"Food is nothing without freedom! We Need Freedom
”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!
Friday, 13 July 2012
እግዜር ኢህአዴግ ቢሆን ኖሮ የአቶ መለስን መያዝ አስመልክቶ የሚሰጠው መግለጫ
ከአቤ ቶኪቻው
ዛሬ አዲሳባ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የምትወጣ ስለ አቶ መለስ መጥፋት አበክራ የምትጠይቅ እና የምትጨነቅ አንድ ጨዋታ አለችኝ። ለዝች ብሎግ አንባቢዎች ነገ ትለጠፋለች። እስከዛ ይቺን መቆያ እንኩማ፤
ያው ሁላችንም እንደሰማነው አቶ መለስ ተይዘዋል። ስንቱን ሲይዙ የነበሩት ሰውዬ አሁን ግን ራሳቸው በእግዜሩ በሽታ ተይዘዋል። በህመማቸው ሳቢያም ፓርላማው እንኳ ይኸው የ2005 ዓ.ም በጀቱን እስካሁን አላፀደቀም።
እኔ የምለው ግን በቃ አቶ መለስ ከሌሉ ሁሉም ነገር አለቀለት ማለት ነው? የምር ይሄ ነገር በጣም ያሳስባል።
ልክ እንደ አቶ መለስ ሆኖ የሚጫወት “ካስት” እንዴት አይኖርም!? እሳቸው ስለታመሙ እከሌ ወይም እከሊት እንደ አቶ መለስ ሆነው ይጫወቱልናል! መባል የለበትም እንዴ!? የቡድን ስራ ምናምን የሚባል ነገር የለም ማለት ነው…? አይበልባቸውና የሆነ ነገር ቢሆኑ ታድያ ምን ሊውጠን ነው!
ለማንኛውም ይቺን ያኽል ከተንደረደርን ወደ ፉገራችን እንግባ፤
እንግዲህ ይህ ዘገባ የሚተላለፍላችሁ በእግዜር ቁጥጥር ስር በሚገኘው ቴሌቪዥን ነው አሉ። በእግዜር ቁጥጥር ስር የሚገኝ ቴሌቪዥን የቱ ነው? ካሉኝ ህልም መሆኑን እገልፃለሁ። የምር ግን እግዜር ህልምን ያህል ቴሌቪዥን በእያንዳንዳችን ላይ ገጥሞ ሳለ ለገዛ ፕሮፖጋንዳው መጠቀም ሲችል በነፃነት የፈለገንን እንድናይ ማድርጉ ምን ያህል ዲሞክራት ቢሆን ነው ብለው አይደነቁም! በእውነቱ እንደ እግዜር አይነት ነፃነት የሚሰጠንን መንግስት ያምጣልን! እንደርሱ እንኳ የትም አይገኝም ግን ቢያንስ የሚቀራረብ…
ለማንኛውም እግዜር ኢህአዴግ አይደለም እንጂ ቢሆን ኖሮ የአቶ መለስን መያዝ አስመልክቶ በቴሌቪዥኑ እንዲህ ይል ነበር፤ ብለን ብንገምት ምን ይለናል!? በነገራችን ላይ ይህ ዜና ቃል በቃል ከዚህ በፊት እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ አንዳለም አራጌ፣ እነ ውብሸት እና ርዮት የተያዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያነበበልን ነው። ልዩነቱ እነ አስክንድርን የያዛቸው ፖሊስ ነው አቶ መለስን ደግሞ በሽታ ነው፤
አባቴ በህመም አይቀለድም ይለኝ ነበር። ነገር ግን በላዬ ላይ ያደረው በል ብሎኛልና እንደሚከተለው እጀምራለሁ፤ አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ። እርስዎም ሲጀምሩ እግዜሩ ይቅር ይበልህ ብለው ከጀምሩልኝ ችግር የለውም!
ገመትን፤
አቶ መለስ ዜናዊ ራሱን ኢህአዴግ ብሎ ከሚጠራ አሸባሪ ድርጅት ጋር የህዝብን መሰረተ አንድነት እና የሀይማኖት አውታሮችን ለማፈራረስ ሲንቀሳቀሱ በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በፌደራል በሽታ እና ፀረ ሽብር ወቅስፈት ግብረ አይል በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ግለሰቡ በውጪ ሀገር የሚንቀሳቀሰው ቻይና ኮሚኒስት የተባለ አፋኝ ድርጅት የሀገር ውስጥ አደራጅ፣ ቀስቃሽ እና አንቀሳቃሽ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ስልጣንን ሽፋን በማድረግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አክራሪነት እንዲስፋፋ፣ አንድ ለአምስት የሚል ህዋስ በመፍጠር በመላው ሃገሪቱ መረብ ዘርግተው ሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሽብር ጥፋት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ታውቋል።
ተጠርጣሪው ግለሰብ በልማት ስም ሰላማዊ የሀይማኖት ሰዎችን ከፀሎት ስፍራቸው በማፈናቀል እንዲሁም ህገ መንግስቱን ሽፋን በማድረግ በርካታ ሙስሊሞችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ሲፈፅሙ እንደነበር ፌደራል በሽታ እና ፀረ ሽብር ወቅስፈት ቡድን አረጋግጧል።
ተከሳሹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ህመሞቹ የመያዣ ፈቃድ እንዳሳዩዋቸው እና በአሁኑ ሰዓት በተኙበት ቦታ የተለያዩ በሽታዎች በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች ማግኘት ያለባቸውን ተገቢ እንክብካቤ እያደረጉለት መሆኑን ተጠርጣሪው ራሳቸው አረጋግጠዋል!
አቶ መለስ ዜናዊ በአሁኑ ሰዓት የተያዙ ሰዎች መብት እንዲያገኙ መደረጉን ለማረጋገጥ የተለያዩ ጎብኚዎች እንዲመለከቷቸው ተፈቀዷል። ጎብኚዎቹም ተጠርጣሪው እንደፈለጉ ማቃሰት እና የሚያስፈልጋቸውን ነገርም ያለ አንዳች ገደብ ሲጠይቁ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የተጠርጣሪው ግለሰብ ፍርድ ነፃ እና ገለልተኛ በሆነው መንግስተ ሰማያት መታየት የተጀመረ ሲሆን ጥፋታቸውን አምነው እና ተፀፅተው ይቅርታ ከጠየቁ ምህረት ሊደረግላቸው እንደሚችል ተያይዞ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
በድጋሚ ይቅር ይበለን ዜናው አበቃ!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment