"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday, 2 June 2012

የኖርዌይ ፖሊስ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ስለወሰደው የኃይል እርምጃ በተመለከተ


 | 

የኖርዌይ ፖሊስ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ስለወሰደው የኃይል እርምጃ በተመለከተ፤አኢጋን


ከጥቂት ቀናት በፊት ለተባበሩት መንግሥታ የስደተኞች ኮሚሽነር በዓለም ዙሪያ ግፍ እየተቀበሉ ስላሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በጻፍነው ደብዳቤ ላይ የኖርዌይ ስደተኞችን ሁኔታ በዝርዝር መጥቀሳችን የሚታወስ ነው፡፡ ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከል በኖርዌይ እስከ 16 ዓመታት የኖሩ የሚገኙበት ሲሆን በእነዚህ ዓመታትም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ባይሰጣቸውም ባገኙት ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ እንደስደተኛ የመንግሥትን ድጎማ እየተቀበሉ ከመኖር ይልቅ ያገኙትን ሥራ እየሠሩ፣ ግብር እየከፈሉ እንዲሁም ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ ጋር ለማዋሃድ ቋንቋ በመማር፣ ቤት በመሥራትም ሆነ በመግዛት ቤተሰባቸውን በዓቅማቸው ለማስተዳደር ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከኖርዌይ መንግሥት የተሰጣቸው ምላሽ ያልጠበቁት ከመሆን ባሻገር ኑሮዋቸውን እጅግ አስከፊ ደረጃ በፍጥነት እንዲደርስ ያደረገ ሆኗል፡፡
በቅርቡ ስደተኞችን አስመልክቶ የኖርዌይ መንግሥት ያደረጋቸውን ለውጦች የተቃወሙ 63 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን (ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ) በኦስሎ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ጠለላ ባኙበት ወቅት የቤ/ክኑ ኃላፊዎች ከመንግሥት ጋር (ከኢሚግሬሽን ጽ/ቤት) ተነጋግረው በተስማሙት መሠረት እዚያው ኦስሎ ውስጥ ወደጊዜያዊ የስደተኛ ካምፕ ተዛውረው ነበር፡፡ ከእነዚህ ወገኖቻችን መካከል አንዲት የስድስት ወር እርጉዝ፣ ሌላ የ14 ህጻን ሴት ልጅ ያላት እናት፣ በኖርዌይ ለበርካታ ዓመታት ሲሰሩ የቆዩና በሌሎች የምዕራብ አገሮች ቤተሰቦች ያላቸው ዕድሉም ከተሰጣቸው ወደዚያው ለመሄድ የሚችሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ወደዚህ ካምፕ ተዛውረው ከኖሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ማክሰኞ ሚያዚያ 18፣ 2003 ዓም ያልተጠበቀ ሁኔታ ተከሰተ፡፡
የኖርዌይ የደኅንነትና የፖሊስ አካላት ወደካምፑ በመምጣት ኢትዮጵያውያኑን ከዚያ እንዲወጡና ወደፈለጉበት እንዲሄዱ ድንገተኛ የሆነና ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ በአንድ በኩል የኢሚግሬሽን ጽ/ቤቱ በካምፑ እንዲቆዩ ሲፈቅድ በሌላ በኩል ደግሞ የፖሊስ አካላት እንዲህ ዓይነቱን እርስበርሱ የሚጋጭ ትዕዛዝ መስጠት እንደኖርዌይ ካለ አገር ሳይሆን እነ አቶ መለስ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ›› ከሚሉት ራሱን በመርህም ሆነ በፖሊሲ የሚቃረን አገዛዝ ስንሰማ የቆየነው ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህንን የፖሊስ ትዕዛዝ ለመቀበል አስቸጋሪ የሆነባቸው ወገኖቻችን በድርጊቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በገለጹበት ወቅት በተለይም አቶ ልዑል አለማየሁ የተባለውን የቡድኑን አስተባባሪ ፖሊሶቹ በሠንሰለት አስረው በሚወስዱበት ወቅት ተቃውሟቸውን የገለጹትን ሴቶች እህቶቻችንን በአሰቃቂ ሁኔታ መሬት ለመሬት እየተጎተቱ ሲወሰዱ ከዚህ በታች የሚታዩት ፎቶግራፎች ህያው ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ በተለይ መሬት ላይ በፖሊሶች ከተዘረረች በኋላ ታስራ የተወሰደችው እህታችን ወርቅዬ አማረ በግራ እግሯ ላይ ስብራት የደረሰባት ሲሆን ሌላኛዋ እህት ህሊና ሰለሞን ደግሞ በእጆቿ ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሶባቸዋል፡፡
እንዲሁም ከላይ የተጠቀሰችው የስድስት ወር ነፍሰጡር በደረሰባት እንግልት እንዲሁ ወደሆስፒታል ተወስዳለች፡፡ ምንም ዓይነት ወንጀል ያልፈጸመው ነገር ግን ለራሱና ለሌሎች መብት መከበር የሚሟገተው አቶ ልዑል አለማየሁ ወንጀለኞች ከሚታጎሩት ተወስዶ ለ7 ሰዓታት ያህል ከቆየ በኋላ ተፈትቷል፡፡
የቀኑን የፖሊስ ግርግርና ግፍ የተቋቋሙት ወገኖቻችን ካምፓቸው ቢቆዩም ምሽት ወደ 4 ሰዓት አካባቢ ጨለማን ተገን አድርገው የተመለሱት ፖሊሶች በርካታ የማጎሪያ መኪናዎችን ከተጨማሪ የፖሊስ ኃይል ጋር በመያዝ ተመልሰው በመምጣት እነዚህን ወገኖቻችንን በጭለማ እያስገደዱ ወደየመኪናው ካጎሯቸው በኋላ በተለያየ አቅጣጫ ከከተማ ውጪ አውጥተው በመጣል ‹‹የኖርዌይ መንግሥት እናንተን አይፈልግም፤ ከዚህ ወደፈለጋችሁበት ሂዱ›› በማለት የማስፈራሪያና የዛቻ ቃል በመናገር ለብዙዎቹ ፈጽሞ እንግዳ የሆነ ቦታ ላይ በጭለማ እንዳይገናኙ አድርገው በትነዋቸዋል፡፡ በከባድ ፍርሃት እና ጭንቀት ውስጥ የገቡት ወገኖቻችን ከያሉበት በስልክ በመገናኘት እንዲሁም ከተማ ውስጥ የሚገኙ ወዳጆቻቸውን በመጥራት ካሉበት እንዲወስዷቸው በርካታ ሙከራ ከተደረገ በኋላ እኩለሌሊት ላይ ሁሉም እንደገና ለመሰባበሰብ ችለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ወደካምፕ መመለሱ ለህይወታቸውም ጭምር የሚያሰጋ እየሆነ የመጣ በመሆኑ ቀድሞ ጠለላ አድርገው ወደነበረበት ቤ/ክ ሜዳ ላይ ድንኳን በመትከል ሌሊቱ አሳልፈው መጻዒ ዕድላቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡
ታሪካችንን ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ለኢትዮጵያዊ ስደት ማለት የውርደት መጨረሻ እንደነበር ከብዙዎች ሲነገር እንሰማለን፡፡ በቀድሞው ዘመናት ለትምህርት ወደውጪ አገር የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ለምረቃ ለመቆየት ካለመፈለጋቸው የተነሳ የትምህርት ማስረጃቸውን በኤምባሲ በኩል አዝዘው ወደአገራቸው በፍጥነት ይመለሱ እንደነበር የብዙዎች ትዝታ ነው፡፡ ‹‹እናት ኢትዮጵያ›› በማን ተተክታ ነው ስደት እንደ ክብር ተቆጥሮ በሰው አገር የሚኖረው? በማለት ወደ አገራቸው የሚሄዱበትን ቀን እንደ እርጉዝ ሲቆጥሩ ነበር የሚቆዩት፡፡
አሁንስ? አሁንማ ስደት ‹‹ክብር›› ከመሆን አልፎ ዓለምአቀፋዊ መለያችን ሆኗል፡፡ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ውስጥ የሚኖሩት በየቀኑ ወደውጪ የሚሄዱበትን በናፍቆትና በተስፋ ካልሆነም ወደሚክሲኮና አረብ አገራት እንደሚሄዱቱ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ለመጣል በመዘጋጀት ነው፡፡ ለቅኝ ገዢዎች የእግር እሣት የነበረው የኢትዮጵያዊነት ኩራት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ማየትን የመሰለ ውርደት የለም፤ አይኖርምም፡፡ ይህንን በህዝባችን ላይ ከተለያየ አቅጣጫ ለሚደርስ በደል መከታ የሚሆን አለኝታ መንግሥት የሌለን መሆናችን ደግሞ ሃዘናችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያችን ችግር የስደት ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያውያን የስደት ችግር በኖርዌይ ብቻ ተጀምሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በጃፓን፣ በስዊድንና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች፣ በሳዑዲአረቢያና በበርካታ የአረብ አገሮች፣ በአጠቃላይ በመላው ዓለም የአገራችን ሕዝብ ተበትኖ የሰው ልጅ ሊደርስበት ይችላል ተብሎ የማይገመት መከራ እየተቀበለ ይገኛል፡፡ ጥያቄው ያለው ‹‹ሕዝባችን ለምንድነው ይህንን የስደት ኑሮ መፍትሔ አድርጎ የመረጠው?›› የሚለው ላይ ነው፡፡ መልሱንም በጥየቄ መመለስ ይቻላል፡፡ በአገራችን ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ፣ ሰላም ቢኖርና ሁሉም እንደዜጋ ተከብሮና አኩል የመሥራትና የመኖር ዕድል አግኝቶ መብቱም ተከብሮ ለመኖር ቢችል ለመሰደድ የሚፈልግ ምንያህሉ ይሆን ነበር? ለዚህም ነው የጋራ ንቅናቄያችን ‹‹ከዘረኝነት ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጥባትን›› እና ‹‹ሁላችንም ነጻ›› የምንሆንባት ‹‹አዲሲቷን ኢትዮጵያን›› ለመመሠረት የሚታገለው፡፡ ለዚህ ዘርፈብዙ ለሆነው ችግራችን ዋንኛው መፍትሔ ከዚህ ውጪ ፈጽሞ ስለማይሆን ሁላችንም በምንችለው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ነጻነት፣ መብት መከበርና እኩልነት በያለንበት እንቁም፡፡
ማሳሰቢያ፡- በአሁኑ ጊዜ ይህንን ከፍተኛ ችግር እየተጋፈጡ ያሉትን በኖርዌይ የሚገኙትን ወገኖቻችንን ይረዳ ዘንድ ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽነርና ለሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአንድ ጊዜ በኢሜይል መልክ እንዲደርስ ያዘጋጀነውን አቤቱታ እንድትሞሉ በድጋሚ ጥሪ እናደርጋለን (http://solidaritymovement.net/signPetion.cfm) እንዲሁም እዚያው ኖርዌይ ድረስ በመደወል የሞራልም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለመስጠት ለምትፈልጉ ሁሉ የስደተኞቹ ጉዳይ አስተባባሪ የሆኑትን አቶ አዳነ አስረስን 47 47 62 65 79 መደወል ወይም በኢሜይል(Adeew2000@yahoo.com) ማግኘት የምትችሉ መሆናችሁን እየገለጽን በተለይም በዓለምአቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ላይ ባለሙያ የሆናችሁ በሙሉ የምትችሉትን የሙያ ድጋፍ እንድትሰጡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
**************************************************************************************************
ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ዋና ዳይሬክተሩን ለአቶ ኦባንግ ሜቶ (obang@solidaritymovement.org) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment