"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday 29 May 2012

ኢህአዴግ በደንብ ጎረመሰ…! (አቤ ቶኪቻው)


ኢህአዴግ በደንብ ጎረመሰ…! (አቤ ቶኪቻው)
SHARE THIS
       
TAGS

abetokichaw@gmail.com

በመጀመሪያም

ጋሽ ግርማን አየኋቸውኮ!

በዛን ሰሞን “ሞቱ” ተብሎ ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ከተውን የነበሩት መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ድንገት ተከስተው “እንኳን ለግንቦት ሃያ አደረሳችሁ” ብለው ፡”ሰርፕራይዝ” አድርገውናል። ትንሽ ሸንቀጥ ቢሉም እየተነፈሱ እንደሆነ በማየታችን እኛም ከመቀመጫችን ብድግ ብለን “እንኳን አብሮ አደረሰን!” ብለናቸዋል።

ኢህአዴግ አዲሳባን ከተቆጣጠረ 21 ዓመት ሞላው። ይህንንም ለማረጋገጥ ዛሬ ጠዋት አዲሳባ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶላታል። ለገና እና ለመውሊድ 9 ጊዜ ብቻ እንጂተኮስ የተወሰነው መድፍ ለኢህአዴግ ልደት ሃያ አንድ ግዜ መተኮሱ መንግስት “ከሁሉ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው” ሊለን ፈልጎ እንደሆነ ግልፅ ነው።

እንግዲህ ኢህአዴግ አሁን በደንብ ጎረመሰ ማለት ነው። ይህ ወቅት ጡንቻ የሚፈረጥምበት ጢም የሚቀመቀምበት ከመሆኑም በላይ እግዜር ላልባረከው፤ ልብ የሚነፋበት ጆሮ የሚደፈንበት አስቸጋሪ ወቅት ነው። በዚህ ዕድሜ ላይ ያለ ያልተባረከ ጎረምሳ ኮረዳዎች “ሳመኝ” ሲሉት እንጂ አዋቂዎች “ስማኝ” ሲሉት ጥሪ አይቀበልም። ከላይ ከላይ መናገር እና ከኔ በላይ ላሳር ማለት ልዩ ባህሪያቱ ናቸው። (አይ ጉርምስና!) እናም ኢህሃዴግ አሁን ዋናው የአፍላ ጉርምስና ወቅቱ ላይ ይገኛል። በአራዶች ቋንቋ “ፍንዳታ” ሆነ የሚባለው ማለት ነው። ወደ ጨዋታችን ዘልቀን ከመግባታችን በፊት “ኢህአዴግዬ ጉርምስናውን በቅጡ ያድርግልህ” ብለን እንመርቀዋለን!

“ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬድዬ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል ግንቦት 20 ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሶስት አመተ ምህረት!” የተባለ ጊዜ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነትን እና አባታችን ኢህአዴግን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ የተቀበለው ቴሌቪዥናችን በአሁኑ ግዜ ዋና የኢህአዴግ ፓስር ሆኖ ስብከቱን ሲያሰማ ውሎ ያድራል። በተለይ ሰሞኑን ኢህአዴግ ጉርምስናውን ሲያከበር ኢቲቪ ውዳሴ እና ዝማሬ በማዝነብ የሚስተካከለው አልተገኘም። እኛም በተለይ ከህዝቡ ዘንድ የተደበቀውን ጥጋብ ለመየት የታደለው ኢቲቪ ይህንን ይመለከት ዘንድ የተቻለው “እንደምን ያለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መንፈስ ቢሰርፅበት ነው!?” ስንል አድንቀናል።


አፈር ስሆን ትንሽ ቆየት ባለ ጨዋታችን ላይ ያወጋነውን የአንድ የኢቲቪ ጋዜጠኛ ገጠመኝ እዝች ጋ እናምጣት፤

ጋዜጠኛው በልማታዊ ዘገባ የሚታወቅ ነው። ፐርሰንትን ማውራት ለጥጋብ የሚዳርግ ቢሆን ኖሮ ከሁሉም በላይ ይህ ጋዜጠኛ ለመንደሩ ሰው ሁሉ ጥጋብን የሚያከፋፍል በሆነ ነበር። የሆነ ግዜ ቤቱ እንግዳ መጣበት። ከዛም በአባወራ ደንብ ሳሎን ቁጭ ብሎ “እስቲ ምሳ አቀራርቢ” ብሎ ለሚስቲቱ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ከእንግዳ ጋር ይመጣል ብላ ያልገመተች ሚስትም “ምናባቴ ይሻለኛል ባዶቤት እንግዳ ይዞብኝ መጣ…!” ብላ እየተጨነቀች ለእርሱ የተዘጋጀውን እንደነገሩ የሆነ ምሳ አቀረበች። አባወራ ሆዬ እንገዳውን፤ “ብላ እንጂ አልጠፈጠህም እንዴ?” ብሎ አየጋበዘ አንገቱን ወደ ጓዳው ቀለስ አድርጎ “ትንሽ ቅቤ ጣል አድርገሽ ወጥ ጨምሪልን እስቲ…” ሲል አዘዘ። ሚስት ክው ብላ እየደነገጠች እንግዳ ፊት “ከየት አምጥቼ…” አይባልም እና፤ “እሺ” በማለት እዛው ጓደ ቁጭ አለች።

ባልም ትንሽ ከእንግዳው ጋር ከተጨዋወተ በኋላ “የት ጠፋሽ አረ እንጀራም ጨምሪልን እንጂ…” አለ እና “ይሄውልህ ያ አለቃችን ደግሞ…” እያለ መውጋቱን ቀጠለ። ሚስት “እሺ መጣሁ” ብላ አሁንም ጓዳዋ ቁጭ ማለትን መረጠች… ቢጠብቋት… ቢጠብቋት አትመጣም፤ ከዛ ባል ሆዬ “የት ሄድሽ ቡናስ አታፈይልንም እንዴ…?” ብሎ ተጨማሪ ትዕዛዝ ቢያዛት ከቡናው ቀድሞ ደሟ ፈልቶ እየተብከነከነች፤ ጓዳዋ ኩርምት ብላ ቁጭ! በዚህ ግዜ ባል እንግዳውን ሳሎን ጥሎ “ቀረሽ እኮ!” እያለ ወደ ጓዳው ሲገባ ከተቀመጠችበት ብድግ ብላ “ስማ እንጂ ይሄ እኮ በኢቲቪ የምታሳየው የልማት ፕሮግራምህ ሳይሆን መኖሪያ ቤትህ ነው… ቅቤ ጣል አድርጊ፣ እንጀራ ጨምሪ፣ ቡና አፍዬ… ትለኛለህ ቤቱ ባዶ እንደሆነ አታውቅም…!?” በማለት ስቅስቅ ብላ አለቀሰች።

የኢቲቪ ጋዜጠኞች በቤታቸው የሌለውን ምቾት በሀሪቱ ሞልቶ ተትረፍርፏል ብለው ሲሰብኩን ትንሽም ድንቅፍ አይላቸውም። ይሄ በእውነቱ ከፍ ያለ “ምንፍስናን” የሚጠይቅ የፃድቅ ሰው ስራ ነው።

የሆነ ሆኖ ሰሞኑን ከመቼውም ግዜ በበለጠ ቴሌቪዥኔ ዋና ካድሬ ሆኖብኝ ከርሟል። ላለፉት ስምንት አመታት ተከታታይ እደገት ማሳየታችንን፣ አራት ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን ማከናወናችንን፣ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጣችንን፣ በምግብ ምርት ራሳችንን መቻላችንን፣ ከአገር አልፈን የአፍሪካ መኩሪያ መሆናችንን አስረግጦ ነግሮኛል። (“ይሄ ሁሉ ሲሆን እኔ የት ነበርኩ!?” ብለው እንዳይጠይቁኝ ብቻ)

እኔ የምለው ግን ኢህዴግ ይህንን የጉርምስና ግዜውን በሚያከብርበት ወቅት አዲስ ስድብ ማስመዘገቡን ልብ ብላችሁልኝ ይሆን? “ሟርተኛ” የሚለውን ስድብ በቴሌቪዥኔ ስንት ግዜ እንደሰማሁት ለመቁጠር ፈልጌ ደክሞኝ ነው ያቆምኩት። ይህንን ስድብ ከኢህአዴግ አደረጃጀት ሃላፊው አቶ ሬድዋን ጀምሮ ሁሉም ሃላፊዎች እና ጋዜጠኞች እንደየ ሃላፊነታቸው መጠን በተደጋጋሚ ሲጠቀሙበት ሰምቼ አንድ ስድብ ላይ ከሚሻሙ ለምን፤ “መተተኛ” “አስማተኛ” “ድግምተኛ” “ሰላቢ” እና የመሳሰሉትን ተመሳሳይ ስድቦች እየቀላቀሉ አይጠቀሙም? ስል ተጨንቄላቸዋለሁ። ለነገሩ ለቀጣዮቹ ግዚያት እንቆጥብ ብለው እንጂ ከእኔ ያነሰ የስድብ ዕውቀት አላቸው ብዬ አላስብም። እውነትም ደግሞ ቁጠባን ባህል ማደረግ ጥሩ ነው።

ለማንኛውም ዛሬ የኢህአዴግ ልደት ነው። ልደቱን አስመልክቶ ምን ያህል ጥጋብ እና ተድላ ላይ መሆናችንን መንግስታችን ነግሮናል። አልጠገብንም ብሎ መከራከር አይቻልም። በአገሪቱ የመፃፍ እና የመናገር ነፃነት ያለ ምንም ገደብ እንደተፈቀደም ተነግሮናል። የለም እየታፈንን ነውኮ! ብሎ መጨቃጨቅ አይቻልም። ምንያቱም ይሄ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። ጠግባችኋል ተብለናል። አዎ ጠግበናል። ዴሞክራሲ ሰፍኖላችኋል ተብለናል አዎ ሰፍኗል።  እግዜር ይስጥልና! (ይቺ እግዜር ይስጥልና እንዴት ያለች ምርቃት መሰለቻችሁ…!?)

ከሁሉ የሚያስገርመኝ 1

ህገ መንግስቱ

ኢህአዴግ እጅግ በጣም ከሚመካባቸው ትህምክቶቹ መካከል “ህዝብ ተወያይቶበት” ያፀደቀው ህገ መንግስት ባለቤት አደረኳችሁ” የሚለው ይገኝበታል። ነገር ግን በዚህ ወቅት በርካታ ተንታኞች ኢህአዴግ ራሱ ህገ መንግስቱን እያከበረ እንዳልሆነ ይናገራሉ። (እንደው ለትህትና ተንታኞች አልኩ እንጂ እኔ ራሴ አረ ብዙ ታዝቤያለሁ)

ህገ መንግስቱ “ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረኑ ማነኛቸውም አዎጆች ደንቦች እና መመሪያዎች ተቀባይነት የላቸውም” ይላል። ግን ማን ይሰማዋል…? መንግስታችን የሚያወጣቸው የተለያዩ አዋጆች እና መመሪያዎች ህገ መንግስቱ ከሚለው በተቃራኒ እየታወጁ እና ተግባራዊ እየተደረጉ ተመልክተናል። በትሹ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነት በተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች “ተከልክሏል” ለማለት ያስደፍራል። የቅርብ ግዜ ምሳሌ ብናመጣ እንኳ ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ ዳግም የታሰረች ግዜ ደጋፊዎቿ ሰልፍ ሊወጡ ሲሉ “ከ250 በላይ ሰው ማሰለፍ አይቻልም” ተብለዋል። በአዲሳባ “መድረክ” የመሰብሰቢያ አዳራሽ አጥቶ ሁልግዜ ኡኡታውን የሚያሰማው ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን መመሪያ ሰለባ በመሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጪ ሀገር ተቃውሞ ሰልፍ እና የህዝብ ቁጣ ሲያጋጥማቸው “ክው” የሚሉት። ሀገር ውስጥ ቢፈቅዱልን ይለምዱት ነበር። (የሚሉ ወገኖች አሉ ብለው ይጨምሩልኝ)

በደንብ እናጥና ካልን ሌሎችም መመሪያዎች እና አዋጆች ህገ መንግስቱን ሲረመርሙት ማየት ብርቅ አይደለም። በቅርቡ ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት እንኳ ከአቅሟ የማትመው “ፅሁፋችሁን መጀመሪያ መርምሬ ነው” ብላናለች! አረ ህገ መንግስቱ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱርን) ይከለክላል ብለው ዋይ ዋይ ቢሉ “ይሄ የማተሚያ ቤቱ መመሪያ ነው” ይባላሉ!።

ከሁሉ የሚገርመኝ 2

ኢህአዴግ ልደቱን ባከበረ ቁጥር የጦር ገድሉን አንስቶ አይጠግብም። በገድሉም ይህንን ትግል ለማድረግ ያነሳሳውን ምሬት እና ብሶት ደጋግሞ ያነሳል። ቀጥሎም ከዚህ ምን እንማራለን? ብሎ ይጠይቃል? በርግጥ መልሱ “አሁንም ብሶት ከበዛ ቆርጦ መታገል ነው” የሚል ነው። (በቅንፍ የትግሉን አይነት የሚመርጠው ታጋዩ እንደሆነ አስታውሳለሁ።) ግን ይህንን ጥያቄ መጠየቅ በዚህ ወቅት ተገቢነውን?


Meles Zenawi as a child www.maledatimes.com

ከሁሉ ያሳቀኝ
አሁን የግንቦት 20 ልደት እያከበረ ያለው ኢቲቪ አንድ ነገር ሲናገር ሰማሁት “ከዚህ ቀጥሎ ምርጫ ከድምፅ ካርድ እንጂ ከጠመንጃ አፈ ሙዝ አይገኝም” የሚል ንግግር። እኔ የምለው “ተኳሾቹ” በምርጫ 97 የነበረውን ሰው በሙሉ ገድለን ጨርሰናል። ብለው ነው እንዴ ሪፖርት ያደረጉት… (አረ ፍሬንድ ወቅቱን የታዘቡ ብዙ አሉ!) “ከጠመንጃ አፈ ሙዙ ስልጣን አይገኝም…” የምሬን ነው የሳኩት… አሃ ምናልባት የአጋዚዎች ተኩስ የጠመንጃ አፈሙዝ አይባልም ይሆን…? ይቺ የጦር እውቀት ማጣት እኮ የምታስጠቃው ይሄኔ ነው!

Share this:


Facebook
inShare
Print


No comments:

Post a Comment