"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday 17 July 2012

መድረክ ምሩቃን በኮብልስቶን ሥራ መሰማራታቸው የፖሊሲ ውድቀትን ያሳያል አለ


“አንድ የኢሕአዴግ ባለሥልጣን ልጅ ኮብልስቶን ሲፈልጥ አሳዩንና አሳፍሩን” ዶ/ር መረራ ጉዲና
source reporter 
የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የኮብልስቶን ሠራተኞች መሆናቸው የአገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ ውድቀት የሚያሳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሰፊው የሚጣሱባትና ሠርቶ መኖር እጅግ የከበደባት አገር መሆኗንም ድርጅቱ ገልጿል፡፡
በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ትምህርትንና የትምህርት ተቋማቱን የሚጠቀምባቸው ለአገር ዕድገት ከማሰብ አንፃር ሳይሆን፣ ለፖለቲካ ፍጆታና ለቁጥር ማሟያ ለማዋል መሆኑን የጠቆመው መድረክ፣ “በትምህርት ጥራቱ መውደቅ ለዘመናዊ ሳይንስ፣ ለዘመናዊ ቴክኖሎጂና ለዘመናዊ ራዕይ ብቁ የሆኑ ተማሪዎችን ማፍራት የተሳነው የኢሕአዴግ ትምህርት ፖሊሲ፣ ይግረማችሁ ብሎ ተመራቂ ኮብልስቶን ጠራቢዎች እያፈራ መሆኑን በኩራት እየተናገረ ይገኛል፤” ብሏል፡፡

እንደ መድረክ እምነት ይህ ድርጊት የአገሪቱን ክብር የሚያንኳስስ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ መንግሥት በቂ መምህራንና ቁሳቁስ ባልተሟላባቸው ተቋማት ተማሪዎች ማስመረቁን እንጂ “ምን ይሠራሉ?” ብሎ አለመዘጋጀቱ ያሳያል፡፡ “በመሠረቱ ኮብልስቶን በትምህርት ላልገፉና ገቢ ለሌላቸው ዜጎች የአጭር ጊዜ ሥልጠና ተሰጥቶ የሚሠሩበት እንጂ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ዕውቀት የሚጠይቅ የሥራ መስክ ሊሆን አይገባም፤” ይላል መድረክ፡፡
ስደትን በሚመለከትም አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን በምሥራቅ አፍሪካ ጫካዎችና በቀይ ባህር እያለቁ እስከ ዛሬ በወጉ እንኳን አስከሬናቸው ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥቶ መቀበር ያልተቻለበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆመው መድረክ፣ ለኢትዮጵያውያን ስደት መባባስ፣ ሰቆቃና ሞት መንስዔው የኢሕአዴግ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ መሆኑን አስታውቋል፡፡ “ስደት ለአንድ ዜጋ የመጨረሻ አማራጩ ነው” ያለው መድረክ፣ ሥራ ፍለጋ መጥተው ሲንከራተቱ በሰው አገር በረሃ ውሰጥ ሕይወታቸው የሚያልፈው ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ሠርተው የመኖር ዕድል ቢኖራቸው ኖሮ ስደትን አይመርጡም ነበር ብሏል፡፡
“ሰው በአገሩ ሠርቶ የመኖር ህልውናው አደጋ ውስጥ ሲወድቅ መኖር ስላለበትና ነገን ስለሚያስብ አማራጭ ይፈልጋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ምርጫም አማራጭም በሌለበት ሁኔታ የሚመጣው ብልኅትና ዘዴ መሰደድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሰፊው የሚጣሱባትና ሠርቶ መኖር እጅግ የከበደበት አገር ከመሆኗ አንፃር፣ ኢትዮጵያዊያ ሴቶችና ወጣቶች የሚደርስባቸውን ችግርና መከራ ችለው በቦሌም፣ በሁመራም፣ በሶማሊያም ብቻ ባመቻቸው መንገድ ስደትን ተያይዘውታል፤” ይላል የመድረክ መግለጫ፡፡
መድረክ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው በዚህ መግለጫ፣ ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተጠብቆና የሕይወት ዋስትና አግኝተው በአገራቸው መሥራት አንዲችሉ ኢሕአዴግ በአስቸኳይ ያጠበበውን የፖለቲካ ምኅዳር በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲያስተካክልና ሕዝቡ ያለምንም ፍርሃትና ጭንቀት በነፃነት ተሰባስቦ በአገሩ ጉዳዮች ላይ መወያየት እንዲችል ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ጠይቋል፡፡ በሥራ ፍለጋና በተለያዩ ምክንያቶች የሚሰደዱ ዜጐች ፍልሰት የሚቆምበትን ሁኔታ በመፈለግና ተገቢውን ዕርምጃ በመውሰድ መንግሥት ከፕሮፓጋንዳ የፀዳ ተጨባጭ ዕርምጃ እንዲወስድ፣ በአገር ውስጥ ያሉ በአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ መንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲያደርግና ኤጀንሲዎቹ ስለሚልኳቸው ዜጐች ደኅንነት ኃላፊነት እንዲወስዱ አስገዳጅ ሕግ አውጥቶ ተግባራዊ እንዲያደርግም አሳስቧል፡፡
በዕለቱ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ‹‹ስደት ዓለም አቀፋዊ ነው፤ የኢትዮጵያውያን ስደት ከሌሎች ስደተኞች ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው? አንድ ፒኤችዲ ያለው ኢትዮጵያዊ አሜሪካ ውስጥ ነዳጅ ሲቀዳ ታይቷል፡፡ እዚህ አገርስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ድንጋይ ቢፈልጡ ምን ችግር አለው?›› የሚሉ ጥያቄዎች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ቀርበዋል፡፡
ለቀረቡት ጥያቄዎች ማብራሪሪያ የሰጡት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ስደት ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም በአገራቸው ተስፋ ቆርጠው በየበረሃው የአውሬ ሲሳይ የሚሆኑት እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አገር ያላቸው ዜጐች ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ኮብል ስቶንን በሚመለከትም ‹‹የቸገረውና የሚበላው ያጣ ሰው ኮብልስቶን ሠርቶ ለመኖር ቢጥር አንቃወምም›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ለተከታታይ ስምንት ዓመታት ከ11 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግቤያለሁ፣ 32 ዩኒቨርሲቲዎችን ገንብቼያለሁ የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት ሥራ መፍጠር ሲያቅተው የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ኮብልስቶን ሠርተው መኖር ይችላሉ ወደሚል ቀልድ መግባቱ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ይህንን ጥያቄ የጠየቃችሁ የመንግሥት ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ተዘዋውራችሁ አንድ የኢሕአዴግ ባለሥልጣን ልጅ ኮብልስቶን ሲፈልጥ አሳዩንና እኛን አሳፍሩን፤” ብለዋል፡፡
ዶ/ር መረራ እንዳሉት፣ በአሁኑ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የኢሕአዴግ አባል ካልሆኑ በስተቀር ሥራ ማግኘት ስለማይችሉ እርሳቸው የሚያስተምሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “በአካዳሚክ ‘A’ ከምናገኝ ይልቅ በኢሕአዴግ መሥፈርት ‘C’ ብናገኝ ሥራ ማግኘት እንችላለን” ብለው ስለሚያምኑ ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ አይደሉም፡፡
ሌላው የመድረክ አመራር አባል አቶ ገብሩ አሥራት በበኩላቸው፣ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ የሚወጣ አንድ የተማረ ሰው በተመረቀበት ሙያ ተሰማርቶ የወጣበትን ወጪ መመለስ እንዳለበት፣ የኢኮኖሚን ሀሁ የሚያውቅ ማንኛውም ግለሰብ የሚረዳው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንድ ሰው ጋዜጠኝነት ተምሮ ድንጋይ የሚፈልጥ ከሆነ ትምህርቱ ዋጋ የለውም፡፡ 15 ዓመት የተማረው ሙያ ከንቱ ነው ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ስደት ከሌሎች አገሮች ስደት የሚለይበትን ሲያብራሩም፣ ‹‹ጣሊያኖች ሊሰደዱ ይችላሉ፣ ግሪኮች ሊሰደዱ ይችላሉ፣ ነገር ግን ወደ ተሻለ ሕይወት እንጂ ወደ ሞት አያመሩም፡፡ ወደ ሞት የሚያመራ ስደት የጭንቀትና የተስፋ መቁረጥ ውጤት ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment