"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday 19 July 2012

አንድ ብስጭት፤ ኢቲቪ ሀይማኖቱ ምንድነው!?


አንድ ብስጭት፤ ኢቲቪ ሀይማኖቱ ምንድነው!?


እስቲ ቆይ ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ከማምራታችን በፊት አንድ ዋዛ ብጤ እናምጣ አሁን በቅርቡ አንድ ወዳጄ አንድ ፈታኝ ጥያቄ ጠይቆኝ ነበር። ምን አለኝ መሰልዎ “አቶ መለስ እና ኢቲቪ ተጣልተዋል እንዴ!?” አለኝ ሲቀጥልም፤ “ያኔ ጋሽ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ገና ትንሽ ሲወራባቸው “ፕሬዘዳንቱ በህክምና ላይ ናቸው አትደናገጡ!” ብሎ የነገረን ቴሌቪዥናችን ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ ዝም ማለቱ ምን ቢያስቀይሙት ነው!?”  ብሎኛል።
የምር ግን ገቡ የለ ወጡ የለ ሀገር ሁሉ በርሳቸው ጉዳይ ሲጨነቅ ኢቲቪ ፀጥ ማለቱ የምርም ተጣልተው ይሆን እንዴ…? ያሰኛል። ስለ ኮብልስቶን መቀበር እና መቀጥቀጥ ደጋግሞ የሚነግረን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ህመም ሲቀጠቅጣቸው እና “ቀብራቸው ደረሰ” እያለ ሀገሩ ሲያሟርትባቸው እርሳቸውን ከኮብል ስቶን አሳንሶ አንዳችም ነገር ትንፍሽ አለማለቱ በእውነት የታሪክ ተወቃሽ ያደርገዋል።
የእውነት ግን ወዳደጄ  የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ነገር ስንቱ ተወርቶ ስንቱ ቀርቶ… አይነት ነገር ነው። አሁን መቼለታ የኮምቦልቻ አካባቢ ሙስሊም ነዋሪዎች በአዲሳባ የተቀሰቀሰውን የሙስሊሙን ተቃውሞ አወገዙ ብለው በአወልያ ላለፉት ስድስት ወራት ፍፁም ሰላማዊ ተቃውሞ እያሰሙ የነበሩ ሙስሊሞችን የሚቃወሙ ሰዎች ቃለ ምልልስ አድርገውላቸው ነበር።

በበኩሌ፤ የአወሊያ ሰላማዊ ተቃዋሚ ሙስሊሞችን  የሚቃወሙበት አላማ ምንም ይሁን ምን መሰማት እንዳለባቸው ብዬ አምናለሁ። እነርሱን መቃወም እንደሚቻልም  አምናለሁ። እነሱን የሚቃወሙ ሌሎች ሙስሊሞች እንደሚኖሩም አምናለሁ። ይሄ ጤናማ ነው።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለአንዱ ወግኖ አንዱን ማብጠልጠሉ በእውነቱ ደባሪ ነገር ነው። የክልል እና የፌደራል ባንዲራ ይዘው ጎዳና ወጥተው ኮምቦልቻንም ይሁን፣ ባቲንም ይሁን፣ ከምሴን በሰልፍ ሲበጠብጡ የነበሩትን እየደገፈ፤ ላለፉት ስድስት ወራት ጎዳና ሳይወጡ ውስን ቦታ ብቻ በቤተ መስጊዳቸው እና በአወሊያ ግቢ  ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩትን  ማውገዝ በእውነት ነውር ነው…?
ለመሆኑ ኢቲቪ ሃይማኖቱ ምንድነው!? ህገ መንግስቱ “የመንግስት የሚባል ሃይማኖት የለም ሁሉም ሃይማኖቶች በመንግስት አይን እኩል ናቸው!” ይላል። ታድያ አንዱን አክራሪ እያሉ ማኮሰስ አንዱን የሰላም አባት እያሉ ማሞካሸት ይሄ ነው ሃይማኖትን በእኩል አይን ማየት?
ቆይ አንዴ፤ ከላይ የጀመርኩትን ሳልጨርስልዎ ነው ለካ ወደሌላ መስመር የገባሁት፤ እናልዎ “የኮምቦልቻ ሙስሊሞች አክራሪነትን እንደሚቃወሙ አስታወቁ” ብሎ ቴሌቪዥናችን እኛ ሰዎቹ ላይ ምልክት የማናደርግ መስሎት ይሁን ወይ ደግሞ ሰዉ ኑሮውን እንጂ እኛን አይከታተልም በሚል ተስፋ መቁረጥ  እንጃ እነዛኑ ሰዎች መለሶ “አንዳንድ የአዲሳባ ሙስሊሞች” የሚለው ዘገባ ላይም መልሰን አይናቸው!
ወይ ኢቲቪ… እኛ እኮ እንኳንስ ሰዎች ላይ ይቅርና የልማት ከብቶች እና ጥቅል ጎመን ላይ ምልክት የምናደርግ ትጉሃኖች ነን! ከዚህ በፊትም ለጎጃም ያየነውን የልማት ጥቅል ጎመን ለደቡብ አይተነው ስንደነቅ ነበር። አሁንም የተደረገው ተመሳሳይ ነው!
አረ በናታችሁ በዚች በትንሹ ካልታመናችሁ ትልልቅ ነገሮች ላይ እንዴት ነው የምናምናችሁ? ዉ…..ዉ….ዉ! የምሬን ነው ይሄ ነገር ያሳሰበኝ።
ለማንኛውም አሁን ደግሞ እንደደረሰኝ ወሬ ከሆነ (ደሞ መሆኑም አይቀርም!) ባለፈው ሌሊት በአወሊያ ግቢ የፖሊስ ልብስ ለብሰው የገቡ ሰዎች በግቢው ውስጥ ራሳቸው የጦር መሳሪያ በማስቀመጥ  የተቃዋሚዎቹ ኮሚቴ ህዝቡን መሳሪያ ሊያስታጥቅ ነበር። በሚል ዶክመንተሪ ፊልም ሊሰራ እንደሆነ ተሰምቷል። (በቅንፍም ኢቲቪ ቢሰማም ባይሰማም እመክራለሁ በናታችሁ አንዳንዴም አራዳ ሁኑ “ከተነቃ ይቀራል!” በሉ እና ይሄንን ዶክመንተሪ ከመስራት ተቆጠቡ!)
ሌላ ደግሞ የመንግስት አቃቤ ህግ በህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑንም  ውስጥ አዋቂ ምንጭ ጠቅሶ አንድ ወዳጄ ወሬ አቀብሎኛል።
አቃቤ ህጉ ክሱን የሚመሰርተዉ 1ኛ). ህገ ወጥ ስብሰባና ህገ ወጥ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ለማጨናገፍ ባደረጉት ጥረት በሚል ሁሉንም የኮሚቴዉ አባላት፤
2ኛ) በህገ ወጥ ስብሰባዎች ላይም ህዝብን በመንግስት ላይ እንዲያምፅ በማነሳሳት ሁከትና ረብሻ ለመፍጠር በመሞከር በሚል ክስ ደግሞ የኮሚቴዉን አባላት በተለይም የኮሚቴዉን ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ የታሪክ ምሁሩን ኡስታዝ አህመዲን ጀበልን እና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱን ለመክሰስ ተዘጋጅተዎል::
እናም የመንግስትም ሆነ የመንግስት ቴሌቪዥን ነገር በጣም ያስደንቃል። እስቲ ጠይቁልኝ እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታቸው ምንድነው?

No comments:

Post a Comment