"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday 18 July 2012

መለስ ላልተወሰነ ጊዜ ስራ አይጀምሩም፤


በ21 ዓመታት የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በጤንነት ችግር በ19ኛው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ ያልተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸው ተሰማ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የውጭ ሕክምና ክትትላቸውን ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
Azeb Mesfin, wife of Ethiopian Prime Minister Meles Zenawi, leaves the venue of general assembly, Organization of African First Lady against HIV/AIDS meeting,on July 16,2012 during the 19th African Union summit in Addis Ababa. (Photo Getty Images)

ላለፉት አሥር ቀናት አካባቢ ሕክምናቸውን በውጭ ሲከታተሉ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ወደ አገራቸው ሲመለሱም በቶሎ ሥራ እንደማይጀምሩ ታውቋል፡፡ ለ21 ዓመታት ያለዕረፍት ከፍተኛ የአገር ኃላፊነትን ሲወጡ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሕመማቸውም ምክንያት ካለባቸው የሥራ ጫና ብዛት የመጣ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተወሰኑ ጊዜያት ካለባቸው ከባድ ኃላፊነት ርቀው ዕረፍት እንዲያደርጉ በሐኪሞቻቸው መመከራቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕክምናቸውን ሲከታተሉበት የቆዩበት አገር ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይገለጽ የጠየቁት ምንጮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እሳቸውን ሄደው መጐብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዳሉም ታውቋል፡፡ ባለፈው እሑድ በይፋ በተከፈተው 19ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ አምባሳደር ብርሃነ ያልተገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን የወከሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ተቀዳ ዓለሙ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ልዩ አማካሪ በአቶ ንዋይ ገብረ አብና በአምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ተከበው ታይተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን የባለቤታቸው ጤንነት እየተሻሻለ በመምጣቱ በመሪዎቹ ስብሰባ ላይ መሳተፍ ችለዋል፡፡ ወይዘሮ አዜብ ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባም ላይ ነበሩ፡፡

ምንጮች አክለው እንደገለጹት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጆችም ጤንነታቸውን በቅርበት ሲከታተሉ ነበር፡፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ግርማ ብሩ፣ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሥዩም መስፍን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚታከሙበት ቦታ ሄደው ከጐበUቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት የ57 ዓመቱን ጠቅላይ ሚኒስትር በተመለከተ በርካታ መረጃዎች በተለያዩ የሚዲያ ተቋማትና ሶሻል ሚዲያዎቹ ሲሰራጩ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመም የተገለጸው ግን ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የኔፓድ ስብሰባ ላይ ሲሆን፣ መንግሥት ስለጉዳዩ ይፋዊ መግለጫ ባለመስጠቱም እስካሁን በርካታ ወሬዎች እየተናፈሱ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩትና ሪፖርት እንዲያደርጉ ሲጠበቁበት በነበረው 27ኛው የኔፓድ ስብሰባ ላይ እሳቸውን ተክተው ስብሰባውን የመሩት የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳሊ ስለጤንነታቸው ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሳሊ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በጤና ችግር ምክንያት በስብሰባው ላይ እንደማይሳተፉ ገልጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቶሎ እንዲያገግሙ ያላቸውን ምኞት ለተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ እስከዚያ ደቂቃ ድረስ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕመም በይፋ የተነገረ ነገር ስላልነበር፣ በበርካታ ዜጎች ላይ ውዥንብር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቷን በመምራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው መጠን “ሕዝቡ ስለሳቸው የማወቅ መብቱን ተነፍጓል” በማለት መንግሥት ስለጉዳዩ መግለጫ ባለመስጠቱ በርካቶች ተቃውመውታል፡፡ ከቅርብ ወራት በፊት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በደረሰባቸው የጤንነት መታወክ ሕዝቡ አርፈዋል እስከማለት ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ መንግሥት በወቅቱ ስለጉዳዩ ይፋዊ መግለጫ የሰጠው ዘግይቶ ነበር፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የጤንነት ጉዳይን በተመለከተ ከትናንትና በስቲያ አቶ ኃይለ ማርያም፣ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባድ የሆነ ሕመም አልገጠማቸውም፡፡ ትንሽ የጤና መታወክ ገጥሟቸዋል፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው ሕክምና ስለሚያስፈልጋቸው ሕክምናቸው ተከታትለው በቅርቡ ይመለሳሉ፤” ሲሉ ለብሉምበርግ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለመጨረሻ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት በታዩበት ወቅት ከፍተኛ የሰውነት መቀነስ የታየባቸው ሲሆን፣ መንግሥት ይፋዊ መግለጫ ባለመስጠቱ ምክንያት “አርፈዋል” እስከመባል ተደርሶ ነበር፡፡ የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተክቶት የሚሠራ ሲሆን፣ ይህ የሚሆነው ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ ያለው የፖለቲካ ድርጅት በምትኩ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሚመርጥ ድረስ ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ጊዜውን ፈጽሞ የሚዘጋበት ሰኔ 30 ቀን ያለፈበት ምክንያት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና መጓደል ምክንያት ሲሆን፣ ትናንት እሳቸው በሌሉበት የአፈ ጉባዔው ሪፖርት ተሰምቶ ምክር ቤቱ ተዘግቷል፡

No comments:

Post a Comment