ። በኦሮሚያ የጫት መቆጣጠሪያ ኬላና በአርሶ አደሮች ማኅበራት አማካይነት ከአገር የሚወጣውን የጫት መጠን በማስላት ከጫት ኤክስፖርት የሚገባውን የውጪ ምንዛሬ መረጃ በማመሳከር ከፍተኛ ማጭበርበር እንደሚካሄድ ለፌደራል መንግስት አሳበቁ። ኦህዴድ ሶማሌ ጫት ንግድ ውስጥ ለመግባት ሞክሮ እንዴት ማጅራቱን እንደተመታና እንዴት ጅቡቲ ውስጥ ተወትፎ እንደቀረ በሌላ ዜና እንመለስበታለን።
ሱራ ከየአቅጣጫው የሚነሳባቸውን ተቃውሞና ቁጥጥር እንዴት እንደሚመክቱ ኦህዴድ ውስጥ መነጋገሪያ ሆነ። በከፍተኛ ደረጃ ያሉ የኦህዴድ አመራሮችና ባለስልጣናቱ ከጫት ንግዱ በስተጀርባ ያለውን አሻጥር ቢያውቁም ሊጋፉት የማይችል ስለሆነባቸው ቀረጥ ላይ አተኩረው በመስራት ክልሉ ከጫት በኪሎ ስድስት ብር ቀረጥ እየሰበሰበ እንዲቆይ ማሳሰቢያ ሰጡ። በዚህም ከሚመዘበረው የኬላ ገቢ ወጪ ቀሪ ክልሉ በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እየሰበሰበ ቆየ። በመካከሉ ሱራ በዘረጉት ሰንሰለት አማካይነት ኬላ እንዲነሳ የጀመሩት ዘመቻ በድል መጠናቀቁ ይፋ ሆነ። ኦሮሚያ ላለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ ሲያገኝ የነበረውን ገቢ ተነጠቀ። በወቅቱ ውሳኔውን ተከትሎ የክልሉ የገቢዎች ቢሮ ውሳኔውን ተቃወመ። በኦሮሚያ የቢሮው ሃላፊ በያዙት አቋምና በሼኽ መሐመድ አላሙዲ ድርጅቶች ላይ በያዙት አስገድዶ ግብር የማስከፈል ርምጃ ተዳምሮ መጨረሻቸው ወህኒ ሆነ።

ኬላ ተነሳ — ቀረጡን ሱራ መሰብሰብ ጀመሩ

የጫት ኬላ እንዲነሳ ቀደም ሲል በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩና በንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚኒስትሩ አማካይነት የውጪ ምንዛሪ ገቢ እንዲጨምር በሚል ሰበብ ሃሳብ ቀረበ። ያለ ቁጥጥር ጫት ቢወጣ የውጪ ምንዛሬ ገቢውን ይጨምራል ተብሎ ዓይን ያወጣ ክህደት ክልሉ ላይ ተበየነ። ክልሉ ሃሳቡን በመቃወሙና በክልሉ ቀረጥ የመሰብሰብ መብቱን ስለሚጋፋ ተግባራዊ ሊሆን አይገባም ቢባልም ከሱራ ጀርባ ያሉት ክፍሎች በኦሮሚያ በኩል የቀረበውን ቅሬታ ወግድ አሉት። ሱራም ባሰማሯቸው ጉዳይ አስፈጻሚዎች አማካይነት ኬላው እንደሚነሳ ሲያስነግሩ የነበረው እውን እንደሚሆን ፉከራው ቀጠለ። በመጨረሻም አቶ መለስ የጫት ኬላ እንዲነሳ የቀረበውን ሃሳብ አጸደቁትና ኦሮሚያ ከጫት ቀረጥ ሲያገኝ የነበረውን ብር ትቶ እጁን ታጥቦ የበይ ተመልካች ሆነ።
አስገራሚ ተብሎ በመረጃው ውስጥ የቀረበው ጉዳይ የጫት ኬላው ቢነሳም ጫት ለወ/ሮ ሱራ የሚያቀርቡት አርሶ አደሮች ሂሳብ ሲሰላላቸው በኪሎ ስድስት ብር “ቀረጥ” በሚል እንዲከፍሉ መደረጋቸው ነው። ቀረጡ የሚሰበሰበው ሱራ ባደራጁዋቸው ክፍሎች ሲሆን፣ ለሚሰበሰበው ብር ማስረጃ አይቀርብም። መረጃው እንደሚለው ኦሮሚያ እንዳይሰበስብ የተከለከለውን ቀረጥ ወ/ሮ ሱራ ሰብስበው የት ያደርሱታል ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል።
“ኬላ ከተነሳና ቀረጥ የምንከፍለው ለማን ነው?” በሚል አርሶ አደሮች ሲጠይቁ “ለባለስልጣኖች ይከፈላል” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው የደደርና አካባቢውን አርሶ አደሮች በመጠቀስ አግራሞቱን የሚገልጸው ጥቆማ፣ በንግድ ትስስር ውስጥ አሉበት የተባሉትን  ባለስልጣናት ይጠቁማል። መረጃው ለኦህዴዱ የንግድ ድርጅት ለቱምሳ ኢንዶውመንት የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ግርማ ብሩ ደርሷቸው እንደነበር አስረድተዋል። አቶ ግርማ ራሳቸው በከፍተኛ ንግድ ውስጥ ስለሚሳተፉ ዝምታን መምረጣቸውንም አመልክቷል።

የሱራ ኃይል

ሱራ የፈጠሩት ኃይል በቀላሉ የሚደፈር አይደለም። በቅርንጫፍ በተበጀ ድርጅት ይሁን በሽርክና በውል ባይታወቅም ሱራ የወ/ሮ አዜብ የቅርብ ወዳጅነት የመሰረቱት አሁን አይደለም። የጫት ንግድ ገቢ ጆሯቸው የዘለቀው ወ/ሮ አዜብ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ጋር ወዳጅነት የተጠናከረበት ዋና ምክንያት ይኸው ሱራ የዘረጉት መስመር እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርብ ነን የሚሉት የኦህዴድ ሰዎች ይናገራሉ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚኒሰትርና የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ የተንቦጫረቁበት የጫት ንግድ በወ/ሮ አዜብ ሾፌርነት ታግዞ ከኦሮሚያ ጉሮሮ ላይ የቀረጥ ገቢውን ነጠቀው። የኦህዴድ ሰዎችም ሆኑ የክልሉ የገቢዎች ቢሮ ትግል በነነ። ወ/ሮ አዜብ ዳር ሆነው በጫት ስራ ላይ ያሰመሯቸው የመከላከያ ሹማምንትና ከፍተኛ የጦር አመራር በገንዘብ እየተራጩ ነው። ኦሮሚያ የክልሉ ቢቀር የህዝቡን መብት ማስከበር አቅቶት እስካሁን በገባሪነት ይኖራል።
“ገንዘብ ያላቸው ከክልል በላይ ገዝፈው የሚዋጓቸውን ማባረርና ማሳሰር ችለዋል። የቀሩትም በስጋት ተወጥረዋል። ኦሮሚያን እየመራን ያለነው እንዲህ እንመስላለን” የሚል ሃረግ ያለበት መረጃ፣ ሱራ መንግስትና ውስን ገቢ በሌለበት አገር የሃርጌሳን ህዝብ ማስተዳደርና ስራ ማሰራት መቻላቸውን ያደንቃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገበያ ሳይቀር የተሻሙት ሱራ ካሉበት ቦታ ለዚህ ጽሁፍ ምላሽ እንዲሰጡ፣ መልስ ሲሰጡም በኪሎ ስድስት ብር ሂሳብ የሚቆረጠው የቀረጥ ብር ስሌቱና ክፍፍሉን በመቶኛ በማስቀመጥ እንዲጠቁሙ ይጠይቃል።

ከዝግጅት ክፍሉ

የኦህዴድ የንግድ ተቋም ቱምሳ ኢንዶውመንት ጫት እነግዳለሁ ብሎ ሃርጌሳ ገብቶ የደረሰበትን ኪሳራና፣ ፑንት ላንድ ብቸኛ ጫት አቅራቢ ለመሆን በረሃ ለበረሃ ተንከራቶ መጨረሻ ላይ ያፈሰውን ቅሌትና የቅሌት ድራማ እናስከትላለን። ለጊዜው አሁን በቀረበው በዚህ ጽሁፍ ላይ ማንኛውም ማስተባበያና የተቃውሞ ጽሁፍ ማቅረብ እንደሚቻል አስቀድመን ለመግለጽ እንወዳለን።

No comments:

Post a Comment