ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ጣጣው ይሄው ነው። እያንዳንዷ ጥቃቅን ጉዳይዎ ሁላ ለአደባባይ ትበቃለች። ባለፈው ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ደሞዝ ልክ የሰማን ሰሞን፤ ፕሮፌሰር መስፍን በፃፉት አንድ መጣጥፍ ላይ “ስድስት ሺህ አራት መቶ ብር ላጥ እያደረጉ ማሰር ሰለቸን አይባልም! በአግባቡ ከሆነ ማሰርም መፍታትም ስራዎ ነው!” ብለው ወረፍ አድርገዎት ነበር። እናም መተቸትም መወረፍም የስራዎ አካል ነው ማለት ነው። እናም ቻል ያድርጉት!
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰውነት ጎዳና መውጣታቸውን አስመልክቶ በርካታ የኢንተርኔት አሳቢ ወዳጆች አስተያየቶችን ሲሰጡ ተመልክተናል።
ከአስተያቶቹ ውስጥ የተወሰኑትን ለማየት ያክል…
“የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል” በሚል ርዕስ አንድ ስዕል ተለጥፎ ተመልክተናል። ስዕሉ አቶ መለስ ክስት ብለው በመከራ ለመሳቅ ሲሞክሩ እና አበበ ገላው ከላይ ሆኖ “መለስ ዜናዊ አምባ ገነን ነው… እስክንድር ነጋ እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ነፃነት፣ ነፃነት፣ ነፃነት” ሲል የሚያሳይ ነው።
በነገራችን ላይ እነ እስክንድር ነጋ ላይ ዛሬ ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔውን ይሰጣል ተብሎ ይገመታል። በርካቶችም በየ ፌስ ቡካቸው ላይ ንፁሀንን ፍቱልን እነ በርባንን እሰሩልን! እያሉ እወተወቱ ነው… ወደ በርባን ስንመለስ… ብዬ ወደ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሬ የጀመርኩትን ብቀጥል ሌላ ይመስልብኝ ይሆን…!? ስለዚህ እንዳይቀየሙኝ ዝም ብዬ ፌቴን ወደ እርሳቸው አዞራለሁ፤
(ፈጥኖ በደረሰኝ ዜና እነ አስክንድር ነጋ ዳግም ለመጨረሻ ውሳኔ ሰኔ ሃያ እንደተቀጠሩ ሰምቻለሁ! እንኳንም ሰኔ ሰላሳ አልሆነ ሰኔ ሰላሳ የፀብ ቀጠሮ ነው! ብሎኛል መረጃውን አደረሰኝ አሽሟጣጭ!)
ወደ እርሳቸው ስንመለስ…
አንዱ ወዳጃችን ደግሞ “እኔ የምለው ቁጣም እንደ ጂምናዚየም ያከሳ ጀመር እንዴ!?” ብሎ ለጥፏል። ከዚህ ስር ከተመለከትኳቸው አስተያየቶች ውስጥ፤ “ሰውየው እኮ በስብሰባ ፍቅር ጉሉኮሳቸውን ነቃቅለው ነው የተነሱት!” የሚል አስተያየት አይቼ አረ ተዉ ግፍ አትናገሩ ብዬ ሳላበቃ ሌላው ደግሞ “እኚያ ሼክ አላሙዲ አንጠልጥለው ወደ ሀኪም ቤታቸው ቢመልሷቸው ጥሩ ነበር!” የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ደንግጠዋል። ድንጋጤውም ህመም ሆኖባቸዋል። ህመሙም አክስሏቸዋል። አክስታቸዋልም። እንግዲህ በዚህ ላይ ደግሞ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ምን አይነት ፊልም እንደሚያዘጋጁ እንጠብቃለን…
በዚህ በቡድን ሃያ ስብሰባ ላይ አባላቶቹ እና ተሳታፊዎቹ በሙሉ ተደርድረው በተነሱት ፎቶግራፍ ላይ ደግሞ አሁንም ከሰው አፍ አይውጡ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን የመሰወር አደጋ ደርሶባቸዋል። እናም በርካቶች “ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያያችሁ አፋልጉን!” እያሉ ማስታወቂያ ለጥፈዋል።
እውነት ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በቡድን ሃያ ስብሰባ ላይ መካፈልዎን ለማረጋገጥ እኮ በዚህ ፎቶግራፍ ላይ የግድ ልናይዎት ይገባል። አለበለዛ ይሄ በየሰበባ ሰበቡ የሚዞሩትን ነገር… ከቤተሰብ ጋር ያቆራርጦታል። እኛ እንኳ የትም ቢሄዱ ግድየለንም… (የመዘዋወርም ሆነ የመሰወር መብትዎን እናከብራለን!)
አረ እዝች ጋ ዛሬ አወራታልሁ ብዬ ያላሰብኳት አንድ ቀልድ ትዝ አለችኝ የፈጀውን ይፍጅ እና ልንገራችሁ፤
የግንቦት ሃያ በዓል ሲከበር ሁለት ዋና ካድሬዎች በበዓሉ ድግስ ይሄንን ያላበው ቢራ ሲለጉ አምሽተው ሞቅ ብሏቸዋል። ታድያ እንዲህ ሆነን መኪና ከምንነዳ ብለው ለጥንቃቄ ታክሲ ሊይዙ ያነጋግሩ ጀመር! (በቅንፍ እነ አጅሬ ለራሳቸውኮ ጠንቃቆች ናቸው ለኛ ጠንቅ ሆኑብን እንጂ… ልበል ወይስ አልበል…!?)
የሆነው ሆኖ ባለታክሲውን “ሲኤም ሲ ውሰደን እስቲ ዋጋው ስንት ነው!?” ብለው ጠየቁት… ባለታክሲውም ባለጊዜዎች መሆናቸው ገባውና “አምስት መቶ ብር ክፈሉ” አላቸው ይሄኔ በጣም ተበሳጭተው። “እንዴት አምስት መቶ ብር ትለናለህ መቀሌ ውሰደን ብንልህ ስንት ልትለን ነው…!?” ብለው በሞቅታና በብስጭት ጠየቁት። ባለ ታክሲውም “መቀሌ… ሄዳችሁ የማትመለሱ ከሆነ በነፃ እወስዳችኋለሁ!” አላቸው። አሉ። ይህንን ቀልድ ወዳጄ እንደነገረኝ ወድያው በአዕምሮዬ የመጣው የመቀሌ ህዝብስ በምን እዳው ይችላቸዋል…? የሚለው ነበር ስለዚህ ባህር ማሻገር ይሻል ይሆን…!?
እናልዎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቡድን ሃያ ስብሰባ ብለው ሄደው ነበር። ነገር ግን ተስብሳቢዎቹ ፎቶግራፍ ላይ የሉም ክሳታቸው ይሄንን ያህል እንዳይታዩ አድርጓቸው ነው ወይስ ፎቶግራፍ አንሺው እሳቸው ነበሩ!?
ጠቅላይ ሚኒስተሬ ከወዴት አሉ!?
No comments:
Post a Comment