"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday 10 July 2012

ይዞህ ይሂድ ከመባል ያድናችሁ




ዳኛቸው ቢያድግልኝ

ይህ ጽሁፍ የተንደረደረው ሰሞኑን በተለያዩ ድህረ ገጾች፣ ፓልቶክና ሰሞነኛ የቡና ወሬዎች ላይ የኢትዮጵያ አውራ ነኝ የሚሉትና ፓርቲያቸው እያስገደደ ስልጣን ላይ ያቆያቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ህመም አስከትሎ በሚሰነዘሩ አስተያየቶች መነሻነት ነው። የሰው ልጅ ጥላቻ እዚህ ጥግ ድረስ ደርሶ በእግዜር ይማረው ምትክ ይዞት ይሂድ የሚሉ አስተያየቶች በዝተው ሳይሆን ተትረፍርፈው ማየቴ አሳስቦኝ አብረዋቸው ላሉ ለታመሙና ገና ላልታመሙ ሁሉ ይዞህ/ሽ ይሂድ ከመባል ያድናችሁ በማለት ወገናዊ አሳቤን ማቅረብ ከዝምታ ይሻላል በማለት ነው። እግረመንገዴንም ነገ የሚሆነው እያሳሰበኝ ዛሬን ካላወቃችሁበት ነገ የናንተ አይደለምና ምርጫችሁን አስተካክሉ ለማለት ነው። አባ ጳውሎስ አሉላቸውና የኔ እግዜር ይማሮት ግን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አይጠቅምም። ሰው ናቸውና አፍረውም አንገት ደፍተውም ወደ አፈር መመለሳቸው እውነት ቢሆንም የምትማር ነብስ ካለቻቸው በፈጣሪ ስራ ውስጥ አኔ አልገባም።

የሰው ልጅ ነብሱ ከስጋው የመለየት ምጥ ውስጥ ስትገባ እግዜር ይማረው/ራት ማለት ባሕላችን ነው። ሰብዓዊነት በራሱ ሞትን እንደዚህ አድርገን እንድናየው ያደረገን ህልፈቱ የስጋዊ ማንነት መጨረሻና መመለሻ የሌለው ነገር ስለሆነ ነው። ሟች ቀሪ ቤተሰብና ቤተዘመድ ይኖረዋልና የነርሱንም ጥልቅ ሀዘን በማሰብ ሞት ላይ ጨከን የሚል ጥቂት ነው። ያ ጭካኔ የሚታየው ፍልሚያ ላይ ከሆነ፣ ጦርነት ላይ ከሆነ ነው። ሰው በመሰሪነቱ ረቅቆ፣ በአፍራሽነቱ ልቆ፣ በአስገዳይነቱና በልቅ አንደበቱ ታውቆ በዚህ ምድር ከተመላለሰ የሞተው ከፍጥረቱ በፊት ነውና በስጋ መለየቱ ማንንም አይቆረቁርም። የመለወጥ እንጥፍጣፊ ተስፋ የለውምና እንዲያውም ይዞት ይሂድ ይባላል። እንዲህ የሚባሉ ሰዎች በተለይ መሪዎች እጅግ ብዙ አይደሉም። በዘመናችን እንዲህ ከተባሉ ሰዎች ውስጥ የቅርቡ ሰው ቢኖር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና በዙርያው ያሉ ታማሚዎች ናቸው።


በተለይ አገር መሪ የነበረ ሰው ጠላቶች ቢኖሩትም እንኳ እንደዚህ በዝተው ሞቱን የሚመኙለት አሟሟቱን የከፋ እንዲሆን በድፍረት የሚናገሩለት መኖራቸው አቡነ ዘበሰማያት ያስብላል። ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ጸጸትና ሀፍረትም ነው። የዚህ ሰው ወዳጅ፣ ዘመድ ወይም ጉዋደኛ መሆን ምን አይነት አሳፋሪ ነገር እንደሚሆን መገመትም አይከብድም። ከዚህ ሰው ጋር ወግኖ በስልጣን ላይ መቀመጥም እጅግ አስፈሪና ራስን ለማጥፋት መትጋት ይመስላል። ስም ደግሞ ተከትሎ ሂያጅ ነውና ወያኔ በእግሩ እንዲቆም ለፍርፋሪ ሲባል የወገኑ ሰዎች ይዞህ ይሂድ ወይም ይዞሽ ይሂድ መባልን ይፈልጉ ከሆነ በያዙት መንገድ መሄዱ ምርጫ ነው። ከዚህ ለዘርማንዘር ከሚተርፍ ውርደት መዳኛው ጊዜ ግን አሁን ነው። የዚህ አይነት ማፈርያ ስልጣን አልፈልግም የማለት አስፈላጊው ጊዜ አሁን ነው።

ይህንን እንድል ያደረገኝ በየድህረገጹ ላይ የመለስ ዜናዊ የደም ካንሰር አጣድፎ ወደሞት አንዲወስደው ብቻ ሳይሆን ዘለዓለማዊ እሳት ውስጥ  እንዲቃጠል የሚመኙለት መብዛታቸው ዘግናኝ ሆኖብኝ ነው። እንዳይሞት የሚፈልጉት ደግሞ እንደዚህ ይላሉ። መለስ የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ማቅቆ ለያዥ ለገናዥ አስቸጋሪ ሆኖ ራሱ ሞቱን እየናፈቀ ሞትም ቶሎ አልወስድ ብሎት ቀስ በቀስ አንዳንድ ሴሎቹን እየገደለበት ለሊት በላብ ተጠምቆ በርሱ ክፋት የሞቱት አንተ ሌባ እያሉ ሲያስጨንቁት እንዲያድር ይሻሉ።  ጣዕረ ሞትም እያላገጠበት፣ አንተንማ አልነካህም ከሞትክ እኮ ቆየህ እያለው እንዲሰቃይ ሲተወው ጥቁር ቀሚሱን እየጎተተ እባክ ውሰደኝ በቃኝ እያለ ሲጮህ እንዲያድር የሚመኙ ወገኖች ብዕራቸውን በድፍረት ሲጠቀሙበት እጅግ ይዘገንናል።  በጣምም አስፈሪ ነው።

ይህን እየተመለከቱ ቀን ዘንበል ሲል በድንጋይ ተወግረው የሚሞቱ ባለስልጣኖችን ማሰብ ይሰቀጥጣል። ከወዲሁ በእጅጉ የሚያስፈራው የነሱ ነገር ነው። በባለሀብትነት ተንሰራፍተው እብሪትን ተሞልተው እንደ ውጭ አገር ወራሪ ቀሪውን ሕዝብ ቁልቁል የተመለከቱ ያከማቹትን ሀብት ዞር ብለው ለመመልከት እንኳን እድል ሳያገኙ ሲጠራረጉ በአይነህሊና ማሰብ ምንኛ አስፈሪ ነው። እነዚህ በዘር ያዋጉት በሀይማኖት ያናከሱት ሰዎች ሕዝቡ ፊቱን አዙሮባቸው ሲያዋክባቸው አይኖቻቸው እየተቁለጨለጩ ማሩን ሲሉ ማሰብ እጅግ አስፈሪ ነው። በግብርና ስም የሀገሪቱን መሬት ለባዕድ ያስቸረቸሩ፣ ያስተባበሉ፣ ብር የበሉ እየታደኑ ወደ እስር ሲወርዱ ማሰብ እጅግ ያስፈራል። የተመኩበት ትምህርታቸው ሳናውቅ አደረግነው ከማይሉበት ደረጃ የአዋቂ አጥፊ ነውና የሚያደርጋቸው ለልጆቻቸው ምን አሳፋሪ ታሪካቸውን ነው የሚተዉላቸው? የባንዳ ልጅ እየተባሉ እንዲወገዙና እንዲሸማቀቁ ማድረግ ምን ያህል ደካማነት ነው። ትምህርታቸውንና እውቀታቸውን ሀገር ለማስፈረስ የተጠቀሙበት ፊታቸው ላይ ምራቅ እየተተፋ ወደ እስር ሲጓዙ ማሰብ በጣም ይሰቀጥጣል። ምክንያቱም አሁን ባለንበት መፈናፈኛ በጠፋበት አደገኛ ሁኔታ ምንም ነገር ሊፈጠር ይችላልና ነው። የሚፈጠረው ነገር ደግሞ አሁን ባለፈው አፈና ከቀጠለ አስፈሪ ነው። በጊዜ ስልጣን አስረክቦ ወደ ሕዝብ ጉያ መግባት ወይም ጥሎ መውጣት አማራጭ የሌለው ዘዴ ነው የሚሉ አሉ። ጭላንጭል ተስፋ ከተገኘ መውጫው ጊዜ አሁን ነው። ሽፍቶቹ እንደሆን ቀን ሲጨልም ገንዘባቸውን ወዳከማቹበት አገር ጥለው መሄዳቸው የታወቀ ነው። የወገነውን ያዳነ አምባገነን በታሪክ የለም። ምክንያቱም ራሱንም ለማዳን አቅም አይኖርውምና። እነዚህ ክብረ ጠል ባለስልጣኖች፣ ወሬ አቀባዮችና አቀባባዮች ወገኖቻችን ናቸውና ለነሱ ይዞአችሁ ይሂድ ከመባል ያድናችሁ ማለት አስፈላጊ ነው።

አንዷ ቀልደኛ ከጓደኞችዋ ጋር ሆና እንዲህ ማለቷን ልዘግብ። “… መልዐከ ሞት” አለች “ የመቶ አለቃ ግርማን ሆድ በቦክስ መትቶ ነብሳቸውን አስተፍቶ ወደ ሰማየ ሰማያት ይከንፍና የእለት እንግዶችን ለማስመዝገብ ተራውን ይጠብቃል። የመጣው ነብስና ቀጠሮ የተያዘለት ነብስ አጠራጣሪ ሆነው ቢገኙም ተረኞቹ መዝገብ ላይ ካመሳከሩ በሁዋላ ጌታን ከመገናኘታቸው በፊት ወደ ገብርዔል ጋ ይወሰዳሉ። ገብርዔል ገና መቶ አለቃን እንዳያቸው ይሄን ማን አምጡት አላችሁ መልሱትና አለቃውን አምጡ ብሎ ነብሳቸው ከሰማይ ወርውሮ የተንጋለለው ስጋቸው ውስጥ ወተፉት። ሰውየው አይናቸውን እንደገለጡ እህል አምጡ ብለው ያማራቸውን የጎድን ጥብስ አቀላጠፉት። የሰሙትን ግን ትንፍሽም አላሉም ከግምገማ በፊት ሰውየው ቢሰናበት ደስ ሳይላቸው አይቀርም ይባላል።” ብላ ስትቀልድ መስማቴ ሰዉ የነሱን ሕመም መዝናኛ ማድረጉ በመሆኑ አስገረመኝ። በዚህ ሰዐት እነሱን ያለመሆን መታደል ነው ብዬ ጌታን አመሰገንኩት።

ወደተነሳሁበት ልመለስና ይህንን ኢትዮጵያን የሚጠላ ጠልቶም ለማፍረስ ወደሁዋላ የማይል ሰውና መሰሎቹን ተከትላችሁ ያላችሁ በጥቅም የታወራችሁ ምስኪን ወገኖቻችን ለቤተሰቦቻችሁና ለልጆቻችሁ ይህንን ያደፈ ታሪክ አታቆዩአቸው። ይዞአችሁ ይሂድ ከሚል የወገን እርግማን ያድናችሁ። ይዞህ/ሽ ይሂድ ከመባል እኛንም ይጠብቀን።

አሜን

ዳኛቸው ቢያድግልኝ

biyadegelgne@hotmail.com

ዳኛቸው ቢያድግልኝ

No comments:

Post a Comment