"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday 9 June 2012

“ቬነስ ፕላኔት በአዲስ አበባ ፀሀይን ማቋረጧ የልማቱ ውጤት መሆኑ ተዘገበ!”


“ቬነስ ፕላኔት በአዲስ አበባ ፀሀይን ማቋረጧ የልማቱ ውጤት መሆኑ ተዘገበ!”
Posted by admin on June 6, 20120 Comment
በአቤ ቶኪቻው
ዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ በአዲስ አበባ ፀሐይ ስር ቬነስ የተባለችው ፕላኔት ስታቋርጥ ለ18 ዲቂቃዎች እንደምትታይ መሰለ ገብረ ህይወት የተባለው የኢቲቪ ዜና አንባቢ ትላንት ማታ በፈገግታ እና በታላቅ ድል ስሜት ታጅቦ ነገሮናል። ከፈገግታውና ከአነጋገሩ እንደተረዳሁት ከሆነ ነገ ይህንኑ ዜና ምን ብሎ ሊነግረን እንደሚችል እንደሚከተለው እገምታለሁ…
ቬነስ ፕላኔት በአዲስ አበባ ሰማይ ስር ማለፏ ያስመዘገብነው ልማት ውጤት መሆኑ፤ የተለያዩ ባለስልጣናትን አነጋግሮ የዘገበው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ፕላኔቷ በ18 ደቂቃ ቆይታዋ በአገሪቱ መልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲ ሰፍኖ መመልከቷን አያይዞ ዘገቧል።
ለዝርዝሩ… (“ትልና…” አሉ የዞን 9 ልጆች አንዳቸው ወይም ሁለታቸው…! (እዝችጋ አንድ ማስታወቂያ ተናግሬ እቀጥላለሁ ዞን 9 የተባለ ብሎግ መከፈቱን ሰምታችሁ ይሆን? ወደ አስር የሚጠጉ “ጦማሪያን” በአንድ ላይ በመሆን የከፈቱት ይህ “ጦማር” “ስለሚያገባን እንጦምራለን!” በሚል መሪ ቃል የተከፈተ እንደሆነ አናቱ ላይ የተፃፈውን አይቼ ተረድቻለሁ… ጎራ ብላችሁ ብታዩት አሪፍ አሪፍ “ጡመራ” እንደሚኖር ድንጋይ ነክሼ እመሰክራለሁ…!) http://zonenine.wordpress.com/author/zonenine/ ይኸው መግቢያው!
ወደ ዜናችን ስንመለስ…

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንደገለፁት “አሁን ሀገራችን ከምዕራብ ሀገራት እና ከቻይና በተጨማሪ ከቬነስ ፕላኔት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ ጀምራለች” ካሉ በኋላ፤ “ቬነስ ከሌሎች ሀገራት በሙሉ እኛን መምረጧ ያለን ልማታዊ ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ግልፅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ኃይለማሪያም አያይዘውም፤ “በአሁኑ ወቅት ከአለም ሀገራት በተጨማሪ ሌሎች ፕላኔቶችም ሀገራችን እየተከተለች ያለችው የልማትና ዴሞክራሲ አቅጣጫ ትክክል መሆኑን አምነው የተቀበሉበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልፀውለታል።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ባለስልጣንና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ጸረ ሽብር ግብረ ኃይል እንዲሁም የመከላከያ ቃል አቀባዮች በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “በአገራችን ያለው አስተማማኝ ፀጥታ ቬነስ በአዲሳባ ፀሀይ ስር ማቋረጥን እንድትመርጥ አድርገዋታል” ያሉ ሲሆን፤ “ለፕላኔቷ ስጋት ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ የሻቢያ ተላላኪ ፀረ ሰላም ኃይሎች በህብረተሰቡ ጥቆማ ቀድመው በቁጥጥር ስር በመዋላቸው ያለ አንዳች ችግር ፕላኔቷ በሰላም ከተማችንን ለማቋረጥ አስችሏታል።” ብለዋል። አክለውም፤ “ፀረ ሰላም ሀይሎቹ ባይከሽፍባቸው ኖሮ በከተማው ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ በማስነሳት ፕላኔቷ የምታደርገውን ጉዞ ለማጨናገፍ እና የሀገሪቱን መልካም ስም ለማጠልሸት አስበው እንደነበር ገልፀዋል።
የአዲሳባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በበኩላቸው ቬነስ በአዲስ አበባ ከተማ ፀሀይ ስር ባደረገችው የአስራ ስምንት ደቂቃ ቆይታ የከተማዋን እድገት እንዳደነቀች በተለይም ወጣቶች በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው እየሰሩ ያሉት የኮብል ስቶን የመንገድ ንጣፍ በጣም እንደማረካት ገልፀው በእርሷ ከተማ እንዲህ አይነት ነገር እንዲለመድ ልምድ መቅሰሟንም አስረድተዋል።
ቬነስ ፕላኔትን ባነጋገርናት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በተመለከትችው በሙሉ እንደተደነቀች እና በመቶ አመት ውስጥ በርካታ ለውጦችን መመልከቷን የገለፀች ሲሆን፤ አዲስ አበባ በዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳደር የተሳካላት ከተማ መሆኗን እንዳስተዋለች በአድናቆት ገልፃ፤ ያየችውን በሙሉ ለሌሎች ፕላኔቶች እንደምትነግር እና እርሷም ከእንግዲህ ቶሎ ቶሎ ብቅ እያለች ማራኪዋን እና ልማታዊዋን ከተማ እንደምትጎበኝ ገልፃለች!

No comments:

Post a Comment