"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday 12 June 2012

ሳላዲን ጥቁር ሰው! አበበ ጥቁር ሰው! አስክንድር ጥቁር ሰው… እኛስ!? (አቤ ቶኪቻው)


 | 

ሳላዲን ጥቁር ሰው! አበበ ጥቁር ሰው! አስክንድር ጥቁር ሰው… እኛስ!? (አቤ ቶኪቻው)


የዛሬ ሳምንት ከደቡብ አፍሪካ ባፋና ባፋናዎች ጋር በሳላዲን ሰይድ ጎል አቻ ተለያይቶ መነጋገሪያ የነበረው ብሄራዊ ቡድናችን ትላንት ደግሞ አሁንም በማይጨበጠው አጥቂ ሳላዲን ሰይድ ሁለት ጎሎች አስቆጥሮ፤ ሁለት ለምንም በሆነ ውጤት መካከለኛው አፍሪካን አሸንፏል። በስታድየም፣ በቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት ስንከታተል የነበርን በርካቶችም ፈንድቀናል።
ሳላዲን ሰይድም ከስታድየሙ ታዳሚ “ጥቁር ሰው” የሚል ማዕረግ ተሰጥቶታል። እንደውም አንድ የፌስ ቡክ ወዳጃችን እንዲህ ብሎ ለጥፏል።
“ብራዚል ሊሄድ ሳላዲን ኑ ካለ
አረ አይቀርም በኢትዮጵያ ስለማለ
ታድያ ልጁስ ሲጠራው ምናለ….
ወ….ይ…
ወይ ባለለው ያኔ
አዝናብኝ ነበር ሀገሬ”
እንግዲህ ሀገሩን የሚያኮራ የጀግና ስራ የሚሰራ ሁሉ በአሁኑ ግዜ “ጥቁር ሰው” የሚል ማዕረግ የሚያገኝበት ሁኔታ ነው ያለው! (እንዲህ ነው እንጂ የኔ ኢቲቪ አይሉኝም!)
እዝች ጋ ውድ ቴዲ መለኪያ ሰጥተከናል እና እግዜር ይስጥህ! ብለን ማመስገን ይገባናል። እውነቱን ለመናገር ራስህም “ጥቁር ሰው” ነህ ብዬ ደፍሬ ለመናገር እወዳለሁ። እንዴት…? የሚል ካለ ምንም እንኳ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሚኒሊክ ሲባል ደማቸው ቢንተከተክም የመጣው ይምጣ ብሎ “ጥቁሩን ሰው” አሞካሽቷልና… እደግመዋለሁ ቴዲም “ጥቁር ሰው” ነው!

በነገራችን ላይ ከላይ በርዕሴ ያልጠቀስኳቸው በርካታ “ጥቁር ሰዎች” እንዳሉን ለማስታወስ እወዳለሁ።
ባለፈው ጊዜ እንዳየነው አበበ ገላው ቆሌ ገፋፊውን ጠቅላይ ሚኒስተር ቆሌያቸውን የገፈፈ ጊዜ በበርካቶች ዘንድ “ጥቁር ሰው” የሚል ማዕረግ ተሰጥቶት እንደነበር እናስታውሳለን። አረ እዚህ ጋ ሳይጠቀስ የሚያልፍ ነገር አለ። ትላንት አዲስ አድማስ ጋዜጣን በኢንተርኔት መስኮት ጎብኘት አድርጌው ነበር። “አበበ ገላው በድጋፍ እና ተቃውሞ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል” የሚል አንድ ዘገባ ወጥቶ አየሁ። ፅሁፉን ልብ ብዬ ስመለከት ጠቅላይ ሚኒስትራችንን እና እጅግ ወዳጆቻቸው የሆኑ ግለሰቦችን ከደረሰባቸው የቅስም ስብራት ለማከም የተፃፈ ይመስላል።
አረ እንደውም፤ “አበበ ገለው ዋሽንግተን ዲሲ ያልሄደው የኢህአዴግ ደጋፊዎችን ፈርቶ ነው!” የሚል ነገርም አይቻለሁ። እሰይ አድማሶች እንዲህ ነው እንጂ… ለዚህ አኩሪ ተግባር “ጥቁር ሰው” ባልላችሁም ለጊዜው “አስር አለቃ” ልበላችሁ ይሆን…!? ግን ለምን ይዋሻል…? በአዲስ መስመር እወቅሳችኋለሁ፡
እኔ የምለው ለምን ድርጅታችንን ታሳስቷታላችሁ? በእውነቱ ኢህአዴግ እንኳንስ ከፍቶት በተሰደደው የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ ይቅርና በአገርቤቱ ደሴ እንኳ እናንተ እንደምትሉት አይነት ደጋፊ አለውን…? (ዲሲ እና ደሴ ለማመሳሰል ብዬ ደሴን ጠቀኩ እንጂ በመላው ኢትዮጵያ… የኢህአዴግ ደጋፊ ማነው…?) በእውነቱ በመላዋ ኢትዮጵያ ኢህአዴግ ብዙዎችን ራሱ በአበል እየደገፈ ነው እንጂ ህብረተሰቡ ኢህአዴግን ለመደገፈ አቅም አለውን!? በእውነቱ በዲሲ በርካታ ደጋፊዎች ቢኖሩት ኖሮ ባለፈው ጊዜ ባለስልጣኖቻችንን ለአባይ ገንዘብ ስብሰባ በሄዱ ወቅት በተቃውሞ ብዛት ንግግር እንኳ ማደረግ ተስኗቸው ይመለሱ ነበር? ለማንኛውም አድማሶች ድርጅታችን አታሳስቷት…! በተለይ ውጪ ሀገር ከኤንባሲው የጥበቃ ሰራተኞች ውጪ ይሄ ነው የሚባል ደጋፊ እንደሌለን እኛም እናውቀዋለን!
ወደ ዋናው መስመር ስንመለስ… ሀገራችን በተለያየ ቦታ የተለያዩ “ጥቁር ሰዎች” እያፈራች ትገኛለች። ልብ አድርጉልኝ እነዚህ ጥቁር ሰዎች ባንዲራዋን ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡ ናቸው እንጂ ባንዲራዋን የሚዘቀዝቁ አይደሉም። በድፍረት የሚናገሩ ናቸው እንጂ በአፍረት አንገት የሚደፉ አይደሉም። ሀቅን የሚለብሱ ናቸው እንጂ ውሸት የሚቀዱ አይደሉም።
ሳላዲን ሰይድ ኢትዮጵያ ለአለም ዋንጫ ለማለፍ ባደረገችው ማጣሪያ እስከ አሁን ያስቆጠረቻቸውን አምስት ጎሎች በሙሉ አስቆጥሯል! በዚህም ባንዲራችን ከፍ ብሎ ተውለብልቧል እኛም ሳላዲንን ብለነዋል “ጥቁር ሰው” ይህንን ማዕረግ መላው የብሄራዊ ቡድኑ አባላትም ይጋራሉ!
አበበ ገላው እና እስክንድር ነጋ ሁለቱም የሚወክሏቸው ህዝቦች አሏቸው አበበ በውጪ ሆነው ደከመኝ ሳይሉ ለሀገራቸው መልካም እንዲመጣ አበሳቸውን የሚያዩ ሰዎችን፣ እስክንድር ደግሞ “ሀሰት ለመናገር አትሻም ምላሴ ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነብሴ” ብለው በየ እስር ቤቱ መከራቸውን የሚያዩ የኢትዮጵያ ልጆችን ይወክላሉ። ወክለውም የ “ጥቁር ሰው” ማዕረግን ያገኛሉ።
“ጥቁር ሰው! ያብዛልን እኛንም “ጥቁር ሰው” ያድርገን አሜን በሉ!

No comments:

Post a Comment