"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Sunday 3 June 2012

አንገት ሲደፋ ምን ፈሰሰ?


                                                  አንገት ሲደፋ ምን ፈሰሰ?
SHARE THIS
       
TAGS

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

ሰሞኑን አዲስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶግራፍ በብዛት በያለበት ይታይ ነበር፤ ያዘነ፣ የተከዘና አንገቱን የደፋ መለስ ዜናዊ! እኔን ቀልቤን የሳበው የጠቅላይ ሚኒስትሩን አንገት ሊያስደፋ የቻለው ነገር አይደለም፤ ወይም አበበ ገላው የተናገረው ነገር አይደለም፤ አበበ ገላው የተናገረውን ለመናገር ሙሉ መብት አለው፤ በተባለው ነገር የማይስማማ ሰው በማስረጃም ሆነ ያለማስረጃ የተባለውን ለማስተባበል መሞከር መብቱ ነው፤ የአሜሪካኑን ፕሬዚዳንት፣ ወይም የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥማቸው፣ ወይም በጆርጅ ቡሽ ላይ አንዱ ኢራቃዊ እንዳደረገው ጫማውን እያወለቀ ቢወረውርም ምንም የሚያስደንቅ ነገር አይኖርም፤ በ1928 ነው 29 አጼ ኃይለ ሥላሴ በቀድሞ የዓለም መንግሥታት ማኅበር መድረክ ላይ ሲናገሩ የኢጣሊያ ፋሺስቶች ያሰማሩአቸው ሰዎች ንግግሩን ለማደናቀፍ ጩኸትና ፉጨት ያሰሙ ነበረ፤ አጼ ኃይለ ሥላሴን አንገታቸውን አላስደፋቸውም፤ አበበ ገላው የወረወራቸው ቃላት ናቸው፤ ቃላቱ እውነትን የሚገልጹ ከሆነ በተግባራዊ ማረሚያ ይለወጣሉ፤ ቃላቱ ሐሰትን የሚገልጹ ከሆኑ እውነትን በሚገልጹ ቃላት ይደመሰሳሉ።


                                                      አንገት ሲደፋ ምን ፈሰሰ?

Mesfin Woldemariam (Prof.)

እዚህ ላይ አንድ ሌላ ነገር እናስታውስ፤ በመስከረም ግድም ይመስለኛል አቶ ኢሳይያስ አፈወርቅ በኒውዮርክ ነበረ፤ በዚያን ጊዜ በአንድ ስቴድየም ውስጥ የኤርትራ ተወላጆች ሁሉ (የቀረም ያለ አይመስልም!) በስቴድየሙ ታምቀው የኢሳያስን ዲስኩር ከሰሙ በኋላ አስተያየታቸውን እየሰጡና ጥያቄያቸውንም እየጠየቁ ሲወያዩ ነበር፤ ያስቀኑ ነበር፤ የኤርትራም ማኅበረሰብ እንደኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስብስብና ጉራማይሌ ነው፤ መሪው ህዝቡን ሳይፈራ፤ ሕዝቡም መሪን ሳይፈራ ተቀራርበው ለመወያየት መቻላቸው እኛን የትና የት ጥለውን እንደሄዱ አያሳይም የሚል አለ? ይህንን እውነት ቢያንስ የዛሬ አሥራ አምስት ዓመት ግድም ሪፖርተር የመጀመሪያውን መጽሔት ባወጣ ጊዜ ሽፋኑ የኢሳይያስ አፈወርቅ ፎቶግራፍ ነበር፤ የመለስ አልነበረም፤ ለኢሳይያስም ከተደረደሩት የውዳሴ ርእሶች አንዱ ኢሳይያስ ለሕዝብ ቅርብ መሆኑ ነበር፤ በአንፃራዊ ዝምታ መለስን ይጎሽም ነበር፤ ዛሬ በጠብ ላይ በመሆናችን እውነትን የምናይበት ዓይናችን ተቸግሮ ይሆናል፤ ለማናቸውም የሪፖርተርን ዘገባ ያስታወስሁት በኒውዮርክ በተደረገው የኤርትራ ተወላጆች ስብሰባ የተነሣ ነው፤ ለመሆኑ በኒውዮርክ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ስብሰባ ቢጠራ መጀመሪያ ስንት ሰዎች ይገኛሉ? ከተገኙትስ ጋር የሠለጠነ ውይይት ይደረጋል? ወይስ በፓርላማ እንደተለመደው ያለ ይሆናል? ሳይናናቁ መሪና ሕዝብ ተከባብረው በነፃነት ሀሳባቸውን መለዋወጥ መቻል ትልቅ እርምጃ ነው።
በኒውዮርክ የተሰበሰቡትን የኤርትራ ተወላጆች ቁጥር የሚያህል ኢትዮጵያውያን ተሰብስበው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየት የሚችሉ ቢሆን እንዴት ያኮራኝ ነበር፤ በበኩሌ ባንስማማም እንነጋገር እያልሁ ስጮህ ብዙ ጊዜ ሆነኝ፤ ክርር ምርር ብሎ ከዚህ ፍንክች አልልም፤ ለአጭሩም፣ ለረጅሙም፣ ለወፍራሙም፣ ለቀጭኑም፣ ለክርስቲያኑም ለእስላሙም፣ ለሁላችሁም የሚበጀውን እኔ አውቃለሁ ማለቱ አያቀራርበንም፤ መናናቅ አያቀራርበንም፤ መፈራራት አያቀራርበንም፤ አበበ ገላው የተናገረው እውነት መሆኑንና አለመሆኑን ወደጎን እንተወውና በኢትዮጵያ ውስጥ እነዚያኑ ቃላት፣ በዚያው የጋለ ስሜት ያለፍርሃት በልበ ሙሉነት መግለጽ የሚቻል ቢሆን የአሜሪካው ድራማ አያስፈልግም ነበር፤ ዋጋም የሚሰጠው አይሆንም ነበር፤ በአሜሪካ በድንገትና ዓለም ሁሉ በሚያይበት መድረክ ስለ መለስ ዜናዊ የተባለው ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ተዝናንቶና ኮርቶ ሊያዳምጥ የሚችልበትን መድረክ በሃያ ዓመታት ውስጥ ሳያዘጋጅ መቅረቱ አንገቱን ለማስደፋቱ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ሳይሆን በአሜሪካ፣ በኢትዮጵያ ፓርላማ ሳይሆን በትልቅ ዓለም-አቀፍ ስብሰባ፣ ጥቂት የአፍሪካ መሪዎች ብቻ በተጋበዙበት ስብሰባ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአፍሪካ ተናጋሪ ሆኖ በተጋበዘበት የታላላቅ መሪዎች ስብሰባ ላይ መገኘቱ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ሊያኮራ የሚገባው ነገር ነበር፤ ቢመቸን የሚያኮራን ነበር፤ መኩራቱ ሳይሆንልን ቢቀርም የማናፍርበት በሆነ መልካም ነበር፤ ምስጋናና ከንቱ ውዳሴ እንደጠበል በሚረጭበት ትልቅ ዓለም-አቀፍ ስብሰባ ላይ ዘለፋና ነቀፌታ መስማት አንገትን ያስደፋል፤ ነገር ግን ከመለስ ዜናዊ ጋር ኢትዮጵያ በዚያ ስብሰባ ላይ አንገትዋን አልደፋችም?
በግድም ይሁን በውድ አንድ መሪ አንድ ሕዝብ አናት ላይ ከተቀመጠ፣ ብዙ ነገሮች ያያዝዋቸዋል፤ ከነዚህ ነገሮች አንዱ ክብር– ወይም ውርደት ነው፤ ሕዝብ ተዋርዶ መሪው ክብር አያገኝም፤ መሪው ተዋርዶ ሕዝብ ክብር አያገኝም፤ የአንዱ ውርደት ለሌላው ክብር ሊሆን አይችልም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስብሰባው ላይ የተጋበዘው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን አህጉርንም ወክሎ ነበር፤ በዚህ ሁኔታ ክብር ቢያገኝ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን በሙሉም ያስከብር ነበር፤ ስለዚህም የዜና ማሰራጫዎች ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲያወድሱ ኢትዮጵያም አፍሪካም አብረው ይወደሱ ነበር፤ አሁን ግን አንገቱን ስለደፋው ሰው ሲናገሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እያሉ ነው፤ ያኔ እኛም አንገታችንን ባንደፋም ወደግብዣው ቋጥረነው የገባነው ትንሽ ክብር ይደፋብንና ውርደቱ ይሰማናል፤ የሚገዙትን ሕዝብ ሳያከብሩ ማስክበር ያስቸግራል፤ የሚገዙትን ሕዝብ ሳያከብሩ መከበርም ያስቸግራል፤ መሪና ሕዝብ ክብርንና ውርደትን ይወራረሳሉ።
በሃያ ዓመት የመሪነት ቦታ ተቀምጦ አንገቱን ቀና አድርጎ በኩራት የሚወረወርበትን ጉድፍ ሁሉ ለመቀበል የሚችልበትን፣ የሚናገርበት ብቻ ሳይሆን አንገቱን ሳይደፋ ለማዳመጥ የሚችልበትን መድረክ ሳያዘጋጅ በመቅረቱ የደረሰበት ውጤት በዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ አንገት መድፋት ነው።
በስንቱ ነገር ነው አንገታችንን የምንደፋው? በደሀነትና በችጋር፣ በመረጃ ማነቆ፣ በቴሌቪዥን እኛ የምንፈልገውንና የምንመርጠውን ለማየት አንችልም፤ በቴሌቪዥን ፕሮግራም እንኳ አጥፍቶ መጥፋት ሊባል ወደሚችል እልህ ውስጥ ገብተን ከዓለም ጋር ብቻ ሳይሆን ከእውቀት ጥበብ (ከቴክኖሎጂ) ጋር የምንታገል ይመስላል፤ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እየተባለ መራራ ኮሶ የሚጋቱበት ዘመን አክትሞአል፤ ዓለም በሙሉ ጎረቤት ሆኖአል፤ በአንዱ አገር ውስጥ የሚሆነው ውቅያኖስንና አህጉሮችን አቋርጦ ይሰማል፤ ይታወቃል፤ ከጎረቤቶቻችን ከአፍሪካ አገሮች ጋር በመረጃ ልውውጥ በጣም ዝቅተኛ ነን፤ በቴሌቪዥን ብቻ ሳይሆን በኢንተርኔት አገልግሎት ችግር ፍዳችንን እየበላን ነው።
ለዚህ ነው አንገታችንን የምንደፋው፤ አንገታችንን ስንደፋ ክብራችን ይፈስብንና ገበናችን ይጋለጣል፤ መከባበሩ የሚበጀው ለዚህ ነው።


No comments:

Post a Comment