"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday 29 May 2012

ነዋይ ደበበ ኢትዮጵያ በመመለሱ ደስተኛ አለመሆኑን እየገለጸ ነው


About Us
Jobs (minnesota)
Short Stories
Poem
Video
Free Media
American Law
Contact Us

Tuesday, May 29th, 2012 | Posted by zehabesha
ነዋይ ደበበ ኢትዮጵያ በመመለሱ ደስተኛ አለመሆኑን እየገለጸ ነው
13
Share

(ዘ-ሐበሻ) አሜሪካን ሃገር ያለውን ትዳሩን እና ልጆቹን በትኖ ኢትዮጵያ ለመኖር የገባው ድምዳዊ ነዋይ ደበበ አዲስ አበባ ገና ከመግባቱና ከኤርፖርት ወጥቶ ከተማውን ሳይዘዋወርና ሳይመለከት ለራዲዮ ፋና በሰጠው ቃለምልልስ “አዲሳባ ተለውጣለች፤ የሕዝቡም የኑሮ ሁኔታ ተለውጧል” የሚል ቃለ ከሰጠ በኋላ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሊያደርጋቸው የነበሩት የሙዚቃ ኮንሰርቶች በተመልካች እጦት የተነሳ ተስተጓጉለውበታል።
ወደ ኢትዮጵያ “እነአስቴር አወቀን፣ አበጋዝ ክብረ ወርቅ ሺዎታን እና ሌሎች ባለሙያዎችን ተከትዬ ገብቼ በአሁኑ ወቅት ሙዚቃዬን የሚያቀናብርልኝ እንኳ አጥቻለሁ” በሚል ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሰይፉ ፋንታሁን የራድዮ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ የተናገረው ነዋይ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ያን ቃለምልልስ በወያኔው ሚዲያ ራድዮ ፋና ከሰጠ በኋላ ባደረገው የጊዮን ሆቴል የሙዚቃ ዝግጅት ላይ 20 ሰው የማይሞላ ተገኝቶ በነሱም የለስላሳ ጠርሙስ መድረክ ላይ “ሃገሬን አልረሳም” እያለ እየዘፈነ ሲወጣ እንደተወረወረበት የቅርብ አመታት ትዝታ ነበር።

ሰለሞን ተካልኝ የወያኔ ተላላኪ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ክፉኛ ሲያወግዝ የነበረው ነዋይ እርሱን ተከትሎ ወዲያው ኢትዮጵያ በመግባቱ በብዙዎች ዘንድ ተቃውሞን አስከትሎበት ነበር። በአሁኑ ወቅት “ወይኔ እነ አስቴርን ተከትዬ ገብቼ ጉድ ሆንኩኝ” እያለ በቁጭት ነዋይ እንደሚናገር የገለጹት የአርቲስቱ የቅርብ ምንጮች “እንዴት የኔን ካሴት የሚያቀናብር ልጣ?” በሚል ከአሜሪካ ወደኢትዮጵያ መሄዱን በቁጭት በመናገር ላይ ነው። በሁሉም ንግግሮቹ ላይ “አሜሪካ እኮ እንዲህ ነው እያለ…ከኢትዮጵያ ኑሮ ጋር በማነጻጸር” መናገር አብዝቷል የሚሉት ምንጮቻችን ኑሮውን ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ በማድረጉ ደስተኛ አለመሆኑንም አሜሪካንን ከኢትዮጵያ ጋር በማነጻጸር በመግለጽ ላይ ነው ብለዋል።
ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ነዋይ ደበበ አዲስ ሊያወጣው ያሰበው ካሴት አቀናባሪ ያላገኘ ሲሆን ኢትዮጵያ ያሉ የሙዚቃ አቀናባሪዎችም ለምን ለነዋይ መስራት እንዳልፈለጉ ለማጣራት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ከነዋይ ብቃት ጋር በተያያዘ ይሁን ወይም በፖለቲካው ዙሪያ በለወጠው አቋሙ የተባለ ነገር የለም።
ነዋይ በሼህ አላሙዲ ጋባዥነት በሸራተን ሁቴል በ2010 የፈረንጆች ዓመት ያልተሳካ የሙዚቃ ዝግጅት አድርጎ እንደነበር ይታወሳል። አርቲስት ነዋይ ደበበ ድምጹን አውጥቶ ለመዝፈን እና ትክክለኛውን ዜማ ለማምጣት የተቸገረ ሲሆን፤ ”ይቅርታ ነርቨስ ስለሆንኩ ነው። ለድምጼ መበላሸት ይቅርታ እጠይቃለሁ” በማለት የድምጹን መበላሸት አምኖ እዛው መድረክ ላይ ይቅርታ ጠይቋል። አያይዞም ለዛ መድረክ ያበቁትን ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲንን አመስግኗል። በወቅቱ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደ ነዋይ ያሉ ታዋቂ አርቲስቶች ሥራቸውን እንዲያቀርቡ የሚጋበዙት በችሎታቸው ሆኖ እያለ እንዲህ ያለ ምስጋና ማቅረቡ ተገቢ እንዳልነበር ገልጸዋል።
ለግንዛቤ ይረዳችሁ ዘንድ የዘ-ሐበሻዋ ጋዜጠኛ ሊሊሞገስ ስለነዋይ ደበበ ሕይወት ከ5 ዓመት በፊት የጻፈችውን ታሪክ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የኢትዮጵያ ሙዚቃን እድገት በሦስት ደረጃ እከፍለዋለሁ :: የመጀመሪያው በእነአሰፋ አባተ ዘመን የነበረውና እነ ጥላሁን ገሠሠ ከሱዳን እና ከሕንድ ዜማዎችን እያመጡ ያሳደጉትን ሲሆን : ሁለተኛው ደግሞ እነ ነዋይ ደበበ ከሮሀ ባንድ ጋር በመሆን የሙዚቃውን ደርጃ ከፍ ያደረጉበት ነበር :: አሁን ሙዚቃ በአንድ ኪቦርድ ብቻ በመስስራት በኮምፒውተር ድምጽን አሳምሮ መምጣት በሆነበትና ካሴትና መድረክ በተለያዩበት ዘመን ሮሀ ባንድ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የሠራው ገድል የማይናቅ ነው ::
ሙዚቃን በሙሉ ባንድ በመስራት የመካከለኛውን ዘመን ሙዚቃ ጣሪያ ላይ የሰቀሉት ሮሀ ባንዶች ዛሬ በሞትና በሌሎችም የሕይወት ውጣ ውረዶች ባይነጣተሉ ምን ሊሰራ ይችል እንደነበር ሳስብ ያመኛል :: በእውነቱ ሮሀ ባንድ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አብዮተኛ ነበሩ ብል አላጋነንኩም ::
ሦሰተኛውና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ትንሣኤ የቴዲ አፍሮ እና የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ ) ነው :: በትክክለኛው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አብዮተኞች ተብለው በያሬድ ሙዚቃ አዋቂዎች የተመረጡት ሁለቱ ድምጻዊያን ሙዚቃን ዛሬ ለዚህ አብቅተዋታል :: በተለይ ቴዲ አፍሮ አብዛኞቹ ሙዚቃዎቹ ”ጠዋት ተመርቶ ከሰአት መርካቶ ” የሚለውን ብሂል ያስታውሰናል :: ይህን ለማረጋገጥም በሀይሌና በቀነኒሳ ዙሪያ የሰራውን ዘፈን እና እንዲሁም ለአዲሱ ሚሊኒየም ያቀርባቸውን ሥራዎች ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው ::
ቴዲ አፍሮ ለዛሬው የሙዚቃ መሠረትህ ማነው ? ሲባል ”ነዋይ ደበበ ነው ” ያለው :: ስለ ነዋይ ደበበ የሙዚቃ ሥራዎች : የግጥም ውበት እና አዘፋፈን ስልት አንስቶ የማይጠግበው ቴዲ ”በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የምሰጠው ነዋይ ደበበን ነው ” ይለናል :: በተለይ ቴዲ ገጣሚም : ዜማ ደራሲም ጥሩ አቀንቃኝም መሆኑ ከነዋይ ጋር ያመሳስለዋል ::
”ነዋይ ደበበ የገበያ ዘፈኝ ነው ” ይለናል የአለም ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ሙኒር ኑርጀቦ :: ከ 2 አመታት በፊት በኮፒራይት ሕግ መውጣት የተነሳ ኮፒ ካሴቶችን ያባዛል በሚል ታስሮ ከእስር የተፈታው ይህው የአለም ሙዚቃ ቤት ባለቤት ”ሕዝብ ምን ይፈልጋል ? የሚለውን የሚያውቅ ዘፋኝ ያስደስተኛል :: ነዋይ ሕዝብ የሚፈልገውን ነገር ያውቃል ::… ነዋይ ዛሬ ካሴት ቢያወጣ ሕዝቡ በአንድ ጊዜ ግጥምና ዜማውን መስማት ስለሚችልም ጭምር ገበያውን ይቆጣጠረዋል ” ይለናል ::
ዘንድሮ 30ኛ አመት የሙዚቃ አገሎግሎት ዘመኑን የሚደፍነው ነዋይ ደበበ እንዴት ነበር ወደሙዚቃው አለም የገባው ? የሚለው የተለመደና አሰልቺ ሊሆን ስለሚችል በሙዚቃ አጀማመሩ ላይ ስላጋጠሙት አስልቺ አሳዛኝ ታሪኮች ልነሳ ::
ራስ ቲአትር በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር ሲቋቋም ለትያትር ቤቱ የተለያዩ አርቲስቶች በየሥራ ዘርፉ ይፈለጉ ነበርና በወቅቱ የወጣውን ማስታወቂያ በመመልከት ለፈተና ወደ አምባሳደር ትያትር ያመራል :: ይህ ወቅት ነበር ከነኤልያስ ተባበል : ሻምበል በላይነህ እና ከነጸሀይ ዮሀንስ ጋር ሊያስተዋውቀው የቻለው :: ነዋይ በወቅቱ ከወጣትነቱም ጋር በተያያዘ ድምጹ ቀጭን ቢሆንም ከፈታኞቹ መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ነዋይ ወደፊት ብዙ ሊሰራ ይችላል : ስለዚህም ራስ ቲያትርንም ለምንፈልገው ነገር ሊያግዘን ይችላል በሚል እንዲቀጠር አደረገው ::
“ወደ ሙዚቃው አለም የገባሁት እነጋሽ ጥላሁንን አይቼ ነው :: በጋሽ ጥላሁን እጅ ተፈትኜ የራስ ትያትር አባል ሆንኩ > የሚለው ነዋይ በራስ ቲያትር ጥሩ ጥሩ የሙዚቃ ልምዶችን እንዳገኘ አስታውቆ በወቅቱ በነበረው የግጥምና የዜማ መድረስ ችሎታው ለትያትር ቤቱ ዘፋኞች ግጥምና ዜማ ይሰጥ እንደነበር አስታውቋል ::
ከኤልያስ ተባበል : ጸሀይ ዮሀንስ : ሻምበል በላይነህ ጋር በመሆን ራስ ቲአትርን ገና በአዲስነቱ ሕዝብ በሕዝብ እንዲሆን ያደረገው ነዋይ በትያትር ቤቱ እየሠራ ሙዚቃ ለማውጣት ፈለገ ::
“ተስፋ አስቆራጭ ነገር ነበር :: ሙሉ ካሴት ሠርቼ ነበር :: ሙሉ በሙሉ ወቅቱን የጠበቀና ግጥሞቹም ዜማዎቹም ጥሩ ነበሩ :: የሙዚቃ አዋቂዎችም አይተውት ሥራዎቼን ወደዋቸው ነበር :: ይህ ከሆነ ለምን አስቀርጬ ለሕዝብ አላደርስም ብዬ በመጓጓት ሥራዎቼን ይዤ ወደ ሙዚቃ ቤቶች ይዤ ቀረብኩ :: በእውነቱ ከሙዚቃ ቤቶች አካባቢ ያገኘኍቸው ምላሾች ተስፋ አስቆራጭ እና በሙዚቃው አለም እንድቀጥል የማያደርጉ ናቸው ”” ይላል ::
ይቀጥልና ያጋጠሙትን ፈተናዎች ይተርካል ”…..የጥበብ ሥራ ላይ ስትሆን የሚያበረታታ ነገር ያስፈልግሀል :: ደካማ ነገህ ተነግሮህ ጠንካራ ነገሮችህ ሲነገሩህ ደስ ይላል :: ሆኖም ካሴቴን ለማሳተም በፈለግኩበት ጊዜ በሙዚቃ ቤቶች አካባቢ ያገኘሁዋቸው ምላሾች አንተ ድምጽህ ቀጭን ስለሆነ ለዘፈኝነት አትሆንም ” የሚሉ ነበሩ ይላል ::
በወቅቱ አብሮት የነበርው ጻሀዬ ዮሀንስ እድል አጋጥሞት የመጀመሪያ ካሴቱን ለሕዝብ ሲያደርስ የነዋይ ተሳትፎ የነበረበት ሲሆን በሙዚቃ አሳታሚዎች ይደርስበት የነበረውን ”አንተ ለሙዚቃ አትሆንም ” ትችት ተቋቁሞ ራሱን በማሻሻል ጥረቱን ቀጠለ ::
”የኢትዮጵያ አርስቲስት ኑሮ ከማንም የተደበቀ አይደለም :: በወቅቱ ካሴቱን በራሴ ላሳትም ብል ምንም አቅሙ አልነበረኝም :: አንዳንድ አሳታሚዎች እንደውም ግጥሙን እና ዜማውን ስጠንና ሌላ ዘፋኝ ይዝፈነው ሁሉ እያሉ ሞራሌን እስከመንካት ቢደርሱም በእግዚአብሄር ጥረት የታንጎ ሙዚቃ ቤት ባለቤት በመጨረሻም እስኪ ይሞከር ብለው ካሴቴን አሳተሙልኝ ” ይላል ::
ራስ ትያትር በተቀጠረ በ 3ኛው አመት ዝነኛው ድምጻዊ ጸሀዬ ዮሐንስ ‘ተይ ሙኒት ‘ የተሰኘችውን አልበሙን አወጣ :: ከሕዝብ ጋር መልካም አቀባበልን ያደረገው ጸሐይ በአመቱ ፍንጭቷ የተሰኘውን ካሴት ደገመ ::
ነዋይ ደበበ ድምጽህ ለካሴት አይሆንም ተብሎ ሞራሉ ሳይነካ ጥረቱ ጥረቱ ቀጥሏል ”የኢትዮጵያ አርስቲስት ኑሮ ከማንም የተደበቀ አይደለም :: በወቅቱ ካሴቱን በራሴ ላሳትም ብል ምንም አቅሙ አልነበረኝም :: አንዳንድ አሳታሚዎች እንደውም ግጥሙን እና ዜማውን ስጠንና ሌላ ዘፋኝ ይዝፈነው ሁሉ እያሉ ሞራሌን እስከመንካት ቢደርሱም በእግዚአብሄር ጥረት የታንጎ ሙዚቃ ቤት ባለቤት በመጨረሻም እስኪ ይሞከር ብለው ካሴቴን አሳተሙልኝ ” ይላል ::
ነዋይ በወቅቱ ከጎኑ የነበሩትን ታዋቂ የሙዚቃ ባለሙያ ጋሼ ተስፋዬ ለማን እጅጉን ያመሰግናል :: የወቅቱ የራስ ትያትር ስራ አስኪያጅ የነበሩትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን መስርተው የነበሩት እኚሁ አርቲስት በነዋይ ደበበ የዛሬው የሙዚቃ ስኬቱ ላይ ትልቅ ድርሻ አላቸው :: ለዚህም ነው አርቲስት ተስፋዬ ለማን ”ጋሼ ” ብሎ የሚጠራቸው ::
”ጋሼ ተሰፋዬ ብዛት ያላቸው የሙዚቃ ጥበቦችን አስተምረውኛል :: በራስ ትያትር ውስጥም ሆነ ራሳቸው በመሰረቱት ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ትምህርቶችን እንድቀስም አድርገውኛል ” ሲል ምስክሩን ይሰጣል ::
ነዋይ እስኪ ሞክር ተብሎ የመጀምሪያ ካሴቱን በታንጎ ሙዚቃ ቤት አማካኝነት አወጣ :: በአሳታሚዎች ድምጽህ ቀጭን ነው ተብሎ ይፈራ የነበረው ነዋይ : ለዘፋኝነት ሳይሆን ለግጥምና ዜማ ደራሲነት ነው የምትሆነው የተባለው ነዋይ : አሳታሚዎች ፊት የነሱት ነዋይ ማንነቱን አሳየ :: በመጀመሪያ ሥራውም ከሕዝብ ጋር ለመተዋወቅ በቃ ::
በወቅቱ ነዋይ መሀል ፒያሳ ወደ ሚገኘው ታንጎ ሙዚቃ ቤት ይመላለስ ነበር :: የሚመላለሰው እንደሚባለው የመጀምሪያውን ካሴቱን ሲያወጣ በከቨር ሽያጭ በመሆኑ በየቀኑ የተሸጡትን ኦሪጂናል ከቨሮች ለመከታተልም : እንዲሁም ስለቀጣይ ስራዎችም ለመነጋገር ሲሆን በመጀምሪያው ካሴቱ የተማረኩት የታንጎ ሙዚቃ ቤት ሰዎች ሁለተኛውን ካሴት እንዲደግም አደረጉት ::
ሁለተኛው የነዋይ ደበበ ካሴት በሕዝብ ዘንድ እጅጉን የተወደደ ከመሆኑም በተጨማሪ የተለያዩ አድናቆቶችን ያጎርፉለት ጀመር :: በወቅቱ ከነበሩት የጥበብ ሰዎች መካከል የራስ ቲአትር የኪነጥበባት ክፍል ሀላፊ የነበረችው የቀድሞዋ የጸሐዬ ዮሀንስ ባለቤት አዳነች ወልደገብርኤል ለነዋይ ደበበ ቅርብ ነበረች ::
”የነዋይ ውስጡ ያለው ጥበብ ይገርመኝ ነበር :: በየቀኑ ጠዋት ወደ ትያትር ቤታችን የሙዚቃ ክፍል ይዞ የሚመጣው አዳዲስ ነገሮችን ነበር :: በተለይ ግጥምና ዜማዎቹ ከእርሱ የሚወጡ አይመስሉም ነበር ” ስትል አድናቆቷን ትገልጻለች ::
አርቲስት አዳነች ወልደገብርኤል የጸሀዬ ዮሀንስ የቀድሞ ባለቤቱ ስትሆን ከድምጻዊውም ኢየሩሳሌም የምትባል ልጅ አለቻት :: ከጸሐዬ ጋር ከተለያዩ በኍላም አርቲስቷ በጸሐዮ ዮሐንስ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ”የእሳት እራት ” የተሰኘ ፊልም መነሻ ሀሳብ ሰጪ በመሆን ማሰራቷ ይታወሳል :: ይህ ፊልም በ 1992 አካባቢ የወጣ ሲሆን ጸሐዬ ”የእኔ ታሪክ አይደለም : እኔን ለመጉዳት ሆን ብላ ያሰራችውና የተጋነነ ፊልም ነው ” ሲል አዳነችን መተቸቱን አስታውሳለሁ ::
ፊልሙን ከሰሩት መካከል ታዋቂዋ አርቲስት መሰረት መብራቴ (ጉዲፈቻ ፊልም ላይ ያለችው ቆንጆ ) ”ፊልሙን ሥሰራው የጸሐዬ ዮሐንስ ታሪክ መሆኑ እየተነገረኝ ስለሆን አልቅሻለሁ ” ብላ ራሴው በምሳተፍበት ጋዜጣ ላይ መግለጫ መስጠቷም ይታወሳል :: ይህ ፊልም ከወጣ በኍላ ጸሀዬ ዮሀንስ ”ተበድዬስ ይቅርታ አልልም ” የሚለውን ተወዳጅ ዘፈኑን በቴሌቭዥን አስቀርጾ ለሕዝብ ወዲያው ማድረሱን ተከትሎም ለአዳነች የተሰጠ ምላሽ ነው ተብሎም ተተችቶ ነበር ::
ወደ ነዋይ ታሪክ ስንመለስ 2ኛ ካሴቱን ከታንጎ ሙዚቃ ቤት አውጥቶ ከስኬት እና ከገንዘብ ጋር ከሙዚቃ ቤቱ ይዞ የሄደው የአሁኗን የልጆቹን እናት ባለቤቱን ጭምር ነበር :: ብዙ የአርቲስቶቻችን የፍቅር ሕይወት ግልጽ ስለማይሆን እንጂ በዚህ ዙሪያ ላይ ብዙ ማለት ይቻል ነበር :: ሆኖም የነዋይ ባለቤት ሙስሊም ከመሆኗ አንጻር ማስታወሻ የሚባል የኪነጥበብ መጽሔት ”ነዋይ ባለቤትህ ሙስሊም ናት :: አንተ ደግሞ ክርስቲያን ናት :: አስባችሁበታል ወይ ? የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነዋይ ”አዎ :: ባለቤቴ ወላሂ ስትለኝ አምናታለሁ እኔ ደግሞ ኪዳነምህረትን ስላት ታምነኛለች ” ያለው መልሱ እስከአሁን ከአእምሮዬ አይጠፋም ::
“ዘፈኖቼ ሁሉም የየዘመኑ ውለታና ትዝታ አለው :: ሁሉም የየዘመኑና አስተዋጽኦ ሁሉ አለውና ይህኛው ከዚኛው ለማለት ባልደፍርም ሁል ጊዜ እኔ መጀመርያ ስራ የጀመርኩበት ሥራ ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀኝ ነውና “እሸት በላሁኝ”: “የጥቅምት አበባ” ከሌሎቹ ለየት ይልብኛል :: ከዚያ ውጭ ያሉት በሂደት ላይ ስለሆነ አንዱ ከአንዱ ለመለየት ያስቸግራል::” የሚለው ነዋይ ደበበ በ30 አመት የሙዚቃው አለም ቆይታው ክፉንም ደጉንም አይቶአል
“የነዋይ ደበበ አድናቂ ነኝ :: ከዘፋኝነቱ ውጭ ባህሪው እንዲሁም የግጥምና ዜማ ደራሲነቱን አደንቃለሁ :: ብዙ ጊዜም መድረክ ላይ የእርሱን ዘፈኖች እዘፍናልሁ :: ባጠቃላይ አፌን የፈታሁት በነዋይ ደበብ ሥራዎች ነው ማለት እችላለሁ”
- ቴዲ አፍሮ
“በ 1994 አ .ም ከአሌክስ ጋር በጋራ በሰራነው ካሴት ላይ ስለ ሀመር የዘፈንኩበት ዘፈን አለ :: ኢቫንጋንዲ የሚለው :: ይህን ስራ ከወደዱት አርቲስቶች መካከል አድናቆቱን የሰጠኝ ነዋይ ደበበ ብቻ ነው :: ነዋይ ስለሀመር እኔ ሳልዘፍን አንተ ስለዘፈንከው አመሰግናለሁ ብሎ አብረታቶኛል :: በተለይ ለወጣት ድምጻዊያን ሞዴል ነው ::”
- ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ
በርከት ከት ያሉ ወጣት ድምጻዊያን ስለነዋይ የሚናገሩት አንድ አይነት ነግሮችን ነው :: ከአሁኑ ዘመን ወጣት ድምጻዊያን መካከል አብዛኞቹ አርአያ አድርገው የሚጠቅሱት ነዋይን ነው :: ሙዚቃ ቤቶችም ቢሆኑ የነዋይን ካሴት በጉጉት ነው የሚጠብቁት :: በ 1994/5 ነዋይ ”ደሀ ናት ” የሚለውን ካሴቱን ሲያወጣ በኢትዮጵያ ውስጥ የኮፒ ራይት ህግ ባለመኖሩ አንዱ በሰራው ያልሰራው የሚጠቀምበት ጊዜ ነበር :: ያን ጊዜ አሳታሚ ሙዚቃ ቤቶች በአንድ በኩል ኦሪጅናል በሌላ በኩል ቅጂ ካሴት የሚሸጡበት ወቅት በመሆኑ ለነዋይ ደበበ ካሴት ተገቢውን ክፍያ ከፍሎ የሚያከፋፍል ሙዚቃ ቤት ጠፋ :: ታዋቂው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት በኮፒ ካሴት ሽያጭ የተነሳ ዋናውን ሳልመልስ እከስራለሁ በሚል ራሱ ካሴቱን አላከፋፍል አሉ :: የዛን ጊዜ ነበር አዳነች ወ /ገብሬል ለነዋይ ደበበ ትልቅ ሥራ የሰራችው :: ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምታውቁት ኮፒ ካሴት 7 ብር እና 6 ብር ነው የሚሸጠው ::: ኦርጂናሉ ደግሞ 13 ብር :: አዳነች ከነዋይ ጋር በመመካከር የኦርጂናሉን ካሴት ዋጋ ወደ 10 ብር ቀንሳ እንዲሸጥ አደረገች :: ለ 3 ብር ብሎ ቅጂ ካሴት የሚገዛ የለምና ካሴቱ እንደጉድ ተሸጠ :: የነዋይን ይህን ካሴት ተከትሎ በርካታ አርቲስቶች የካሴት መሸጫ ዋጋቸውን ወደ 10 ብር ዝቅ አድርገውት እንደነበር አስታውሳለሁ :: ጥሩ ፈጠራ ነበር። ሰላም ቆዩኝ።

No comments:

Post a Comment