"Food is nothing without freedom! We Need Freedom
”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!
Friday, 15 June 2012
ማመልከቻ፤ “ኢህአዴግ” ከሚለው ውስጥ ዴ እንድትወጣ ስለመጠየቅ
እኔ የምለው ኢህአዴግ ድሮ “ብሶት የወለደው” ነበር የሚባለው። አሁን ደግሞ የሚሰራውን ልብ ብለው ያዩ አንዳንድ ግለሰቦች “ጭንቀት የወለደው እያሉ” ሲጠሩት እየሰማሁ ነው። ስጠረጥር የሆኑ እጣ ፈንታ ነጋሪ፤ “መጨረሻህ እየደረሰ ነውና ከባድ ጥንቃቄ አድርግ” ብለው አስጨንቀውታል መሰለኝ! በየቦታው የሚወሰዱ ከእርግጫ የሚስተካከሉ እርምጃዎችን ልብ ብትሉ የምርም ጭንቀት የወለዳቸው ናቸው! (እኔን ጭንቅ ይበለኝ! ወይስ አይበለኝ…?)
እናም ሀገሬው “ጭንቀት የወለደው የኢህአዴግ ሰራዊት በሃያ አንድ አመቱም በርካታ ነገሮችን እየተቆጣጠረ እና እየቆጣጠረ ይገኛል” እያለ እየቦጨቀው ይገኛል።
በየጊዜው የሚወጡት አዎጆች እና ህጎች በሙሉ “አይቻልም” የሚሉ ናቸው። ማንኛውም ታጋይ እና የታጋይን ገድል በየ ግንቦት ሃያው የሰማ ሰው እንደሚያስታውሰው ህውሐት ያኔ ጫካ እያለችም የማትከለክለው ነገር አልነበራትም። እንኳንስ ሌላው ቀርቶ ተፈጥሯዊ የሆነውን የወንድና ሴት ግንኙነት ራሱ በጥብቅ ከልክላ ነበር።
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ “ታጋዮቹ የፈለጉት ነገር ሁሉ ሲፈቀድላቸው እኛ ህዝቦቹ በተራችን ሁሉንም ነገር እየተከለከልን ነው።” የሚል ሰው ተበራክቷል። እስከ አሁን በይፋ ያልተከለከለው የፍቅር ግንኙነት ብቻ ነው። እርሱም ቢሆን፤ “ተገናኝተን ሻይ ቡና እንኳ ለማለት የሚያስችል አቅም በማጣታችን እንደተከለከለ ቁጠረው!” ያሉኝ ወዳጆች አሉ።
የምር ግን ወዳጄ ዘንድሮ ያልታገደ ነገር ምንድነው? በየነጋው የምንሰማው ሁሉ እንትን ተከለከለ፣ እንትን ታገደ፣ እንትን ተዘጋ፣ የሚል ብቻ ሆኗል። ከዚህ በፊት ኢቲቪ እንደነገረን፤ “የአሁኑ መንግስት ልማታዊ መንግስት ነው።” ጠቅላይ ሚኒስትሩም ልማት እንጂ ለዚህ ህዝብ ዴሞክራሲ ምንም አያደርግለትም በሚለው ዜማቸው ሲናገሩ እንደሰማነው “ዴሞክራሲ እና ልማት ምንም ግንኙነት የላቸውም።” ብለውናል። አንዳንድ ካድሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ሲተረጉሙ ዴሞክራሲ “እንደውም የእድገት ፀር ነው።” ብለው እየተናገሩ ነው።
ታድያ እንደዚህ ከሆነ በአውራው ፓርቲ ስያሜ ኢህአዴግ ውስጥ “ዴ” ምን ልታደርግ ተሰነቀረች? ሰዉ እኮ ፊልም ሲታገድ፣ ስካይፕ ሲታገድ፣ ዌብ ሳይቶች ሲዘጉ፣ ራዲዮ ጣቢያዎች ሲጠረቀሙ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ሲታወኩ “እንዴ!” እያለ የሚደነቀው እኮ በስማችን ውስጥ “ዴ” በመኖሯ ሳቢያ ነው።
“ዴ” ማለት ዴሞክራሲ ማለት ነው። እንግዲያስ ከልካዩ መንግስታችን ሁሉን ነገር እየከለከለ አረ የ ”ዴ” ስራ ምንድነው? በሚል ለተቺዎች አጋልጦ ከሚሰጠን አንድ ጊዜ ስያሜውን ቢያስተካክለው ግልግል ይሆናል የሚል አስተያየት አለኝ። ስለዚህም እንደሚከተለው አመለክታለሁ።
እኔ አመልካቹ ግለሰብ በሀገሪቱ ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ገደብ የለሽ ክልከላ በሙሉ ልቤ የምደግፍ ስሆን፤ በዴሞክራሲ እና “በልማት መካከል ምንም ግንኙነት የለም” የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትሬን ንግግር ወደ መዝሙር ቀይሬ ጠዋት ማታ የማንጎራጉር መሆኔንም ለማሳወቅ እወዳለሁ።
መንግስታችን ሁሉንም ነገር መከልከሉ ለእኛው አስቦ እንዳንበላሽ ሰግቶ እንደሆነም አምናለሁ። ዴሞክራሲ የሚባለው ነገርም አጉል ቅብጠት መሆኑ ገብቶኛል። በመሆኑም በገዢው ፓርቲ ስያሜ “ኢህአዴግ” ውስጥ ያለችውን “ዴ” እንድትወጣልን በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment