የጠፋው ትውልድ እና የታህሪር ናፍቆት – ተመስገን ደሳለኝ
(ከርዕሰ ጉዳያችን በፊት ጥቂት ‹‹ስለ ጥቁር ሰው››)
ኢትዮጵያ ሀገሬ የአፍሪካ መገኛ ናት
የነፃነት አርማ የሉአላዊነት
ያናብስቶች ምድር የአርበኞች ተራራ
በአለም አደባባይ ግርማሽ የተፈራ
የጥበብ ምልክት የፍቅር ማደሪያ
ኑሪ ለዘላለም ቅድስት ኢትዮጵያ
ዳግማይ ምኒሊክ፣ ዳግማይ ምኒሊክ
ምኒሊክ፣ ምኒሊክ፣ ዳግማይ ምኒሊክ…
(እነዚህን ስንኞች ያገኘሁት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ጥቁር ሰው›› ለተሰኘው ሙዚቃው የሰራውን የቪዲዮ ክሊፕ (ስዕል ለበስ ሙዚቃ) ከሁለት ቀን በፊት በሂልተን ሆቴል ባስመረቀበት መድረክ ከበርካታ አጃቢዎች ጋር ለበአሉ ድምቀት ይሆን ዘንድ ከዘመረው አዲስ መዝሙር ነው)
በዕለቱ በአዳራሹ የነበረው ድባብ እና ሀገራዊ መነቃቃት ልብን ከማሞቅም አልፎ ብርታትን የሚሰጥ ነበር። በዚህ በተዋጣለት ዝግጅት ላይ አባት አርበኞች በእንግድነት ከመገኘታቸውም ባሻገር፣ መድረክ ላይ ወጥተው የሀገር አንድነት ያስከበሩበትን ‹‹ወኔ ቀስቃሽ›› ፉከራ /ቀረርቶ/ ለታዳሚው አቅርበዋል። አባት አርበኞችን ባሰብኩ ቁጥር የሚገርመኝ ኢህአዴግም ሆነ የቀድሞዎቹ ሁለቱ መንግስታት አባት አርበኞችን ለፖለቲካ ትርፍ ካልሆነ በቀር በመንግስታቸው አስበዋቸው አለማወቃቸው ነው፡፡ ቴዲ አፍሮ ግን በግሉ አስቧቸዋል፡፡ የክብር እንግዳም አድርጎ ለውለታቸው ያለውን አክብሮት ገልጿል፡፡ ‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ›› ሲል ምን ማለቱ እንደሆነም የኋለኞቹን ወደፊት አምጥቶ ለማሳየት ሞክሯል፡፡
በነገራችን ላይ የቴዲ አፍሮ አልበም ለአድማጭ ከቀረበ በኋላ የአልበሙ መጠሪያ ከሆነው ከ‹‹ጥቁር ሰው›› ዘፈን ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ‹‹እንክርዳድ›› ፍለጋ ሲዳክሩ ማየቱ አሳዛኝ ነው-ለእኔ። ‹‹አባ ነፍሶ›› የባልቻ ፈረስ ስም እንጂ አባቱ አይደለም ከሚለው ጀምሮ ለአይን የማይሞላ ክርክር አንስቶ፣ ተራ ማረሚያ እስከመስጠት ሲሞከር ማየቱም አሳዛኝ ነው። ሌላው ቢቀር እንዲህ እንደዋዛ ሀገር የቆመበት ታሪክ ሲፈራርስ፣ የዩንቨርሲቲዎቻችን የታሪክ ፕሮፌሰሮች በ‹‹እናውቃለን-ግን ብንናገር እናልቃለን›› ፍርሃት ተሸብበው፣ አይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ በሆኑበት በዚህ የትዝብት ዘመን ‹‹ምኒሊክ ባይኖር ኖሮ፣ ባልቻ ባይጀግን ኖሮ፣ አሉላ ባይቀድም ኖሮ፣ ሀብተጊዮርጊስ ከፊት ባይሆን ኖሮ፣ መንገሻ ባይዋጋ ኖሮ…ዛሬ ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያዊ አይሆንም ነበር›› የሚል ታሪክ ነጋሪን ¬‹‹ጥቁር ሰው›› ሙዚቃን ያህል ወደ ጎን ገፍቶ ‹‹ቴዲ አፍሮ የአባት ስምን ገደፈ›› የሚል ነቀፌታ መሰንዘሩ ቢያንስ ቅንነት የሚጎለው ይመስለኛል-በእኔ እምነት፡፡
…ከአቶ መለስ ዜናዊ ‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው›› እስከ አቦይ ስብሃት ነጋ ‹‹ሀገር ያፈረሰው ምኒሊክ ነው›› ድረስ ያሉ አፍራሽ ድምፆችን ላለፉት ሃያ አንድ አመታት እስክንደነቁር ሰምተናል፤ ቴዲም ሰምቷል፤ ተቺዎቹም ሰምተዋል። ነገር ግን ‹‹የካፊያ ዝናብ›› ያህል እንኳ ጉልበት ከሌለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምላሽ ውጪ፣ ለህወሓት እንዲህ በይፋ እና ‹‹ትውልድ ተሻገሪ›› ኃይል ባለው ሁኔታ መልስ የሰጠ የለም። ወይም የዳግማዊ ምኒሊክን የሀገር ባለውለታነት ጠቅሶ የተከራከረ አላየንም። ቴዲ ያደረገው ያንን ነው። ያውም በግለሰብ ደረጃ። በቃ! ተቀበልነውም አልተቀበልነውም በመሬት ያለው እውነት ይህ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለእኔ ዋነኛ አሳሳቢው ጉዳይ ‹‹የባልቻ አባት ሳፎ እንጂ አባ ነፋሶ አይደለም›› የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ሳይሆን ይህች ሀገር እስከመቼ ድረስ እንዲህ በግለሰቦች የተናጥል ትግል ህልውናዋ ሊጠበቅ ይችላል? የሚለው ስጋት የሚቀድምብኝ። በተጨማሪም ታሪክ ከሚፋለስ የአባት ስም መፋለስ በስንት ጣዕሙ የሚያስብል ነው፤ ምክንያቱም የዚህ አይነቱ ፍልሰት ታሪክን አይቀይርምና፡፡ ደግሞስ በአባት ስም መፋለስ የጠፋ የሀገር ታሪክ ስለመኖሩ ሰምቶ የሚያውቅ ማን ይሆን? …እንጃ፡፡
የሆነ ሆኖ የጥቁር ሰው ሙዚቃ ክሊፕ የምረቃ ፕሮግራም ከሂልተን ጥቂት መቶ ሜትር ዝቅ ብሎ የሚገኘውን የሰማዕታት ሃውልት እና ከሆቴሉ ጥቂት መቶ ሜትር ከፍ ብሎ የሚገኘውን ቤተ-መንግስት በእዝነ ህሊና የሚያስቃኝ ነው፡፡ ለ‹‹ሰማዕታት›› መፈጠር ምክንያት የሆነው ቤተ-መንግስቱም ሆነ የቀይ ሽብር እና የነጭ ሽብር ሰማዕታቶች ስለታሪካቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ስለምኒሊክ እና ኢትዮጵያም እንዲሁ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ተረኛው ባለቤተ-መንግስቱ ‹‹ዕድል ፈንታው›› ቤተመንግስት፤ ሰማዕታቱ ደግሞ በግዙፉ ሀውልት ድንጋይ ስር ለምን እና እንዴት እንደሆነም ሁለቱም በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ለዚህም ነው አንዱ የሌላኛውን መንፈስ የሚረብሸው፡፡ በሀውልቱ ላይ ‹‹መቼም የትም እንዳይደገም›› የሚለው የፅሁፍ መልዕክትም ከታይታ እንዳላለፈ ሰማዕታቱ በአደባባዩ ስር ሆነው በተለያየ ጊዜ ታዝበዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በድህረ ምርጫ 97፡፡ ምክንያቱም እንዲህ እንደወጡ የቀሩት መንግስቱ ኃ/ማሪያም የተባሉ ወታደርን መለስ ዜናዊ በተባሉ ታጋይ ለመተካት አልነበረም፡፡ እናም የቴዲ አፍሮ ‹‹አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ›› የሰማዕታቱ ድምፅ ነው፤ ሌላ አይደለም፡፡
ከዚህ ውጭ በእዚህ በእኛ ዘመንም ህወሓት በዛው በፀረ ምኒሊክ አቋሟ እንደፀናች ነው፡፡ ለምሳሌ የህወሓት አጋፋሪና ገራፊ የነበረ አንድ አንጋፋ ታጋይ በዚሁ አመት ‹‹ፍኖተ-ገደል-የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ታሪካዊ አነሳስና ጉዞ የመጀመሪያ ዓስር ዓመታት (1967-1977 ዓ.ም.)›› በሚል ርዕስ በፃፈው ‹‹ጭራና ቀንድ›› አልባ መጽሐፍ ስለምኒሊክ አፍራሽነትና አይረቤነት እንዲህ ይላል፡-
‹‹ከቴዎድሮስ እና ከዮሐንስ ይልቅ የምኒሊክ ወደ ስልጣን መምጣት ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ የገጠሟት ሰፊና ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ጐሳዊ ችግሮች ያስከተለ ክስተት ነበር። ኢትዮጵያን በሚገርም ጀግንነት እና ልበ ሙሉነት ማስከበሩ ተረስቶ በሴራ እና በክህደት የተካው የአፄ ሚኒሊክ ስራ በኢትዮጵያ ህዝቦች ቅራኔን ቀስቃሽ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ግዛቶችን ለውጭ ሀይሎች ፈርሞ መስጠት፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ፤ በየቦታው ተደጋግሞ የሚከሰት የጎሳ ግጭት እና የማያባራ የኢኮኖሚ ድቀት አገሪቷን ለረዥም ጊዜ ሲያጨናንቁ ታይቷል፡፡
አፄ ምኒሊክ እና ተከታዮቹ ወደ ስልጣን ሲመጡ ስለሀገሪቷ የተጠራቀመ ባህላዊ እና ታሪካዊ ገፅታ እምብዛም አልተጨነቁም። ስልጣን እንደያዙ በሀገሪቱ ባሉ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጐሰኝነትና አድልዎ ፈጥሮ ለማዋከብ ጊዜ አልፈጀባቸውም››
እርግጠኛ ነኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህንን አንቀጽ ያነበበ ደራሲው በሌላ ሃገር ስለሚገኝ ንጉስ እንጂ ስለኢትዮጵያዊው ምኒሊክ ነው የሚያወራው ብሎ ለማመን ይቸገራል፡፡ ነገር ግን ቢጎመዝዘውም ማመን አለበት፡፡ ታጋዩ እያወራ ያለው ስለአድዋው ምኒሊክ ነውና፡፡ መቼም ፀሀፊው የኢትዮጵያን ታሪክ በርዞ ከፃፈው ከህወሓት የታሪክ መፅሀፍት ጋር በፍቅር ለመውደቁ ነጋሪ አያስፈልገንም። እንዲህ አይነት እርስ በእርሱ በሚጣረስ ትርክት የተሞላ፣ የፈጠራ መጽሐፍ በአክሱም ሆቴል በተመረቀ ጊዜ ሌላኛው የህወሓት የርዕዮተ-አለም አርክቴክት አቦይ ስብሃት የክብር እንግዳ ሆነው ተገኝተው ሲያበቁ መጽሐፉ የኢትዮጵያን ታሪክ ተአማኒነት ባለው መልኩ እንዳብራራ መሰከሩ። ነገር ግን የመፅሀፉ ተአማኒነት እና ሚዛናዊነት የቱ ጋ እንደሆነ አላብራሩም፡፡ (ደግነቱ የሀገሪቱ አንድነት እንደፀና ይቀጥል ዘንድ ይህ አይነቱ የፈጠራ ታሪክ እውቀት የህወሓት አመራር እንጂ የትግራይ ህዝብ አለመሆኑ ነው) እናም ይህ መፅሀፍ በራሱ ሊቆም የማይችል ስለመሆኑ ከጠቀስኩት አንቀፅ ውስጥ ብቻ ጥቂት የማይባል እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነገር መዞ ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ‹‹አፄ ምኒሊክ እና ተከታዮቹ ወደ ስልጣን ሲመጡ…›› የሚለውን ብናስተውል ደራሲው ምን ለማለት እንደፈለገ እንደማያውቅ ይገባናል። ለነገሩ ህወሓትም አያውቀውም። ወይም ሁለቱም ሊያውቁት አይፈልጉም። ምክንያቱም ምኒሊክን ‹‹በጎሳ መከፋፈል›› እና ‹‹በአድሎአዊ አስተዳደር›› ለመክሰስ በተጠቀሙበት ምዕራፍ ‹‹ምኒሊክ እና ተከታዮቹ…›› የሚል እውነት ሰንቅረዋል፡፡ መቼም በሀገራችን የታሪክ ትርክት የምኒሊክ ዋነኛ ሹሞች ራስ መንገሻ እና ራስ አሉላ…ከትግራይ፤ ራስ መኮንን.-ከአማራ፤ ራስ ጎበና፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዴነግዴ፣ የጅማው አባጅፋር፣ የወለጋው ኩምሳ (ገብረእግዚአብሔር) ሞረዳ… የመሳሰሉት ከኦሮሞ የሚጠቀሱ ናቸውና፡፡ ለዚህም ነው እዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄ ‹‹የጎሳ ግጭት እንዲፈጠር ያሴሩት የሶስቱ ብሄር ተወላጆች ናቸው ወይ ለማለት ነውን?›› የሚል የሚሆነው፡፡ …ለዚህ ጥያቄ ህወሓት መልስ ይኖረው ይሆን? በእርግጥ ለጊዜው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የቴዲ አፍሮ ‹‹ጥቁር ሰው›› ግን ምኒሊክንም ሆነ ሹሞቻቸውን ለሚያብጠለጥለው፣ አሊያም አድዋን ከአቶ መለስ የትውልድ መንደርነት ባለፈ አሻግሮ ማየት ላልቻለው የእኔ ትውልድ መሳጭ በሆነ መልኩ እውነተኛውን ታሪክ ቢያንስ በጨረፍታ የሚያሳይበት ነው፡፡ በተለይ ከ400ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት በነፃ የተበተነውን የዘፈኑ በምስል የተደገፈ ገለፃ (ክሊፕ) ከ100 አመት በፊት የሆነውን ያንን የመላው ጥቁር ህዝብ ታላቅ ገድል ዛሬ የሆነ ያህል እንዲሰማን የሚያደርግ መንፈስ የመጫን ኃይል አለው።
…በእርግጥ የዚህ ፅሁፍ አላማ ስለምኒሊክ ብፅእነት መስበክ ወይም እርኩሰት መከራከር አይደለም፡፡ አላማው ስለጠፋው ያ ትውልድ፣ እየጠፋ ስላለው ትውልድ እና በታህሪር (የግብፃውያን የነፃነት አደባባይ) ናፍቆት ስለተቃጠለው ትውልድ ማውራት ነው፤ ወይም መናገር ነው፡፡
ያ ትውልድ
ከሞላ ጎደል የ1960ዎቹ ትውልድ ነው ‹‹ያ ትውልድ››፤ መቼም ስለትውልዱ ባተሌነት፣ ከርታታነት፣ ግብታዊነት፣ የአላማ ፅናት፣ የሀገር ፍቅር፣ የስልጣን ፍቅር፣ የሴራ ችሎታ፣ የጭካኔ አባትነት… ጂኒ ቁልቋል ብዙ ተብሏል፡፡ ያን አልደግመውም፡፡ ነገር ግን የእኔ ትውልድ እንዲህ ሀገር እንደ ጓዝ ነቅሎ በሚሰደድበት ደረጃ ይደርስ ዘንድ፣ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ያ ትውልድ ስለመሆኑ መከራከሩ ውሃ ቢወቅጡት… ነው፡፡
እዚህ ጋር ግን አንድ እውነት መገለፅ አለበት፡፡ የያ ትውልድ የ‹‹ስደት›› ምክንያት ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ጦስ ስለመሆኑና የዚህ ትውልድ ደግሞ ከፖለቲካው እኩል ኢኮኖሚያዊ ጥያቄም እንዳለበት፡፡ በእርግጥ ይህ ጥያቄም ቢሆን ዞሮ ዞሮ ከስርዓቱ ራስ አይወርድም፡፡ ወይም መውረድ የለበትም፡፡ ለመራብም ሆነ ለመታፈን ተጠያቂው መንግስት ነውና፡፡
የሆነ ሆኖ ያ ትውልድ የ1966ቱን ታላቁን አብዮት ተከትሎ በተነሳ ልዩነት (ልዩነቱ የርዕዮተ-አለም ሳይሆን የፓርቲ ነው) በአደባባይ በተለይም ስልጣን ከያዘው አብዮታዊ ሰደድና መኢሶን ጋር በጥይት ተጨፋጭፏል፡፡ በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ደግሞ አማፂያኖቹ እራሳቸው እርስ በእርስ እንዲሁ ተናንቀው ወድቀዋል፡፡
እናም የከተማውን የጠመንጃ ትግል ተከትሎ የፖለቲካ ስልጣን የያዘው ኃይል በወሰደው የጅምላ ጭፍጨፋ ብዙዎች ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በክርክር እና በአመቻማች ፖለቲካዊ ውይይት ሊፈቱ ይችሉ የነበሩ ልዩነቶቹን ካለዋጋቸው ከፍ አድርጎ በማጎኑ እርስ በእርሱ ተላለቀ። የዚህ የአንድ ብሩህ ትውልድ ማለቅ ብቻውን ሀገሪቱን የልባም ምሁራን ምድረ በዳ እንድትሆን ዳርጓታል። ከዚህ አሳዛኝ ሀገራዊ ዕውነት ባለፈ የዚያ ትውልድ ቀዳሚ የመንፈሱ ወካዮች ከምድረ-ገፅ መጥፋት እና መሰደድ ከራሳቸው የብሄር ፍላጎቶች ውጪ ሌሎች ማህበረሰባዊ እሴቶችን መመልከት ላዳገታቸው ጠርዘኛ ልሂቃን የፖለቲካው መድረክ የተመቻቸ ሆነ። ግዙፍ ሀገራዊ ራዕይ በነበረው ትውልድ መቃብር ላይ ‹‹ስልጣን ካልሰጣችሁን እንገነጠላለን›› የሚሉ፣ ከላሽ ታሪክን የሚያቀነቅኑ፣ እንወክለዋለን ባሉት ብሄር ላይ ተፈፅመዋል የሚባሉ በደሎችን በማጦዝ ከራሳቸው ጩኸት ውጪ የሌሎችን ዜጐች የጋራ በደል መስማት ያዳገታቸው ብሄርተኞች ማበብ ያዙ። የግብታዊውን ትውልድ ስር-ነቀልተኛ ፅሁፎች በማንበብ ራሳቸውን ለማብቃት የታተሩት የህወሓት ብላቴኖችም፤ በታላላቆቻቸው ደም ላይ የቆመውን ስርዓት አፈረሱት። ይሄን የሀገራችንን ተጥመዝማዥ የፖለቲካ ታሪክ ‹‹ምፀታዊ›› ከማለት ወዲያ ምን ልንለው እንችል ይሆን?
እነሆም በኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዘንድ የስደት ሀሁ በዚህ መልኩ ነበር በልቦናቸው ያደረው፡፡ ለስደት ተመራጭ እና ቀላል የነበረችው ሀገር ደግሞ ፍፁም አምባገነን የነበረው የጄነራል ጃፋር ኔመሪ ሱዳን ናት፡፡ በነፍስ አድን ሽሽትም ሱዳን የደረሰውን ኢትዮጵያዊ UNHCR የተባለው አለም አቀፍ ድርጅት ግዙፎቹን የስደተኞች ካምፕ ከፍቶ በሰፊው ከመቀበል አላመነታም፡፡ ኡምራ ኩባ አንድ እና ሁለት፣ ትዋዋ፣ ኡማ ሰቃጣ፣ ትንደባ፣ሃዋዝ፣ አምዳይት፣ ወዲል ሂለው… የመሳሰሉት የስደተኞች ካምፕ በወቅቱ ከመሸሸጊያነት ባሻገርም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መመልመያ እና መስበኪያ አውድ እስከመሆን ደርሰው ነበር፡፡
ከዚህ ውጭ በዛ ዘመን በጦርነቱ የደነገጡ፣ የተማረሩ እና የእርሻ መሬታቸውን ለማረስ አዳጋች ከሆነባቸው አርሶ አደሮች በቀር ሁሉም ስደተኛ የፖለቲካ እንጂ የኢኮኖሚ አይደለም። ለነገሩ ጦርነቱም ቢሆን መነሻው የፖለቲካ ጥያቄ ነውና የአርሶ አደሩም ስደት ከፖለቲካው ጋር መያያዙ አይቀሬ ነው፡፡
ሌላው የያ ትውልድ ሰንኮፍ ከመቻቻል ልዩነትን እንደ ምክንያት አድርጎ በጥላቻ የመተያየት ባህሉ ነው። ለዚህም የዛ ዘመን ታሪክ ተጋሪ የሆኑት የዚህ ዘመን ገዢዎችም፣ በዚህ ዘመን ‹‹መሀል ሰፋሪ››ነትን እና በሃሳብ መለየትን እንደ ‹‹ጠላት›› ቆጥረው እስከ አፍንጫው የታጠቀ ሠራዊት የሚያሰልፉበትን ፈሊጥ ማየቱ ብቻ በቂ ነው።
በአናቱም ያ ትውልድ ከሚወቀስበት ዋነኛ ምክንያት አንዱ የአባትነት ወይም የሽማግሌ ሚና የመጫወት ባህልን ጨርሶ ከሃገሪቱ ማጥፋቱ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ትውልዱ ይከተለው የነበረው ርዕዮተ አለም ከወጣበት ማህበረሰብም ሆነ ካደገበት ባህል ፍፁም የተለየ በመሆኑ ነው። እናም የዚህ ርዕዮተ አለም አራማጆች የሃሳብ መለየትን በሀይል ለመፍታት በእጅጉ የቀረቡ ሲሆኑ፤ እምነታቸውንም ለማስረፅ ማንኛውንም መስዋዕትነት ይከፍላሉ፤ ወይም ያስከፍላሉ። ለምሳሌ በዚህ ሃሳብ (በሶሻሊዝም) ግንባር ቀደም ተደርጋ የምትወሰደው ሩሲያን የመራውና በ1953 እ.ኤ.አ የሞተው ጆሴፍ ስታሊን የሩሲያን አብዮት ያሳመረው ተቀናቃኞቹን ‹‹ከላሾች›› እና ‹‹አደሀሪያኖች›› ሲል ወንጅሎ በመጨፍጨፍ እና ወደ አደገኛው ሳይቤሪያ ለግዞት በመላክ መሆኑን አይተን ስንመለስ፤ በዚህችው ሀገራችንም ይህን ሁኔታ ሳይቀነስ፣ ሳይጨመር ለመድገም የተሞከረበትን ዘመን ዋጋ ከፍለን ተሻግረናል። በደርግም በተቀናቃኝ ኃይሎችም። ምክንያቱም ሁሉም ‹‹ጠላቴ›› ለሚሉት ኃይል ምላሻቸው የእሳት ላንቃ ነውና።
በእርግጥ ያ ትውልድ ከዚህ ውጭ አርአያ መሆን የሚችልባቸው በርካታ ተሰጥኦዎች እንዳሉት መካድ አይቻልም። ለምሳሌ ላመነበት አላማ እፍኝ የማትሞላ ቆሎ ቆርጥሞ ጦር ሜዳ ለመዋል አንዳች አለማመንታቱን ከትውልዳችን ጋር ብናነፃፅረው የመለኮት እንጂ የሰው ጽናት ላይመስለን ይችላል። ይሄኔም ነው ያ ትውልድ እና ይሄ ትውልድ የመንፈስ ተወራራሽነት እንደሌላቸው በግልፅ የሚገባን፡፡
አምላጭ ትውልድ
የያ ትውልድ ተተኪ ነው። በአብዛኛው ‹‹አምላጭ ትውልድ›› (Escapist generation) እየተባለ የሚጠራው። ይህንን መካድ አይቻልም። ከሁለት ሳምንት በፊት የ‹‹መለስ አምልኮ›› በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ዳሰሳውን ያቀረበው የታሪክ ምሁሩ ብርሃኑ ደቦጭ የህዝቡን /የትውልዱን/ አድርባይነት እንደማልተች ጠቅሶ ሲያበቃ ‹‹ተመስገን የሚያንቆለጳጵሳቸው ‹ወጣቶች›ም የት ናቸው? ቢባል በቂ መልስ ያለው አይመስልም›› ሲል ተችቶኛል። ሆኖም ምን ያህል አጥጋቢ እንደሆነ እርግጠኛ ባልሆንም ለወዳጄ ወቀሳ የሚሆን መልስ ከወደታች ለማቅረብ እሞክራለሁ። አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ያ-ትውልድን ከአደባባዩ ያጠፋውን ቀይና ነጭ ሽብርን እንዲሁም የህወሓት/ሻዕቢያ- ደርግ ጦርነቶችን እየሰማ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያሳለፈው ድህረ- ያ-ትውልድ፤ ፖለቲካዊ መነቃቃቱን ያገኘው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት ሊወስዳቸው በሞከራቸው ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ግፊት መሆኑ ነው። ይሄን አንዳንዶች ‹‹የሽግግር ዘመን ትውልድ›› ብለው የሚጠሩት፤ አንድም በደርግ ማምሻ ዘመን ላይ ጉልበቱ ቀና ማለት መጀመሩ፣ በሌላ ጫፍ የህወሓት መሩ ስርዓት ‹‹የኤርትራን መገንጠል›› መሰል ጉዳዮች ላይ የወሰደውን አቋም በአደባባይ ለመቃወም በመድፈሩ ነው። የዚህ ትውልድ ተፅዕኖ በፖለቲካው በኩል ብዙም አልታይም። ምናልባት በ1980ዎቹ አጋማሽ የተፈለፈሉት ፓርቲዎች ለየራሳቸው ለማድረግ አለቅጥ ስለተቀራመቱት ይሆን? ወይስ እየሰማና እያየ ያደገው የደርግ እቀባ፤ ግድያና የግዳጅ ወታደራዊ ዘመቻ ከፈጠሩበት “Trauma” መላቀቅ አቅቶት? የዚህ መልስስ ስንተኛው ሰማይ ላይ ይሆን እርቆ የተሰቀለው? … በቀጣዩ አንቀጽ ግን ‹‹አምላጭ›› እየሆነ ስላለው የትውልድ ተጋሪዬ መነጋገራችንን እንቀጥል።
በእርግጥም ከዚህ ከእኔ ትውልድ ከፊሉ ምንም እንኳን በመገዳደል የሚያምን ባይሆንም ላመነበት ነገር ቆሞ የመጣውን በፀጋ ለመቀበልም ዝግጁ አይደለም። በዚህ ዘመን የያ-ትውልድ ተፅዕኖ ፅሁፎችን በመበተን እና የሀገር ውስጥ የተቃውሞ ቡድኖችን በሎጀስቲክ በመደገፍ ላይ ብቻ የቆመ ይመስላል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያለው ተፅዕኖ እየተሸረሸረ የመጣም ይመስለኛል። ቢርበው ወይም ስራ ቢያጣ ይህ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ሀገር ከሚመሩት ሰዎች ለማወቅ ከመሞከር ይልቅ ወደ ቤተ አምልኮ ሄዶ ፈጣሪውን መለመን ይቀናዋል። መቼም በዚህ ዘመን አብዛኛው ሰው ወደ ቤተ አምልኮ የሚሄደው ለምስጋና አይደለም። ከገባበት ችግር ይላቀቅ ዘንድ በፀሎት ለመለመን እንጂ።
ከቤተ አምልኮ ቀጥሎ ያለው የችግሩ መፍቻ ብቸኛ አማራጩ ደግሞ ‹‹ስደት›› ነው። እናም ሀገር በመልቀቅ ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል ችግሩ ምን ያህል የከፋ መሆኑን የሚያሳየን ለስደት እነጅቡቲ እና የመን ሳይቀሩ መመረጣቸው ነው። በተጨማሪም ከሀገሪቱ የታወቀ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ሱዳን ስራ ፍለጋ የሚሄደውን ኢትዮጵያዊ ቤት ይቁጠረው።
በሱዳን ምን ይገጥመው ይሆን? ለሚለው ጥያቄ በሚቀጥለው ሳምንት በጁባ የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ የኢትዮጵያውያኖች ህይወት ምን እንደሚመስል ጨርፈን ወደ ‹‹ታህሪር ናፍቂዎች›› እንመለሳለን። ምክንያቱም በ1997ቱ ምርጫ ደሙ መሞቅ የጀመረው የኔ ትውልድ መንፈስ ከያ-ትውልድ አቻው በምን ይለያል? ብዬ ሳስብ የሚመጡልኝ የቀዩ አደባባይ እና የታህሪር ተመሳስሎ /analogy/ ነው። የቀደመው ትውልድ ወደ ቀዩ አደባባይ አማትሯል። ይሄ-ትውልድ ደግሞ ወደ ታህሪር እየተመለከተ ነው። የታህሪር መንፈስ ከመገዳደልና ከመተጋገድ የነፃ ነውና።
ለዚህ ምዕራፍ መዝጊያ ይሆን ዘንድ እና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከሀገር ከመሸሽ ይልቅ ወደ ሀገር ተመልሶ የድርሻን ለመወጣት ምሳሌ እንዲሆነን የታዋቂውን ደራሲ አቤ ጉበኛን መጨረሻ አይተን በቀጠሮ እንለያይ። ነገሩም እንዲህ ነው። አቤ አብዮቱ ሲፈነዳ የትምህርት እድል አግኝቶ አሜሪካን ሀገር ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ የፈነዳው አብዮት እሱንም እንደሚመለከተው ስለገባው ወደ ሀገሩ ለመመለስ ጓዙን መሸካከፍ ጀመረ። በዚህ ጊዜም ጓደኛው የነበረ አሜሪካዊ ወደ ኢትዮጵያ መሄዱ አደጋ እንዳለው በማወቁ አቤን ሃሳቡን እንዲቀይርና እንዳይሄድ መከረው፡፡ ‹‹እንዴት እንዲህ አደገኛ በሆነበት ሰዓት ወደ ሀገርህ ትሄዳለህ? ግዴለም ይቅርብህ እዚህ እኔ ነገሮችን ላመቻችልህ?›› ሲል አግባባው። አቤም መለሰለት ‹‹አይሆንም! ከሀገሬ ህዝብ ጋር በመሆን ከአብዮቱ የሚመጣውን መከራውንም ሆነ አዱኛውን ካልተካፈልኩ ምኑን ኢትዮጵያዊ ሆንኩ?›› አሜሪካዊውም በጣም ተገረመ። ምክንያቱም አቤ በኃይለሥላሴ ዘመን በተደጋጋሚ ጊዜያት ለእስር መዳረጉን ያውቃል። እናም በመደነቅ እንዲህ አለው ‹‹መቸገር የማይሰለችህ!›› አቤም እንደፎከረው ሳይውል ሳያድር ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ከዛስ? ከዛማ በወቅቱ ሀገሪቱ በግራ ዘመም ፖለቲካ ከንፋ አገኛት፡፡ የግራ ዘመም ፖለቲካ ደግሞ እንደ አቤ አይነቶቹን የ‹‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ›› አቀንቃኞች በመአት አይኑ ማየቱ ሳይታለም የተፈታ ነው። …ከዕለታት አንድ ቀንም አቤ መርካቶ አካባቢ በብረት ዱላ ተደብድቦ ሞተ። ለሀገር ዋጋ መክፈልም ይሏችኋል ይህ ነው። ሌላ አይደለም።
ሳምንት ይቀጥላል።
No comments:
Post a Comment