"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday, 16 June 2012

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኛ በፖሊሶች ተደብድቦ መሞቱ ተገለጸ

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል

ላለፉት አምስት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ይሠራ የነበረው አቶ ሀሚድ ወዳጆ የተባለ ግለሰብ፣ ሰኔ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ምሽት ላይ ቄራ አካባቢ በፖሊሶች በደረሰበት ከባድ ደብደባ ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ አቶ ሀሚድ በፖሊሶች ተደብድቦ ሕይወቱ ሊያልፍ የቻለው ከጓዳኞቹ ጋር ሲዝናኑ አምሽተው የ2012 የአውሮፓ ዋንጫ ተፋላሚ የነበሩትን የጀርመንና የፖርቹጋል ጨዋታን በሚመለከት የተወሰኑት ‹‹ወደ ቤት እንግባ›› ሲሉ የተወሰኑት ደግሞ ‹‹ጨዋታውን እንመልከት›› በማለት ሲነጋገሩ ‹‹ለምን ትረብሻላችሁ?›› በማለት ፖሊሶቹ ባነሱት ጥያቄ አለመግባባት ላይ በመድረሳቸው፣ በደረሰበት ድብደባ መሆኑን ከጓደኞቹ የተረዱት ቤተሰቦቹ ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ አብሮት የነበረው ጓደኛው እንደገለጸው፣ ቄራ አካባቢ ሲዝናኑ ቆይተው  መስቀልኛ ጫፍ ላይ ሲደርሱ ‹‹ኳስ እንይ ወይስ ወደቤት እንግባ?›› እየተባባሉ ሲነጋገሩ፣ አራት ዱላ የያዙና ሁለት ክላንሽኮቭ መሣሪያ የያዙ ስድስት ፖሊሶች ተጠግተዋቸው ‹‹ምን ያስጮሀችኋል? ለምን ትረብሻላችሁ?›› ብለው ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው ተናግሯል፡፡



መኖሪያቸው ጎፋ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም በመሆኑ ላዳ ኮንትራት ይዘው ወደ ቤታቸው ለመግባት እየተነጋገሩ እንጂ እየረበሹ አለመሆኑን ለፖሊሶቹ መናገራቸውን የገለጸው ጓደኛው፣ ፖሊሶቹ ዝም እንዲሉ በመሳደብ ሲያስጠነቅቋቸው፣ ሟች ‹‹ምን አደረግን?›› እንዳላቸውና መከራከር መጀመሩን ገልጿል፡፡ 

በምልልሱ እየተናደዱ የመጡት ፖሊሶች ሟችንና አንደኛውን ጓደኛቸውን በዱላ መምታት ሲጀምሩ ሟች፣ ‹‹ፖሊስ ሆናችሁ ከመታችሁን ምን ዋስትና አለን? ለምን ትደበድቡናላችሁ?›› እያለ ሲጮህ፣ ሦስቱ ፖሊሶች እሱን ለብቻው ነጥለው ከጓደኞቹ ራቅ በማድረግ ሲደበድቡት፣ ሌሎቹ ሦስቱ ፖሊሶች እነሱን በመሣርያ እያስፈራሩ እንዳይገላግሏቸው በማድረጋቸው አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ጎፋ ፖሊስ ጣቢያ መሄዳቸውን ጓደኛው ተናግሯል፡፡

የጎፋ ፖሊስ ጣቢያ ድርጊቱን ከማዳመጥ የዘለለ ዕርዳታ ሊያደርግላቸው እንዳልቻለ የሚናገሩት ጓደኞቹ፣ ተመልሰው ሲመጡ ሟችን ለቀውት በማግኘታቸው አብረው ወደ ቤታቸው በመጓዝ ላይ እያሉ እግሩ እየተሳሰረ መሄድ ሲያቅተው፣ የስልክ እንጨት ተደግፎ ለመቆም ሲል እጁ በመጎዳቱ ሊደገፍ ስላልቻለ ራሱን ስቶ መውደቁን አስረድተዋል፡፡ 

በአካባቢው ያገኟቸውን ሁለት ግለሰቦች ዕርዳታ ጠይቀው ከወደቀበት ቦታ አንስተው ወደ አስፋልት በማውጣት በላዳ ታክሲ ቄራ አካባቢ ወደሚገኘው ቅድስት ማርያም ክሊኒክ ሲያደርሱት ሕይወቱ ማለፉን አንድ ጓደኛው ገልጿል፡፡ በወቅቱ ፖሊሶቹ ሲጠራሩ ስማቸውንና መልካቸውን ለይተዋቸው እንደነበር የገለጸው ጓደኛው፣ ‹‹አንድ ግለሰብ ተደብድቦ እኛ ጋ ሲደርስ ሞቷል›› በማለት ክሊኒኩ ለፖሊስ ሪፖርት ሲያደርግ፣ አንደኛው ተጠርጣሪ ሌላ ሰው መስሎት በመምጣቱ መያዙንና ሌሎቹም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጓደኛው አስረድቷል፡፡ አብሯቸው የነበረ ሌላ ሲቪል የለበሰ ግለሰብ አለመያዙንም ጠቁሟል፡፡

የ27 ዓመት ዕድሜ ያለው አቶ ሀሚድ ወዳጆ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት መሆኑን የገለጹት ቤተሰቦቹ፣ የቀብር ሥርዓቱ በተወለደበት አካባቢ መፈጸሙን ገልጸው መንግሥት የወንድማቸውን ደም እንዲወጣላቸው ጠይቀዋል፡፡ 

ተፈጠረ የተባለውን ግድያና ተያዙ የተባሉትን ተጠርጣሪዎች በሚመለከት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጠን ለማነጋገር ብንሞክርም ምላሽ ለማግኘት ሳንችል ቀርተናል፡፡

No comments:

Post a Comment