አቤ ቶኪቻው
በትላንትናው ሌሊት የመንግስት ታጣቂዎች በአወሊያ ግቢ ባደረሱት የአስለቃሽ ጭስ እና አስለቃሽ ጥይት ጥቃት በአካባቢው የነበሩ ክርስቲያን ወገኖች ለሙስሊም ወንድምናእህቶቻቸው ውሃ በማቀበል እና ቤታቸው በማሳደር ያላቸውን ወገናዊነት ሲያሳዩ እንደነበር ተሰምቷል። ይሄ በጣም አስደሳች ነው!
ከዚህ በፊትም እንዳወጋነው ባለፈው ጊዜ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሙስሊሙን፤ “ክርስቲያን መጣብህ!” ክርስቲያኑን ደግሞ “ሙስሊሙ መጣብህ” በማለት አንዱን በአንዱ ላይ የሚያነሳሳ ፕሮግራም ቀደሞ የሰራው በእንዲህ ያለው ጥቃት ጊዜ እርስ በርስ መተባበር እንዳይኖር ለማድረግ አስቦ ነው ሲሉ በርካቶች ይወቅሳሉ… (ለነገሩ በበርካቶች አሳበብኩ እንጂ አንዱ እና ዋናው ወቃሽ እኔ ነኝ! እንደውም ከትላንትናው እስለቃሽ ጭስ እኩል የኢቲቪ ከፋፋይ ፕሮግራም አስለቅሶኛል! ብዬ ብናገር ግነት አለው ብላችሁ እንዳትጠረጥሩ!)
በነገራችን ላይ “መንግስታችን” በሌሊት እንዲህ አይነት ጥቃት ማድረሱ ደግሞ ለሌላ መከፋት ዳርጎኛል። በጦርነት ህግ እንኳ በሌሊት አንድ አካባቢን መደብደብ የሚቻል አይመስለኝም። እንደዛኛው ሰውዬ “ጦርነት ህግ የለውም!” ብለን ካልተሳለቅን በስተቀረ አግባብ አይደለም።
“ሌሊት ለአራዊት ቀን ለሰራዊት” ከሚለው የመፅሐፍ ቃል ባፈነገጠ መልኩ፤ እንደ አራዊት በለሊት የተደረገውን ወረራ የመጣው ይምጣ ብዬ አወግዛለሁ! ነውር ነው! ብዬም እጨምራለሁ!
አሁንም ጭምር አንዋር መስጊድ ፌደራል ፖሊሶች እና ባለ ቀይ ቆብ ወታደሮች በተለምዶ “አጋዚ” የሚባሉት በብዛት ይታያሉ። በርካታ ሙስሊም ወገኖችም በአንዋር መስጊድ “አሏህ ዋክበር” በማለት ላይ ይገኛሉ!
ከሁሉም በላይ በግሌ ክርስቲያን ወገኖች የሙስሊም ወንድሞቹ ጥያቄ ከአክራሪነት ጋርም ሆነ ከኢስላማዊ መንግስት ጋር ምንም ዝምድና እንደሌለው። ተረድቶ ከወገኖቹ ጋር በመቆሙ ለማመስገን እወዳለሁ!
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእኔ እና የወዳጄ ሁሴንን የቆየ ወዳጅነት በ “ዶክመንተሪ ፊልም” ማጠልሸት ይቻላል ብሎ ማመኑ የሚያስቅም የሚያሳቅቅም ነው!
አንድነታችን ለዘላለም ይኑር!
No comments:
Post a Comment