"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday 31 May 2012

ጨዋታ ወፖለቲካ፡- ‘አንተ’ታ እና ‘አንቱ’ታ!


ጨዋታ ወፖለቲካ፡- ‘አንተ’ታ እና ‘አንቱ’ታ!




SHARE THIS
TAGS
Share in top social networks!


ጨዋታ ወፖለቲካ፡- ‘አንተ’ታ እና ‘አንቱ’ታ!

(ሰሎሞን ተ ጂ. /ከአ.አ.) semnaworeq.blogspot.com
ይሄንንስ መቼም እነግራችኋለሁ፡፡ “ወሰድ ያደርግሃል እንዴ?” አይለኝ መሰላችሁ፡፡ መድኃኔዓለም ይውሰደውና፡፡….አርባ-አራቱ ታቦት ይውሰዱትና! ምናባቱንስና ደግሞ እሱ ብሎ ባለ ዲግሪ!….እኔማ ልክልኩን ነገርኩት፡፡ “አሁን አንተ የማስተማር ዲግሪ ምናምን አለኝ እንዴት ትላለህ?” አልኩት፡፡ ልብ-ልቡን አሳጣሁት፡፡ “እኔ በግሌ ዲግሪህን ነጥቄሃለሁ!” አልኩና ቁርጡን ነገርኩት፡፡ አሃሃሃሃ…..!!! ጭራ ሲያበቅል አየሁት፡፡ “… ስማ መልስልኝ፣ ምናምን እንዳትለኝ፡፡ ስማ! እኔ በግሌ ነው – ነጠቅኩህ – ያልኩህ፤” አልኩት፡፡ ይሄንንም መቼውንም እነግራችኋለሁ፡፡…..
“ወይ አሳምነኝ! ወይ ደግሞ እመነኝ!….ሁለቱንም ወዶ – ለሁለቱም አብዶ፣ ለሁለቱም ሰግዶ፣  አይቻልም መቀመጥ! አንዱን ምረጥ!” አልኩት፡፡ ሊሰማኝ ነው፡፡ አሻፈረኝ አለ! እንቢኝ አለ!….. እንደሱ ያለ ልብ አውልቅ ገጥሞኝም አያውቅ!…. ሰዉ ግን ምን ነክቶታል-ጃል! ባሰቀመጡት ቦታ አልገኝም አለሳ፡፡….ባለፈው ሰሞን፣ “እርሳቸው ታላቅ አፍሪካዊ መሪ ናቸው! ባለራእይ ናቸው፡፡” ምናምን እያለ ሲደሰኩርና ሲነዘንዘኝ ሰንብቶ፣ ድንገት ሰውዬው አምልጦት ይሁን አዳልጦት “መጀመሪያም የችሎታ ማነስ እንዳለባቸው እያወቅን ነው ያቆየናቸው፡፡ ገለመሌ” ሲል ጊዜ ወባ እንደያዘው ሰው ምን አንዘፈዘፈው? ድንገት በጠፍ-ጨረቃ ተነስቶ፣ “እርሱን ተወው ባክህ!” ይለኛል እንዴ? መጀመሪያውንስ፣ “አፍሪካዊ ታላቅ መሪ ናቸው! ባለራእይ ናቸው፡፡” እያለ ምን አንጫጫው! ሰውየው ሃዋርያው ዮሐንስን የሆነ መስሎት ነው ወይስ ዮሐንስ ባለረሰዕዩን? የአንዳንድ ጭፍን ቲፎዞዎች ነገር ግን ያስተዛዝባል፡፡ ማታ የቅዱሳን ማህበር አባል የደረጓቸውን ሰዎች፣ በጠዋት ተነስተው የዲያቢሎስ ካቢኔ አባል ለምን ያደርገዋቸዋል? (እኔ እምለው ግን፣ ሰዉ ምን ነክቶታል-ጃል!)……..
“አቶ መለስንና የስራ ባልደረቦቹን ለምንድነው አንተ እያልክ የምታወራው?” አልኩት፡፡ “ከመቼ ወዲህ ነው “እሱ ሰውዬ” እያልክ መዘርጠጥ የጀመርከው ደግሞ?” አለኩት፡፡ ምንም ሳያመነታ፣ “ካለፈው የፓረላማ ንግግሩ ወዲህ ነው፡፡” አለኝ – ፍርጥም ብሎ፡፡ “እኮ ምን ተገኘ?…እኔ “እርሱ” እያልኩ ሳወራ፣ እንደዚያ ትንቀጠቀጥ የነበርከው ሰውዬ፣ በምን ምክንያት ነው “አንቱታህን” የገፈፍከው?” ስል አበክሬ ጠየቅኩት፡፡ እንዲህ አለኝ መምህሩ ወዳጄ፣ “ያኔማ…በካድሬነቴ ወይ ክፈለ-ከተማ፣ ወይ ደግሞ የአንድ ወረዳ ካቢኔ አባልነት፣ በእርሱ የሊቀመንበርነት ዘመን እመረጣለሁ ብዬ….” መጨረስ አቃተው፡፡ እንባ አነቀው፡፡ “…..አድጋለሁ፣ ከመምህርነት ወጥቼ ሹም እሆናለሁ፤ ይሄንን መከረኛ ህዝብ አጉላላዋለሁ/ እጅ መንሻና ኮንዶሚኒየምም አገኛለሁ፤” እያለ ሲያሰላ ኖሮ፣ ድንገት ይሄ አሳረኛ የደሞዝ ጭማሪ ነው፣ የእርከን ማስተካከያ ያሉት ነገር መጣና ያለ ምንም ደብዳቤ፣ ትምህርት ቤቱ ውስጥ በተለጠፈ ቁጥር ያለጨበጠ መናኛ ማስታወቂያ ተባረረ፡፡ “ችሎታ ያነሳቸው” መምህራን ዝርዝር ውስጥ ስሙ ገባ ፡፡ ለዚህም ነበር፣ አቶ መለስንና ባለደረቦቹን “አንተ” እያለ ያንጓጠጣቸው፡፡…..የሰጠኝም ምክንያት ስላላሰመነኝ ነበር፣ አንተ መለስንና ጓደኞቹን ያለ አጥጋቢ ምክንያት “አንቱታ” ከነጠቅካቸው፣ እኔም “ዲግሪህን ነጥቄኃለሁ” ያልኩት፡፡
የኋላ-ኋላ ግን አድራጎቴ ከንክኖኛል፡፡…ያ ወዳጄ፣ “ራሱን ቤቱ ወስጥ ሰቅሎ ተገኘ!” የሚል ወሬ የደረሰኝ እለት የተነጋገርነውን ሁሉ ምነው ባላልኩኝ ብዬ ተብሰከሰክኩ፡፡ “…የማስተማር ችሎታ አንሶሃል” ሲባል ጊዜ፣ ራሴንም የመስቀል ችሎታ አለኝ ብሎ…..ለዘላለሙ ነጎደ! (“መድኃኔ ዓለም ይውሰድህና!” ያልኩትን እርግማን ሰምቶኝ ይሆን እንዴ-መድኃኔ ዓለም? ምን እኮ የእርሱ ነገር አይታወቅ! ሁሉም ነገሩ ጆሮ ይሆን-ይሆናል!)…እኔ ልንጎድልህ! እኔ ላርግልህ! እኔ ለመንጠቅልህ!….. “ዲግሪህን ባልነጠቅኩህ ኖሮ ምን ነበረበት!…..” ብያለሁ፡፡ ተንገብግቤያለሁ፡፡ …ባታውቁም-እወቁልኝ፡፡
                              *************************
በድጋሚ የምለው፤ ከያኒ (artist) እና ፖለቲከኛ አንቱ አይገባም ያለው ማን ነበር? ጉድ! ጉድ! ጉድ! ሳልሰማ ቀርቼ፡፡ ነገሩስ ለካ ቡሬ ነው – ቡራቡሬ፡፡ ሲፈልጉ “አንተ!” አለዚያም “አንቱ!” መባባል ልክ እንደጥሬ፡፡…..ዘፋኞቹን እንደሆን አንዴም “አንቱ!” ሲሏቸው አልሰማም እሳ? ጥላሁንንና ሙሃመድን፣ አሊ ቢራንና ብዙሽ በቀለን የሚያካክሉ ድምፃውያን፤ በዚያ ላይ፣ ሁሉም ከስልሳ አምስት አመት በላይ ነው እድሜያቸው፡፡ ታዲያን “አንተ!”፣ “አንቺ!” እየልን ለምንድነው የምንዘረጥጣቸው፡፡ (ይሄማ እውቅ ነው፡፡ ባህላዊም ነው፡፡ “ዘፋኝ ነን! ድምፃዊ ነን!” ምናምን፣ ቢሉም ያው አዝማሪዎች ናቸዋ፡፡ ዘመናዊ፣ “አባውዴዎች!” ዘመናዊ፣ “ሃሚናዎች!” አይደሉ እንዴ! የምን ማስተባበል ነው! ማሲንቆ ካልገዘገዙ አዝማሪነት የለም ያለው ማነው? ማነው?! ኧረ ማነው?!)
ባለፈው እንኳን ጋዜጠኛና ደራሲ ስብሃት ሲሞት፣ ሚዲያው ሁሉ “አንተ! አንተ!” እያለ  አልዘረጠጠውም፡፡ (የሰማኋቸውማ ጊዜ ክው ብዬ ደነገጥኩ፡፡) “ሰው እንዴት በ78 አመቱ አንቱታ ይነፈገዋል!” ስልም ጦፍኩኝ፡፡ ኧረ! በዚያው ሰሞን ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ሲሞቱ፣ ይሄ ዘባራቂ ሚዲያ ሁሉ፣ “አንቱ! አንቱ!” አላላቸው መሰላችሁ፡፡ ለምን ይሆን?      (አታውቁም እንዴ! ጋሽ ማሞ’ኮ ስብሃትን በሁለት አመት ይበልጡታል፡፡) ስብሃት ግን ክብሩን በገዛ እጁ አልጠብቅም ብሎ፣ “የተከበሩ አቶ ስብሃት! የተወደዱትና ተናፋቂው የወሲንና የመኝታ-ቤት ሚስጢሮች ፀሐፊው! ውድ ስባኃታችን” ሊባል ይችል የነበረው ሰውዬ-ትልቁ ዳቦ….ምናምን ሆነ፡፡ ምን ያደርጋል፤ ስብሃት ሆዬ! በኔ-ብጤው አበሻ ዓይን፣ “ተወዳጁ ክብረ-ቢስ” ሆነ፡፡
የሆነስ ሆነና፣ ሚዲያው ሁሉ፣ አፈወርቅ ተክሌን ለምንድን ነው ከከያኔያን ሁሉ ተለይተው “አንቱ” የተባሉት? (ይሄንንም አታውቁም ለካ? ስታሳዝኑ! ስማቸውና ስራቸው ከብዶ፣ የከባዶች ከባድ፣ ባለ ዘጠና-ዘጠኝ ሜደሊያ ሆነውብን እኮ ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ የፒያሳ አራዶች፣ ሰውዬውን-አፈወርቅ “አካብዴ” ነበሩ ይላሉ፡፡ እንደስብሃት “ጋሽ አፈወርቅ” ተብለው፣ በፌስታል ቅራቅንቦ ቀርቅበው አይዞሩም ነበር-አሉ፡፡ ኧረ! እንዴት ሆኖ! ሲያልፍም አይነካካቸውም ነበር፡፡ ባይሆን እንኳን ይሄንን ልጠይቃችሁ እስቲ፡፡ አንቱታም በማዳላት ሆነ እንዴ? ወይስ በማስፈራራት ነው? ኧረ እኔ እንጃ! የዚህን ሚስጥር፣ ያ የጠቢቦች ጠቢብ የገለጠላቸው ካሉ ቢነግሩን ይሻላል፡፡
አፄ ቴዎድሮስን፣ አፄ ዮሐንስን፣ አጤ ሚኒሊክንና ጃንሆይ-ቀ.ኃ.ሥን “አንቱ” ስንል ኖረን፣ ልጅ እያሱንና ኮሎሌል መንግስቱን “አንተ” እያልን መዘርጠጣችንስ ለምን ይሆን? (አታውቁም እንዴ ለካ?! ዘውድ ስላልጫኑ ነዋ! ….ዘውድ ያልጫነውን ሁሉ “አንተ” ማለት ከተቻለማ፣ ከስልጣን ሳይወርዱ በፊት ይሁና፡፡)….ያንን ዳሪዎስ ሞዲን ግን ታዘብነው፡፡ በግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ቀትር ላይ፣ “የደርጉ ሊቀመንበር፣ የኢህዲሪ ፕሬዚዳንትየነበረው፣ መንግስቱ ኃይለማርያም አገር ጥሎ ፈረጠጠ” ብሎ አነበበ፡፡ ያንን ሁሉ ዘመን፣ “ጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ ሃይለማሪያም፣ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የኢሰፓኮ ዋና ፀሀፊና… ምንትስ!” እያለ ሲያነበንብ ኖሮ፣ ከመቅፅበት ዝርጠጣ ማካሄድ ይቻላልና?!
ዳሬዎስማ በ1984 ዓ.ም ሲጠየቅ – ተኩራራ፡፡ መንግስቱን፣ “አንተ አይደለም አንቺም አለማለቴ እኔ ሆኜ ነው” አለን፡፡ ያልገቡኝ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ ዳሪዎስ ሆይ፣ “ጓድ መንግስቱን አንዴ ፈረጠጠ አንዴ ኮበለለ ማለትህ ሳያንስ፣ “አንቺ” ለማለት የዳዳህ ለምን ይሆን?” “ይሄማ ዕውቅ ነው፤ መንጌ (ቾምቤ) ቦቅቧቃ ፈሪ ስለሆነች ነዋ!” ይለን ይሆናል እኮ ይህኔ! ቾምቤ፣ ሰዎቹ ጀማ ወንዝን ተሸገሩ የሚል ወሬ ሲደረሳት ጊዜ ላጥ አለች! (ይህንንም እነግራችኋለሁ፡፡ በበኩሌ፣ መንጌን “አንቺ መንግስቱ!” ብያታለሁ፡፡ ለምን ብትሉ፣ ለ“አንተ”ነትም አልበቃችምና ነዋ!) ዳሪዎስ ሆይ፣ ሁለተኛው ያልገባኝ ነገር ምን መሰለህ፤ እርግጥ ፈረጠጠ የሚለውን ዜና ወይም መግለጫ እራስህ ነበርክ እንዴ የፃፍከው? እኔ አይደለም፤ ተደርጎም አይታወቅምም፡፡ ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢ.ዜ.አ (የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት) መቼም ቢሆን ይህቺን አኩሪ ገድሉን አሳልፎ ለማንም ጋዜጠኛ እንደማይሰጣት እናውቃለን፡፡ (ዳሪዎስ ሆይ፣ የደርግን ዝብዝብ የማያውቁትን “ቱሪስቶች እንክት አድርገህ ብላቸው!”….እኛማ የሳንሱሯንም ሆነ የሰሞኗን የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ዳርዳርታ ነቅተንባታል፡፡….ጥርሳችንን ነቅለንባታል!…. የደንቧንና የአሰራሯን ሁኔታ ነቄ ነን!…)
“አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስከሚቀር ወደ ፊት!” እያለች ስታስቦካን ቆይታ፣ ቾንቤ ሆዬ ሾለከች! አጃቢዎቿን እነውብሸት አደራን አስከትላ እግሬ አውጭኝ አለች፡፡ (አሁን ታዲያ የምን “ትግላችን፤ ምንትሳችን” እያሉ ማለባበስ ነው፡፡ መንጋ ፍርሃት በልብ ጭኖ እየኖሩ – ፉከራ፤ ለጉራ ካልሆነ ምን ፋይዳ አለው! (እያረሩ እንደመሳቅ ነው – መቼም፡፡) መንግስቱ ሆይ፣ “ቅጽ ሁለትም ይቀጥላል…” ያልሺውን መጣፍሺን እርሺው፡፡ ለነገሩ ባትረሺውም-ግድ የለም፡፡ (ግድ የለም! ግድ የለም! ግድ የለም! ግድ የለም! ሰው እንዳይሆነው የለም!) ማለቴ፣ ኢህአፓዎች በስካነር አማካኝነት ብሽሽትሽን ብለው ይጥሉሻል፡፡ ነግሬሻለሁ….ሁለቱም ኢህአፓዎች ላነቺ ሲሆን አንድ ናቸው፡፡
የአሴይ ልጅ ዳዊት፣ “ክብር ለሚገባው ክብርን ስጥ!” ብሏል፡፡…. ክብር የሚባው ታዲያ የሚያከብር ከሆነ ነው፡፡ በየፓርላማው ላይ፣ ጣይ ላጣይና በየአደባባዩ ህዝብን የሚያንጓጥጠውን እና የሚዘልፈውን ግን፣ ክብር አይገባውምና-አናከብረውም፡፡ ለምን ብለን፡፡ በየታክሲውና በየታክሲ ተራው የሚገላምጡንን ወያላዎችና ተራ አስከባሪዎች በግድ ልናከብራቸው አንችልም፡፡ “ክብር ለሚገባውና ክብር ለሚገባው” እንጂ ለማንም አጉራህ-ዘለል ክብርን የሚያህል ፅላት አናሸክምም፡፡ (ክብር የሚሸከሙበት ራስና አንገትም የላቸውማ! ምን እናርጋቸው ታዲያ!…)
ኧረ ለመሆኑ፣ የዛሬዎቹን ፖለቲከኞች፣ ማለቴ ገዢዎቻችንን፣ ሚዲያው “አንቱ” የሚላቸው ከልቡ ነውዴ?! እንጃ! እንጃ! ኧረ እኔ እንጃለት!……..እኛስ ብንሆን፣ ከፕሬዚዳንቱ በስተቀር ሌሎቹን ሁሉ የምንዘረጥጣቸው ለምንድነው? የዚህንማ መልስ ማንም ያውቀዋል፡፡ ድሮውንስ ቢሆን ሽፍታን ማን “አንቱ” ብሎት ያውቃል?! እኔስ ያልሸፈቱትን ፕሬዝዳንት አከብራለሁ፡፡ ከልቤም አከብራቸዋለሁ፡፡ “አንቱ ሆዬ! አንቱዬ!” እላቸዋለሁ፡፡ “ኧረ ከሱ’ሳ! ኧረ ወፋፈሩ! ሰሞኑን ደግሞ ትንሽ ወዛዙ እሳ – ምን ተገኘ!’’ እላቸዋለሁ::
        *************************
ይሄን ሰሞን “ፕሬዝዳንት እከሌ ሞቱ! የእከሌም አገር ፕረዝዳንት ሞቱ!” የሚል ሟርትና ወሬ፣ ብሎም አሉባልታ ለምን በዛ? …. ያ ሞገደኛ ጋዳፊ (ቀጣፊ)…እየጠራቸው ይሆናላ፡፡ እርሱ እንደሆን፣ ያኔ ትሪፖሊም ላይ የነበረ ጊዜ፣ ጥሪና ግብዣ ይወድ ነበር፡፡ (ሲፈልግ ከዳርፉር፣ ሲፈልግም ከኤርትራ፣ ኧረ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮችም ቅጥረኞችን ጋብዞ ነበር፡፡ ሄዱለታ፡፡ ይሞታል እንዴ-ሳይንፈራገጡ፡፡ “ሞት ላይቀር ማንቋረር” አይቀሬ ነውና፡፡) ሊቢያ ላይ እንደለመደው ጀነትም ሄዶ እያወከ ይሆናል እኮ ይህኔ፡፡ እዚህም ሳለ፣ እኔ ካልታጀብኩ፤ “ህብረት ነው?….የለም! አንድነት ነው?…የለም!” ብሎ ማስቸገር ይወድ ነበር፡፡ (ውድ ጋዳፊ ሆይ፣ ፕሬዚዳንት አልሳላህንና ሙባረክን ለምን ታስቸግራቸዋለህ? እንደ’ኔ ለምን ሳይገደሉ ወንበራቸውን ለቀቁ ብለህ፣ ቀንተህባቸውም ነው አይደል?! (መቼ አጣነው! መች ዓጣናት ይችን-ይቺን የአህዮ ጠባይ!)
ጋዳፊ ሆይ፣ ስማኝ! ምንም ያላስቸገረውን ሆስኒ ሙባረክን፣ አጎበር ላይ አጋድመህ ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ከምታሳቀቅው፣ በተለመደው ድፍረትህ በሽር አላሳአድን ጥራው፡፡ ሶሪያን ገላግለው፡፡ የባህሬንንም ንጉስ ወደ ሄድክበት አገር ጋብዘው፡፡ አንተ ከጠራሃቸው ስልጣናቸውን ለቀው ለመምጣት አያመነቱምና ጋደፊዬ ሆይ፣ በርትተህ ጥራቸው፡፡ አንዳንዱቹንም ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ የግብዣ ወረቀት ላክላቸው፡፡ አንተ ከጠርራኸው መቼም የማይመጣ የለም፡፡ ቶኒ  ብሌር እንኳን ተሯሩጦ መጥቶ አልነበር! እባክህን የኔ ቀጣፊ፣ የአፍሪካንም ጠቅላዮች በሙሉ ወደ ሰማያዊቷ ሲርጥ ጥራቸው፡፡ (ሰማያዊት እየሩሳሌም ካለች፣ ሰማያዊት ሲርጥስ ለምን አትኖር?!….መኖርም አለባት፤ ወዳ ነው፡፡)
*************************
ወደ “አንተ”ታ እና “አንቱ”ታ እንመለስ! ሚዲያውን ስሰማ “አቶ መለስ፣ አቶ አባዱላ፣. አቶ ኩማና አቶ ሃይለማርያም…” ምናምን ሲል  ተሳስቶ ወይም እንደዚያ የተባረረ መምህር፣ “ይሄ መለስ! ይሄ ኩማ!” እንዳይልብን፣ እንዳይዘባርቅና እንዳያዘበራርቅብን እንፈልጋለን?! እነዚህን የተከበሩ ሹማምንት የዘረጠጠ መስሎት፣ ወንበራቸውን እንዳይዘረጥጥም ያስፈራል፡፡ (“ካልዋሹ አይነግሱም!”-ያለው ማን ነበር? ማን ነበር? የምታውቁ ካላችሁ ሚስ-ኮል አድርጉልኝ፡፡ እነግራችኋለሁ፤ ባልደውልም-እደውልላችኋለሁ፡፡ እንደመታውቁት ብዬ ልጀምር (ታወቃላችሁና)፣ ካልዋሹ የማይነግሱትማ አንባገነኖችና በጥባጮች ናቸው፡፡ አይደል እንዴ?)
“ካፍ የወጣ ቃልና፣ ከእጅ የወደቀ እንቁላል” አንድ ናቸውና፤ ይሄ ዘባርቄ ሚዲያ፣ እንደልማዱ የሰዎቹን ክብር እንዳይሰባብር ይጠንቀቅ! በተለይ-በተለይ የመንግስት ሚዲያ ጋዜጠኞች በጣም “ምጥንቃቅ” ማድረግ አለባቸው፡፡ መቼም ወደውና ፈቅደው ሳይሆን ኢ.ዜ.አ ጽፎ የሰጣቸውን እንደሚያንበለብሉ እናውቃለን፡፡ ከእስፖርትና ከዘፈን ምርጫ በስተቀር ኢ.ዜ.አ. ወይም አለቆቻቸው “ልማታዊ ወሬ” እየቆነጠሩ እንደሚሰጧቸው እናውቃለን፡፡ (እንኳን ይችን፣….ሌላም-ሌላም እናውቃለን! የዝንብ ሸውራራ፣ የንብ መላጣም ሳይቀር አሳምረን እናውቃለን፡፡)
እኔ በበኩሌ፣ አንዴ “አንቱ” አንዴ “አንተ” እያልኩ አልዘላብድም፡፡ ሁሉንም “አንተ” ነው የምል፡፡ ለምን ብትሉ፣ ፖለቲከኛና ከያኔ የሕዝብ (public figures) ናቸውና፡፡ ፖለቲካንና ኪነትን የሚነካካ ቄስና ሼካም ካለ እንደዚያው፡፡ ለምን ጳጳስ ወይም ኢማም አይሆንም፡፡ ቀዩዋን መስመር ከረገጠ፣ “አንተ እከሌ” ነው የምለው፡፡ ካልሞቱ በስተቀር አንተ ነው የምላቸው፡፡ (ክብር ለሰማዕታት ይገባል ብዬ ስለማምን ነው-ሙታኑን አንቱ የምለው፡፡ ) የፈለገው ይምጣ፡፡ “ዘላለም ከመፍሳት፣ አንድ ቀን …ምን ማለት ይሻላል” ነበር ያለው - ያ መንግስቱ ኃይለማርያም፡፡ (ሳይሆን አይቀርም፡፡)
ባለጊዜዎች ሆይ፣ እኛ ግን ባሕሉን ተከትለን እንጠራችኋለን፡፡ አንዘላብድም፡፡ አድርባዮችም አንሆን፡፡ ለምን ብለን፡፡ እንደወጉ እንደባሕሉ እንጠራችኋለን፡፡ ኦሮሞዎቹን፣ “ኢልማ ደበሌ!… ኢልማ ደመቅሳ!…ኢልማ ገመዳ! ወይም ኢልማ ሳዶ!” እያልን እንጠራቸዋለን፡፡ የትግራዮቹንና የኤርትራዎቹንም ሰዎች ቢሆን፣ “ወዲ ዜናዊ! ወዲ አፈወርቂ! ወዲ በርሄ! ወዲ ፀሐዬ!” እያልን እንጠራቸዋለን፡፡ ማናባቱ ይከለክለናል?! እንዴት የትግራይንና የኤርትራን ሰዎች ጎን ለጎን ትጠራለህ ብሎ ማናባቱ ይከለክለናል፡፡ “ወዲ”ዎቹ ተጣሉ እንጂ፣ ባህሉ አልተጣላ!…. የአማርኛ ተናጋጋሪዎቹንና ደቡቦቹን ግን “የእገሌ ልጅ! የእከሊት ልጅ!” ለማለት አይስማማም፡፡ ለአንደበት ይቀፋል፡፡ ለምን ቢሉ ፣ ባህሉና ቋንቋው ወዶና ፈቅዶ አልሰጠንማ፡፡ በግልባጩ ግን፣ “የኑኑ አባት! የኑኑ እናት!” እያሉ ለመጠራራት ያስችላል፡፡
ሰሞኑን ወዲ ዜናዊ አልቃይዳዎቹንና ቅዱሳኖቹን አስፈራራቸው፡፡ እሰይ! እንኳን አስፈራራቸው፡፡ መጀመሪያውንስ፣ ሙሴ አስሩን ነገር ድፎ  የሰጣቸው ጊዜ፣ የመጀመሪያው ቃል፣ “ከኔ ሌላ ማንም አምላክ አይሁርህ፡፡ ምድራዊም ቢሆን!” አልነበር ያለው? ምን ይሄ ብቻ፤ “እኔ አምላክህ ቀናተኛ ነኝና በፊትህ ሌሎች አማልክት አይሁርህ፡፡ ለማናቸውም አትስገድ!” (እጅም አትንሳ) ብሏል፡፡ (ወዳጄ ተመስጌን ደሳለኝ ታዲያ ምን ነካው? “የመለስ አምልኮ!” ይላል  እንዴ? መለስ ጣኦት ነው ያለው ማነው? አምላኪዎቹስ አምላክ የሌላቸው  አረመኔዎች ናቸው እንዴ? ልጅ ተመስጌን ሆይ፣ ውስጠ-ወይራህን ወድጄዋለሁ፡፡)
ወዲ ዜናዊ፣ “አልቃይዳ መጣ! መጣ! መጣብኝ! ምናምን!” ለምን ይላል? ኧረ እንዴት ይላል፡፡ ድሮውንስ ቢሆን አልነበረም እንዴ? ነበረ! ነበረ! ነበረ እንጂ፡፡ የምን ማምታታት ነው ፡፡ እንዴ “አልቲሃድ”፤ ሌላ   ጊዜ “ኢዝላሚክ ኮርት”፣ ሲያሻቸው ደግሞ “አልሸባብ (ወጣቶቹ) ነን” እያሉ ስማቸውን ቀየሩ እንጂ መቼ ጠፉ! ያኔም ኮረኔል አውየስ! አሁንም ሼክ አውየስ ነው! ስሙን ስለቀየረ አቶ መለስን አምታታው እንዴ?! (እኛ አበሾችን፣ በርበሬና ቀይ ሥርማ አያሳስቱንም፡፡ አሳምረን እናውቃቸዋለን!)
ቅዱሳኑስ ቢሆኑ ምን አጠፉ? ዋ! ዋ! ዋ! እነሱማ፣ ምን ያላጠፉት አለ? በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ሀገራችን በዲሞክራሲና በልማት፣ በብሄሮች በብሄረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት በተቀደሰችበት ዘመን፣ ራሳቸውን “የቅዱሳን ማህበር” ነን ምናምን እያሉ ይዘላብዳሉ እንዴ – ደግሞ፡፡ እሺ እኛስ ራሳችንን ማን ብለን እንድንጠራላቸው ፈለጉ?መቼም “ማህበረ-ርኩሳኖች ነን” ብለን እንድንልላቸው አይጠብቁም፡፡ ከጠበቁ ግን በድጋሚ ስያሜያቸውን ያስቡበት፡፡ አለበለዚያ ግን መዲ ዜናዊ፣ የእነዚያን ጢም በጂሌት ምላጭ ሲላጭላቸው፣ የእናንተንም ማህበር ከምድረ-ኢትዮጵያ እንዳይላጨውና ሌላ ዙር ደቂቀ እስጢፋኖሶችን እንዳታሳዩን አስቡበት፡፡……
ኧረ! የእነዚህ የዋልድባ መነኮሳት የሚያሰሙት ጩኸት በረታ እሳ! “ለስኳር እርሻ ተብሎ ሶስቱም የዮርዳኖስ ምሳሌ ወንዞቻችን ተወሰዱብን፣ አፅሞቹም ፈለሱብን፣ የገዳሙም ቅጥር ተደፈረብን” የሚሉት ምን ደረጃ ደረሰ? የወልቃይቶችም ጀግንነት ተመልሶ ተቀስቅሷል አሉ፡፡ የሚባለው ወሬ እውነት ከሆነ፣ አሰደሳች ዜና ነውና በዚህ ዙሪያ እኛ ብዙም አንናገርም፡፡ አንተችምም፡፡ እንዲያው ዝም ነው! ዝም፡፡ ዝም፡፡ (“ሆድ ይፍጀው” ብለ-ጥላሁን ገሠሠ፡፡)
መምህራኑ ግን ምን ነካቸው? የደመወዝና የእርከን ማስተካከያ ተደረገላችሁ ሲባሉ ምን አንጫጫቸው? ምን አሳደማቸው? (አታውቁም ለካ፤ እነጋሼና እነእትዬ እኮ የእርከን ማስተካከያውና የደረጃ እድገቱ ከ11 አመት በኋላ ሲለቀቅላቸው ጊዜ ተደናጡ፡፡ እንጂ፣ ወደው እኮ አይደለም፡፡ አንዴ በውጤት-ተኮር፣ ሌላም ጊዜ በቢ.ፒ.ር እየተላከከ መብታቸው ሲገፈፍ ኖሮ ድንገት፣ “ያልተስተካከለው-ማስተካከያ” መጣ ሲባሉ ጊዜ ተደናገጡ፡፡ (መጣብህ ሲባል የማይደናገጥ ማን አለ?)……. የአቶ መለስ መልስ ግን ይገርማል፡፡ “ችሎታ ያነሳቸው ናቸው የበጠበጡት፤ ያሸበሩት!” አለ፡፡ የመምህራንን ችሎታ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ከነሙሉ ክብሩ፣ ጥቅሙና መብቱ ከሰጧቸው በኋላ “ተማሪ ነኝ” የሚል፣ “ወላጅ ኮሚቴ ነኝ” የሚል “ኧረ የፖለቲካ አመራርም ነኝ፤” የሚል እንዴት ብሎ “አቅመ-ቢስ ነበሩ፡፡ መገረፍ ነበረባቸው…ምናምን!” እንዴት ይላል? እንጃ! እንጃለቱ…! ኧረ ይሄንንስ ጉድ፣ ጠንቋይ መጠየቅ ሳይሻል አይቀርም:: ለነገሩማ እኮ፣ ታላቁ ፕሌቶ ጨርሶታል፡፡ “ሃኪም በሌለበት ጊዜ ምግብ አብሳዮች ዶክተር መሆን ይቃጣቸዋል፡፡” ብሎ ነበር፡፡ እንዴታ! “ይህቺን ብላት! ይህቺ ለጤናህ ፍቱን ናት! ይህንን ጠጣ – ፊትህን ያሳምረዋል! ይሄንን ተመገብ – ሰውነትህ ሸንቃጣ ይሆናል!” ሲሉ ይቆዩና፣ “ልክ ዶክተሩ ተመልሶ ሲመጣ፣ ሹክክ ብለው ወደ ማብሰያ ክፍላቸው ይገባሉ፤” ብሎ እኮ ነበር፡፡ ልክ ፕሌቶ እንዳለው ነው መምህራኑንም የደረሰባቸው፡፡……….
ዘለላ እንባ እያፈሰስኩላችሁ ነውና፣ ይህቺን ብቻ ስሙኝ! ከዚያም በኋላ ብትፈልጉ የንባቡን መንገድ “ጨርቅ ያድርግላችሁ፡፡…..” ባለፉት መንግስታት መብታቸው ተገፎ፣ ክብራችውንና ባህላቸው ተንቆ የነበሩት ጋንቤሎች፣ ሱማሌዎችና አማሮች ምን ቁርጥ አድርጓቸው ነው፤ “ልማቱን ለማስተጓጎል፣ ሰላሙን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱት?” በስንትና ስንት ሰማዕታት ደምና አጥንት፣ እንዲሁም መስዋእትነት፣ በ”ግንበት 20” የተገኘውን ምቹ የልማትና የብሄሮች እኩልነት ሁኔታ ለማስተጓጎል ምን አሯሯጣቸው? ድሮውንም እኮ “…. ፊት ካሳዩት!” ማንም አይቻልም፡፡ እግዜሩስ ቢሆን፣ አንድያ ልጁን “ሂድ! ተቀላቀል፡፡” ብሎ ሲልከው ጊዜ አይደል አንዴ፣ “የእግዜርን ልጅ አየን ማለት፣ እግዜርዬ ግማሽ ፊቱን አሳየን ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ጨክኖም በጠፋት ውሃና በሰዶምና ገሞራ ድኝ አይቀጣንም!” ብለው እንዳይሞት  እንዳይሽር አድርገው የሰቀሉት፡፡ (ሳግ እየተናነቀ አላናግር ስላለኝ ትንሽ ፋታ ስጡኝ እስቲ፡፡ ሶፍት ያላችሁ፣ እስቲ እንያችሁ?!)
እኛ ግን ሰላማችን ስትሰቀል፣ ልማታችን ስተወገር አናይም፡፡ ዝምም አንልም፡፡ ባይሆን እነ ፕሬዚዳንት አሞትና እነ ፕሬዚዳንት ሽፈራው ዝም ቢሉ ምን አለበት፡፡ “ካፍ ካመለጠ አፋፍ!” የሚለውን የአማራ ተረት አያውቁትምን? “ጨቋኝ ነበር! ነፍጠኛ ነበር!” እየተባለ የሚወቀሰውን የአማራን ህዝብ ኢትዮጵያዊት አለማወቃቸው ሳያንስ፣ ተረቶቹንና ጥልቅ አስተሳሰቦቹን አለማወቅ ግን፣ አሞትና ሺፈራው ሆይ - ራስን ላደጋ ማጋለጥ ነው፡፡ ስለዚህ አፋችሁን ሰብስባችሁ የዛፍ ላይ እንቅልፋችሁን ለጥጡ! ለዚያውም እኮ እንቅልፍ ከወሰዳችሁ ነው!…..
በመጨረሻም፣ “መጅሊሱ ይፍረስ እያላችሁ የምተጮኹ ሰዎች ሆይ! (ወንድሞቻችንና እህቶቻችን) እንኳን ደስያላችሁ!!!……የደስታችሁ ተካፋይ በመሆኔ የተሰማኝን “ምቹ የሕዳሴ” ስሜት  እንዳትረሱ፡፡ አንድ ድምጽ ካሰሙና በአንድነት ከዘመሩ እንኳን የኢማሞች ስብስብ የሆነው መጅሊስና ኢያሪኮም ትፈርሳለች፡፡ ኢትዮጵያም በነጻነትና በእኩልነት መንፈስ ትገነባለች፡፡ ሃሳቤን አልጨረስኩም፡፡ ግን ቻው!……..ቻው! ቻው! ቻውውውው……….!

No comments:

Post a Comment