"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday 5 June 2012

በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ Coordinating committee of exiled members of Ethiopian Teachers Association የተሰጠ መግለጫ

በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ
Coordinating committee of exiled members of Ethiopian Teachers Association
የተሰጠ መግለጫ                         
                                                             ግንቦት 23 ቀን 2004 ዓ.ም
ለማደናገር ሰይጣንም ከቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳል!!
የሌባ ዓይነደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ!!
ያለንበት ወቅት እንደ አገር፣እንደ ሕዝብ የምንገለጽባቸው እሴቶች ሁሉ ተከልሰው፣ተበርዘው፣ፈር
ስተው እንዲያዘግሙ በሂደትም ከተቻለ ጭራሹን እንዲጠፉ የሚሠራበት ወቅት ነው።ለዚህ ደግሞ የጥፋት
ፊታውራሪው ወያኔ/ኢህአዴግ ነው።ይህ በመንግስት ስም በጫንቃችን ላይ የተጫነ ድርጅት አባላቱ አፋሽ
አጎንባሽ አጫፋሪዎቹ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ለኢትዮጵያዊነት፣ ለሕዝብ ወሳኝነትና ለሰብአዊነትም
እንጥፍጣፊ በጎ አመለካከት በተፈጥሮ ባህርያቸው የለም።
በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ፣ በአገር፣ በአህጉር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቅቡል የሆኑትን
ቁምነገሮች ማለትም ዲሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብት፣ ሕግና ፍትህ እያነሱ እየጣሉ መደስኮሩ ላይ ከኛ በላይ ላሳር
ነው የሚሉን።ከውስጥ የሚመነጭ ጽኑ እምነትና ለታይታ የሚነገሩና ወይም የሚሰሩ ግን ለየቅል ናቸው።
እንዲያውም አሁን አሁንማ ወያኔ ማስመሰሉንም እየተወ ባፈጠጠና ባገጠጠ መልኩ በማናአለብኝነት ያሻውን
የሚሰራ እንደሆነ ነው እውነታው የሚያሳየው። ሺህ ዓመታት የቆየውን ታሪካችንን እየሰረዘ እየደለዘ የራሱን
መንደር በቀል ወያኔያዊ ህልም እንደታሪክ ሊያስተምረን ይዳዳዋል።በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያ
እንፈጥራለን እያለ በማሾፍ በዘር፣ በሃይማኖት……… በመከፋፈል የቻለውን ያህል ጥሯል። ተዋዶ፣ ተዋልዶ፣
በደምም ተዋህዶ ለረዥም ዘመናት በኢትዮጵያዊነት ክር የተሳሰረውና በአብሮነት የቆየው ሕዝብ ይኽን
በክፋትና በዘረኝነት የሰከረው ቡድን የማጥፋት ዕቅዱ ግብ እንዲመታ አልተባበረውም።ይህ እንዳለ ሆኖ2
የትናንቱን ማስታወስ፣ የዛሬውን መረዳት፣ የነገውንም መገመት የተሳናቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የቆየውን
የአንድነት ትስስርና ብሔራዊ ማንነት ለማዳከም በመስራት ላይ ይገኛሉ።
በአሁኑ ጊዜ ወያኔ በአንድ ጎሳ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በደቡቡ የአገሪቱ ክፍል የሚያከናውነው ማፈናቀል
የዘር ማጥፋት/ማጥራት የአፍራሽ ተልዕኮው አንዱ መገለጫ በመሆኑ ነው።ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዜጎች
በአገራቸው የመኖር መብታቸውን በመግፈፍ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የማፈናቀል ተግባር እየተካሄደ
ሰፍረው ይኖሩበት የነበረውን መሬት ለውጭ አገር ባለሃብቶች በመቸብቸብ ለከፍተኛ ሥቃይ እንዲጋለጡ
አድርጓል።በኃይማኖትም ተቻችለውና ተከባብረው የቆዩትን የኦርቶዶክስና የእስልምና ተከታዮች ምዕመናን
አቶ መለስ በአምሳሉ የቀረጻቸው አምባገነን ገዢዎች ከመጽሓፍ ቅዱስም ከቅዱስ ቁርአንም የጥራዝ ነጠቅ
ጥቅስ እየመዘዙ ሕዝቡን ለማበጣበጥና በሂደቱ አገዛዙ እንዲሰነብት የማይጎነጉኑት ሸር ያለመኖሩን እያየነው
ነው።የሚገርመው የራሳቸውን ምኞት፣ ተግባርና እንቅስቃሴ ወደማይመለከተው አካል ወርውረው ለመለጠፍ
የሚያሳዩት የቅሌት ተግባር ነው።ራሳቸው ሕዝብን በጠመንጃ እያሸበሩ፣ እየገደሉም፣ እያፈናቀሉ፣ እያሳደዱ
ሌላውን ሠላማዊና ወረቀትና ብዕር አንስቶ የሕዝብን ሰቆቃ ያጋለጠ ጦር እንደሰበቀባቸው፣ መድፍ
እንደተኮሰባቸው፣ አሸባሪ ብለው ይወነጅላሉ።ከምዕራባውያን የቀዳነው ወርቃማ ህግ ነው ብለው ዜጎች
እንዳይተነፍሱ፣ እንዳይላወሱ፣ ቡና እንኳን በጋራ እንዳይጠጡ፣ በየቤታቸው ዘግተው እንዲቀመጡ የሽብር
ሕግ አውጥተው አብሮነታችንን ተፈታትነዋል።የዕምነት ተቋማት በሆኑት ቤተክርስቲያን፣ ገዳማት፣ መስጊዶች፣
ሲኖዶስ፣ መጅሊስ……ወያኔ ጣልቃ እየገባ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አንድ ከንፍ ሆነው እንዲሰሩ በማድረግና
ኃይማኖትና መንግሥት የተለያዩና አንዱ በሌላው ላይ ጣልቃ ያለመግባት ራሱ ያፀደቀውን ሕገ-መንግሥት
አለመተግበሩን የተቃወሙ አማኞችን አሸባሪዎች ናቸው እያለ ከማላዘኑም በላይ ሌሎችም ሚዛን ላይ
የማይቀመጡ ተራ ውንጀላዎችን ማራገቡ የመንግሥትነት ባሕርይ የሌለው ወሮበላ ቡድን መሆኑን ነው
ያረጋገጠው።3
የወያኔን አገርና ሕዝብ የማጥፋት ታሪክና ባህል የማርከስ እኩይ ተግባራት በዚህ ጽሑፍ ለማጠቃለል
መሞከር ውቅያኖስን በጭልፋ እንዲሉ ነውና ለርዕሰ ጉዳያችን መግቢያ ያህል ነው ለመጠቀም ያሰብነው።
ስለሆነም ከዚህ ቀጥለን የምናተኩርባቸው ነጥቦች ባመዛኙ በኢትዮጵያ መምህራንና በሙያ ማህበራቸው
በኢመማ ላይ በወያኔ/ኢህአዴግ ተዘጋጅቶ በቀጠለው አሉታዊ የተውኔት ገቢር ላይ ይሆናል።
ከ 1985 ዓ.ም መጋቢት ወር በኋላ ወያኔ/ኢህአዴግ ሓቀኛውን ኢመማን አፍርሶ ሌላ ተለጣፊ ማህበር
የፖለቲካው አንድ ክንፍ አድርጎ ሲያደራጅ የመምህራን መብት የሚገስስ፣ ትምህርቱም ያለጥራት
የሚንከላወስ፣ የአገር ዕድገትና ራዕይ የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ የጨለማ ጉዞ እንደሚሆን የሚጠበቅ ነበር።
ኢመማ በአንድ በኩል በመደራጀትና አባላቱን በማሰባሰብ በሌላ በኩል በወያኔ ፍ/ቤት ግብግብ ገጥሞ የሞት
ሽረት ትግል ሲያካሂድና ብዙ መሥዋዕትነት ሲከፍል መምህራን እንኳንስ ደጀናቸው ኢመማ እያለ ያለምንም
ቀስቃሽ አካል የዘንድሮውን የ 2004 ዓ.ም እንቅስቃሴ ያህል በሥራ ማቆምም ሆነ በሰላማዊ ሰልፍ ትግሉን
ቢያጅቡት ኖሮ ያሁኑን የግፍ ቀንበር ቀድመው በሰበሩት ነበር።መዘናጋትና የጠላትን ተፈጥሮአዊ ባሕርይ
አለመረዳት ለባሰ ጥቃት መጋለጥ መሆኑን ይኽው እያየነው ነው። “ ነዳማ ቢያጭዱት ክምር አይሞላም “
ነውና ባለፈው ስህተት መፀፀት ሳይሆን መቆጨትን አንግበን በአዲስ መልክ የተቃጣብንን የጥፋት ዘመቻ
መመከትና ለማያዳግም ድል መብቃት ይጠበቅብናል።
በቀደሙት ዓመታት ወያኔ/ ኢህአዴግ ኢመማን ሲያፈርስና አመራሩን በካድሬዎቹ ሲተካ የሄደባቸውን
የማጭበርበር፣ የመከፋፈል እና የፕሮፓጋንዳ ክንዋኔዎች ስናስታውስ በመንግሥት ስም የተቀመጠ አካል
ያደርገዋል ተብሎ የማይታሰብ ስለነበር ድርጊቱ አሳፋሪም አሳዛኝም ሆኖ አልፏል።ከእባብ እንቁላል ርግብ
አይፈለፈልምና ከአለፈው የወያኔ የተንኮል ተግባር ተመክሮ ይዘን ዳግመኛ ስህተት እንዳይፈጠር እያሳሰብን
ወያኔ በኢመማ ላይ የፈጸማቸውን የውንብድና ተግባር በትንሹ ለአስረጅነት ቀጥለን እናቀርባለን።በኢመማ
ላይ የተፈጸመው የጥፋት ሥራ በሁሉም መስክና በሁሉም መሥሪያ ቤቶች የተፈጸመ እንደነበርም
እንጠቁማለን።4
በዚያን ጊዜ ይሰበክ የነበረው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ማህበሩን በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ለማደራጀት የሚል
ሆኖ ተገባራዊ የሆነው ግን በተቃራኒው እንደሆነ እንመልከት።በስብሰባና በውይይት ወቅት የብዙሃን ድምጽ
ወሳኝነት እንዳለው ቢታመንም መቶ ሃምሳና ሁለት መቶ አባላት በታደሙበት ስብሰባ የስብሰባውን አካሄድ
በመቃወም ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ረግጠው በወጡበት አጋጣሚ አዳራሽ በቀሩት ሠላሳና አርባ የድርጅቱ
አባላትና ወላዋዮች ባሉበት ውሣኔ በማስተላለፍ ይሠራ ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ከት/ቤቶች አንድና ሁለት ኮር አባላት ካድሬዎች ከተገኙ ራሳቸውን
ወክለው ወደተጠሩበት አካባቢ ተጉዘው በድብቅ ስብሰባ የሃሰትና ሕገወጥ ውሣኔ አስተላልፈው አመራር ላይ
የሚቀመጡበት አጋጣሚ ነበር። ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በየተ/ቤቱ ተዋቅረው የነበሩትን በመሠረታዊ መምህራን
ማህበር ሕጋዊ አመራሮች እያሉ የአዲስ አበባ ት/ቤቶች ጽ/ቤት በ1985 ዓ.ም ወያኔ ከመሰረተው ተለጣፊ
ማህበር ጋር በመተባበር መምህሩ ያልመረጣቸውን ካድሬዎች የየትምህርት ቤቱ የመምህራን ማህበር አመራር
ናቸው በማለት ስም ዝርዝራቸውን በማስታወቂያ ሠሌዳ ላይ እንዲለጥፉ የት/ቤት ዴሬክተሮችን በማዘዝ
ግልጽ ጣልቃ ገቢነቱን አረጋግጦ ነበር። ከዚህ የከፋው ደግሞ ቢሮዎችን በታጣቂዎች አጃቢነት እየሰበሩ
መግባትና መምህራን ለዓመታት በላባቸው ያፈሩትን ንብረት አንደኛው በዕቅድ የሚሠራ የዘረፋ ስልት ሆኖ
ቀጥሏል።አሁን በተለጣፊው ማህበር አመራር ላይ የሚገኙት በባንክ የነበረውን በብዙ ሚልዮን የሚገመት
ገንዘብ እየመዘበሩ ይገኛሉ።ከመምህራንም ያለፈቃዳቸው ከደመወዛቸው እየተቆረጠ ተሰብስቦ ለምዝበራ
ተጋልጧል።ይህ በሁሉም ክልሎች የተፈጸመና የታየ ክስተት ነው።አሁንም ድርጊቱ ተባብሶ ቀጥሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ በመምህሩ ላይ በግዴታ የተጫኑት የማህበሩ መሪ
ተብዬዎች ስብዕና ነው።ወያኔ /ኢህአዴግ አገሪቱን በመላ በጠመንጃ ኃይል ሲቆጣጠር ከደርግ ሠራዊት
ወዶገብና ምርኮኞቹን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በጦር አመራርና በሲቪል ተቋማቱ መድቦ እንዲያጅቡት
አድርጓል።እስከ መጨረሻው የሥልጣንና የጥቅም ፍርፋሪ ተጋሪ ሆነው የዘለቁም አሉ።ከዚህም ሌላ ከመሓል
አገር ከመንግሥት ካዝና ዘርፈው የተሰወሩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንደዚሁ ገንዘብ ቦጭቀው5
የኮበለሉትንም ይዞ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከመግባቱም በላይ ከነዚሁ መካከል በተለያዩ መሥሪያቤቶች
በኃላፊነት ስለመደባቸው ድርጊቱ ለሌላው ሕዝብ ግራ ያጋባ ቢሆንም ወያኔ ግን ሆን ብሎ ያደረገውና
በአንፃሩም ማንነቱን ያጋለጠ ድርጊት ነበር።ለምሣሌ ያኔ በተሰጠው ስያሜ የኮር አባል ተብለው ወደ ክልል
የኢህአዴግ ቢሮ ለካድሬነት ሥልጠና ከደቡብ ወሎ ዞን ባህር ዳር ከተማ የተላኩት በማህበራዊ ግንኙነታቸው
በህዝቡ ተቀባይነት ያልነበራቸው ግለሰቦች ስለነበሩ የደሴ ከተማ ህዝብ ስትመጡ ሠርቀው የተሰወሩትን እነ
እገሌን ይዛችሁ ገብታችሁ ሥልጣንና ሹመት ሰጣችሁ አሁን ደግሞ እነእገሌን ለካድሬነት መለመላችሁ ይህ
ማለት ነወይ ዲሞክራሲ እያለ ህዝቡ በምጸት ጥያቄ እያነሳ ነበር።
በተለጣፊው መምህራን ማህበር አመራር ላይ የተቀመጡትም እንደዚሁ በተለያየ ነውረኛ ስብዕና
የመገለጫ ባሕርይ የተጠመዱ ነበሩ።በ 1985 ዓ.ም ግንቦት 29 ቀን በዞን አስተዳደር ከየጓዳው በወረንጦ
ተለቅመው ለመምህራን ማህበር መሪነት የታጩት ራሳቸውን ለማሳወቅና የመምህሩንም የልብ ትርታ
ለመለካት በደሴ ከተማና በዙሪያው ባሉ ሃያ አራት በሚደርሱ ት/ቤት ርዕሳነ መምህራን ጥሪ እንዲያስተላልፉ
ሆኖ ስብሰባ ተካሄደ።በሁሉም ስፍራ የመምህራን ሓሳብና አቋም አንድ ስለነበር የተለጣፊው ቡድን
በየደረሰበት በገበያ የተገኘች ውሻ ያህል ሆኖ ተባረረ።
ግንቦት 30/ 1985 ዓ.ም በዞን ትምህርት መምሪያ እነዚህ ምልምሎች ተሰባስበው የዞን መምህራን ማህበር
እንደ አዲስ ማቋቋማቸውን ሰኔ 3/ 1985 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በዜናው ፕሮግራም ተነገረ።ወደሌላ
ከመሸጋገራችን በፊት እላይ ያነሳነው በማህበሩ ለአመራር የበቁት ከመምህሩ ዕውቅናና ይሁንታ ውጪ
በጉልበትና በማጭበርበር መሆኑ ሳያንስ ለዚህ ቦታ ሲታጩ ያሳጫቸው የየግላቸው ስብዕና እንዴትነት ነበር
ጉድ ያሰኘው።
ከተመረጡት መካከል አንደኛው በነፍስ ገዳይነት ታሥሮ የነበረና ወያኔ አካባቢውን ሲቆጣጠር ከወህኒ
ወጥቶ ወዲያው የወያኔ ወዶ ገብ ሆኖ ታጥቆ ማህበሩን ለማፍረስ ቃል ገብቶ የተንቀሳቀሰ ነበር።ሁለተኛው
ቀደም ሲል ወታደርነት የሞከረ ከዚያ ወጥቶ ወደ መምህርነት የገባ ይኖርበት በነበረው የወረዳ ከተማ6
ለችግረኞች የሚታደል ስንዴ ሰርቆ ተይዞ በአደባባይ ተሸከሞ እንዲዞር የተደረገ በሌላ ጊዜም ከተማሪዎች
በነፍስወከፍ የቅመም እህል/የቅባት እህል እየሰፈሩ እንዲያመጡ አዞ የተጠራቀመውን ሸጦ መጠቀሙ
ተደርሶበት አስተዳደራዊ የዲሲፕሊን እርምጃ የተወሰደበት ሆኖ ሳለ ማህበሩን ለማፍረስ ባደረገው ንቁ
ተሳትፎ የዞኑ የደህንነት ተጠሪ እስከመሆን የደረሰ ነበር።ሌላው ሦስተኛው በአንድ የአውራጃ ከተማ
በማስተማር ተሰማርቶ በሚሠራበት ወቅት በግሮሰሪዎች በዱቤ ጠጥቶ፣ በምግብ ቤቶች በዱቤ ተመግቦ
ላለመክፈል የራሱን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም የዱቤ ተጠቃሚዎች ስም ዝርዝር ያለበትን መዝገብ በስውር
ወስዶ ቀዶ የሚጥልና በዕምነት የተዋዋሉትን ነጋዴዎች ኪሣራ ላይ የጣለ ነበር። የመምህራን ማህበርን
በማፍረስ ላደረገውም አስተዋጽኦ ከማህበሩ መሪነት አልፎ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ(ድንጋይ ማምረቻ) ገብቶ
ከሰለጠነ በኋላ ሰሜን ወሎ በዳኝነት እንዲሠራ ተመድቦ ነበር።
ታዲያ እነዚህን የመሳሰሉ ዋልጌ መምህራን በተለጣፊው አመራር ውስጥ እንዲቀመጡ ያደረጉት የወያኔ
ቁንጮ መሪ፣ በቅርቡ ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግራቸው ለመብታቸው የቆሙትንና በሙያቸውም
ታታሪና ሥነ-ምግባር ያላቸውን መምህራንን “ ወላጆችና ተማሪዎች ” ከማስተማሩ ሥራ እንዲወገዱ ጠይቀው
ነበር ብለው የቀጠፉት። ይህ የሚያረጋግጠው የሥርዓቱ የቅጥፈትና የእኩይ ተግባሮች ዋናው ምንጭ ጠቅላይ
ሚኒስትሩ መሆናቸውን ነው። ከዚህ አንጻር ውሸትና ክህደት የሥርዓቱ የፖለቲካ መልህቅ ሆነው
መቀጠላቸው የሚደንቅ አይሆንም።
የዚህ ዓይነት አሠራር በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎችና መ//ቤቶች የሚታዩ ስለሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስቃይ
ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ከላይ የተጠቀሰው ጭብጥ አጠቃላይ ስዕሉን ያሳያል።የዚያን ጊዜ መምህራን ይኽን
የመሰለውን ሕገ ወጥ አካሄድና ማህበሩን የተለጣፊዎች መሰባስቢያ እንዳይሆን በኢመማና በሓቀኛ መምህራን
ብዙ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ወያኔ በከፈተው ጣልቃ ገብነት ትግሉ ውስብስብ ሆኖ ቆይቷል።በዚህ በያዝነው
2004 ዓ.ም የመምህራን የመብት ጥያቄ ከማቅረባቸው ጋር ተያይዞ አገዛዙ ባረጀውና ባፈጀው የፈጠራ ክስ
መምህራንን በሽብርተኝነትም፣ በአሸባሪዎች ተባባሪነትም፣ ብቻ ግርጌና ራስጌ በሌለው መናኛ ሰበብ7
መወንጀሉን ቀጥሎበታል።መምህራንም ሆኑ አጠቃላይ ሕዝቡ የወያኔ/ኢህአዴግ ንፁሐንን የመወንጀል
ተከታታይ የክስ ድራማ እንደቁምነገር ቆጥረው ጆሮ አልሰጡትም ሊሰጡትም አይገባም።እንዲያውም
በመድረኮች ሁሉ በነጠሩ ማስረጃዎች እያስደገፉ የሥርዓቱን መሪዎችና አጫፋሪዎቻቸውን የሐሰት
ፕሮፓጋንዳ አምክነውታል።ታዲያ እነአጅሬ በዚህ የሚቆሙ ብቻ መች ሆኑና።
ከላይ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ መምህራንን ለማጎሳቀልና ማህበራቸው መገልገያ እንዲሆናቸው በማመቻቸት
የፈጸሙት ሕገ-ወጥ፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ እና ኢ-ሰብአዊ ተግባር የሚታወስ ሆኖ መምህራን በቅርቡ ካቀረቡት
የመብት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ሌላ ዘመቻ መከፈቱን ከወደ አገር ቤት ብዙ መረጃዎች እየደረሱን ነው።
በአንዳንድ ክልሎች በማህበሩ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም የሚሉትን ማዘናጊያ እንኳ ጭራሽ ከቁብ ሳይቆጥሩ
የሙያ ማህበሩ አመራር ከት/ቤት መሠረታዊ መምህራን ማህበር እስከ ላይ ድረስ በኢህአዴግ አባላት መያዝ
እንዳለበት የሚያሳስብ ጽሑፍ ከትምህርት ቢሮዎች ከላይ እስከ ታች መተላለፉ ተረጋግጧል።ወያኔ ተለጣፊ
ማህበሩን ሙሉ በሙሉ በካድሬ አባለቱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ የትምህርት ሚኒስቴር መ/ቤትን በማዘዝ
ፍጹም ጣልቃ ገብነቱን አሣይቷል።
ቀደም ሲል ለማሳየት እንደተሞከረው ከመነሻው ማህበሩን አፍርሰው በአዲስ ታማኝና የጥፋት
መልዕክተኞች መተካቱ ሳያንስ የአሁኑ ሙሉ በሙሉ በወያኔ ኢህአዴግ አባላት ለመተካት የሚደረገው እርምጃ
በፊቱንም ቢሆን ነጻ ሆኖ የማይንቀሳቀስ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም የ አሁኑን ለየት የሚያደርገው ነገር አለ
ቢባል እንደ አግአዚ ጦር ስብስብ ምህረት የለሽ መቺ ሀይል ከመምህራን መካከል እየተመለመሉ በአባላቱ
አንገት ሸምቀቆ ለማስገባት የማያመነቱትን ለማስቀመጥ የታለመ መሆኑ ነው።ልብ በሉ መምህራን! የመብት
ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ የወጡላው ስሞች በማንኛውም መመዘኛ ለመምህራን የሚሰጡ ሳይሆን ጭራሽ
የሚታሰቡም አይደሉም። ተራብን፣ ታረዝን፣ እንግልቱ በዛብን፣ በአገልግሎታችንና በደረጃችን እንደ ሌላው
የሲቪል ሰርቪስ መ/ቤት ሰራተኛ ለኛ ተመጣጣኝ ክፍያ ይከፈለን ማለት በአሸባሪነት አያስፈርጅም።ከዚያም
አልፎ በችሎታ ማነስ ስብስብ የተሞላው የወያኔ /ኢህአዴግ ድርጅትና ቢሮክራሲው ሆኖ ሳለ መምህራንን8
በዚህ ሰድቦ ለሰዳቢ ለመስጠት መሞከር “ ለማያውቅሸ ታጠኚ ”  እንዲሉ ከመሆን አያልፍም።እጅግ
አስከፊው የወያኔ ኢህአዴግ እኩይ ተግባር ደግሞ በአደባባይ መምህራንን በመዝለፍ የመብት ጥያቄ
በማቅረባቸው ከሥራ ማባረሩ ነው። ሥቃይ መከራው ቀጣይነት እንዳለው የሃያ ዓመታት ተሞክሮ
አሳይቶናል። የእግር ብረቱ፣የእጅ ካቴናው፣ የአንደበት ልጓሙ እየጠበቀ ነው የመጣው።ወገኖቻችን ያሳያችሁ!
መምህራን አድማ ከመቱ በሁዋላ አዲስ የክፍፍልና የክትትል ሥልት ተዘጋጅቶላቸው “ የአድማ ጠንሳሽ ”፣ “
አነሳሽ ”፣ “ ተከታይ ” በሚል ፍረጃ ሁሉም መምህራን በደህንነት ስለላ መረብ እንዲጠመዱ ተደርጓል።
በስያሜው መሠረት ለአደጋ የመጋለጡ ዕድል፣የአደጋው ዓይነትና የሚወሰደው እርምጃ ይለያይ እንደሆን
እንጂ ለሁሉም የማይቀር ፍዳ ለመሆኑ ግን አዝማሚያው ያለጥርጥር ያሳያል።
ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆነው ሐቀኛ መምህራንን በአንዳንድ ተሳትፎ የማግለልና ሞራልን የመስበር ርምጃ
ነው።ከመምህራን የመብት ጥያቄ ሰላማዊ የስራ ማቆም አድማ ጋር በተገናኘ መልኩ ለ12ኛ ክፍል ፈታኝነት
እንደማንኛውም መምህር ተመዝግበው ሲጠብቁ የነበሩት ከላይ በሶስት ምድብ ተመድበው ከተያዙት
መምህራን መካከል ብዙዎቹ ባለመመረጣቸው ለምን እንዳልተመረጡ ለት/ቤታቸው አስተዳደር ጥያቄ
ቢያቀርቡም የተሰጣቸው መልስ “በአፈጻጸም” ነው የሚል ፌዝ መሆኑ ይሰማል።ይሁን እንጂ
የወያኔ/ኢህአዴግ የአፈጻጸም ስልት አይደግፉኝም የሚላቸውን ሁሉ ከየትኛውም ጥቅማጥቅም ከሚገኙባቸው
መስኮች ማግለልና ሆዳሞቹን እየደለለ የተግማማ ሥርዓቱን ጠጋግኖ ለማቆየት ከመሞከር ሌላ የሚያስገኘው
ፋይዳ የለውም።
ይህ የወያኔ/ኢህአዴግ ክፉኛ መወራጨት ትክክል ነው ባይባልም የሚጠበቅ ነው።እኛም ብዙ ጊዜ
ለማሰተጋባት እንደሞከርነውና ብዙዎች ወገኖቻችን በጽሑፍም በንግግርም ከእኛ ጋር እንደተጋሩት
“መምህራን ተማሪዎች ናቸው፣ወላጆች ናቸው፣ወላጅ ደግሞ ሕዝብ ነው፣ ሕዝብም አገር ነው”።
ወያኔ/ኢህአዴግ ከሕዝብ ጋር ከአገር ጋር ጠብ ፈጥሮ አጠፋለሁ አንጠፋም በሚል ግብግብ ላይ ነን።ጠቡ
ከመምህራን ጋር ብቻ እንዳልሆነ ግን ይሠመርበት።እንደተገለጸው መምህራን የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል9
አካል በመሆናቸው ለአመጽ ማሰባሰብና ማታገል እንደሁም ሥርዓቱን የማናጋት አቅም አላቸው። መምህራን
ምንጊዜም የሥርዓት ሹም ሽር ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የአገር አንድነት ላይ የተመሰረተ
ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ነው ፍላጎታቸው፣ ምኞታቸው፣የትግላቸውም አልፋና ኦሜጋ።
ይህ በዕውን በታሪክ ያስመዘገብነው የትግል ሰንደቅ ሆኖ እንዲቀጥል በአሁኑ ጊዜ ለዚህ የምር
ቆመንለታል ወይ? የሚል ትልቅ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ሊቀ ለቃውንት አለቃ አያሌው በአንድ ወቅት
በጋዜጠኛ ኢትዮጵያዊነት ምንድነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልሳቸው “ ሆኖ መገኘት “ የሚል ነበር።
ከላይ በመጠኑም ቢሆን የጠቃቀስናቸውን የመምህራን መገለጫዎች ሆነን ካልተገኘን በታሪክ ተወዳሽ
መሆናችን ቀርቶ በታሪክ ተጠቃሸና የትውልዱም ማፈሪያዎች እንዳንሆን በአገሪቱ ያንዣበበውን የጥፋት
ደመና ለማሰወገድ እንነሳ። አያያዙን አይቶ ጭብጦውን ቀሙት እንዳይሆን እንጠንቀቅ-ትግላችንንም
እንቀጥል። አሁንም በስልት እንደራጅ!!
በወያኔ ሥርዓት የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የአገር አንድነት፣የፍትህ ርትዕ መስፈን ባጠቃላይ የዴሞክራሲያዊ
ሥርዓት መረጋገጥ አደጋ ላይ መውደቁ ግልጽ ነው። ይህን አውዳሚና የዘረኛ ሥርዓት ለመለወጥና በምትኩ
በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል በተናጠል በሚያደርገው ትግል
ውጤት አይገኝም። መምህራን ትግላቸውን ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ማቀናጀት ይጠበቅባቸዋል።
የሁሉም የጋራ ትግል ይጠይቃልና።
በ1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ መምህራን እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍል ሲያደርጉት የነበረውን ትግል
በመቀላቀል ተማሪዎች መሬት ላራሹ፣ዴሞክራሲ ያለገደብ፣ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም በማለት
ከመምህራንና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍል ጋር ወግነው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።ዛሬም
አስተማሪዎቻቸው ሲራቡና ሲጠሙ ምግብ ለህብረተሰቡ፣ የመምህራን የሥራ ዋስትና ይጠበቅ፣ከስራ
የተባረሩ መምህራን ወደ ስራቸው ይመለሱ፣ አሁንም መሬት ላራሹ፣ የገበሬው መሬት ለባዕድ አገር
ከበርቴዎች መቸብቸብ ይቁም፣ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም በእኩልነት ይዳረስ በማለት እንደተለመደው10
የሕዝብ አጋርነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሕብረተሰቡ፣
የባሕር ዳርና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ እንዲሁም በአገሪቱ ከሚገኙት ሌሎች ኮሌጆች የተነሳው
የመብት ጥያቄ የሚደገፍ ነው። የሁለተኛ እና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም በትግሉ ውስጥ ድርሻ
መወጣት ይጠበቅባቸዋል። በተመሳሳይም ሌላው ኢትዮጵያዊ ነጋዴው፣ገበሬው፣ሠራተኛው፣ወታደሩ፣ በጾታ፣
በሃይማኖት፣ በዘር ሳይለያይ በጋራ ቆሞ ትግሉን እንዲያፋፍም እና ያለአግባብ የታሠሩት የፖለቲካ
እሥረኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ከመሬታቸው የተፈናቀሉት ዜጎችን፣ ከሥራ የተባረሩ መምህራንን…. እንዲረዱ እና
የበኩላቸውን ድርሻ አንዲወጡ እንጠይቃለን።
የወያኔንም የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ማጋለጥና መመከት ከሁላችንም ይጠበቃል።አለበለዚያ በኢትዮጵያ
ሕዝብ ሃብትና ንብረት በተቋቋመው የመገናኛ ብዙሃን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እያሰፈንኩ ነው በማለት የሌባ
አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ ነውና ለማደናገርም ሰይጣንም ከቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚጠቅስ ሁሉ
ወያኔም የማይቧጥጠው ነገር ባለመኖሩ ከእንግዲህ ለወያኔ ፕሮፖጋንዳ ጆሮ መስጠትና መዘናጋት የለብንም።
የመምህራን አንድነት ይጠንክር!
ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት!
ኢትዮጵያዊነት የማይደለዝ፣የማይሰረዝ ማህተም ነው!
የኢትዮጵያ ሕዝብ በመተባበር ያሸንፋል!!
ለበለጠ መረጃ፦ በ eta1941@yahoo.com በመጻፍ ሊያገኙን ይችላሉ።

No comments:

Post a Comment