"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Monday, 9 July 2012

እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን--ከሰንሰለቶቹ በስተጀርባ


እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን--ከሰንሰለቶቹ በስተጀርባ
የአእምሮ ሕሙማኑን ለሁለት ለሁለት እያደረጉ በሰንሰለት አስረው ወደ ፀበሉ ስፍራ ማድረስ የዕለት ተዕለት የማለዳ ሥራቸው ነው፡፡

ለሕሙማኑ ማጠቢያና ምግብ ማብሰያ የሚያገለግለውን ውሃ ከእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከሚገኘው ምንጭ በጀሪካን ለመቅዳት ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ባለው ጊዜ መውጣት ደግሞ ሌላው ኃላፊነታቸው ነው፡፡ ሕሙማኑ ራሳቸውን የማያውቁ ከመሆናቸው የተነሣ በቤተ ክርስቲያኒቷ አካባቢ ከተከራዩላቸው ቤት ውስጥ የተፀዳዱትንና ያበላሹትን መጥረግ፣ ሕሙማኑን ማጠብ እንዲሁም የተበላሹ ልብሶቻቸውን ወንዝ ውስጥ ማንጨፍጨፍ የሥራቸው አካል ነው፡፡

ወደ ፀበል ስፍራ ሲሔዱ በአካባቢው ያገኙትን እንዳይመቱ፣ ከተመለሱ በኋላ ደግሞ በተከራዩላቸው ቤቶች አካባቢ የሚገኙትን ሰዎችም ሆነ እንስሳት እንዳይደበድቡና እንዳይጐዱ መቆጣጠርም ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚኖሩበትን ቤት ግድግዳ እንዳይቆፍሩና እንዳይፈነቅሉ መጠበቅም እንዲሁ፡፡ ያም ሆኖ ግን ዶሮ ጠምዝዞ የሚገጽል፣ እንስሳ የሚያሳድድ፣ ሰው የሚደበድብ፣ የያዙትን መንጥቆ የሚያበላሽ ምግብም ከሆነ የሚበላ ውኃም ሆነ ዘይት ድንገት ቀምቶ የሚጠጣ መኖሩ አልቀረም፡፡ የአእምሮ ሕሙማኑ ይህንን ሁሉ የሚያደርጉት በሰንሰለት ባልታሰሩበት ወቅት ነው፡፡ ለሁለት ለሁለት በመሆን እጅና እጃቸው በሰንሰለት የታሰሩት የአእምሮ ሕሙማን እጃቸው ከሰንሰለቱ ከተፈታ ምድር አትበቃቸውም፡፡ በአንድ በኩል ደስታቸውን በሌላ በኩል ጉልበታቸውን ያሳያሉ፡፡

በመሆኑም እስኪሻላቸውና ራሳቸውን እስኪገዙ ድረስ በሰንሰለት አስሮ ማስቀመጡ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኗል፡፡

በፀበሉ ስፍራ የሚገኙት የአእምሮ ሕሙማን ልብሳቸውን በላያቸው ላይ ያነትቡታል፡፡ መልበስ የማይፈልጉም አሉ፡፡ ራሳቸውንና የመጡበትን የማያውቁ፣ ስማቸውን የማያስታውሱም ይገኙባቸዋል፡፡ ቤተሰብ አምጥቶ ጥሏቸው የጠፋ፣ ቤተሰብ አስቀምጧቸው በረዥም ጊዜ መጥቶ የሚያያቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በራሳቸው መጥተው አድራሻቸውም ሆነ ቤተሰባቸው የማይታወቁ ናቸው፡፡

በሥፍራው በሞት ከተለዩ የአእምሮ ሕሙማን ውስጥ ጠያቂ ያልመጣላቸውም ይገኛሉ፡፡ ጠያቂ ካላቸው ይልቅ አስታዋሽ የሌላቸው፣ ፍጹም ራሳቸውን የማያውቁ፣ ልብሳቸውን ጥለው የሚሔዱና ምግብና አፈርን ለይተው የማይመገቡት ይበልጣሉ፡፡ ሕመሙ ፀንቶባቸው የሚሰቃዩም አሉ፡፡

“ታናሽ ወንድም ነበረኝ፡፡ አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ሲመጣ አእምሮው ታውኮ ነበር፡፡ ስቃዩ አሁንም ይታየኛል፡፡ ኃይለኛ ጉልበት ነበረው፡፡ እኔ፣ እናቴ፣ አባቴና ሌላው ቤተሰብ ቁጭ ብለን እንጠብቀው ነበር፡፡ ምንም ኃይለኛ ቢሆንም መጀመርያ ላይ ለማሰር አልሞከርንም፡፡ እያደር ግን ቤተሰቡን መደብደብና ቤት ማጥፋት ጀመረ፡፡ ጉልበቱም አየለ፡፡ ሕመሙን ያስታግሳሉ የተባሉ መድኃኒቶችን እንዲጠቀም አድርገናል፡፡ ሆኖም ሊሻለው አልቻለም፤ ከኛም አቅም በላይ ሲሆን ከአልጋው ጋር ማሰር ጀመርን፡፡ ታስሮም ግን የሚቻል አልሆነም፡፡ ለስድስት ዓመት ያህል እሱም ተሰቃየ፤ እኛም ተቸገርን፡፡ ሕይወቱ ካለፈ ዓመት ሆኖታል፡፡”

ይህን ያሉን አቶ መለሰ አየለ የአእምሮ ሕሙማንን ማስታመም ምን ያህል ፈተና እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ለእናቶች ከባድና ከማኅበራዊ ሕይወታቸው ሁሉ አግልሎ አካላቸውም ሆነ ሥነ ልቦናቸው እስኪጐዳ ድረስ ከአእምሮ ሕመምተኛ ልጃቸው ጋር ተጣብቀው ቀጣይ ሕይወታቸውን በሰቆቃ የሚገፉ መሆኑን ከእናቱ ተሞክሮ ማየቱ በእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፀበል አካባቢ የሚገኙ የአእምሮ ሕሙማንን በበጎ ፈቃደኝነት እንዲንከባከቡ መነሻ ሆኗቸዋል፡፡

ጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበርን ከጥቂት አባሎች ጋር በመሆን በመመሥረትና በሥራ አስኪያጅነት በመምራት በእንጦጦ ማርያም ፀበል አካባቢ የሚገኙ የአእምሮ ሕሙማንን በበጎ ፈቃደኝነት መንከባከብ ከጀመሩ ከስድስት ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ሕጋዊ ፈቃድ ካገኙ ደግሞ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡

አቶ መለሰ እንደሚሉት፣ በፀበሉ አካባቢ ያሉት የአእምሮ ሕሙማን በአብዛኛው ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተው ሊሻላቸው ያልቻሉ ናቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸው የረሷቸው፣ ለአስታማሚ የሚሰጡትን ገንዘብ ሲያቋርጡ አስታማሚ አውጥቶ የጣላቸው፣ ጎዳና ላይ የነበሩ፣ ረዥም ዓመት ቤተ ክርስቲያኒቷ ደጃፍ የቆዩ፣ ሕመማቸው ብሶባቸው አንደበታቸው የተዘጋም ይገኙባቸዋል፡፡ ማኅበሩ ከሚንከባከባቸው 25 የአእምሮ ሕሙማን ውስጥም አንድም ቤተሰብ ነኝ ብሎ የመጣ የለም፡፡ ባለፈው ዓመት አምስት ሞተውባቸው የቀበሩ ቢሆንም ቤተሰብ ነኝ ብሎ የጠየቀም አንዳች አልተገኘም፡፡

ማኅበሩ ከሚንከባከባቸው ሕሙማን አብዛኞቹ ወንዶች ቢሆኑም በእንክብካቤ ረገድ ሲታይ የሴቶቹን ንጽሕና ለመጠበቅ ከባድና ለየት ያለ እንደሆነ አቶ መለሰ ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳን የማኅበሩ አባላት የተቻላቸውን እያደረጉ ቢገኙም የምግባቸውን ወጪ ለመሸፈን፣ የንጽሕና መጠበቂያዎችን ለመግዛት እየተቸገሩ መምጣታቸውን፣ ውኃ በጀሪካን እየቀዱ የሚያጠራቅሙበት ገንዳ ስለሌላቸውም በየቀኑ ማመላለሱ እንደ ከበዳቸው ይገልጻሉ፡፡

ከአእምሮ ሕሙማኑ መካከል በፀበሉ እንዲሁም ፀበልና ሳይንሳዊ መድኃኒቱን በማጣመር ተፈውሰው ወደ ሥራቸው የተመለሱ መኖራቸውን የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፋሲል አበበ ይገልጻሉ፡፡

ሕሙማኑን ፀበል ከማስጠመቅ ጎን ለጎንም በአማኑኤል ሆስፒታል ሕክምና እንዲያገኙ እንዲሁም ከቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ባገኙት ትብብር መሠረት ከአእምሮ ሕሙማኑ በተጨማሪ ከኤድስ ቫይረስ ጋር የሚኖሩት፣ ሕፃናትና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያን ነፃ ሕክምና እንዲከታተሉ አመቻችተዋል፡፡ ሕሙማኑን ወደ ሆስፒታል ወስዶ መመለስ ግን ፈተና ነው፤ በተለይ መርፌ የሚወጉ ከሆነ ሕሙማኑ በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ይወድቃሉ፤ በዚህ ሰዓት ለሁለትና ሦስት እንኳን በሸክም ማንቀሳቀሱ ከባድ በመሆኑ እነርሱን ወደ ሆስፒታል የሚያመላልሱት ደግሞ የማኅበሩ አባላት የሆኑ ባለታክሲዎች በበጎ ፈቃደኝነት ነው፡፡ ዓላማቸውም የሚንከባከቧቸውን የአእምሮ ሕሙማን በፀበሉና በሳይንሳዊ ዘዴው ተፈውሰው ወደ ሥራቸው የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡

በዓለም ከ360 በላይ ዓይነት የአእምሮ ሕመም እንዳለ የሕክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያ በአእምሮ ሕመም ከሚሰቃዩትም 85 በመቶ ያህሉ የሚሄዱት ወደ ፀበል ሥፍራ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም የአእምሮ ሕሙማንን ወደ ሕክምና ከመውሰድ ይልቅ እንደየእምነቱና ባህሉ ይድናሉ ብለው ወደሚያምኑበት ስፍራ መውሰድን ይመርጣል፡፡

ቀደም ካሉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የአእምሮ ሕሙማንን ወደ ሕክምና የማምጣቱ ግንዛቤ እየጨመረ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል አልሔደም፡፡ በር ዘግቶ አሊያም በሰንሰለት አስሮ ማስቀመጡ በከተማውም ሆነ በገጠሩ ለሚኖረው ኅብረተሰብ የተለመደ አካሔድ ነው፡፡

ሆኖም የአእምሮ ሕሙማን እንደየእምነታቸው በፀበልና በፀሎት የሚድኑበት ሁኔታ ቢኖርም ሳይንሳዊ ዘዴን በመጠቀምና መድኃኒትንም አጣምሮ በማስኬድ ሕሙማኑን ከተዘጉባቸው በሮች ማስወጣት፣ የታሰሩባቸውንም ሰንሰለቶች መበጠስ እንዲሁም የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲሠሩ ማድረግ ይቻላል በማለት የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች አንድ ዕርምጃ ወደፊት ለመሔድ እንቅስቃሴያቸውን ጀምረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ጆን ሆፕኪንስ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል ከአእምሮ ጤና ክብካቤ ማኅበር ጋር በመተባበር በእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ የአእምሮ ሕሙማን ፀበሉንና ሳይንሳዊ መድኃኒቱን አጣምረው እንዲከታተሉ፣ ሕክምናም እንዲያገኙ ለማስቻል መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የአእምሮ ሕሙማንን ለመታደግ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ክብካቤ ስትራቴጂ ነድፏል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ዶክተር ተድላ ወልደጊዮርጊስ እንደሚሉት፣ የአእምሮ ሕሙማንን ለመታደግ የተነደፈው ስትራቴጂ ዋና ዓላማም የአእምሮ ሕሙማን ሕክምና የሚያገኙበት ዕድል ተመቻችቶና ታክመው መልካም ሕይወት የሚመሩበትን ዕድል ለመፍጠር ነው፡፡

በሠለጠነው ዓለም ከሚገኙ የአእምሮ ሕሙማን የሕክምና ክትትል በማድረግ መልካም ሕይወት መምራት የጀመሩ፣ ቤተሰብ የመሠረቱ እንዲሁም ለአገራቸው አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እንደሚገኙ የሚገልጹት ዶክተር ተድላ፣ በኢትዮጵያም የሚገኙ የአእምሮ ሕሙማንን በማከም ሕይወታቸውን መለወጥ ይቻላል ይላሉ፡፡

ዓለም የተሻሻሉ መድኃኒቶችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝና ኢትዮጵያም የዕድሉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩንም ያክላሉ፡፡

በስትራቴጂክ እቅዱ እንደሰፈረው በኢትዮጵያ የአእምሮ ሕክምናን ለማስፋፋት እስከ ጤና ኬላ ድረስ ወርዶ ለመሥራት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል፡፡ የአእምሮ ጤና ሕክምና ትምህርት ማስፋፋትን አስመልክቶም እንዲሁ፡፡

በሚኒስቴሩ የተነደፈው ስትራቴጂ ተፈጻሚ የሚሆነውም የእምነት ተቋማት፣ የባህል ሐኪሞች፣ የታማሚ ቤተሰቦችና የሚመለከታቸው አካላት በመቀናጀት  የአእምሮ ሕመምን እንደማንኛውም ሕመም ሊታከም የሚችል መሆኑን አምነው በየቤቱ የተደበቁ፣ በር የተዘጋባቸውንና በሰንሰለት የታሰሩትን ማውጣት ሲችሉ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በሕይወት ዘመን ውስጥ ከሚከሠቱት የጤና ችግሮች ጫና ውስጥ 13 በመቶ የሚሆነው ከአእምሮ ጤና ሁኔታዎች ጋር ይያያዛል፡፡ በኢትዮጵያ የአእምሮ ሕመም ተላላፊ ካልሆነ በሽታዎች ውስጥ ከፍተኛ ጫና በማድረስ ይታወቃል፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች የአእምሮ ሕመም የመዘንጋት በሽታና ጭንቀትን ጨምሮ 11 በመቶ ከአጠቃላይ የበሽታ ጫናዎች እንደሚይዝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ኤችአይቪ ኤድስ ከሚያደርሰው ጫና እንደማይተናነስ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የአእምሮ ጤና ችግር በኢትዮጵያ በስፋት የሚገኝ ሲሆን በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሕመም፣ የአካል መጓደልና ሞትን ያስከትላል፡፡ በዚህም የተነሣ የምእት ዓመቱ የልማት ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ ላይ ያልታወቁ ተጽእኖዎች በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡

በአእምሮ ጤና ዙርያ ሕክምና የሚሰጡት ተቋማት ቢኖሩትም ከግንዛቤ ማነስ የተነሣ ኅብረተሰቡ በነዚህ ተቋማት የመገልገል ልምዱ አነስተኛ ነው፡፡ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ከአስሩ አንዱ ብቻ ወደ ሕክምና ተቋማት መጥቶ አገልግሎት ያገኛል፡፡ ስለሆነም የአእምሮ ጤና አገልግሎት ለማስፋፋትና የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለማሳደግ የተጠናከረ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ ነው፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተነደፈው አዲሱ የአእምሮ ጤና ስትራቴጂ ይህን ችግር ለመቅረፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚጫወት ይጠበቃል፡፡
Posted by MINILIK SALSAWI at 08:46

No comments:

Post a Comment