"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday, 5 June 2012

ትንሽ ቀደዳ፤ ስፖርት ለበስ ፖለቲካ ቀመስ! (አቤ ቶኪቻው)




Tuesday, June 5th, 2012 | Posted by zehabesha
ትንሽ ቀደዳ፤ ስፖርት ለበስ ፖለቲካ ቀመስ! (አቤ ቶኪቻው)
Share

ይህንን ጨዋታ ትላንት ላካፍላችሁ ነበር ያሰብኩት በቴክኒክ ምክንያት ሳይሳካልኝ ቀረና ይኸው ለዛሬ ሆነ!
በአለም ዙሪያ ያላችሁ የዝች ብሎግ አንባቢዎች እንዴት አላችሁልኝ…? ሰንበቶቹ እንዴት አለፉ!? ባመዛኙ አሸወይና እንደነበሩ እገምታለሁ! ከፊል ደመናማ የሆኑ እንደሚኖሩም እጠረጥራለሁ። ስለዚህ በጥቅሉ ደመናው እንዲጠራ፤ አሸወይናው እንዲጠናከር እየተመኘሁ እንደሚከተለው ይቺን ቀደዳ ይዤ ቀርቤያለሁ።
የቃላት መፍቻ
አሸወይና… ማለት አስደሳች፣ ማራኪ እና “ጣመኝ ድገሙኝ” የሚሉት ጊዜ ሲሆን፣
ቀደዳ … ማለት ደግሞ ወሬ፣ ወግ፣ ጨዋታ በማለት የአራዳ ልጆች ይፈቱታል። (እዝችው ጋ አራዳ ማለት ብዬ ደግሞ ልቀጥል እንዴ…? አራዳ ማለት ምን ማለት አንደሆነ የጋሽ ፍቅሩ ኪዳነን የፒያሳ ልጅ መፃፍ ሲያነቡ ወለል ብሎ ይገለጥልዎታል።
ቀደዳችን ተጀመረ፤

በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተጫውቶ የነበረው ብሄራዊ ቡድናችን ሳላዲን ሰይድ በሃያ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ድንቅ ግብ እስከ ሰባ ሰድስተኛው ደቂቃ ድረስ ሲመራ ቆይቶ፤ በሰባ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ደቡብ አፍሪካዎች ባስቆጠሩት ግብ አንድ እኩል በሆነ ውጤት ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል። (ድሮም ይሄ ሰባ ሰባት አይመቸንም… ብለን እንመፀትና እንቀጥላለን፤)
ይሄ ውጤት ቡድናችን ላይ ተስፋ የምንጥልበት እንደሆነ አሳይቶናል። እስከዛሬ ድረስ በኒያላዎቹ ተስፋ ቆርጦ የነበረው የእግር ኳስ ደጋፊ ብሔራዊ ቡድኑን “ቡድን” ከሚለው ውስጥ “ቡ” በመግደፍ እና “በ” በማድረግ፤ “ብሄራዊ በድናችን” እያለ እሰከመጥራት ደርሶ የነበረ ሲሆን፤ የትላንቱ ውጤት ይህንን ስም ለማደስ እነ ሳላዲን ቆርጠው መነሳታቸውን አላህም ሊረዳቸው ተነሳሽነት እንዳሳየ የሚያመላክት ነው።
ሰሞኑን በስፖርቱ አዳዲስ ውጤታ ውጤቶችን እያስመዘገብን ነው። ሉሲዎቹ የሴቶች እግር ኳስ ብሄራዊ ብድን በታንዛኒያ ቡድን ላይ ያስመዘገቡትን አንድ በሉልኝ፤ ከእንደገና ደግሞ በጣሊያን ሮም ላይ በአጭር እርቀት ሩጫ በሺህ አምስት መቶ እና በስምንት መቶ ሜትሮች አሪፍ ውጤት አግኝተናል። እሰይ እሰይ እንትፍ እንትፍ እያልን ብሎ መመረቅ ይገባል።
በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሴት እግር ኳስ ቡድን አባላት ታንዛኒያን ካሸነፉ በኋላ ላስመዘገቡት ውጤት ከ አንድ ሺህ እስከ ሁለት ሺህ ድረስ ቦንድ ተገዝቶላቸዋል። ይሄም “ለቀጣይ ስራ የሚያበረታታ” እንደሆነ የሴቶቹ ተወካይ ገልፃለች። የተወካይዋን ንግግር ከመመህራን ማህበር ኃላፊዎች ጋር ያመሳሰሉት ወዳጆች ነበሩ። ምናለበት ግን የምር ማበረታቻ ቢሸልሟቸው…!? ብለን አስተያየት ብንሰጥ “ከዚህ የበለጠማ የምር ሽልማት የለም” ሊሉን እንደሚችሉ እንገምታለን…
እዝችጋ አንድ ሃሳብ አለኝ…! እንደዚህ አይነት ሽልማት የሚያቀርቡ ባለስልጣናትን እኔም አንድ ሽልማት ልሸልማቸው አስቤያለሁ። ምን መሰላችሁ…? እዛው አባይ ወንዝ ላይ ወርደው ለአንድ ወር ድንጋይ እንዲያቀብሉ ቁፋሮ እንዲቆፍሩ…! (አዎና ከልማት የበለጠ ሽልማት ከየት ይመጣል? በርግጠኝነት ሽልማቴ ባለስልጣኖቹን ለወደፊት ስራ የሚያበረታታቸው እንደሆነ አምናለሁ።)
አረ በደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ላይ የሆነውን ከ “ከረንት አፌርስ” ድረ ገፅ የኮረጅኩትን ትንሽ ልንገራችሁ እንጂ…!
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በብዛት በስታድየሙ ታድመው ነበር። በቅርቡ አክቲቪስት እና አርቲስት ታማኝ በየነን በጀግና አቀባበል ተቀብለውት የነበሩት ኢትዮጵያውያን፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እዝች ሀገር ድርሽ እንዳይሉ ብለው ያስከለከሉ ኢትዮጵያውያን፤ ትላልቅ እና ኮከብ ሳይኖርባቸው እንዲሁ በሚያበሩ በርካታ የኢትዮጵያ ባንዲራዎችን የደቡብ አፍሪካን ስታድየም አድምቀውት ነበር። “ኢትዮጵያ የኛ መመኪያ” የሚለው መዝሙር “የዜግነት ክብር” የሚለውን ብሄራዊ መዝሙር ተክቶ ነበር። (እኔ የምለው ግን መንግስታችን በዮቦታው እንዲህ ተጠምዶ እና አይንህ ላፈር ተብሎ እስከመቼ ይኖራል…!?)
ለማንኛውም የፊታችን ቅዳሜ ሉሲዎች በዳሬሰላም፤ እንዲሁም ኒያላዎቹ እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እናስ… እናማ ሆ ብለን ሄደን ድጋፋችንን እንሰጣለና!
ወይኔ አዲሳባ ስታድየም እንዴት እንደናፈቀኝ አትጠይቁኝ…! በዙሪያው ካለው ድራፍት ጀምሮ ውስጥ እስከሚገኘው ሽንብራ ደቤ፤ ከተጨዋቹ ጨዋታ እስከ ደጋፊው ሆታ…! የምር ናፍቆኛል። እሁድ ከች ልበል ይሆን…!?
ዘግይቶ የደረሰኝ ኩምክና…
እግር ኳስ ፌዴሬሽን “በደቡብ አፍሪካ የተካሄደውን ጨዋታ የሚያሳይ ቪዲዮ የለኝም” አለ በማለት ሰይድ ኪያር አሁን በኢቲቪ ሲናገር ሰማሁት… እንዴ ፌዴሬሽንዬ ትንሽ ሼም የለም እንዴ…? እንዴት አንድ እንኳ ጋዜጠኛ መላክ ያቅታችኋል!? ሌላው እንኳ ቢቀር በሞባይላችሁም ቢሆን መቅረፅ ነበረባችሁ እነጂ ይህንን የመሰለ ታሪካዊ ጨዋታ ቪዲዮ የለኝም ማለት በእውነቱ ትልቅ ኩምክና ነው። “የት ሄጄ ልፈንዳ…!?” ያለችው ማን ነበረች!?
እስቲ ሰላም ይግጠመን ወዳጄ!
ከፌስ ቡክ ግድግዳችሁ ላይ ፎቶ የወሰድኩባችሁ ወዳጆች ሳላስፈቅዳችሁ በመውሰዴ ይቅርታ ጠይቄ እግዜር ይስጥልኝ! ብዬ ልመርቃችሁ!

No comments:

Post a Comment