ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
ከምን ግዜውም በላይ አስፈላጊ የተባለ የአንድነት ጥሪ ተላለፈ፤
በአዲስ አበባ የተለያዩ አቅጣጫዎች ድንገተኛ ጥሪ “አዛን” ጥሪ የተላለፈላቸው ወገኖች ወደ አወሊያ ሲያመሩ በፌደራል ፖሊስና በመከላከያ ሃይል የሃይል ርምጃ እንደተወሰደባቸው ለማወቅ ተችሏል። ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አወሊያና አንዋር መስጊድ ሲያመሩ በነበሩት የዕምነቱ አባላት ላይ የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር ባይገልጹም ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ተሰምቷል።
“የምንፈራው አስከፊ አደጋ እየመጣ ነው። መንግስት የሙስሊሙን ህዝብ ጥያቄ ለማፈን እየወሰደ ያለው ርምጃ ፈር ለቋል” ሲሉ በአትላንታ ከተማ የሚገኘው የሙስሊም አንድነት ኮሚቴ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ አስታውቀዋል። ኮሚቴው ለጋራ ንቅናቄው የህዝብ ግንኙነት እንዳስታወቀው አኢጋን ከቆመለት ዓላማ አንጻር ቀደም ሲል እንደሚያደርገው ሁሉ የአደጋውን አስከፊነት ለህዝብና ለሚመለከታቸው ሁሉ አስቀድሞ ይፋ እንዲያደርግም አመልክቷል።
የዘር፣ የጎሳና የሃይማኖት ልዩነት በመፍጠር በልዩነት የስልጣን እርከኑን ለማስጠበቅ ላፍታም የማይተኛው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የፌደራል ፖሊስ ሃይሎች በትናትናው ዕለት ሀምሌ 6 ቀን 2004 ዓ ም በአወሊያ የጁምአ ጸሎት ስርዓት ላይ ለመካፈል በተገኙ የዕምነቱ ተከታዮች ላይ የፈጸሙት ድርጊት የቀሰቀሰው ቁጣ ከወትሮው ሁሉ የተለየ መሆኑን የኮሚቴው አባላት ያስረዳሉ።
እንደ ኮሚቴው ገለጻ በተለመደው የጁምአ ጸሎት ላይ የተገኙ ሰፊ ቁጥር ያላቸው የዕምነቱ ተከታዮች በተሰባሰቡበት አወሊያ ቅጥር ግቢውን ዘልቀው የፌደራል ፖሊስ አባላት ይገባሉ። “የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄዎች አስፈጻሚ የሆኑት አስራ ሰባቱን የኮሚቴ አባላት አፍኖ ለመውሰድ ደብዳቤ አዘጋጅተው የመጡት የታጠቁ ፖሊሶች የህዝቡን ቁጣና ብዛት ሲመለከቱ የአመጣጣቸውን መልክ ቀየሩ” ብለዋል። አያይዘውም “በቅጥር ግቢው (አወሊያ) ውስጥ የታሰሩትን በሬዎች ማረድ አትችሉም” ሲሉ ታጣቂዎቹ አስገራሚና አስደንጋጭ ትዕዛዝ በማስተላለፍ በሬዎቹን ለመውሰድ እንደመጡ ገልጸዋል።
“ይህን ጊዜ” ይላሉ እኙሁ የኮሚቴው አባል፤ “ይህን ጊዜ ህዝቡ ተቆጣ። ተቃውሞውን አሰማ። የእምነት ቦታ ዘልቀው በመግባታቸውና ላለፉት ተከታታይ ወራት በደረሰባቸው በደል ውስጣቸው የተቀየመ አመጻቸውና ተቃውሟቸው አየለ…” የመጡበትን ዓላማ ማሳካት ያልቻሉት የታጠቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት አንድ አስገራሚ ትዕዛዝ በመስጠት ግቢውን ለቀው ወጡ። እንደ ኮሚቴው ገለጻ የተሰጠው መመሪያ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው፣ አንድ ህዝብ እመራለሁ ከሚል አካል የማይጠበቅ ተራና ህዝብን የናቀ ትዕዛዝ ነበር።
ከኦርቶዶክስ፣ ከካቶሊክ፣ ከፕሮቴስታንትና ከሙስሊም ሃይማኖቶች አገልጋዮችና ተከታዮች ያሉበት፣ የሁሉም እምነት ተከታዮች ፍቅራቸውን፣ አንድነታቸውንና የኖረውን አጋርነታቸውን እንዲገልጹበት ታስቦ የተዘጋጅ ያንድነት የሰደቃ/የምሳ ግብዣ የፊታችን እሁድ እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ለዚሁ ስነስርዓት የሚውሉ ሰንጋዎች አስቀድመው ተገዝተው አወሊያ ግቢ ውስጥ ታስረዋል። የኮሚቴው አባል በመገረምና “አዝኛለሁ” በማለት በደረሰው ጉዳት ሃዘን እየተናነቃቸው ሳግ በያዘው አንደበት ስለተላለፈው ትዕዛዝ አስረዱ።
እርስ በርስ ተዛዝኖ፣ተዋዶና ተከባብሮ ለዘመናት የኖረውን የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳና በሃይማኖት እየለያ የአገዛዝ ዘመኑን የሚያራዝመውና በሌሎች አለመስማማት ውስጥ ተመሽጎ የመኖር ስልት የሚከተለው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ እነዚህ ህዝቦች አብረው መመገብ እንደማይችሉ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ የሰጠው ምክንያት “እሁድ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ስለሚካሄድ ተሰብስባችሁ ባንድነት መመገብ አትችሉም” የሚል እንደነበር ከኮሚቴው አባል ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። ማምሻውን የአገዛዙ ቴሌቪዥን በዜና እወጃው ይህንኑ አዋጅ ይፋ አድርጓል።
የአትላንታው የሙስሊም አንድነት ኮሚቴ አባሉ ለግርምታቸው ጥያቄ በማንሳት ማብራሪያ ያቀርባሉ “የአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያለው ከሜክሲኮ በታች የቀድሞው ከርቸሌ ቄራ ጥግ፤ አወሊያ ያለው አስኮ፤ አሁን አስኮና ቄራ ጥግን ምን ያገናኛቸዋል?” ይጠይቃሉ። አክለውም “ስርዓቱ ህዝቦች ሲዋደዱና የኖረውን ፍቅራቸውን ጠብቀው ሲኖሩ የማይመቸው በመሆኑ ውሃ ቀጠነ ትዕዛዙን በሰላማዊ መንገድ የሚቃወሙትን አምልኮ ቤታቸውን ዘልቆ ይገላል፣ ያስራል፣ ይገርፋል፣ ያስፈራራል፣….. በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ምሬቱ ከልክ በማለፉ ለመብቱ መከበር ወደኋላ ስለማይል አደጋው አስጊ የሚባል ደረጃ ደርሷል” ሲሉ ስጋታቸውን ይፋ አድርገዋል።
የከፋው ህዝብ፣ እምነቱ እየተነካ ያለ ህዝብ፣ ወገኑን እያጣ ያለ ህዝብ የሚወስደው ራስን የመከላከልና እምነትን የማስጠበቅ ርምጃ የሚያስከፍለው ዋጋ ተጠያቂው አገዛዙ ቢሆንም ወገን የኢትዮጵያ ህዝቦችና የሚመለከታችው ሁሉ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ከምንጊዜውም የላቀ አንድነት ሊፈጥሩ የሚማማሉበት ወቅት ላይ እንዳሉ የአንድነት ኮሚቴው አሳስቧል።
የጉዳዩን አሳሳቢነት ሲያብራሩ ለጁምአ ጸሎት የወጣው ህዝብ ሲቀንስ ከምሽቱ አምስት ሰአት አካባቢ የአወሊያን የላይኛው በር ዘልቀው በመግባት የፌደራል ፖሊስ አባላት ተኩስ ከፍተው ለጊዜው ባላቸው መረጃ አንድ ሰው ገድለዋል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በሁለት ተሽከርካሪ ታጉረው ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደዋል። የአንድነት ኮሚቴ አባሉ እንዳስታወቁት “… ይህ ከተፈጸመ በኋላ በየመስጂዱ በተደረገ ግንኙነት የችግር ቀን አዛን ጥሪ ለምዕመናኑ ተላልፎ ህዝቡ በያቅጣጫው ወደ አወሊያ እየተመመ ነው። የፌደራል ፖሊስ ሃይል መንገድ በመዝጋት የህዝቡን ፍሰት ቢከለክልም ሃይማኖታዊ ጥሪ የተላለፈላቸው ወደ አወሊያ አንዳይሄዱ መከልከል አልቻለም” ፖሊስ የህዝቡን ፍሰት ለመከላከል መሳሪያ መተኮሱና፣ የሰልፍ መበተኛ ቁሳቁስና ከልክ ያለፈ ሃይል በመጠቀም ለጊዜው በውል ያልታወቀ ጉዳት ማድረሱና በርካቶችን ማሰሩን ለማወቅ ችለናል።
ይህንን መረጃ በሰጡበት ወቅት የሟቾችና የታሳሪዎች ቁጥር እንደሚጨምር መረጃ እየደረሳቸው እንደሆነ ያስታወቁት የኮሚቴው አባል በሬዎችን የተሰራውን ዳስ በማፍረስ በሬዎቹን ለመውሰድ የታጠቁ የፌደራል ፖሊስ ሃይሎች በወሰዱት የሃይል ርምጃ ጉዳት የደረሰባቸውንና የጉዳቱን መጠን ይፋ እንደሚያደርጉ አስታወቀዋል። “ሙስሊሙን ከሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ … በማናከስ ጥላቻ እየፈጠረ የስልጣን ዘመኑን በአፈና ለማራዘም የማይታክተው አገዛዝ ካጠመደው የልዩነት ወጥመድ ለመውጣት አንድ የምንሆንበት ጊዜ አሁን ነው። በውጪም ሆነ በውስጥ ያለን የኢትዮጵያ ልጆች ከጥንት ጀምሮ የነበረንን አብሮ የመኖር ታሪክ በማጥበቅ በአሸናፊነት ለመውጣት እንትጋ፣እንረዳዳ፣ እንተጋገዝ” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም እሁድ ይደረጋል የተባለውን የሰደቃና ያንድነት ስነ ስርዓት “ህገወጥ ስብሰባ” ሲል አገዛዙ መግለጫ በማውጣት እገዳ ጥሎበታል፡፡ ይሁን እንጂ የኮሚቴው አባላት የሰደቃው ስነ ስርዓት ሃይማኖታዊና ሰላማዊ በመሆኑ እንደማይቋረጥ የአገር ውስጥ መረጃውን ጠቅሶ አስታውቋል።
ሐምሌ 14 ቀን 2004 ዓ ም ኡስታዝ አቡበከርና ኡስታዝ አህመዲን የሚባሉ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄዎች አስፈጻሚ ኮሚቴ አባለት በተሽከርካሪያቸው እየተጓዙ ሳሉ በድንገት በታጠቁ ሲቪል የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው የወከሉዋቸውን የዕምነቱ ተወካዮች እንዳስቆጣ፣ ታሳሪዎቹ ከድርጊታቸው ካልታቀቡ ህይወታቸውን እንደሚያጡ፣ ቤተሰቦቻቸው ጭምር ችግር ውስጥ እንደሚወድቁ ካስፈራሯቸው በኋላ እንደለቀቁዋቸው በተለያዩ መገናኛዎች መጠቀሱን በማውሳት የአንድነት ኮሚቴው አባላት የችግሩ ውስብስብነት አስታውሰዋል።
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ለአኢጋን ሚዲያና ሕዝብግንኙነትንግብረኃይል (media@solidaritymovement.org) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን(www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡
No comments:
Post a Comment