(ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)
በደርግ ዘመን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ የኪነት ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፤ እንጉርጉሮ በምትል ትንሽ የግጥም ጥራዝ ሳይሆን አይቀርም ለስብሰባው ተጋብዤ ነበር፤ በዚህ ስብሰባ ላይ አቶ አያልነህ ሙላትና ዶር. ኃይሉ አርአያም አስተናጋጆች እንደነበሩ አስታውሳለሁ፤ የመክፈቻው ንግግር ሥርዓት እንዳበቃ መድረኩ ለአስተያየት ሲከፈት የመጀመሪያው ጠያቂ እኔ ነበርሁ፤
‹‹በመድረኩ ላይ የተባለው ሁሉ በትክክል ገብቶኝ እንደሆነ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ፤ ስለዚህም አንድ ጥያቄ ላቅርብ፤›› ብዬ- ‹‹ኪነት ማለት አዝማሪነት ማለት ነው ወይ?››-- ብዬ ተቀመጥሁ፤ በሦስቱም የስብሰባ ቀኖች ‹‹ኪነት አዝማሪነት ነው ወይ?›› የሚለው ጥያቄ እየተነሣ ቆየ፤ አዝማሪነት ስትል ምን ማለትህ ነው ብለው የጠየቁ ነበሩ፤ በቀለለ አማርኛ ልገልጽ አልችልም በማለት እስከ ሦስተኛው ቀን ቆየሁ።
አንድ ሎሌ እየተውዘገዘገ ርእዮተ ዓለምንና አብዮትን የሕይወት ካባ አስመስሎ ‹‹ከርእዮተ ዓለሙ ውጭ ምን አለ!›› እያለ አለማወቁን አሳወቀ፤ ኪነት አዝማሪነት ነው፤ አዝማሪነት ኪነት ነው ማለቱ ነበር፤ ሌሎችም ኪነትንና አዝማሪነትን ለማጋባት የቃጣቸው ሎሌዎች ነበሩ፤ አንዳንዶች ግራ ገብቶአቸው ለቡና ስንወጣ የጠየቁኝ እንደታምራት ሞላ ያሉ የኪነት ሰዎች ነበሩ፤ በእውነቱ እዚያ ውስጥ ከነበሩት ውስጥ ማንኛውም ቢሆን በልቡናው ኪነትንና አዝማሪነትን መለየት ያቃተው የነበረ አልመሰለኝም።‹‹በመድረኩ ላይ የተባለው ሁሉ በትክክል ገብቶኝ እንደሆነ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ፤ ስለዚህም አንድ ጥያቄ ላቅርብ፤›› ብዬ- ‹‹ኪነት ማለት አዝማሪነት ማለት ነው ወይ?››-- ብዬ ተቀመጥሁ፤ በሦስቱም የስብሰባ ቀኖች ‹‹ኪነት አዝማሪነት ነው ወይ?›› የሚለው ጥያቄ እየተነሣ ቆየ፤ አዝማሪነት ስትል ምን ማለትህ ነው ብለው የጠየቁ ነበሩ፤ በቀለለ አማርኛ ልገልጽ አልችልም በማለት እስከ ሦስተኛው ቀን ቆየሁ።
በሦስተኛው ቀን ተነሣሁና በአንዲት ልጅ ፍቅር ተወጥሬ አንድ ግጥም ብጽፍ ርእዮተ ዓለሙ ወይም አብዮቱ በእኔና በልጅቱ መሀከል በምን ቀዳዳ ይገባል? ሕይወት አይቆምም፤ ይቀጥላል፤ ርእዮተ ዓለም ግን በርእዮተ ዓለም ይለወጣል፤ ለአብዮትም አብዮት አለው በማለት ሎሌዎቹን አስደንግጬ ድርሻዬን ተወጣሁ!
ኪነት ነፃነት ነው፤ ኪነት የፈጣሪነት ጥበብ ነው፤ ኪነት ውበት ነው፤ ኪነት ደስታና ሳቅ ነው፤ ኪነት ሐዘንና ለቅሶ ነው፤ ነፃነት፣ የፈጣሪነት ጥበብና ውበት የኪነት መለያ ባሕርዮች ይመስሉኛል፤ ኪነት በሰው ልጅ ውስጥ የፈጣሪው እስትንፋስ መኖሩን የሚገልጽና ፈጣሪነትን ከፈጣሪው የሚጋራበት ስጦታም ችሎታም ነው፤ እንደዚህ ያሉ ሰዎች የአንድ አገር ዓይንና ጆሮ፣ አእምሮና ኅሊና ናቸው፤ የአንድ አገር ሕዝብ የሥልጣኔ ደረጃ በእንደዚህ ያሉ ሰዎች ብዛትና በድንበር-ዘለል ተጽእኖአቸው ይለካል፤ ለምሳሌ ፈረንሳይ የኪነት ሰዎችን ከየትም የመሳብ ችሎታዋ ወደር የሌለው ነው፤ እንዲሁም አሜሪካ በሙሉ ባይባልም ኒው ዮርክ የኪነት ሰዎችን የሚስብ ከተማ ነው።
በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከመቃብር ውስጥ በጥሩ መልኩ በጉዱ ካሣ ያመለከቱት ይመስለኛል፤ ክፉ መልኩ ግን አስቀያሚ ነው፤ ዘፈኖች የሚታሰሩበት አገር ነው፤ የኪነት ሰዎች የሚታሰሩበት አገር ነው፤ መጻሕፍትን ማቃጠልም እናውቅበታለን፤ አሁን ደግሞ ከየመሥሪያ ቤቶች ቤተ መጻሕፍት እያወጡ መጻሕፍትን መሸጥ ፈሊጥ ሆኖአል፤ በአጠቃላይ የፈጠራ ሰዎችን ከነፈጠራቸው ማፈን የሚወራረሱት ልማድ ሆኖአል፤ ከተለመደውና ከተፈቀደው ወጣ ያለ ነገር ወይ ለእስር ወይ ለስደት ይዳርጋል፤ በእውነቱ ከሆነ ኪነት የሚሰደድ አይመስለኝም፤ የኪነት ሕይወቱም ሆነ ሞቱ በነፃነት ነው፤ የተሰደደ ኪነት የሬሳ ጭፈራ ነው።
በብዙ አገሮች ኪነትን የሚደግፉ ሀብታሞች አሉ፤ በኢትዮጵያም አቶ መሀመድ አላሙዲ የዘፋኞች አለኝታ መሆኑ ይነገራል፤ አንድ ሰው መኖሩ የጠቅላላውን ጨለማ አይገፈውም። ግራም ነፈሰ ቀኝ ራሱን ነፃ ያላወጣ ኪነት ከአዝማሪነት ይቆጠራል፤ አዝማሪነት ከመዝፈን ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፤ ውዳሴንም ሆነ ገድልን ለወፍራም እንጀራ የሚጽፍ አዝማሪ ነው፤ በሌሎችም ሙያዎች ያው ነው። አዝማሪነት የፈጣሪነት ጥበብንና ውበትን ሊይዝ ይችል ይሆናል፤ ነፃነት ግን ለአዝማሪነት የባሕርዩ አይደለም፤ ጥቅምን አይቶ የሚነሣ አዝማሪነትና ያለምንም ምኞት አፍአዊ ሁኔታዎች በሚቀሰቅሱት ሀሳብና ስሜት በጥልቀት ነፍሱ ሲነካ ነፍሱን ቧጥጦ የሚወጣው ኪነት አንድ ሊሆኑ አይችሉም። በአንድ ዓይነት ኪነት ላይ ያለውን የባህል አጥር እየጣሱ ስሜታቸውን በመጠኑም ቢሆን የሚገልጹ ሰዎች ነበሩ፤ አዝማሪዎች፣ አልቃሾችና እረኞች፤ በተረፈ ግን ኢትዮጵያ የኪነት አገር ለመሆን አልታደለችም፤ ነፃነት ሲመጣ ኪነት ይነግሣል፤ ችጋርም ይጠፋል።
No comments:
Post a Comment